Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
eden
Member+
Posts: 9272
Joined: 15 Jan 2009, 14:09

ኢትዮጵያችን የገባችበት አይወጤ የሚመስል ቅርቃር ቀላል መፍትሄ አለው ባይ ነኝ

Post by eden » 09 Sep 2021, 21:40

ዋናው ጉዳይ፣ ሰዉ ቅን ልቦና እንዲኖረው ያስፈልጋል። ሲጀመር፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ቅን ልቦና አላጣም። ችግሩ ግን፣ በሁሉም በኩል ባሉ የፖለቲካ ሃይሎች፣ ያለ እረፍት የሚረጨው፣ ይወቁትም አይወቁትም፣ በቀጥታም ሆነ በሌላ፣ ህዝብ ላይ ያተኮረ ጥላቻን የሰነቀ ፕሮፓጋንዳ ነው።

በጣም የምቀርባቸውና የምወዳቸው የቅርብ ሰዎች፣ ውስጣቸው ንፁህ እንደሆኑና ለሌላው መልካም የሚመኙ መሆናቸውን የምመሰክርላቸው ሰዎች፣ በሚያስደነግጥ መልኩ፣ በሚረጨው ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆነዋል። ማለትም፣ በሰዉ እተማመናለው ግን ፕሮፓጋንዳው እንዲስቱ አረጋቸው። ለነገሩ፣ እዚህ ፎረም ላይም፣ አይኔ እያየ፣ የተቀየሩ ነፍ ናቸው። ይህ ነው የአገሪቱን ችግር፣ እንዲሁም መፍትሄውን ያመላከተኝ።

ችግሩ፣ አይነቱና ቅርፁ ቢለያይም፣ በሁሉም በኩል የሚረጨው ፕሮፓጋንዳ ህዝብ ላይ ያተኮረ በመሆኑ፣ በዚሁም ምክንያት፣ ህዝቡ የሌለበትንና ያልነበረበትን መንፈስ መሸከሙ ነው። ይህም፣ ተራውን ህዝብ ሳይወድና ሳያስበው፣የችግሩ ተባባሪ ያደርገዋል ማለት ነው። አዎ፣ ህዝቡ ራሱ ላይ ለሚወርደው የግፍ ዶፍ፣ ተባባሪ እየሆነ ነው - ሳይፈቅድ!

የሚሞተው፣ አካሉን የሚያጣው፣ ንብረቱንና ገቢውንም የሚያጣው፣ ያው የፈረደበት ህዝቡ ራሱ ነው። ትምህርትና ጤናውንም አጥቶ፣ በረዥም ግዜ፣ ምናልባትም እድሜ ልኩን፣ ይባስ ብሎም በልጅ ልጁም ግዜ የማይፈታ ችግር ውስጥም የሚወድቀው፣ አሁንም ህዝቡ ነው።

መፍትሄውም፣ ህዝቡን ማንቃት ነው። ማንቃት ቀላል ነው። እንዴት? ችግሩን ባይፈጥረውም፣ ችግሩን ግን መፍትሄ አልባ እንዲሆን ያስመሰለው፣ የህዝቡ ለፕሮፓጋንዳ እጅ መስጠቱ ነው። ህዝቡ ራሱን ይሁን። ህዝቡ ራሱን ይመን።

እኛም ሳይማር ያስተማረንን ይህን ትልቅ ህዝብ፣ ይሄንኑ ደጋግመን እንንገረው። ፕሮፓጋንዳው እንደሆነ፣ እንደምናየው፣ መመለሻ የለውም። ግን፣ ህዝቡ ራሱን ይሁን። ህዝቡ ራሱን ይመን። መፍትሄው ይሄን ያህል ቀላል ነው ጥያቄው ግን ምን ያህል እንሆናለን ለዚህ የምንሰለፈው፣ ምን ያህልስ እንሆናለን ፕሮፓጋንዳውን እያራገብን፣ ህዝቡን እርስ በርስ የምናናክሰውና የህዝባችንን ችግር የምናስቀጥለው ነው።