Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Ejersa
Member
Posts: 3976
Joined: 05 Nov 2019, 10:39

የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ!

Post by Ejersa » 15 Jun 2021, 07:52

እኛ የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች ከሰኔ 03-07/2013 ዓ.ም. ድረስ በዞናችን በተመረጡ አምስት ከተሞች (ሁመራ፣ ባዕከር፣ ማይካድራ ወፍአርግፍ እና ዳንሻ) የነጻነት ሰልፍ አካሂደናል፡፡ በሁሉም ከተሞች ጠዋት ሕዝበ-ትዕይንት፤ ከሰዓት በኋላ ደግሞ በየደረጃው የምንገኝ የህብረተሰብ ክፍሎች ከዞናችን አመራሮች ጋር ሕዝባዊ ኮንፍረንስ አድርገናል፡፡ የሰልፉም ሆነ የህዝባዊ ኮንፍረንሱ መሠረታዊ ዓላማ በሀገራዊ ሉዓላዊነትችን፣ በርስታችንና በማንነታችን እንደማንደራደር፤ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በትህነግ ወያኔ ለተፈጸመብን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተገቢውን ፍትሕና ካሳ ለመጠየቅ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጻሚ የወያኔ አመራሮችም በዓለማቀፉ ፍርድ ቤት በሕግ እንዲጠየቁልን በአደባባይ ድምጻችን ለማሰ፣ት ነው፡፡ ይህን መሰረት በማድረግ ከሚከተለው ፍሬ ነገር ቀጥሎ የቀረበውን ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡-

እኛ የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ሲደርስብን ለነበረው መዋቅራዊ ጭቆና አልፎም የተጠና የዘር ማጥፋት ወንጀል አንድም ቀን በአደባባይ እንዳንናገር ታፍነንና ተከልክለን ቆይተናል፡፡ በዚህም ጠመንጃ አንስተን ከ‹ከፋኝ› የፋኖ እንቅስቃሴ እስከ ሠላማዊው የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ድረስ ለሰላሳ ዓመታት ታግለናል፡፡ በእነዚህ ዘመናት የነበሩ የትግል እንቅስቃሴዎቻችን ሁሉ በበርካታ ውጣ ውረዶችና መስዋዕትነቶች የተሞሉ ነበሩ፡፡ለሦስት አስርታት ስለዘለቀው የመስዋዕትነት ታሪካችን ከአገር ወስጥ እስከ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ድረስ ችግራችን የተረዱት እጅግ ጥቂቶች ብቻ ነበሩ፡፡

ሐምሌ 05/2008 በጎንደር ከተማ በትህነግ እብሪተኝነት የተቃጣውን የአፈና ሙከራ አይበገዴው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በ‹እጅ አልሰጥም› ባይነት ተጋድሎው አፈናውን ከቀለበሰ ጊዜ ጀምሮ በአዲስ ምዕራፍ የተቀጣጠለው የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ በመጋቢት 2010 ለተመዘገበውና ትህነግን ከአዲስ አበባ አባርሮ መቀሌ እንዲመሽግ ላደረገው አስገዳጅ ለውጥ የወልቃይት ጠገዴ ትግል አይነተኛ ሚና ነበረው፡፡

በለውጡ ሂደት የወልቃይት ጠገዴ አማራ ግፍና በደል ተጠናክሮ ቀጥሎ የነበረ ቢሆንም፣ ሕዝባዊ መሰረት የተከለው የማንነት ትግሉ በመጨረሻው ሰዓት የትህነግን የሀገር ክህደት ተግባር ወደ ዕድል ሊቀይረው ይችሏል፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ፈጣሪ ከተገፉትና ከተበደሉት ጋር ይቆማልና የግፉዓንን እምባና ሰቆቃ ሰምቶ ትህነግ የለመደ የእናት ጡት ነካሽ የባንዳባህሪውን እንዲሰራ አደረገው፡፡ የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ዘብ የሆነው የመከላከያ ሰራዊታችንን ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ምሽት ላይ ከጀርባ የወጋው ትህነግ፣ የክህደት ድርጊቱ ለውድቀቱ የወዲያው ምክንያት ቢሆንም ለዘመናት የፈጸመው ግፍና የዘር ማጥፋት ወንጀል ለዛሬው ታሪካዊ ሽንፈቱ ዳርጎታል፡፡

ትህነግ የሀገር ክህደት ወንጀል ከፈጸመባት ምሽት ጀምሮ በተጀመረው የህልውናና ህግ የማስከበር ዘመቻ ከፌዴራልና ከአማራ የጸጥታ ኃይል ጋር ተሰልፎ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ራሱን ከወራሪ ሀገሩን ደግሞ ከከዳተኛና ባንዳ ነጻ ለማውጣት ተፋልሟል፡፡ ትርጉም የሚሰጥ መስዋዕትነት ከፍሎ ያገኘነውን ነፃነት ዛሬም ማንም ኃይል ጣልቃ ገብቶ ‹በማንነታችሁ እኔ ልወስን› እንዲለን አንፈቅድም፡፡ በነጻነታችን ማግስት ሚዛናዊነት የጎደላቸውና የህዝባችንን የዘመናት መከራና በደል ዛሬም ድረስ የዘለቁ ጠባሳዎችንና የታሪክ ቁስሎቻችን እንዲያመረቅዙ የሚያደርጉ የፖለቲካ ሸፍጦች ከውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ ኃይሎች እየሰማን ነው፡፡

ይህ ፍትህን የማዛባት፣ በመረጃና ማስረጃ ያልተመሰረተ ፍርደ ገምድልነትና የክህደት ተግባር ብቻ ሳይሆን፤ አንዲት ሉአላዊት ሀገር‹አሸባሪ› ብላ የፈረጀችውን ቡድን በፖለቲካም ሆነ በሌላ መስክ አባሪና ተባባሪ መሆን እጅግ አሳፋሪና አስነዋሪ ድርጊት ስለሆነ አምርረን እየተቃወምን፣እኛ የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች ለኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች፣ ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት እናለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ማስገንዘብናማስረዳትየምንፈልገውን ግልጽ አቋማችን በተመለከተ ከዚህ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡-
ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ!

1) የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ትግበራ ትብብርን፣ የጋራ ጥቅምን እና ሉዓላዊነትን በማስከበር እና በማክበር ላይ የተመሠረተ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና በአሸባሪው ትህነግ ላይ ሕግ የማስከበር እርምጃ ከተጀመረ ወዲህ የሀገራችን ኢትዮጵያን ሉአላዊነት በሚጋፋ መልኩ የውጭ ኃይሎች ጫናና ተጽዕኖ በማሳደር ላይ ይገኛሉ፡፡ የሺህ ዘመናት የነጻነት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ሀገራችን፣ ሉአላዊነቷን በልጆቿ ኩራት፣ ጀግንነትና መስዋዕትነት አስከብራ ኑራለች፡፡ ዛሬም ይህ ኢትዮጵያዊ ኩራት፣ ጀግንነትና የመስዋዕትነት ወኔ በአዲሱ ትውልድ ላይ ቀጥሏል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጋፉ የትኞቹንም ውሳኔዎችንም ሆነ በውስጥ ጉዳያችን ገብተን እንወስንባችሁ ለሚሉን የውጭ ኃይሎች፣በእናት ሀገራችን ኢትዮጵያ የሉአላዊነት ጉዳይ አንደራደርም!!

2) የኢትዮጵያና የአሜሪካ የወዳጅነት ግንኙነት ከአንድ መቶ ሃያ ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ ይታወቃል፡፡ አሜሪካ በትምህርት፣ በግብርና፣ በጤና እንዲሁም በቀጠናው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከኢትዮጵያ ጋር ስታደርግ የቆየችው እርዳታና ትብብር ያስመሰግናታል፡፡ ነገር ግን በምስራቅ አፍሪካ ሽብርተኝነት ለመዋጋት ስትራቴጅክ አጋር የነበረችው አሜሪካ፣ ዛሬ በተሳሳተ ግምገማ አሸባሪውን ትህነግ በሚያግዝ መልኩ በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የጉዞ ክልከላ ማዕቀብ በማስቀመጥ ጫና ለመፍጠር መሞከሯ፣ ለቀጠናው ብቻ ሳይሆን ለራሷ ለአሜሪካና ለምዕራቡ ዓለም ከባድ ኪሳራ ነው፡፡

ተለዋዋጭ ፖለቲካ አይነተኛ ባህሪው በሆነው የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ ‹ዓለማቀፍ ድንበሮች አይገድቡኝም› በሚል ጎረቤት ሀገር ኤርትራን ጭምር ለማተራመስ የሚሰራውን ትህነግ፣ የሚደግፍ አቋም የያዙ አሜሪካና ጥቂት አጋሮቿ፣ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎችቸውን ቆም ብለው እንዲያጤኑ እንጠይቃለን፡፡ በየትኛውም መንገድ ትህነግን መደገፍ የሽብር ተግባራትን ማበረታታት ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከሕግ ማስከበር በላይም ከፍ ያለ ተልዕኮ ያለው ሲሆን፤ የተልዕኮው አይነተኛ ባህሪ በሽብር ላይ የተከተፈ ጦርነት ነው፡፡ አሸባሪን ከቀጠናው የማጽዳት ተግባር በመሆኑ በሽብርተኝነት ላይ ጽኑ አቋም ያላቸው አሜሪካና የቅርብ አጋሮቿ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ የሚያዩበትን መንገድ በተለይም የመረጃ ምንጮቻቸውን እንዲፈትሹ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

3) ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ዓለም ጀሮ የነፈገው የዘር ማጥፋት ወንጀል በወልቃይት ጠገዴ የአማራ ሕዝብ ላይ ተፈጽሟል፡፡ ምናልባትም በብዙሃኑ ኢትዮጵያውያንና በተወሰኑ የዓለማቀፉ ማህበረሰብ አባላት ዘንድ የተሰማው የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረ በኋላ ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም በማይካድራ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ብቻ ነው፡፡ እኛ ግን ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በርካታ ማይካድራዎችን አይተናል፡፡ በየትኛውም የዓለም ክፍል የተፈጸሙ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች አንዴ ተጀምረው በተወሰነ የጊዜ ገደብ የተጠናቀቁ ቢሆንም፣ ወልቃይት ጠገዴ ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ግን በአይነትም ሆነ በድርጊት የተለየ ነው፡፡ ለሠላሳ ዓመታት ያለ ማቋራጥ መዋቅራዊ በሆነ መንገድ እኛን የማጥፋት ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ አማሮች በማንነታቸው ተገድለዋል፡፡ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ወገኖቻችን ወደ መቀሌና ወዳልታወቁ ስፍራዎች ታፍነው ተወስደው በእስር ሲማቅቁ ኑረዋል፤ ብዙዎችም ባሉበት አልፈዋል፡፡ በጥቅሉ በሠላሳ ዓመቱ የወያኔ አፓርታይዳዊ ዘመን ከቆላ እስከ ደጋ አምስት መቶ ሺህ የሚደርስ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ከእርስቱ ተፈናቅሎ ወደጎረቤት ሀገራትና ወደጎንደር አልፎም ወደ መሀል ሀገር እንዲሰደድ ተደርጓል፡፡

ዛሬ የዘመናት ትግላችን ሂደትና የትህነግ የሀገር ክህደት የፈጠረው ውድቀቱ የወልቃይት ጠገዴ አማራ የተነጠቀ ማንነቱን ማስመለስ ችሏል፡፡ ዛሬ በዚህ መድረክ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብተን ውሳኔ ካልሰጠን ለሚሉ የውጭ ኃይሎች ልናረጋግጥላቸው የምንወደው ነገር እኛ የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች ያስመለስነው ማንነት እንጅ የነጠቅነው መሬት የለም!! የአማራ ልዩ ኃይል ወልቃይት ጠገዴ ላይ እንጅ ትግራይ ውስጥ የለም!! የማይገባንን አልፈን አንጠይቅም፤ የራሳችንንም አሳልፈን አንሰጥም!! ማንነታችን አማራ ድንበራችን ተከዜ ነው!!

4) የትህነግ አፓርታይዳዊ አገዛዝ ከተዘረጋ ጀምሮ በወልቃይት ጠገዴ የአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ታውጆ ተፈጻሚ ተደርጓል፡፡ ለዚህም የሰውና የጅምላ መቃብር ምስክሮችን አስረጅ ምሳሌ አድርገን እናቀርባለን፡፡ ከሁመራ ኤርፖርት ግቢ የጅምላ መቃብር እስከ ማይካድራው ጭፍጨፋና በየዋሻውና የምድር ውስጥ እስር ቤቶች በጅምላ ያለቀው ወገናችን እልፍ ነው፡፡ ስለተፈጸመብን የዘር ማጥፋት ወንጀል የትኛውም ገለልተኛና ነጻ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ወደወልቃይት ጠገዴ መጥቶ ማጥናት ቢፈልግ በራችን ክፍት መሆኑን እናሳውቃለን፡፡ በእኛ በኩል በዓለማቀፍ መመዘኛዎች ስንመለከተው በወልቃይት ጠገዴ የአማራ ሕዝብ ላይ ያልሰማው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞበታል፡፡ ለዚህም ወንጀለኞች በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲጠየቁ እንጠይቃለን!! የግፉዓን ጠበቃ ለመሆን በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የምትሰሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት፣ በወልቃይት ጠገዴ የአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጸሙ የትህነግ አመራሮች ለፍርድ እንዲቀርቡ በምናደርገው ጥረት ከጎናችን ሁናችሁ ሰብዓዊ ውግንና እንድታሳዩን እንጠይቃለን!

5) በወራሪውና አሸባሪው ትህነግ አገዛዝ ስር የነበረው የወልቃይት ጠገዴ አማራ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ከባድ የሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ አስተናግዷል፡፡ አያሌ ወገኖቹ በጅምላ ተገድለውበታል፡፡ በማንነቱ ሞትን የማስተናገድ መራር ዕጣ ፈንታ በእያንዳንዱ የወልቃይት ጠገዴ ቤት ውስጥ ገብቷል፡፡ እንዲሳደድና እንዲፈናቀል ተደርጓል፡፡ ሃብትና ንብረቱንም ተዘርፏል፡፡ ለዚህም በዓለማቀፍ ተሞክሮዎች መሰረት ለደረሰብን ግፍና በደል ካሣ እንጠይቃለን፡፡ የምንጠይቀው ካሣ ለሰላሳ ዓመታት በዘለቀው የትህነግ የአፓርታይድ የአፈና አገዛዝ ያጣናቸውን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ሕይወት ባይመልስልንም፣ ለደረሰብን ግፍና በደል እውቅናው ቁስላችንን ያሽረዋልና፣ የፍትሕና የካሳ ጥያቄችን ገፍተን እንቀጥላለን፡፡

6) በትህነግ የግፍ አገዛዝ ተማርረውና በእርሱ አስገዳጅነት ከወልቃይት ጠገዴ የተፈናቀሉ አምስት መቶ ሺህ የሚሆኑ ወገኖቻችን ወደቀደመ መኖሪያቸው እንዲመለሱ የማድረጉ ስራ የፌዴራሉ መንግሥት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር ሊሰራው የሚገባ ቁልፍ ተግባሩ እንዲሆን እንጠይቃለን፡፡

7) የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች አስተዳደራዊ ነጻነታችንን በተመለከተ ትላንትም ሆነ ዛሬ ቃላችን አንድ ነው፡፡ ከትግራይ የሚመጣ ጥሩ ጎረቤት እንጅ፤ አስተዳደር ፈጽሞ አንቀበልም! ዛሬ ወደኋላ ላንመለስ ነጻ ወጥተናል፡፡ ስለማንነታችንም ከእኛ በላይ ምስክር ሊሰጥ የሚችል አንዳች አካል የለም፡፡ ከእንግዲህ ከትግራይ ሊመጣ የሚያስብ የትኛውም አስተዳደራዊ ኃይል ከአሸባሪው ትህነግ ለይተን አናየውም፡፡ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ አጀንዳ ፋይሉ የተዘጋ ነው!!

8 ተፈጥሯዊ ድንበራችን የሆነውን ተከዜ ወንዝን በጋራ የምንጋራው የትግራይ ወንድም ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች በወልቃይት ጠገዴ ምድር በሠላምና በነጻነት መኖር ይችላሉ፡፡ ዛሬም ‹ሥርዓት ይመጣል፣ ይሄዳል፤ የህዝብ ግንኙነት ግን ቋሚና ዘላቂ ነው› ብለው ያመኑ የትግራይ፣ የኩናማ፣ የኢሮብ፣… ተወላጆች በዞናችን ውስጥ ደህንነታቸው ተጠብቆ በሰላም ይኖራሉ፡፡ ሕግና ሥርዓትን አክብረው ለሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ዞናችን ክፍት ነው፡፡ ነገር ግን እኛ የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች፣ ማንነታችን አማራ በመሆኑ አስተዳደራዊ ክልላችን በማንነት ከሚዛመደን የአማራ ክልል ጋር ሁኖ በሕግ እንዲጸናልን የፌዴሬሽን ምክር ቤትን አጥብቀን እንጠይቀለን፡፡

9) የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄን መላው ፍትሕና ነጻነት ወዳድ ኢትዮጵያውያን ይጋሩታል፤ ጥያቄውንም ጥያቄቸው አድርገውታል ብለን እናምናለን፡፡ የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች የወልቃይት ጠገዴ አማራ እየጠየቀ ያለው፣ ‹ማንነቴ አማራ ነው፤ ማንነቴም በአስተዳደራዊ ነጻነት ይከበርልኝ› የሚል መሆኑ ታውቆ ያደረ ነውና ከመቼውም ጊዜ በላይ ከጎናችን እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን!!

10) ለሦስት አስርት ዓመታት ግፍና መከራ አልፎም የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞብናልና በእኛ ላይ የተፈጸመው በደል በሌሎች ላይ እንዲፈጸም ፈጽሞ አንመኝም፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን ወደዘላቂ ሠላምና መረጋጋት ተመልሳ ሁለንተናዊ ብልጽግናዋን እንድታሳካ ምኞታችን ነው፡፡ አሁን ባለንበት ፈታኝ ወቅት የሀገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች መረጃዎችን በማሰራጭት ረገድ ለሙያችሁ ያላችሁን ታማኝነት በተግባር እንድታሳዩ እንጠይቃን፡፡ በተለይም የዴሞክራሲ ባህል አለን፣ የዳበረ ሥርዓት ገንብተናል የሚሉ አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች ወልቃይት ጠገዴን በተመለከተ ከሚያሳረጩት ሚዛናዊነት የጎደላቸው መረጃዎቻቸው ተቆጥበው ለተቋማቶቻቸውና ለሙያቸው እንዲታመኑ እየጠየቅን፣ መሬት ላይ ካለው ጥሬ ሃቅ ባፈነገጠ መልኩ የአሸባሪው ትሕነግ ተላላኪ ሁነው መረጃዎችን አዛብተው ለሚያቀርቡ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በያሉበት ድምጻችን እንዲያሰሙልን እንጠይቃለን፡፡

በመጨረሻም!
ዛሬ ከፊት ለፊታችን የተጋረጡትን ሀገራዊ ፈተናዎቻችን የምንሻገረው፣ በአድዋ ድል የመንፈስ ጥንካሬ ነው! አድዋ የድል አድራጊነት፣ የኢትዮጵያውያን የመንፈስ አንድነት ብርታትና ጥንካሬ፣ የአገር ፍቅርና የአይበገሬነት ተምሳሌት ነው፡፡ የትኛውም አይነት ሀገራዊ ጫናና ተጽዕኖ ቢመጣብን በአድዋ የድል አድራጊነት መንፈስ እንሻገረዋለን፡፡ እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን፡፡ በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እና የተሳሳተ ግምገማ በያዙ የውጭ ኃይሎች ጀርባ ተንጠልጥለው የሚመጡ ትህነግ ወያኔን የመሰሉ የታሪክ ተሸናፊ ባንዳዎችን ጨርሰን ወደመቃብር የምናወርዳቸው ያለምህረት በመታገል ነው፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን እጃችን ለፍቅር የሚዘረጋ ቢሆንም፣ ለአሸባሪዎች ምህረት የለንም፡፡

በሀገራዊ ሉዓላዊነታችን፤ በርስትና በማንነታችን አንደራደርም!!

ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለሀገር መከላከያ ሠራዊታችን እና ለአማራ የጸጥታ ኃይሎች ሰማዕታት ይሁንልን!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!