Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
sarcasm
Senior Member
Posts: 10186
Joined: 23 Feb 2013, 20:08

የዋግ ህዝብ የትግራይ ኃይሎችን መዋጋት የለብንም የምልበት ምክንያት - በአሸናፊ ፈንቴ

Post by sarcasm » 24 Jul 2021, 09:44

መዋጋት የለብንም የምልበት ምክንያት
ሰኔ 18፣ 2013 ዓ.ም


ከትላንት ወዲያ ይመስለኛል ህወሓት ያወጣችውን ማሳሰቢያ በማስመልከት አለመዋጋት እንደሚመረጥ ሃሳቤን አቅርቤ ነበር፡፡ ይህን አስመልክቶ አንዳንድ ሰዎች የቁጣ መልስ እየሰጡ ነው፡፡ ኢንቦክስ ያደረጉልኝ አሉ፤ የደወሉልኝ አሉ፤ እኔ ባላያቸውም የእኔን አቋም ጉዳይ አድርገው ፖስት ያደረጉ ልጆች እንዳሉም ሰምቻለሁ፡፡ በግል ያነጋገሩኝ ሰዎች አቋሜ ልክ መሆኑን አምነው ለእኔ በማሰብ ተው ያሉኝ ናቸው፡፡ የፖሰቱት እና ኢንቦክስ ያደረጉት ደግሞ ጦርነት ማድረግ አለብን ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ውስጥ እንደተለመደው በፍረጃ፣ በማጥላላት እና በዛቻ ካልሆነ በስተቀር ሃሳቤን በሃሳብ ለመሞገት የሞከረ ሰው አልገጠመኝም፡፡ ምናልባት ጤነኛ ውይይት ማድረግ የሚፈልግ ካለ፣ መዋጋት የለብንም የምልባቸውን ምክንያቶች ላስቀምጥ፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ በግሌ ህወሓቶች ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ “ሰቆጣ ከተማ እንገባለን” እያሉ ነው ሲባል ከመሰማቴ እና ትላንት ወዲያ ደግሞ ማሳሰቢያ ከመስጠታቸው በስተቀር ወደ ከተማዋ ይገባሉ ብዬ አልጠብቅም፡፡ ከገቡ ግን ልንሰጥ የሚገባን ምላሽ ግብታዊ ሳይሆን በውሉ የተጠና መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ምላሻችንን ከሦስት ጉዳዮች አንፃር መቃኘት ተገቢ ይመስለኛል፡፡

1ኛ) የምንዋጋበት ምክንያት አለ ወይ?

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ህወሓት ሰቆጣ ብትገባ ሰው ልትተናኮል፣ ልትገድል፣ ልታቃጥል እና ልታወድም ትችላለች የሚል ስጋት የለኝም፡፡ ወይም ዋግን ወስዳ የትግራይ አካል የማድረግ ዓላማ አላት ብዬ አላስብም፡፡ ወደ አዋሳኝ የአማራ እና አፋር ክልሎች እየገቡ ያሉት ለአጭር ጊዜ ግብ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ህወሓቶች እነዚህን ቦታዎች እየተቆጣጠሩ ያሉት በወታደራዊ የበላይነት ነው ወይስ በመንግሥት ሳቦታዥ ወይም ስልት የሚለው ጥያቄ ሌላ ጉዳይ ሆኖ አሁን ከክልላቸው ውጭ ብዙ ቦታዎችን እየያዙ እንዳሉ ግልፅ ነው፡፡ በምንም ምክንያት ይግቡ በግሌ አካባቢውን ይዞ የመቆየት ፍላጎት እንኳን ቢኖራቸው አቅሙ ይኖራቸዋል ብዬ አላምንም፡፡ ዋግ ውስጥም ከዚህ የተለዬ መጨረሻ አይታየኝም፡፡

ከዚህ አንጻር ለመዋጋት የሚያበቃ በቂ ምክንያት ሳይገኝ እና የመንግሥት ጦርም እየለቀቀ ባለበት ሁኔታ እኛ የምንዋጋበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ ምናልባት ህወሓት “ዋግ የኔ ነው” የሚል ሃሳብ አንፀባርቃ ቢሆን፣ ወይም ሰዎችን የመግደል እና የማጎሳቆል ወይም በትግራይ የደረሰውን መከራ በሌላው ላይ የማድረስ ፍላጎት ቢኖራት ኖሮ መፋለማችን ተገቢ ይሆን ነበር፡፡ እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ችግር ቢከሰት፣ እኔም ቢሆን ታጥቄ የማልዘምትበት ምክንያት አይኖርም፡፡ አያርገውና በከተማችን ገብታ ህዝብ የመተናኮል ነገር ብታሳይ ከዚህ የተለዬ ምላሽ አይኖረኝም፡፡ አሁን ግን ምንም አይነት ስጋት በሌለበት ሁኔታ የሠላም እድል እያለ በግብታዊነት ወደ ደም መፋሰስ መሄዱን አላምንበትም፡፡

2ኛ) በቂ የውጊያ ዝግጅት አለን ወይ?

ህወሓትን ጠመንጃችን እቤት ሳናስቀመጥ ለመጠበቅ በቂ ምክንያት አለን ከተባለ ደግሞ፣ ነባራዊውን ሁኔታ የሚመጥን በቂ የውጊያ ዝግጅትስ አለን ወይ ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ህወሓት በአሁኑ ሰዓት ምን አይነት ትጥቅ እና ኃይል እንዳላት ይታወቃል፡፡ ጦሩ በምን አይነት ስትራቴጂስቶች እንደሚመራ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ያላቸው ጉልበት አንድ ክልል ሊኖረው ከሚችለው ጉልበት የበለጠ እንደሆነ መካድ የለብንም፡፡ በአንፃሩ በእኛ በኩል ያለው ተዋጊ በክልሉም በፌዴራሉም ትኩረት ያልተሰጠው የደካማ ዞን ጉልበት ነው፡፡ በቂ መሳሪያ፣ ሥልጠና፣ የሰው ኃይል እና ስልታዊ አዋጊ የለንም፡፡ ያለው የኃይል እና የዝግጅት ልዩነት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ መግጠም ማለት ለእኔ ጦርነት ሳይሆን ከወራት በፊት እንደገጠመን አይነት ጅምላ ግድያ ነው የሚሆነው፡፡

ከወራት በፊት 75 አባወራዎችን ለመበተን የተገደድነው በጀግና እጦት ወይም በወኔ አልባነት ሳይሆን በዚሁ የኃይል አለመመጣጠን መሆኑ ከምኔው ተዘነጋ? የዋግ ህዝብ ጀግንነት ከጥንት ጀምሮ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ከምክንያት ቀጥሎ የኃይል ሚዛንም ግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ የኃይል ልዩነቱ በአሁኑ ሰዓት ከወራት በፊት ከነበረው ሁኔታ የበለጠ መስፋቱን እናስተውል፡፡ ከዚህ አንፃር በእኔ እይታ አሁን ከህወሓት ጋር ለመግጠም ብንሞክር ልንከፍል የምንችለው መስዋእትነት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ጦርነት መግደል ብቻ ሳይሆን መሞትም ነው፡፡ አይበለውና ህወሓት ሰቆጣ መግባት ብትፈልግ እና እኛ ደግሞ ለመተኮስ ብንሞክር አሁን የምናጣቸው ልጆች በጣም ወጣቶች፣ የተማሩ፣ ነገ ዋግን ለመቀየር ተስፋ ያላቸው ልጆች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ በስም እና በገቢር የምናውቃቸው ታናናሾቻችን ናቸው፡፡ ይህን ሁኔታ በዝምታ ወይም “በግፋ በለው” ማጀብ ለእኔ የሃላፊነት ስሜት ማጣት ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ አሁን ማሳሰቢያ እየተሰጠበት ያለው ጉዳይ የከተማ ጦርነት ነው፡፡ የከተማ ውጊያ ከተጀመረ ሊደርስ የሚችለው አደጋ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የሚጎዱትም የታጠቁ ልጆቻችን ብቻ ሳይሆኑ ሲቪሊያን ጭምር ናቸው፡፡ ህፃናት ይሞታሉ፤ አሉን የምንላቸው መሠረተ ለማቶች ይወድማሉ፤ ቤቶች ይቃጠላሉ ወዘተ፡፡ በግሌ ይህን ዋጋ ለመክፈል የሚያስችል ምንም ምክንያት አለን ብዬ አላምንም፡፡ ይልቁንም እስካልነኩን ድረስ ሠላማዊ ምላሽ በመስጠት ይህን ክፉ ቀን ጎንበስ ብሎ ማለፍ እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡ አስቀድሜ እንዳነሳሁት ያለመደራረሱን ቀይ መስመር ካለፉ ብቻ ምንም አይነት ጦር ቢኖራቸው መግጠም እና ማሸነፍ እንችላለን፡፡ አሁን እነርሱ ያሸነፉት ከማንም በላይ ጀግና ሆነው ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ግፍ እንዲያበረታው ስለሆነ ብቻ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

3ኛ) ደም የማቃባት ድግስ

የህወሓት ጦር ከመቀሌ ሸሽቶ ተምቤን ከገባበት በተለይም ደግሞ ወደ ዋግ መዝለቅ ከመጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የዋግ ህዝብ ከህወሓት ጋር አለፍ ሲል ደግሞ ከትግራይ ጋር እንዲዳማ ሆን ተብሎ የተሠሩ ነገሮች እንዳሉ አምናለሁ፡፡ ማሳያዎቹን እንመልከት፡፡

ህወሓት ካፈገፈገ በኋላ በተንቤን መመሸጉ መታወቁን ተከትሎ ታህሳስ አካባቢ ጭላ ላይ ጦር ሰፍሯል፡፡ ከዚህ በኋላ በቀጣዮቹ አምስት ወራት ውስጥ የህወሓት ጦር በቁጥር እየገዘፈ መጥቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጭላ በስተመስራቅ በቦራ እና ዛና በኩል ወደ ዋግ ምድር መግባት መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ይህ ጦር ዋግ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ምንም አይነት ጥበቃ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡ በዚህም ህወሓት ለመጀመሪያ ጊዜ ጉልበት ማበጀቱን ያሳያበትን ውጊያ በዋግ ውስጥ አድርጓል፡፡ ይህም የዊርቀ ዲብኑ ውጊያ ነበር፡፡ መንግሥት ይህን ጉልበት ተመልክቶ መደበኛ ጦር በመላክ ፈንታ ድል አድርጎ በፃታ አካባቢ የሰፈረውን ግዙፍ የህወሓት ጦር የዋግ ሚሊሻዎች ሄደው እንዲወጉት በማድረግ አላስፈላጊ መስዋእትነት አስከፍሎናል፡፡

በግሌ ይህ ጉዳይ የዋግ ህዝብን ደም ለማቃበት ሆን ተብሎ የተደረገ የመጀመሪያ ዙር የሞት ድግስ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ እኛም ህወሓት እና ጀሌዎቹ ባለፉት 27 ዓመታት ያደረጉብንን ብቻ በማሰብ ዘው ብለን እንደገባን አምናለሁ፡፡ በእኛ መስዋእትነት ያተረፈ የሞት ደጋሽ እንዳለም አምናለሁ፡፡ ለዚህ ያልተገባ መስዋእትነት ሃላፊነት የሚወስድ ጠፍቶ ዞን እና ክልል ችግሩን ከአንዱ ወደ ሌላው ሲገፉት ከቆዩ በኋላ በመጨረሻ ክልሉ “ህዝቡ ራሱ የሰጠው ምላሽ ነው፡፡ እኛ እጃችን የለበትም” ሲል ፋይሉን መዝጋቱን አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህ በኋላም ቢሆን ቀጣይ ያልተሳካ የሞት ድግስ ተሰናድቷል፡፡

ሰቆጣ ከተማ ጠባቂ ጦሯን በአንድ ጀንበር ማጣቷ እና በፃግብጂ የሰፈረው ግዙፍ የህወሓት ጦር ከፈለገ ወደ ከተማዋ መግባት እንደሚችል እየታወቀ ለወራት ያህል ምንም ጠባቂ ሳይላክ ቀርቷል፡፡ በዚህም ከፃግብጂ ወደ ሰቆጣ የሚያስገቡት የአርፍፅ እና የፀመራ በሮች በሙሉ በሙሉ ክፍት ነበሩ፡፡ እውነቱን ለመናገር በዚህ ወቅት ህወሓት ከተማዋን መተናኮል ብትፈልግ እድሉም አቅሙም ነበራት፡፡ ይህንን ደግሞ የኒርአቑ ከተማን በመውረር አሳይታለች፡፡ በኒርአቑ የአማራ ልዩ ኃይል የነበረ ሲሆን፣ መከላከያ እና የሻአቢያ ጦር ደግሞ ከ11 ኪ.ሜ ባነሰ ርቀት ላይ ነበሩ፡፡ ከዚህ አንፃር ከኒርአቑ ይልቅ ሰቆጣን መያዝ ቀላል ነበር፡፡ ህወሓት ግን ምናልባት መሣሪያ ለማግኘት ይሆናል አበርገሌን መርጣ አጥቅታ ተመልሳለች፡፡ አልተሳካም እንጂ ይህ በር ክፍቶ የመተው ጉዳይ ለእኔ ሌላ ድግስ ነበር፡፡

ከኒርአቑ ወረራ በኋላ ሰቆጣ ከተማን የሚጠብቅ መከላከያ ወደ አካባቢው ተልኳል፡፡ ይህ ጦር ለወራት ከተማዋን ጨምሮ አጠቃላይ ዞኑን ሲጠብቅ ከቆዬ በኋላ ከሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ እንደ ሌሎቹ የቀጠናው ጦሮች ሁሉ ለቅቆ መውጣቱ ይታወቃል፡፡ በዚህም ምክንያት ሰቆጣ ከተማ ለሦስተኛ ጊዜ ተጋላጭ ሆናለች ማለት ነው፡፡ ይህም ሌላ የማፋለም እቅድ ይመስለኛል፡፡ ደጋግምን እንዳየነው የሆነ አካል የእኛን መዋጋት አጥብቆ የሚፈልገው ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በፊት ባልነበረ ሁኔታ ዋግ ውስጥ ሰዎችን ማስታጠቅ የተፈለገውም ለዚሁ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ ወጣቶች መታጠቃቸውንም ሆነ ሥልጠና መውሰዳቸውን በግሌ የምደግፈው ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን በደባ በተበጀላቸው ጦርነት ውስጥ መግባት አለባቸው ብዬ አላምንም፡፡ መዋጋት የለብንም የምለው በዚህ “ማንን ለማስደሰት” በሚል እይታም ጭምር ነው፡፡

ማጠቃለያ

ከህወሓት ጋር አለመዋጋት ማለት ህወሓትን ማፍቀር ማለት እንዳልሆነ አስተውሉ፡፡ ጉዳዩ ከወራት በፊት የገጠምን እልቂት እያንገበገበን ለምን ለተጨማሪ እልቂት እንጣደፋለን የሚል ነው፡፡ ሙግቱ በቂ ምክንያት የለንም፣ የከተማ ጦርነትም የሚያስከፍለን ዋጋ የማይተመን ነው የሚል ነው፡፡ አብዝሃኛዎቻችሁ ታናናሾቼ ናችሁ፡፡ በጦርነት አሳሯን በበላች ምድር ውስጥ ተወልዳችሁ ብታድጉም፣ የቀደመውን እሳት በንግርት እንጂ በአካል የምታውቁት አይመስለኝም፡፡ ታላላቆቻችን ችግር ሲረገዝ ዳር ቆመው መመልከት፣ ሲወለድ ደግሞ መሃል ገብቶ ማልቀስ አባዜ ሆኖባቸው እንጂ ስለጦርነት አስከፊነት ብዙ በመከሩን እኛም በዙ በተማርን ነበር፡፡ ከዚህ ውጭ ጦርነት አስገዳጅ በሆነበት ሁኔታ በዝምታ መመልከት ልክ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ህዝቤ ከተነካ እኔም የምመለስ ሰው አይደለሁም፡፡ ብዙዎቻችሁ ልጅነቴን የት እና እንዴት እንዳሳለፍኩ የምታውቁ ይመስለኛል፡፡

ማስገንዘቢያ

በዚህ ጉዳይ ከዚህ በኋላ አልፅፍም፡፡ ሃሳቤ ያልተረዳችሁ ቅን ልቦች ካላችሁ ሙግቴን ትረዱ ዘንድ ብቻ ነው ይህን መፃፌ፡፡ ምንም ጠንካራ እና ሞጋች ስነ ልቦና ቢኖረኝ፣ እኔም እንደ እናንተ ከስጋ እና ደም የተሰራሁ፣ የሚጎዳ ስሜት ያለኝ፣ ደህንነቴ የሚያሰጋኝ እና ከለላ አልባ ዜጋ ነኝ፡፡ በተለያዩ መንገዶች እየደረሱኝ ያሉት ዛቻዎች እና ማስፈራሪያዎች ከእኔ አልፎ ወዳጅ ዘመዶቼን እያስጨነቁ ነው፡፡ በበኩሌ ህዝቤን የሚጠቅም የመሰለኝን ሃሳብ በማካፈሌ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ወደ ፊትም ይህን ከማድረግ የሚያስቆመኝ ኃይል የለም፡፡ በዚህ ጦርነት ዘሪያ ግን ይህ የመጨረሻ መልእክቴ ነው፡፡
በዋግ ምድር በተለይ በሰቆጣ ከተማ ህወሓት ባትገባ የዘላለም ምኞቴ ነው፡፡ ከገባች ግን ከ40,000 በላይ ህዝብ በሚኖረባት ከተማዬ አንድ የጥይት ድምፅ ባይሰማ፣ ሲቪሊያን አይደለም አንድ የታጠቀ ወንድሜ ሲወድቅ ባላይ፣ የሌለ መሠረተ ልማታችን ሲወድም ባልመለከት ደስታዬም ፀሎቴም ነው፡፡ እንተኩሳለን የምትሉ ወንድሞች የሃላፊነት ስሜት እንዲሰማችሁ እና እንደገና እንድታስቡ በወንድማዊነት እጠይቃችኋለሁ፡፡
Please wait, video is loading...