እብዷ ሃኪም!
Posted: 11 May 2021, 11:03
ኤርትራውያን ለነጻነታቸው የከፈሉት መስዎእትነት፡ በቃላት ለመግለጽ የሚከብድ ነው። ከባህር በጭልፋ፡ ለኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን እናካፍላችሁ። @dejene_2011
POLITICS/አማርኛ
እብዷ ሃኪም!
By Meadi Guasot
https://shidamedia.com/%e1%8a%a5%e1%89% ... %e1%88%9d/
May 11, 2021
ሚኒ ስከርቷን ሊነካ የሚንደረደረው ሃር መሳይ ረጂም ጠጉሯን እያማታች፡ በትምህርትና በማህበራዊ ኑሮዋ የደመቀ ህይወት የነበራት ሃኪም፡ የደረሰችበትን ጥግ ማን ይገምተዋል? የደም ገንቦ የሆነችው ይህች አማላይ ወጣት፡ እድሏ ሰውን የሚታዘቡ እንደሚመስሉት ውብ አይኖቿ ሁሉ ያማረ ነበር፡፡
ለከፍተኛ ትምህርት የነጻ ትምህርት ያገኘቸው፡ ቤላሩስ ነበር፡፡ ትምህርቷን በሚገባ አጠናቃ በጥርስ ህክምና ዶክተር ሆና የተመለሰችው ወጣቷ ምሁር፡ እስከዚህ የህይወቷ ምእራፍ ድረስ ሙሉ ጤናማ ነበረች፡፡ እብደቷ የጀማመራት፡ የፈረስ ጭራ የሚመስለውን ጠጉሯን ቆርጣ አፍሮ የሆነች እለት ሳይሆን አይቀርም! ማን ያቃል፡ መቀሱን ተመስሎ የገባ መንፈስ ቢኖርስ?
ብቻ ከፍተኛ ደሞዝ ከምትከፈልበት ከፍተኛ ሞያና፡ ሊያገቧት ደጇን ከሚጠኑ የዘመኑ ዘናጭ ጉብሎች ኮብልላ፡ ሳህል ተገኘች፡፡ ይህች በዴንቲስትነት የተመረቀችው ወጣት፡ እብደቷ እየባሰባት መትቶ፡ በቦንብ የፈረሰ ፊት፡ ከሌላ የገላ አካል እየቆረጠች መገጣጠም ጀመረች፡፡ እርግጥ ነው፡ እሷንና ኦሮታ ሆስፒታልን ነጣጥሎ ማየት አይቻልም፡፡
ምንም እንኳን ከሌላው የተሻለ አደጋ የሌለበት ስፍራ ቢሆንም፡ እንደሌሎቹ ማግባትና መውለድ ስትችል፡ 'የያዝኩት ጉዳይ መች አነሰኝ' በማለት ስራዋ ላይ ብቻ አተኮረች፡፡ እርግጥ ነው ውበቷ፤ ልጅነቷ፤ እውቀቷ የማያሳሳት እብዷ ሃኪም፤ እኛ እብድ መሰለችን እንጂ፤ ከጋብቻም ከልጅም ከራሷም በላይ ያየችው ቁምነገር ብዙ ቮልዩም የሚፈጁ መጻህፍት የማይበቁት ታሪክ አላት፡፡
የእናት አገር ጥሪ ገጹ ይሞላ ዘንድ፡ ይህች ወጣት ስለዋለችው ውለታ ዝንተ አለማችንን ስናወሳት እንኖራለን፡፡ ዶ/ር ላይነሽ ህይወት የዘራችባቸው ሁሉ፡ ልጆቿ ናቸው፡፡ ሞያዋን ሳትሳሳ ያቀበለቻቸው ሁሉ፡ ልጆቿ ናቸው፡፡ ከ 50 አመታት በላይ ሳትደክም ያገለገለችው የኤርትራ ህዝብ፡ በሙሉ ልጆቿ ናቸው፡፡
ዛሬ የእናቶች ቀን ሲከበር ከዶ/ር ላይነሽ የበለጠ እናት ይገኝ እንደሆነ፡ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ስላፈራሻቸው ልጆችስ በሙሉ፡ ስለአገልግሎትሽም አንቺ ከእናቶች ሁሉ የበለጥሽ እናት ነሽና፡ ፍቅርና ሞገስ ከሙሉ ኤርትራ ህዝብ ይድረስሽ! ተነግሮ ስለማያልቅ ውለታችሁ፡ ለኛ ስትሉ ማህጸናችሁን የዘጋችሁ ሁሉ፡ ታሪክ ሲያከብራችሁ ይኖራል፡፡
እናከብራችኋለን!
እናትም አባትም አገራችን ኤርትራ ለዘላለም ትኑር/ይኑር!