Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

እሳት ወለድ ኣሞሮች - የጀግናው የኢትዮጵያ ኣየር ኃይል ገድል በጭልፋ

Post by Meleket » 26 Oct 2021, 09:40

እሳት ወለድ ኣሞሮች - “የጀግናው” የኢትዮጵያ ኣየር ኃይል “ገድል” በጭልፋ

ምጽዋ በህዝባዊ ግንባር ቁጥጥር ስር ከገባች ሁለት ወራት አልፎ ነበር። በዚያን ጊዜ ገና የ13 አመት ልጅ ብሆንም የተፈጸመውንና የሆነውን ሁሉ ልቅም አድርጌ አስታውሰዋለሁ። በሰው ልጆች ህይወት ላይ ፍጹም ከአእምሮ ሊፋቁ የማይችሉ አስደሳችም ሆነ አሳዛኝ ገጠመኞች ሊኖሩ ይችላሉ። የእድል ጉዳይ ሆኖ በእኔ አእምሮ ላይ ለዘልአለሙ ተመርጎ የቀረው ትዝታ አሳዛኝ ሆኖ ቀርቷል።

ሻዕቢያ ምጽዋን ከመቆጣጠሩ በፊት አባቴ በሳሊና የጨው ማምረቻ ፋብሪካ ሾፌር ነበር። የሞቀ ነበር ቤተሰባችን፣ ሶስት እህቶች ነበሩኝ። የመጨረሻዋ ልጅ ስምረት ገና የሶስት አመት ጨቅላ ስትሆን፤ ታናሼ ራህዋ በመላ ቤተሰቡ ተወዳጅ ልጅ ነበረች። ይህ ደስተኛ ቤተሰብ ከሚያዝያ 22 1990 ጀምሮ ለማሰብና ለማመን የሚከብድ አደጋ ወደቀበት።

ነገሩ ወዲህ ነው . . .

ምጽዋ ከተያዘች በሁዋላ አባቴ ስራ አቆመ። በአባቴ ስራ መፍታት ምክንያት የጎደለውን ለመሙላት ብሎኮ በተባለው መሃል ከተማ እየተዘዋወርኩ ሲጋራና ማስቲካ መሸጥ ጀመርኩ። ማለዳ እና ተስያት ላይ የአይሮፕላን ድብደባ ስለሚኖር ለመዘዋወር ስጋት አለ። ስለዚህ ብዙውን ጊዜ ከቤታችን አካባቢ ባለ ድልድይ ስር ተጠልለን እንውል ነበር።

ሚያዝያ 22 1990 በእለተ ሰንበት ከሁለት ጓደኞቼ ጋር ብሎኮ ነበርኩ። ሳንድሮ እና ማህዲር ይባላሉ። እንደወትሮው ማስቲካና ሲጋራ ለመሸጥ እየሞከርን እየተጫወትንም ነበር። ቦምብ ጣይ ሚጎች ከአሁን አሁን መጡ ስለሚባል ሰው ሁሉ ጨርሶ እስኪመሽ ስጋት ላይ ነበር። አባቴ ከመንገዱ ዳርቻ አንድ ብረት ነገር ላይ ቁጭ ብሏል።

በድንገት ጫጫታ ሆነ።

ሁለት የደርግ ጀቶች ከቀይባህር አግጣጫ አፍንጫቸውን ተክለው መጡብን። ሁሉም ነገር በቅጽበት የሆነ ነበር። አባቴ በተቀመጠበት እና እኔ ባለሁበት መካከል የሆነ ነገር ወደቀ። ሁዋላ እንደተረዳሁት ክላስተር ቦምብ ነው። ቦምቡ ሲወድቅ ሃይለኛ ግፊት ከመሬት አንስቶ ወረወረኝ። ተንከባልዬ ደረቅ መሬት ላይ ወደቅሁ። ስቼ ነበር። ሩሄን ሳውቅ የወደቅሁበት መሬት ቆረቆረኝ። ራሴን ስነካ በስብሷል። ደም መሆንኑን ያወቅሁት ቆይቼ ነው። ላብ ነበር የመሰለኝ። አይኖቼን ገልጬ ሳስተውል ዙሪያዬ ጉም በመሰለ አቧራ ተሸፍኗል


ከወደቅሁበት ቀና ብዬ አካባቢውን ስመለከት ቺፍ አየለ ሻይ ቤት ተደርምሶ ሁለቱ ጓደኞቼ ፍርስራሹ ስር ወድቀው አየሁ። ይጮሁ ነበር መስለኝ። ጆሮዬ ግን አይሰማም። አፋቸውን ከፍተው ሲወራጩ ግን ይታየኝ ነበር። ከሩቅ የሚመጣ የሚመስል ጫጫታም በጆሮዬ አካባቢ እንደ ቢምቢ ይሰማል። አባቴ ወደነበረበት ቦታ ስመለከት ወድቆ አየሁት።

አካባቢውን አስተዋልኩ።

እጃቸው፡ እግራቸውና ጭንቅላታቸው የተቆራረጡ ሰዎች፣ በደም የጨቀየ ሬሳ እዚህም እዚያም ወዳድቆ አየሁ። በቦምብ ፍንጣሪ የተበሳሳ ሰውነት። ጆሮ የሚበሳ ጩኸት ማቋረጫ የለውም። ሰው ያበደ ይመስል ከወዲያ ወዲህ ይካለባል። ድብልቅልቅ ያለ እና አሰቃቂ ነበር።

ወደቤቴ ሮጥኩ። ሶስት እህቶቼና እናቴ ተሸሽገው ከዋሉበት ድልድይ ስር ወጥተው ወደ ቤት ገብተው ነበርና እነርሱን ለማግኘት እየጓጓሁ ሮጥኩ። ቤታችን ከነበርኩበት ቦታ ሩቅ አልነበረም።

ስደርስ እንደ ሃውልት ደንዥዤ ቆምኩ።

ቤታችን በቦታው አልነበረም። ቤታችን ከነበረበት ቦታ ላይ ተቃጥሎ በመጨስ ላይ ያለ የቆሮቆሮና የእንጨት ፍርስራሽ ጠበቀኝ። ደመነፍሴን ወደ ቤታችን ደጃፍ ስጠጋ እናቴ እህቴን ይዛ ከፊቴ ተከሰተች። እህቴ ሰላማዊት በደም ጨቅይታ ነበር። እህቶቼን ባለማየቴ መደንገጤና መጠየቄ ትዝ ይለኛል።

“ስምረት የታለች?”

“ራህዋ የታለች?!”


እናቴ ግራና ቀኝ ክንዶቼን አጥብቃ ይዛ፣ “ሁለቱም ሞተዋል!!” አለችኝ። ከዚያም እጄን ይዛ እየጎተተች ከአካባቢው አራቀችኝ። የተቆራረጠውን የህቶቼን አስከሬን እንዳልመለከት መከልከሏ ነበር። ሁለታችንን ይዛ ቀን ቀን ወደ ምንሸሸግበት ድልድይ ስር መለሰችን።

ህመም ይሰማኝ ጀመር። ራሴ ላይ የተመታሁ ይመለኛል። ምኔ ላይ ጉዳት እንደደረሰብኝ ግን በትክክል አላውቅሁም። እናቴ መላ አካሌን በእጆቿ ከፈታተሸች በሁዋላ በነጠላ ቅዳጅ ራሴ ላይ አሰረችልኝ። በግምት ከአንድ ወይም ከሁለት ሰአት በሁዋላ የደርግ ጄቶች ተመልሰው እንደማይመጡ ተገመተና ቁስለኞችን መርዳት የሞቱትን መቅበር ተጀመረ።

አባቴ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ከድልድዩ ስር ወጣን። ቦምቡ ወደ ወደቀበት ቦታ ስናመራ እናቴ በድንገት ተዝለፍልፋ ወደቀች። በዙሪያዬ የሚታየው ቅዥትና ሌላ አለም ይመስላል። የተቆራረጡ እጆች፣ እግሮችና ጭንቅላቶችን በአንድ ላይ እየከመሯቸው ነበር። ካሜራ የያዙ የሻዕቢያ ታጋዮች እነ ነጭ የውጭ አገር ሰዎች በአካባቢያችን እንደነበሩ ትዝ ይለኛል። ይቀርጹን ነበር። “ማማ! ማማ!” እያልኩ እናቴን ለማንቃት ያደረግሁት ሙከራ፥ ስለ እናቴ መሞት ከእህቴ ከሰላማዊት ጋር ማውጋቴ ትዝ ይለኛል።

እናቴን ከእህቴ ጋር ትቼ አባቴን ፍለጋ ሄድኩ። እዚያው ከነበረበት ቦታ ወድቆ ሲያቃስት አገኘሁት። “ባባ! ባባ!” እያልኩ ስነቀንቀው “እ! እ!” የሚል ድምጽ ከማውጣት በቀር ምንም አያውቅም። ራሱን ስቶ ነበር። ግራ እግሩና አይኖቹ ላይ ነበር የተመታው።

እርዳታ ሰጪ ታጋዮች ደረሱና አፋፍሰው በመኪና ጭነው ወሰዱን። እናቴ ብዙም አልቆየች የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ትሰጥበት ከነበረው ቦታ አረፈች። አባቴ፣ እህቴን እኔ ግን ህይወታችን ተረፈ። በሌሊት ጭነውን ለተሻለ ህክምና ወደ አፍአበት ተላክን። በጉዟችን ወቅትም ሆነ በምናርፍበት ቦታ ሁሉ የደርግ አሞሮች የእሳት አሎሏቸውን ጭነው ያጅቡን ነበር። በእድል አመለጥን እንጂ ከኛ በፊት ይጓዝ የነበረ መኪና ኢላማቸው ውስጥ ገብቶ ጋይቷል። በአፍአበት ህክምና አባቴና እኔ ፈጥኖ ተሻለን። እህቴ ግን ጉዳቷ ስለበረታ በህክምና ጣቢያ እየተረዳች ብዙ ወራት ቆየች።

የነጻነት ትግሉ አልቆ ደርግ ሲወድቅ ወደ ምጽዋ ተመለስን። እናም ከአባቴና ከእህቴ ጋር አዲስ ኑሮ ለመጀመር ጥረት አደረግን። የነበረንን ቤተሰባዊ ደስታ መመለስ ግን የሚቻል አልነበረም። ከውድ ቤተሰባችን ሶስት አጥተናል። በወጉ እንኳ አልቅሰን አልቀበርናቸውም።

የተረፍነውም ጤናችን የተጓደለ ነበር። እኔ የራስ ቅሌ ላይ ስንጥቃት ስለነበር የህመም ስሜት አለኝ። አንደኛው ጆሮዬም አይሰማም። እህቴ እጇ ላይ ህመም አለባት። አባቴ አይኖቹ ተጎድተው ነበር። እንዲህ ሆነን ወደ ምጽዋ ተመለስን።
+ + +
ዛሬ ጎልማሳ ሰው ነኝ። አግብቼ የሁለት ልጆች አባት ሆኛለሁ። እህቴ ሰላማዊትም እንዲሁ ባለትዳርና የልጆች እናት ሆናለች። ስዊዘርላንድ ትኖራለች። አባቴ እድሜ ተጨምሮበት ሁለቱም አይኖቹ ታውረዋል።

በልጆቼ ፊት ደስተኛ ለመምሰል መሞከሬ አልቀረም። ከመወለዳቸው በፊት ምን እንደተፈጸመ አያውቁም። ንጹህ ፈገግታቸው፣ ሳቃቸውና ደስታቸው ያለፈውን ሁሉ እንድረሳ ቢጫነኝም መርሳት እንደማይሆንልኝ ግን አውቀዋለሁ። የአካልና የአእምሮ ጠባሳውን ትቶብኝ ያለፈው መራር ድርጊት በቀሪው የህይወት ዘመኔም አብሮኝ ይኖራል። ምርጫ የለኝም። ልርሳህ፣ ላስወግድህ ብትለውም የሚሆን አይደለም። ይህ ሁሉ ከተፈጸመ ረጅም ጊዜ ሆነ። ያለፈው ሁሉ መልሶ መላልሶ ወደ አእምሮዬ እየመጣ ይረብሸኛል። ትውስታውን አልወደውም። ከህይወቴ የትዝታ ግድግዳ ላይ ፍቄ ለዘልአለሙ ልረሳው ግን አልችልም።

(በ1990 በወርሃ የካቲት ሻዕቢያ የምጽዋ ወደብን ነጻ አወጣ። በአካባቢው የነበረውንም የደርግ ጦር ሰራዊት ጠራርጎ ደመሰሰው። ይህን ተከትሎ ደርግ በተመሳሳይ ኢላማውን የምጽዋ ነዋሪ ከሆኑ ሲቪል ሰዎች ላይ አደረገ።)

(ከሚያዝያ 4 እስከ ሰኔ 12 1990 ባለ ጊዜ በምጽዋ ነዋሪዎች ላይ 7 ጊዜ ብርቱ የአይሮፕላን ድብደባዎች ተካሂደዋል። በዚህም 124 ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ 332 ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በመቶዎች የሲቪል መኖሪያ ቤቶችም ፈራርሰዋል።)

(ሚያዝያ 24 1990 ምሽት 6፡15 ሰኣት ላይ የደርግ ሚጎች ከእንጨትና ከቆርቆሮ ከተሰሩ የምጽዋ የህዝብ መኖሪያ ቤቶች ላይ ባደረጉት የክላስተር ቦምብ ድብደባ በጥቅሉ 37 ሲቪሎችን ሲገድሉ፤ 120 በቀላሉና በከባዱ ማቁሰላቸውን ሰነዶች ይጠቁማሉ። የዚህ ታሪክ ባለታሪክ ተስፋይ አብርሃ ከተጎጂዎች ቤተሰብ አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል።)


(ጃንሆይ እና ደርግ ያልተነገሩ መራር ታሪኮች ገጽ 297-301 "እሳት ወለድ ኣሞሮች" - ጸሃፊ ደምሳስ ጸጋይ፡ አርታኢና ተርጓሚ ተስፋዬ ገብረኣብ ሃምሌ 2018)


+++
እንዲህም አድርጎ ጀግንነት የለም! ጀግንነት ብሎ ዝም ነው! ድንቄም ጀግንነት!

የዛሬን አያድርገውና የኢትዮጵያ አየር ኃይል የኤርትራ ህዝብ ላይ እንዲህ ዓይነት ግፎችን ይፈጽም ነበር። ይህን የመሰለ አሰቃቂ ግፍ ፈጽሞም አየር ኃይሉ ሳያፍር ወታደራዊ ኢላማዎችን ደመሰስኩ ነበር የሚለው። ዛሬ ደግሞ ተረኛዉ የትግራይ ህዝብ እንዳይሆን ኤርትራዉያን የመሃልና የመስመር ዳኞች ከወዲሁ እናሳስባለን ለማለት ነው። ሰላማዊው የኤርትራ ህዝብ ክፉ ያደረገን በክፋት ሳይሆን በፍቅር የማሸነፍ ልቦናን የታደለ መሆኑንም ለመጠቆም ነው።