(በላይ በቀለ ወያ #ከሰላም ግንባር)
የዛሬ ሀያ ዓመት
በሁለት አካሎች ፣ የአስተሳሰብ ጥመት
ለብዙዎች እልቂት ፣ ለጥቂቶች ሹመት
ምክንያት የሆነ ፥ "ክተት" እና "ዝመት"
ልክ እንደ ነጋሪት
በሚጎሰም ጊዜ ፣ የኔ አባት ዘምቷል
የቀኝ አይኑንና ፣ የግራ እግሩን አቷል
በጦርነት ግንባር ፣ ፈሶ ቀርቷል ደሙ
ግን ግን እስከዛሬ
አልተፈታለትም
"አንድነት" የሚባል ፣ ያዘመተው ህልሙ።
ዛሬም አንድ ዓይና ነው ፣ ዛሬም ያነክሳል
ኢትዮ ኤርትራ
እርቅ ወረደ ሲባል ፣ ይስቃል ያለቅሳል
"ወይ ታሪክ" እያለ
ሳቅና እንባውን ፣ ባንድ ዓይኑ ያፈሳል
"ታሪኬ" የሚለው
ታሪክ ሲደገም ሲያይ ፣ ቁስሉን ያስታውሳል።
ይስቃል ያለቅሳል ፣ያለቅሳል ይስቃል
እኔ ግን እላለሁ
"ከታሪክ የሚማር ፣ ታሪክ መስራት ያውቃል
በነግ ታሪክ ያፍራል ፣ ከትላንት ማይማር
ዛሬ ላይ የነቃ
ሺ ህዝብ አያስበላም ፣ ለጥቂቶች ቁማር።
ስለዚህ አልዘምትም!
ወንድሜን አልገድልም ፣ በወንድሜ አልሞትም!
ጠንቅቄ አውቃለሁ!
ፍቅር ያሰረውን ፣ በጦር አይፈቱትም!
።።።።።
ከሀያ ዓመት ኋላ
ለብዙዎች እልቂት ፣ ለጥቂቶች ተድላ
ሀገር እንደ ድመት ፣ ልጇን እንድትበላ
በዛም በዚም በኩል
ዝመት ክተት ብሎ ፣ ጦሩን ያሰልፋል
ከታሪክ ተምሮ
"ታረቅ ተወያይ" ሚል ፣ እንዴት አንድ ይጠፋል?!
ነገ እርቅ ላይቀር
ሰው እንዴት ታሪኩን ፣ ፀፀት ላይ ይፅፋል?!
።።
እኔ ግን እላለሁ!
ባለጊዜ ያልፋል ፣ ሀገር ግን አታልፍም
ወንድሜን ገድዬ ፣ ፀፀቴን አልፅፍም
ለጥቂቶች ስልጣን ፣ ሺህ ሆኜ አልረግፍም!
ስለዚህ አልዘምትም
ወንድሜን አልገድልም ፣ በወንድሜ አልሞትም።
ለጥቂቶች ስልጣን ፣ ለጥቂቶች ቁማር
አውቃለሁኝና
በታሪኩ እንደሚያፍር ፣ ከታሪክ ማይማር
ላሉት ልቦና ይስጥ ፣ ለሞቱት ነፍስ ይማር!!!
Please wait, video is loading...