Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
sarcasm
Senior Member
Posts: 10186
Joined: 23 Feb 2013, 20:08

ድርድር ፈጽሞ ለድርድር አይቀርብም¡¡¡ ተጻፈ በገመቹ መራራ

Post by sarcasm » 30 Nov 2021, 12:15

ድርድር ፈጽሞ ለድርድር አይቀርብም¡¡¡
- - - - - - - - - - - - - - - - - - -
(ጥቂት የግል ምልከታዎች - ከሰሞኑ የድርድር ርዕሰ-ጉዳይ ጋር በተያያዘ፤ አጥሮ በሁለት ክፍል ከሚለጠፍ ይሻላል በሚል የቀረበ ትንሽ ረዘም ያለ ጽሁፍ ነው። a ~6 mins read)

* * * * *
1/ ድርድር ከማን? በማን?


«ከሰይጣን ጋር ትደራደራለህ?» ሲል Bargaining with the Devil በሚለው መጽሐፉ መግቢያ ላይ የሚጠይቀው Robert Mnookin ነው። “በሽብር ዘመን ዓለምአቀፍ መሪዎቻችን የዚህ ዓይነት ጥያቄ በየቀኑ ይገጥማቸዋል። ከታሊባን ጋር እንደራደራለን? ከኢራን? ከሰሜን ኮሪያ? ታጋቾችን ከያዘ የሽብር ቡድን ጋርስ?» የሰላም ድርድር የሚደረገው ለሰላም መታጣት ምክንያት ነው ከምንለው “ጠላት” ጋር ነው፣ ከወዳጅ ጋርማ ወዳጅ ነን።

በአሜሪካ የተፈፀመው «የመስከረም 11ዱ ጥቃት»ን ተከትሎ የወቅቱ ፕሬዚደንት ጆርጅ ቡሽ ለአፍጋኒስታኑ የታሊባን አስተዳደር «የአልቃኢዳን የልምምድ ካምፖች ዝጉ፣ ኦሳማ ቢንላደንን ጨምሮ ወታደሮቹን አሳልፋችሁ ስጡን አለዚያ እንወራችኋለን» የሚል ማስጠንቀቂያ (ultimatum) ነበር የሰጠው። ታሊባን ለዚህ ማስጠንቀቂያ የሰጠው ምላሽ ብዙዎች ያልጠበቁት ነበር፤ ቡሽን ለድርድር ጋበዙት። የወቅቱ የታሊባኑ መሪ ሙላህ ኦማር በይፋ ንግግራቸው «የአሜሪካ መንግሥት ከእስላማዊው የአፍጋኒስታን ኢመሬት ጋር ችግር ካለበት ችግሮቹ በድርድር ሊፈቱ ይገባል» ሲሉ ተደመጡ።
ዛሬ ላይ መለስ ብለው ሲያዩት ቡሽ ድርድሩን መግፋት እንዳልነበረበት የሚያምኑ፣ በወቅቱ ግን «ከአሸባሪ ጋር ድርድር የለም» የሚል ግትር አቋም የነበራቸው ሰዎች በርካቶች ናቸው። የኃይል ወይም ሌሎች አማራጮችን ከመምረጥ በፊት በድርድር መፈታት ይችል እንደሆን መሞከር ተገቢነቱ በተለያዩ ጊዜያት ታይቷል። አፍጋኒስታንን በተመለከተ የቀረውን ታሪክ ሁላችንም የምናውቀው ነው። ጦርነቱ 20 ዓመት ፈጀ። ሀገሪቱ እንዳትሆን ሆና ፈረሰች። በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ዜጎች ሞቱ፣ ተፈናቀሉ። ጦርነቱ ግን በአንዳቸውም ድል አድራጊነት አልተጠናቀቀም።
* *
አንድ መራራ ቀልድ አንብቤ ነበር። «የአፍጋኒስታን ጦርነት ከ20 ዓመታት በኋላ ተጠናቀቀ። ማነው አሸናፊው?» ይላል ጠያቂው፤ ራሱ ሲመልስ «Raytheon, General Dynamics, Northrop Grumman, Boeing and Lockheed Martin» ሲል ይመልሳል። በጦርነቱ በቢልየኖች የሚቆጠር ዶላር ያተረፉት እነዚህ ግዙፍ ኮርፖሬሽኖች የመከላከያ ኮንትራክተር ተቋማት ናቸው። በየትኛውም ቦታ ካለ ጦርነት፣ በተለይም አሜሪካ ከምትሳተፍባቸው ጦርነቶች አትራፊ ናቸው። መንግስታቸውም ይህንንና መሠል የሥራ ዕድል ሲፈጥርላቸው ይኖራል።

በኢራቅ የሳዳም ሁሴን አምባገነናዊ አገዛዝ በአሜሪካ መሪነት እኤአ በ2003 ዓ/ም ሲፈርስ የተተካው ምዕራባውያኑ መሀንዲሶች ያወሩት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አይደለም። ይልቁንም በኢራቅ የተነሳው የርስ በርስ ጦርነት ከግዛቲቱ ባለፈ ሥርዓት አልበኝነትን አስጀመረ። የኢራን ኢስላማዊ ሪፐብሊክን የኃይል ሚዛን ያስጠበቀው የኢራቅ መንግሥት መፍረስ በመካከለኛው ምስራቅ የመንግሥታት ፉክክር እንዲኖርና መረጋጋት እንዲጠፋ ምክንያት ሆነ። ኢራቅም የደከሙ ተቋማት ያሏት፣ ሙሰኛና መዝባሪ ልሂቃን የሚዘውሯት፣ ሕዝባዊ ተቃውሞ የሚደጋገሙባት እና የትጥቅ ትግል የማታጣ ደካማ ሀገር ሆነች። በሱኒና በሺዓ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች መካከል አግላይ የፖለቲካ ምህዳር ተፈጠረ። ይህ ኹኔታ ውሎ አድሮ ዳኢሽን ወይም አይኤስአይኤስን ወለደ።

በሶርያም የተፈጠረው ከሞላ ጎደል ያው ነው። ፕሬዚደንት በሽር አልአሳድ ለሰላማዊ ተቃውሞዎች የሰጠው የኃይል ምላሽ ለሀገሪቱ የርስ በርስ ጦርነት ማስጀመሪያ ፊሽካ ሆነ። አሜሪካና እና አጋሮቿ አሳድ ሥልጣን እንዲለቅ አሳሰቡ። የተለያዩ የሶርያ ተቃዋሚ ኃይሎች ነፍጥ አነሱ፣ ለሀገር ውስጥ ችግራቸው የውጪ ኃይላትን እርዳታ ጠየቁ። ቱርክ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ዩኤኢ፣ እና ኳታር ለሚፈልጓቸው የሱኒ ተቃዋሚ ኃይሎች መሳሪያና ገንዘብ ረዱ። ኢራን በበኩሏ የጦር አማካሪዎች እና ከሊባኖስ፣ ኢራቅና አፍጋኒስታን የተሰባሰቡ ሺዓ ሚሊሻዎች ላከች። ሩስያም የአየር ጥቃት እርዳታ አቀበለች። አሜሪካም ተመልሳ መጣች። የሆነው ሆነ። ዛሬ ሶርያውያን በሸገር ጎዳናዎች ለልመና ሲርመሰመሱ የምናይበት ኹኔታ ላይ ተደረሰ።

በነብያቶቻቸው፣ በጥንታዊ ሥልጣኔያቸው፣ በታሪክ ቀዳሚ የመንግሥት ሥርዓት በመፍጠራቸው ይታወቁ የነበሩት ኢራቅና ሶርያ የጦርነት አስከፊነት ማሳያ ምሳሌ ሆኑ። ስማቸው ሲጠራ ፍርስራሽና የማይቆም ስጋት ያለበት አስፈሪ ቦታ በምናቡ የማይስል ሰው እስኪጠፋ ድረስ ፈረሱ።

እኛስ?

የሲአይኤና ሌሎች የውጪ አካላትን ስክሪፕት እየተወነች የምትኖር ሀገር የሚኖረን እስከመቼ እንደሆነ አላውቅም። ሆኖም ያንን የጣልቃ ገብነት በር በርግደን የምንከፍትላቸው እኛው መሆናችንን አውቃለሁ። እነሱ ጣልቃ የገቡበትና የተሻሟቸው ሀገራት ደግሞ የሆኑትን አይተናል። ዕጣችን ከዚያ የመውጣት ዕድሉ ካለ የሚኖረው መደራደርና የኛን የውስጥ ጉዳይ በራሳችን መጨረስ ከቻልን ብቻ ነው።
* *
በወዳጄ ተባ/ፕሮፌሰር ሀሰን መሐመድ (ባለበት ሰላምና ጤና ይስጠው) ጠቋሚነት ከበርካታ ዓመታት በፊት የማየው በሳምንት ሶስት ወይ አራት ቀን የሚቀርብ The Colbert Report የተባለ ሾው ነበር። የሾዉ አዘጋጅና አቅራቢ ስቲቭን ኮልቤር ተወዳጅ፣ ካሪዝማቲክ የሆነ ገፀ-ባህሪ ነው። በዚህ ሾው ላይ ኮልቤር አክራሪ ቀኝ ዘመም/ወግ አጥባቂ አቋም ያለው ግለሰብን ገፅታ ተላብሶ ነው የሚቀርበው። ነገር ግን ኮልቤር የሚተቸው እና የሚቀልደው በነዚሁ ወግ አጥባቂዎች ላይ ነበር። ድርጊቱና ንግግሩ ብዙ ያደናግራል። ይህንን መደናገር ያስተዋለችው በፊላደልፊያው ቴምፕል ዩኒቨርሲቲ የኮሚውኒኬሽን ምሁር የሆነችው ፕሮፌሰር ሂዘር ላማር ይህንን ሾው አጠናችው።

ፕሮፌሰር ላማር ከሌሎች ቀልድ አዘል አቀራረብ (Humor) በማኅበረሰብ ባህል (popular culture) ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ የሚያጠኑ ማህበራዊ ሳይንቲስቶች ቡድን ጋር ትሰራለች። አደናጋሪው ጭብጥ አንድ ተመልካች የኮልቤርን ሾው ሲያይ ኮልቤር እያደረገ ነው ብሎ በሚረዳው ነገር እና በኮልቤር አቀራረብ የሚፈጠረው ስሜት መሀል ያለው ኹኔታ ነው። ኮልቤር እጅግ ከባዱን ነገር ያሳካ ጂኒየስ የኮሜዲ ሾው ሆስት ነው ያስባለው ኹኔታ እንዲህ ነው፦

ፕሮፌሰር ላማር ሊበራል የሆኑ በርካታ ምሁራን ጓደኞች እንዲሁም ወግ አጥባቂ ቤተሰቦች አሏት። እነዚህ ተቃራኒ ወይም የተራራቀ አቋም ያላቸው ሁለቱ ወገኖች የኮልቤርን ሾው እኩል አስቂኝና አዝናኝ ሆነው ያገኙታል። ምክንያታቸውም ታዲያ ፍፁም ተቃራኒ መሆኑ ነው ያስገረማትና ለጥናት ያነሳሳት። ለምንድነው ወግ አጥባቂዎቹ ሪፐብሊካን ጓደኞቼና ቤተሰቦቼ በየምሽቱ እያዩት አዝናኝ ሆነው የሚያገኙትና ሊበራሎች ላይ የሚቀልድ እንደሆነ ሲረዱት፤ ሊበራል ጓደኞቼም በወግ አጥባቂ ሰዎች ላይ የሚቀልድ መስሏቸው በጣም የሚወዱት እና አድናቂዎቹ የሆኑት እንዴት ነው? ስትል ትጠይቃለች።

ላማር ጥናቷን ስታከናውን የተገነዘበችው ነገር የበለጠ ሊበራል በሆንክ ቁጥር ኮልቤር ወግ አጥባቂዎችን የሚነቁር ሰው ሆኖ እንደምታገኘው፣ የበለጠ ወግ አጥባቂ በሆንክ ቁጥር ስቲቭን ኮልቤር ሊበራሎችን የሚነቁር ወግ አጥባቂ ሰው ሆኖ እንደምታገኘው ነበር። እንደ ጥናቱ መደምደሚያ በመሠረታዊነት እነዚህ ሁለት ተቃራኒ ተመልካቾች The Colbert Reportን ሲያዩ ማየት የሚፈልጉትን ነገር ብቻ ነው ያዩት። ይህ ኹኔታ motivated cognition or biased perception ተብሎ የሚጠራው ሕፀጽ ነው እንግዲህ።

* *
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ብሔርተኞች/ፖለቲከኞች/ልኂቃን ዘንድ እንደኦሮሞ ብሔርተኛ ይወሰዳሉ። በበርካታ የኦሮሞ ብሔርተኞች/ፖለቲከኞች/ልኂቃን ዘንድ ደግሞ አሀዳዊ ተደርገው ይወሰዳሉ። ሁለቱም ወገኖች እንዳወገዟቸው እና እንደተቃወሟቸው ይኖራሉ። ነገር ግን አንድ ነገር ግልፅ ነው፣ መቼም ሁለቱም ወገኖች ልክ ወይም ትክክል ሊሆኑ አይችሉም። አንዳቸው አንዳቸውን ማመንም ሆነ ማሳመን ግን አልቻሉም፣ አይችሉምም። ለኦሮሞ ብሔርተኛ “ጠቅላዩ የኦሮሞ ብሔርተኛ ናቸው” ብትለው ፍርፍር ብሎ ይስቃል፤ (እኔም ያስቀኛል 😃 ) የአማራው ብሔርተኛም “ጠቅላዩ አሀዳዊ ናቸው” የሚለው መከራከሪያ ያቅረዋል። ሁለቱ ወገኖች ላይ ያለው እርግጠኝነት ሁለቱም መስማት የፈለጉትን ብቻ ነው የሚሰሙት ወደሚለው መደምደሚያ ያደርሰናል። ይሄንን የሚያነቡ ሰዎችም ተመሳሳይ ስሜት ውስጥ መግባታቸው ይጠበቃል። ነገር ግን አንዳቸው ሌላኛቸውን የሚያሳምኑበት ስሙር እና አሳማኝ አመክንዮ እና ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ ክርክሩ ለዘለዓለም ሊቀጥል ይችላል። (አደራችሁን በኮሜንት ይህንን የማያልቅ ክርክር እንዳትጀምሩ lol)

በዚህ አካሄድ ሁለቱን ወገኖች የሚያስታርቀው አንድ አሸናፊ «ሀሳብ» ይናፍቀናል እንጂ አይመጣም። ፈፅሞ አንተማመንም። ስለዚህ ለመቀራረብ ድርድር የግድ ይላል። «እውነቱ እኔ ጋር ነው ያለው» የሚል እርግጠኝነት ይዘህ፣ በድርድር የሚመጣውን መሀከለኛ መንገድ መዋጥ የግድ ይላል። የጠቅላዩን ምሳሌ ከስሪቭን ኮልቤር የኮልቤር ሪፖርት ገፀባህሪ ጋር በማነፃፀር በምሳሌነት ያነሳሁት ለዚህ ነው። ጠቅላዩ አሃዳዊም የኦሮሞ ብሔርተኛም እንዳይሆኑ አድርጎ መሀል ላይ የሚያስቀምጣቸው ሁሉን አቀፍ ድርድር እና የድርድሩን ውጤት በሕግና በሥርዓት ቀንብቦ ማስቀመጥ የተቻለ እንደሆነ ብቻ ነው።

«ፍጹም ሥልጣን ያባልጋል» እንዲሉ ላለመባለግ ሁሉም ሥልጣን እና የባለሥልጣን ውሳኔ ከተጠያቂነት ጋር አብሮ መምጣት አለበት። የሕዝብ ጥያቄን በቀላሉ ለውይይት ክፍት ማድረግና መመለስ ያልፈለገው ኢህአዴግ የጉልበት አካሄድ ተጠቅሞ ይኸው የደረስንበት ደርሰናል። እነ አባይ ጸሀዬ (ነፍስ ይማር) በኦሮሞ ፕሮቴስት ወቅት የወጡ ወጣቶችን «ልክ እናስገባቸዋለን» ያለበት ፉከራ አሁን ለደረስንበት ኹኔታ ጥንስስ ሆኗል። ታሪካችን በዚህ ዓይነት የአንድ ወገን ፍፁማዊ የበላይነትን እና አሸናፊነትን በሚፈልጉ ገጠመኞች የተሞላ ነው። እስካሁን ያልተሞከረው ድርድር ነው። ቢያንስ ተሞክሮ «አልተሳካም» ማለት መቻል «ቢሞከር ኖሮ» ከሚለው ቁጭትና speculation ያድናል።

በዚህ ረገድ የድርድር ሃሳብን ደግፎ በመግፋት የሕዝቡ ሚና ትልቅ ነው። የሚጎዳውም የሚያተርፈውም ሕዝቡ ነው። ሰላም ከሌለ ጥራቱን የጠበቀ ሆስፒታል፣ መንገድ፣ ትምህርት ቤት እና ሌሎች የመሠረተ ልማት አውታሮች ሊዘረጋበት የሚገባው የሀገር ሀብት ለጦርነት፣ ለተፈናቃዮች መልሶ ማቋቋሚያ፣ በተቃውሞ ለወደሙ ንብረቶች መልሶ ግንባታ ወዘተ ይውላል። ሰላም ለማምጣትና የሀገር ሁለተንተናዊ ልማት ላይ ለማተኮር የፖለቲካ መሪዎች ከጠላትነት እንዲሁም ከጭፍን ተቃዋሚነት «የምራቸውን» መውጣትና በመቀራረብና በድርድር መሥራት ይገባቸዋል። ሕዝቡ ጽንፍ የያዘ አቋማቸውን የሚቀበልና የሚደግፋቸው ከሆነ ያንን ተቀባይነት ላለማጣት ያንኑ የጽንፍ ፖለቲካ ከማራመድ ወደኋላ አይሉም። ሕዝቡ በተገኘው አጋጣሚ አይ ማለት ያለበት፣ ድጋፉንም በጥንቃቄ ማድረግ ያለበት ለዚህ ነው።
* * * * *

2/ የኦሮሞ ፖለቲካ እስረኞችን በተመለከተ


ኢኮኖሚክስ ውስጥ Externality Theory የሚባል ጽንሰ-ሀሳብ አለ። በሙያተኞች በተለይም በኢኮኖሚክስ ምሁራን በዝርዝር ሲነገር በውስጡ በርካታ ክፍሎች ያሉትና ወሰብሰብ ያለ ጽንሰ-ሀሳብ ነው። በ11ኛ ክፍል የኢኮኖሚክስ ትምህርት ላይ የተዳሰሰ ስለሆነ ታስታውሱት ይሆናል። በአጭሩ ግን «ኤክስተርናሊቲ» ማለት አንድ አምራች የሚፈጠር ነገር ግን ዋጋው በአምራቹ ወይም ለአምራቹ የማይከፈል ወጪ ወይም ጥቅም (cost or benefit) ነው። «ኤክስተርናሊቲ» አዎንታዊ (positive) ወይም አሉታዊ (negative) ሊሆን ይችላል። እንዲሁም ደግሞ «ኤክስተርናሊቲ» አንድን ምርት ወይም አገልግሎት ከማምረት ወይም ከመጠቀም ሊመጣ ይችላል። ወጪና ጥቅሙ ግለሰባዊ (ለግለሰብ ወይም ለድርጅት) ወይም ማህበራዊ (ማህበረሰቡን በጠቅላላ) የሚነካ ሊሆን ይችላል።
ለምሳሌ፣ አንድ ፋብሪካ በአንድ አካባቢ በመገንባቱ ምክንያት በአካባቢው ላይ አካላዊ ወይም የድምፅ ብክለት ቢያመጣና በዚህ ምክንያት የአካባቢው ነዋሪ ቤት የመሸጫ ወይም የኪራይ ዋጋ ቢቀንስ ኹኔታው አሉታዊ «ኤክስተርናሊቲ»ን ይገልፃል። በተቃራኒው ደግሞ ይኸው ፋብሪካ የሚፈጥረው ምንም ዓይነት ብክለት ባይኖረውና፣ ለዚህ ፋብሪካ አገልግሎት ሲባል በአካባቢው በፊት ያልነበሩ መንገድና፣ አትክልቶች ወይም ሌሎች ነገሮች በመገንባታቸው ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች የቤት ዋጋ ቢጨምር ኹኔታው በአዎንታዊ «ኤክስተርናሊቲ» ይገለፃል። «ኤክስተርናሊቲ» አሉታዊ ነው የሚባለው ማህበረሰባዊ ወጪው ከግለሰባዊ ወጪው ሲበልጥ ነው።

* *
ድርድርም የራሱ Positive & Negative externalities አሉት። ድርድሩ ተገቢ ነው? አዋጭ ነው? ጥቅሙ ከጉዳቱ ያመዝናል? ማኅበረሰባዊ ፋይዳው ከግለሰባዊ ጥቅሙ ይበልጣል? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በማንሳት የተሻለው የቱ ነው ብሎና መዝኖ መቀበልና ያለመቀበል የተደራዳሪዎች ፈንታ ነው። አንደኛው ወገን የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ጥቅም እያመዘነ እንደሆነ እያየ፣ መንግሥት ከድርድሩ የሚያተርፈው ነገር መኖሩን ብቻ አይቶ ድርድሩን ያለመፈለጉ ሁሉም ወገን ላይ ኪሣራ ነው ሊያመጣ የሚችለው። «ኃይሌ ፊዳ፣ ሰናይ ሊኬ እና ቡችሎቻቸው ይሰቀሉ» ብሎ አደባባይ የወጣው ሕዝብ አሁንም በሌላ ጊዜ እና አውድ ራሱን እየደገመ ነው። በእስር ላይ እያሉ የረሀብ አድማ ማድረጋቸው፣ መታመማቸው፣ ተገቢውን ሕክምና ያለማግኘታቸው፣ የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው መግለፃቸው እና የመሳሰሉትን ችግሮቻቸውን ሰምተናል። በዚህ መሀል መሪዎቹን በሞት ወይም በቋሚ የጤና ችግር ምክንያት ቢያጣ ከነርሱ ባላነሰ ኹኔታ የሚጎዳው ሕዝቡ ነው። ይሄንን እና መሠል ጉዳዮችን ነው መመዘን ያለብን ብዬ አምናለሁ።

“ድርድር” አንዱን ወገን ብቻ «የሚጠቅም» ውጤት የሚኖረው ከሆነ ምኑን “ድርድር” ሆነው? እዚህ ጋር «የፖለቲካ እስረኞቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊፈቱ ይገባል» የሚል ሀሳብ ሊነሳ ይችላል። ይሄ የኔም ፍላጎት ነው። ነገር ግን let’s be pragmatic, do you really think the government will do that? መንግሥት እንደዚያ ዓይነት አቋምና ፍላጎት ቢኖረው ኖሮ ቀድሞውኑ እስሩ ባላስፈለገም ነበር። ይህ ባልሆነበት ኹኔታ እሱን ማንሳትና የድርድር ሀሳቡን ቢያንስ በሀሳብ ደረጃ እንኳን መግፋት «ብዬ ነበር» ከማለት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም። «እስከዛሬ የት ነበሩ? ለመፍታት ለምን አላሰቡም ወይም አልሞከሩም?» ብለንም መጠየቅ እንችላለን። ጥያቄው የመንግሥትን ዓላማ ያሳየን ይሆናል እንጂ እስረኞቹን አይፈታልንም።

ከዚህ በተጨማሪ “ሀሳቡን ማን አመጣው?” የሚለው ጉዳይም ያን ያህል አስፈላጊ መስሎ አይታየኝም። ከሰውዬው ይልቅ ሀሳቡን እና የሀሳቡን አዋጭነት ነጥሎ ማየትና መመርመር ተገቢ ነው። ምናልባት በዚህ አጋጣሚ ዶ/ር ደረጀ ገረፋ ቱሉን ማንሳት ነገሮችን ግልፅ ለማድረግ ተገቢ ይሆናል። ሦስት እና አራት ዓመታት ወደኋላ ተመልሰን ብናይ ዛሬ የሚከሰስበትን የወገንተኝነት ክስ የሚያነሱት ጥቂት የአማራ ብሔርተኞች ብቻ ነበሩ። በኦሮሞ ጥቅምና ጉዳይ ይደራደራል ብለን ደፍረን ለመናገር በቂ ማስረጃ ማናችንም አልነበረንም። በዋናነት ደግሞ ወከልነው ላሉት ሕዝብ ሳይሆን ለፖለቲካ ድርጅታቸው እና ለግለሰቦች ታማኝ የሆኑ ፌስቡክ ላይ የሚፅፉ ሌሎች ካድሬዎችን እና ባለሥልጣናትን ያየ ሰው ዶ/ር ደረጀን በጅምላ ከመወረፍ ይቆጠባል። እንዲያም ሆኖ ነገሮች ተቀያይረው ዛሬን ደርሰናል። ዛሬ ዶ/ር ደረጀን የመንግሥት ደጋፊ አድርጎ ማየት ይቻላል፣ ነገር ግን ከዚሁ ጭብጥ ብቻ በመነሳት እርሱ ያቀረበውን የድርድርና የእስረኞች መፈታትን ጉዳይ ማጣጣል እና መንግሥትን ለመጥቀም የተነሳ ሀሳብ አድርጎ መደምደም ልክ አይሆንም። ዛሬ ላይ ሁላችንም አምና እና ካቻምና እንዲሁም ከዚያ በፊት ባለን መረዳት እና አቋም ላይ አይደለም ያለነው። ነገም እንዲያው ነው፣ በገጠመኞቻችን፣ በዕውቀታችን፣ በመረጃዎች እና በዕድሜ ስንለወጥ አቋማችን ይለወጥ ይሆናል። በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በለውጣችን ውስጥ ከሚገጥሙን አላስፈላጊ ቁጭት ሊያድነን የሚችለው ሰውየውን ሳይሆን ሀሳቡን መሠረት ያደረገ ግምገማና ውሳኔ ነው።

የፖለቲካ እስረኞችን መፈታት በተመለከተ ብዙ ጊዜ የሚረሳው ነገር ደግሞ በስም፣ በመልክና በዝና የምናውቃቸውን ሰዎች መፈታት የተመለከተ መሆኑ ነው። በተደጋጋሚ የታየ፣ በፖለቲካ እስረኞቹ በራሳቸውም ብዙ ጊዜ በአንገብጋቢ ጉዳይነት ሲነሳ የማንመለከተው ነገር ነው። በዚህ ረገድ ኦቦ ዳውድ ኢብሳን ፈለግ መከተል ያስፈልጋል። ከሦስት ዓመት በፊት በአሸባሪነት ዝርዝር ላይ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ግለሰቦች በመንግሥት ከዚያ ዝርዝር ሲፋቁና ወደሀገር ቤት ሲገቡ ስለ 1500? ወታደሮቻቸው ጉዳይ ጉዳዬ ብለው የተደራደሩት እሳቸው ብቻ ናቸው። እነአቶ ነዓምን ዘለቀ ከወራት በኋላ ተከታዮቻቸው ትዝ ብለዋቸው በጉዳዩ ላይ የፃፉትን ትዊት ያየ ያስታውሳል። ድርድሩ በየዞኑ፣ በየወረዳው፣ በየከተማው የታሰሩ ወጣቶችን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን ይኖርበታል።

እዚህ ጋር ግን ዶ/ር ደረጀም ሲያነሳው የነበረ፣ እኔም ለማወቅ የምፈልገው አንድ ጥያቄ አለ። አደራዳሪዎቹ እነማን ናቸው? ተዓማኒነት፣ ተቀባይነት እና ተሰሚነታቸው ምን ያህል ነው? እስካሁን ድርድሩን ለመጀመር የተደረገ ነገር አለ? እስረኞቹ «ያናገረን ሰው የለም» ማለታቸውን እዚሁ ፌስቡክ ላይ ከነበሩ ልጥፎች አይተናል። ሀሳቡን አንስቶ ማንሸራሸሩ፣ መወያየቱ ጥሩ ሆኖ ሳለ፣ በባዶ ሜዳ ባይሆን መልካም ነው። ዶ/ር ደረጀም የድርድር ሀሳቡን በማህበራዊ ሚዲያ ላለው ሕዝብ ከማቅረብ ባለፈ ቅርበቱንና ተሰሚነቱን ተጠቅሞ ውሳኔ ሰጪ ለሆኑት አካላት አቅርቦ ለማሳመን ያደረገው ነገር ካለ ቢነግረን ጥሩ ነው።
የሆነ ሆኖ ግን ድርድሩ እስረኞቹ በእስር እንዳሉ እንዲደረግ እንዳልታሰበ ዕምነት አለኝ። በመንግሥት ወገን የሚቀርበውን መደራደሪያ ነጥብ ከመቀበል ውጪ ያለው አማራጭ በእስር መቀጠል በሆነበት ኹኔታ መደራደር የተደራዳሪዎችን ዓቅም ይገድላል። የቦክስ/ቡጢ ግጥሚያ (ከድርድር ውጪ ያለ ኹኔታ) ላይ እጆችህ ወደኋላ ታስረው በጉልበት ከሚበልጥህ ይቅርና ከእኩያህ ወይም ከታናሽህ ጋር ቡጢ ገጥመህ ትክክለኛ አቋምህን ማሳወቅ አትችልም። 'ለመኖር' ብለህ ለግጥሚያው ብትስማማም በውስጥህ ''እጆቼ የተፈቱ ቀን አሳይሀለሁ' የሚል ሰውኛ ስሜትን ማሳደርህ አይቀርም። ድርድርም ነፃ ካልሆነ “የተሻለ የመደራደር ዓቅም ሲኖረኝ ይሄንን ጉዳይ ዳግም አንስቼው ለውጠዋለሁ” የሚል አስቀያሚ ኹኔታ መፍጠሩ አይቀርም። አንድ ጉዳይ ላይ በየጊዜው መበጣበጥን ደግሞ ማናችንም አንፈልገውም።
* * * * *

3/ ሲጠቃለል . . .

“ኮሶ” የሚባለው ከኮሶ ዛፍ የሚሠራው ባህላዊው የኮሶ መድኃኒት እጅግ በጣም ይመርራል ይባላል። «ዶሮ ማታ! ዶሮ ማታ!» እየተባለ የሚጠጣ መድኃኒት ነው። ከምሬቱ የተነሳ ትልቅ ሰው እንኳን “ከጠጣህ ማታ ዶሮ ወጥ ይሰራልሃል» እየተባለ በማባበል ነው የሚጠጣው ይባላል። የኮሶ ትል የታየው ሰው ሁለት አማራጮች አሉት፤ በሽታው እስኪገለው ድረስ ከትሉ ጋር በሰው ፊት እየተዋረደና እየተሳቀቀ መኖር ወይም ጨክኖ ኮሶውን ጠጥቶ መፈወስ።
ድርድር ኮሶ ነው! እየመረረን የምንውጠው መድሃኒት! ከተደራዳሪዎቹ መሃል በሕግ እንዲጠየቅና እንዲቀጣልን የምንፈልገው፣ በደሉን ያልረሳንለትና ይቅር ያላልነው፣ ስናየው የሚያመን አካል፣ ግለሰብ ወይም ቡድን ይኖር ይሆናል። ድርድር ከበቀል ወይም ከማሕበረሰባዊ ድኅነትን/ፈውስ መምረጥ ስለሚኖርብን ብቻ ሁላችንም በጋራ እየመረረን የምንጠጣው ኮሶ ነው።
* *
አንድ ወቅት ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ አውሮፕላን ይጠለፋል፡፡ በኋላ ላይ . . . የሰማይ ስባሪ የሚያክል ጠላፊ መነጋገርያውን አንሰቶ . . .
«እኔ ገንዘብ አልሻም . . . ሀገሬም አልበደለችኝም!!! . . . በቃ እኔ . . . የምፈልገው እዚህ ፕሌን ውስጥ ያላችሁትን ሴቶች ሁሉ መተኛት ነው» ምናምን አለ
ፕሌኑ ውስጥ ጉርምርምታ ሆነ!!!

ከመሀል . . . አንዲት መልኩንም ቅርፁንም . . . አዳልቶ ያደላት ልጅ ተነስታ . . . ትንፋሿ ቁርጥ ቁርጥ እያለ መናገር ጀመረች. . .
«ጌታዬ . . .እንደምታየው . . . አውሮፕላኑ ውስጥ . . . ህፃናትም . . . አረጋውያንም ተሳፍረዋል። . . . እባክህ . . . እነርሱን ተውና . . . እኔን እንደፈለግክ አድርገኝ» ብላ ሳትጨርስ ከጀርባዋ የነበሩት አሮጊት ተመንጥቀው ተነስተው በቁጣ ተናገሩ . . .
« አ…..አ……አ…..ይ……..የምን መንቀልቀል ነው? ሁሉንም ብሏል ሁሉንም ነው::…አርፈሽ ቁጭ በይ!!»
* *

አንግዴህ ስለድርድር ከተነሳ ሁሉንም የፖለቲካ ተዋንያን ያካተተ መሆን አለበት። ሁሉን አካታች፣ አሳታፊና ሐቀኛ ሀገር አቀፍ ዲያሎግ ያስፈልገናል!!
ሁሉንም ያሳተፈ ብያለሁ፣ ሁሉንም !!

Please wait, video is loading...