Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Za-Ilmaknun
Member
Posts: 4080
Joined: 15 Jun 2018, 17:40

የሐረሪ ክልል እና የነዋሪዎቹ መብቶች መበላለጥ- The "Federal Democratic Ethiopia" in reality..by DW

Post by Za-Ilmaknun » 30 Apr 2021, 15:09

በፍቃዱ ኃይሉ

የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ላይ “የብሔር ፌዴራሊዝም ነው” የሚል በአንድ በኩል፣ “ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ነው” በሚል በሌላ በኩል የሥያሜ እና አጠራር ቅንጡ ክርክሮች ይደረጋሉ። ነገር ግን መሠረታዊ መብቶች በክልሎቹ እና በፌዴራሉ መዋቅሮች እንዴት እንደሚከበሩ ወይም እንደማይከበሩ ማውራት ነውር የሆነ ይመስላል። ሰሞኑን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና በሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መካከል ፍርድ ቤት የደረሰ እሰጥ አገባ አለ። የእሰጥ አገባው መንስዔ የሐረሪ መንግሥት የራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያጎናፀፈኝ ፀጋዎቼ ናቸው የሚላቸውና በሐረሪ ክልላዊ ሕገ መንግሥት ላይ የሰፈሩ መብቶችን ምርጫ ቦርድ ‘ኢ-ሕገ መንግሥታዊ’ ብሎ ማለቱ ነው።

የሐረሪ ሕገ መንግሥት ከሌሎቹ ክልሎቸች ሕገ መንግሥታት በምን ይለያል? የውዝግብ መንስዔ የሆነው ጉዳይ ምንድን ነው? ውዝግብ ሳይነካው ያለፈ ነገር ግን መጠየቅ ያለበት ነገር ይኖር ይሆን? ከውዝግቡ በስተጀርባ ያለው ፍልስፍናስ ምንድነው? ለሚሉትና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች ይህ ጽሑፍ አጭር መልስ አለው።

የሐረሪ ክልል ምክር ቤቶች

በመጀመሪያ ስለሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሁለት ምክር ቤቶች ማወቅ ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ከፌዴራሉ መንግሥት በስተቀር ሁለት ምክር ቤቶች ያሉት ብቸኛው መንግሥታዊ መዋቅር የሐረሪ መንግሥት ነው። ምክር ቤቶቹ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይባላሉ። የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ 14 አባላት ያሉት ምክር ቤት ሲሆን፣ አባል መሆን የሚችሉት የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች ብቻ ናቸው። የሐረሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ 36 አባላት ያሉት ሲሆን፥ 14ቱ ከሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ ላይ 4 የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች ይጨመሩና 18 የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች ይኖሩታል። ቀሪው 18 ተወካዮች ደግሞ ከሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ውጪ ያሉ የክልሉ ነዋሪዎች እንዲወከሉበት ይደረጋል። በቀድሞው አሠራር የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ) እና የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) በውስጠ ፓርቲ ሥምምነት 18 የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች እና 18 የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጆች እንዲወከሉ ሲያደርጉ ነበር።

በ1999ኙ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት መካከል የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች ቁጥር፣ ከሐረሪ ክልል ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር አንፃር 9 በመቶ ብቻ ነው። ይሁንና የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች ሕዝብ ቁጥር ማነስ ለባሕላዊ መዋጥ ያጋልጣቸዋል በሚል ለጥበቃ የተሰጠ እየተባለ በሚነገር መልኩ፣ በብሔራዊ ጉባዔው በኩል ዘላቂ ውጤት ሊያስከትሉ የሚችሉ ውሳኔዎችን ለክልሉ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳያማክሩ እንዲወስኑ ዕድል ይሰጣቸዋል። ጉባዔው በክልሉ ሕገ መንግሥት 39/5/ሀ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የክልሉን ተወካዮች ምክር ቤት ሳያማክር የመገንጠል ውሳኔ እስከማሳለፍ ድረስ የሚዘልቅ ሥልጣን አለው።

ሕግጋቱ ምን ይላሉ?

1ኛ) ስለ ሁሉን ዐቀፍ የመምረጥና መመረጥ መብት፣

የተባበሩት መንግሥታት አባላት በሙሉ ድምፅ የተቀበሉት የዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀፅ 21/3፣ የዓለም ዐቀፉ የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን አንቀፅ 25/ለ፣ የአፍሪካ ቻርተር በምርጫ፣ ዴሞክራሲ እና የሕግ የበላይነት አንቀፅ 4/2 - ሁሉም ስለ ሁሉን ዐቀፍ የመምረጥና መመረጥ መብቶች ያወሳሉ። ሁሉን ዐቀፍ የመምረጥና መመረጥ መብት (‘ዩኒቨርሳል ሰፍሬጅ’) ዜጎች ወይም ነዋሪዎች ያለምንም የዘር፣ የብሔር፣ የፆታ፣ የትውልድ አመጣጥ፣ ወዘተ. ልዩነት መምረጥ ወይም መመረጥ እንዳለባቸው የሚደነግግ መብት ነው። ሁሉን ዐቀፍ የመምረጥ እና የመመረጥ መብት በብዙ አገራት የረዥም ዘመናት ትግል የተደረገለት መብት ነው።

2ኛ) ስለ ኅዳጣን ቡድኖች ጥበቃ፣

ብዙዎቹ ዓለም ዐቀፍም ይሁኑ፣ ቀጠናዊ ወይም የአገር ውስጥ ሕግጋት የኅዳጣን ቡድኖችን ጥበቃ (‘ማይኖሪቲ ራይትስ’) የሚመለከቱት በእኩልነት ድንጋጌዎች ነው። የዓለም ዐቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌም፣ የአፍሪካ የሰብኣዊና ሕዝቦች መብቶች ቻርተርም ይሁን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እንዲሁም የሐረሪ ሕገ መንግሥት ራሱ (በአንቀፅ 25) ላይ የእኩልነትን መብቶች ለሁሉም ሰዎች ያጎናፅፋሉ። የባንጁል ቻርተር በመባል የሚታወቀው የአፍሪካ ሰብኣዊና ሕዝባዊ መብቶች ቻርተር ከሌሎች የሰብኣዊ መብቶች ሕጋዊ ማዕቀፎች በተለየ “የሕዝቦች መብቶች” የሚለው በተለይም “የብሔረሰቦች መብቶች” በሚል የሚረዱት ብዙዎች አሉ። ድንጋጌዎቹም የተለየ ቋንቋ፣ ባሕል፣ እምነት ያላቸውን ማኅበረሰቦች ጥበቃ ላይ ያተኩራል።የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕደል በራስ የመወሰን መብት የሚላቸው እንዲሁ ለሁሉም የቋንቋና ባሕል ቡድኖች የተቀመጠ ቢሆንም፥ በተግባር ደረጃ ግን በግዛት ላይ ተመሥርቶ አንዱን ከሌላው የማበላለጥ አዝማሚያ አለው።

የኅዳጣንን መብቶች በተመለከተ የኅዳጣን ብሔሮች፣ ዘውጎች፣ ሃይማኖቶችና ቋንቋዎች አባል የሆኑ ግለሰቦች መብቶች ድንጋጌ (Declaration on the Rights of Persons Belonging to National or Ethnic, Religious and Linguistic Minorities) አንቀፅ 2 “የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ ኅዳጣኖች ባሉባቸው አገረ መንግሥታት ውስጥ፣ የኅዳጣን ቡድኖቹ አባል የሆኑ ግለሰቦች ከሌሎች የቡድናቸው አባላት ጋር በማኅበረሰቡ ውስጥ በራሳቸው ባሕላዊ መንገድ የመኖር፣ ሃይማኖታቸውን የመግለጽ እና የመተግበር፣ ወይም የራሳቸውን ቋንቋ የመጠቀም መብታቸውን ሊነፈጉ አይገባም” ይላል። ሆኖም የኅዳጣንን መብቶች ለመጠበቅ ብዙኃንን መሠረታዊ መብቶቻቸውን መንፈግ የሚያስችል ዓለም ዐቀፍ ድንጋጌም ይሁን ፍልስፍና የለም።

ይኸው ድንጋጌ በአንቀፅ አንድና ሁለት መንግሥት የኅዳጣን ቡድኖችን ኅልውና የሚያስቀጥልበት መንገድ እንዲኖረውና በሕጋዊ ማዕቀፍም እንዲኖረው ይደነግጋል።

የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች ልዩ መብት

የሐረሪ ሕገ መንግሥት የክልሉን የራስ የመወሰን ዕድል የደነገገበት አንቀፅ 29 እንደሚያሳየው “የሐረሪ ሕዝብ” ብሎ የሚጠራቸው፣ የሐረሪ ክልል ነዋሪዎችን ሁሉ ሳይሆን፥ የሐረሪ ተወላጆችን ብቻ እንደሆነ ግልጽ ያደርገዋል። በዚህም አንቀፅ 39/5/ሀ ላይ የክልሉን የመገንጠልን ያክል ጉዳይ የመወሰን ሥልጣን የሚሰጠው ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ ብቻ ነው።

የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ አባል ለመሆን የሚወዳደሩት ደግሞ የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች ብቻ ሲሆኑ፥ አባላቱን መምረጥ የሚችሉትም የብሔረሰቡ ተወላጆች ብቻ ናቸው። በክልሉ ተወልዶ ማደግ እና ከክልሉ ውጪ ሌላ ቦታ ረግጦ አለማወቅ የክልሉ ነዋሪ የመሆንን መብት አያጎናፅፍም። ይህም በክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 50፣ ንዑስ አንቀፅ 2 “የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ አባላት ከክልሉ ውስጥና ከክልሉ ውጪ በሌላ የኢትዮጵያ ክልሎችና ከተሞች ከሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ይመረጣል” ይላል። በዚህም በአንድ በኩል ሁሉን ዐቀፍ የመምረጥና መምረጥ መብት ሲጣስ፥ በሌላ በኩል የክልሉ ነዋሪ የሆኑ የሌላ ብሔረሰብ አባላት በነዋሪነታቸው በሚኖሩበት አካባቢ ካላቸው የመምረጥና የመመረጥ መብት ባሻገር፣ የማይኖሩበት ክልል ውስጥ ትልቁን ሥልጣን የሚያስገኘው ምርጫ ላይ ለተወካይነትም ይሁን ተወካዮችን ለመምረጥ መሳተፍ ይችላሉ።



የሐረሪ መንግሥትና ምርጫ ቦርድ

የሐረሪ መንግሥትና ምርጫ ቦርድ ቢያንስ በሁለት ጉዳዮች ውዝግብ ውስጥ ገብተው ነበር። የመጀመሪያው የሐረሪ መንግሥት የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጅ ያልሆኑ ዕጩዎች ይሰረዙልኝ ብሎ ያቀረበው ጥያቄ ነበር። በዚህ ጉዳይ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ምላሽ ማግኘት አልቻልኩም፤ ነገር ግን አሁንም በሐረሪ ክልል ለሐረሪ ብሔራዊ ምክር ቤት የሚመርጡ የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች የሚመዘገቡበት እና የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጅ ያልሆኑ የክልሉ ተወላጆች የሚመዘገቡበት የምርጫ ጣቢያዎች የተለያዩ ሆነው እየሠሩ ነው። ይህ የብሔር መደብ ክፍፍል በምን መመዘኛ እንደሚደረግ በጣም አስቸጋሪ ነው።

ሁለተኛው እና ፍርድ ቤት ድረስ የደረሰው ጉዳይ ከሐረሪ ክልል ውጪ ነዋሪ ለሆኑ የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች የጉባዔውን አባላት እንዲመርጡ ከክልሉ ውጪ 5 የምርጫ ጣቢያዎች ይቋቋሙላቸው የሚለው ጥያቄ ነው። ምርጫ ቦርድ ለጥያቄው እምቢታውን ያቀረበው “ሌሎች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሔረሰቦች ከክልላቸው ውጭ ያሉት አባሎቻቸው በምርጫው እንዲሳተፉ ቢጠይቁ፣ ቦርዱ ልፈፅም አልችልም ቢል የቦርዱን በፍትሐዊነት እና በገለልተኛነት ምርጫን የማስተዳደሩ ጉዳይ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ያደርጋል” በሚል ከቦርዱ የማስተዳደር አቅም አንፃር እንደተመለከተው አሳይቷል።

ይሁንና በዚህም ይሁን በሌሎች አሠራሮች የተዘነጋው፣ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች - ሕጋዊ ነዋሪነታቸው እስከ ተረጋገጠ ድረስ መምረጥም ይሁን መመረጥ የሚገባቸው በክልላቸው እንጂ በትውልድ ሐረግ ቆጠራ በሐረሪ ክልል እንዲሆን የትኛውም የሕግ ማዕቀፍ አይፈቅድም።

መውጪያ መንገድ

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሐረሪ መንግሥትን ይግባኝ አድምጦ ለክልሉ መንግሥት መፍረዱ ለምርጫ ቦርድ ብዙ ሸክም አይሆንበትም፤ ቢያንስ ከሕጋዊ ተጠያቂነት ያድነዋል። ነገር ግን ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ሕጉ በነዋሪዎች ዘንድ መበላለጥን የሚፈጥር ነው። የኅዳጣን ጥበቃ የሚያስፈልገው ከብዙኃን ጭቆና እና ጭፍለቃ አንፃር እንጂ ብዙኃንን ወደ ፖለቲካዊ ኅዳጣንነት በመቀየር መሠረታዊ መብቶቻቸውን ለመንፈግ መሆን የለበትም፤ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትም አያመጣም።

በ1999ኙ የቤቶች እና ሕዝብ ቆጠራ መሠረት ከሐረሪ ብሔረሰብ ያነሰ ቁጥር ያላቸው 34 ብሔረሰቦች ነበሩ። ለሕዝባዊ ለአንዱ ብሔረሰብ ብቻ የሚደረገው ሕጋዊ ጥበቃ ፍትሐዊም አይደለም፣ ዘላቂም አይደለም። ስለሆነም፣ ፌዴራል መንግሥቱ ኅዳጣን ቡድኖች ቋንቋና ባሕላቸውን የሚያሳድጉበት፣ እምነት እና ልማዳቸውን በነጻነት የሚተገብሩበት፣ እንዲሁም በአስተዳደር ውስጥ በአግባቡ የሚወከሉበትን ስርዓት ለሁሉም በሚበጅ መልኩና የማንንም መሠረታዊ መብቶች በማይገፉ አዎንታዊ ድጋፎች ማድረግ መቻል አለበት።