ብልጽግና የሚባለው የጎሳ ጥርቃሞ ድርጅት በኦሮሞና አማራ ተከፍሎ ለጎሳ የበላይነት እርስ በርስ እየተፏከተ፣ ኢትዮጵያዊያንን እያስፈጀ፣ ኢትዮጵያን እያመሰ ይገኛል ። ለምን ይህ ይሆናል?
መልሱ ስልጣን፣ የፖለቲካ የሚሊታሪ ሃይል መያዝ፣ የኢትዮጵያን ሃብት ማካበት፣ መቆጣጠር፤ መታወቅ፣ የዝና በላይነት ለመያዝ እና ከሌሎች መከበርን ለማግኘት ነው ይህን ሁሉ የጎሳ ልሂቃን ነን ባዮች የሚባክኑት ። ሌላ አላማ የለውም።
በመሰረቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከዘመነ ዎያኔ አለተለየም። የዚህች አገር ቁጥር አንድ ችግር የጎሳ ፖለቲካው፣ የጎሳ ክልል ፌዴሬሽን ነው።
አሁን ምርጫ አለ ተብሏል። ግን በውን የሚካሄደው የጎሳ ሽኩቻና የጎሳ ሄጂሞኒ ፉክከር ነው።
ይሁንና በዚህ የኦሮሞና አማራ የጎሳ ሽኩቻ ጉራጌ የት ነው መቆም ያለበት? በሚቀጥለው ምርጫ ጉራጌ ለማን ነው ድምጹን መስጠት ያለበት? ይህን እጅግ ግዙፍና አንገብጋቢ ጥያቄ እያንዳንዱ የጉራጌ ተወላጅ በጥልቀት፣ በጥሞና፣ እጅግ አርቆ በማሰብ ወስኖ መመለስ ያለበት ጉዳይ ነው ።
ላለፉት 30 አመታት የጎሳ ፖለቲካ አሻፈረኝ ብሎ ስለጸና በዎያኔ ኢህአዴግ ስርዓት ሲጠቃ ሲገፋ ሲከፈል ሲወገድ የነበረው ጉራጌ አሁን ደሞ በተረኛ የጎሳ ፖለቲካ ተቀናቃኞች፣ አቀንቃኞችና አዲስ ተለጣፊዎች ወዲህና ወዲያ መጎተት ጀምሯል ።
የሰሞኑን የኦሮሞ ብልጽግና ድራማ እንመልከት ።
የጉራጌኛ ቋንቋ በኦቢኤን ለማስተላለፍ ዛሬ በ2013 ምርጫ ማግስት ለምን አስፈለገ? ለምን እስትራተጂያዊ አላማ? ለምን ዛሬ?
ልብ በሉ አቢይ አህመድ ጉራጌ ክልል እንዲኖረው አይገባውም ያለ አፈጮሌ ነው! እስከዛሬ በጸጥታ በመላ ኦሮሚያ ነብረቱ ነዶ ሚገፋ ሚገደል ጉራጌ ነው። ታዲያ ምን አዲስ ነገር መጣ?
በቅርብ ቀን አቢይ ባደረገው ረጅም ንግግር ደጋግሞ ያነሳቸው ሶስት ጎሳዎች ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጉራጌ እያለ ነበር ። እኔ የዚያን ቀን ኦሮሞ በጉራጌ ላይ አንድ ፕላን ማቀዱን በእርግጠኘት የተገነዘብኩት። ጉራጌ በኢትዮጵያ ያለው ቦታ፣ ተካፍሎ፣ አስተዋጻኦና ፋይዳ ከድሮ ምንም የተለወጠ ነገር የለም ።
ትግሬ ጉራጌን ተለጣፊ ለማደግ 45 አመት ሞክሮ ሳይሳካለት ወረደ። መለስ ጉራጌን በጎሳ ለማደራጀት የሞከረን የዛሬ 45 አመት ነበር ። እምቢ ስላልነው ስልጤን ገንጥሎ ተለጣፊ አደረገ ።
ዛሬም ኦሮሞች ያንን የተበላ እቁብ እንዳይሞክሩት እንመክራቸዋለን።
አንድ፣ አቢይ ከኢዜማ ጋር በሚያደርገው የምርጫ ፉክክር እውነተኛ የኦሮሞ ኢትዮጵያዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የሚያሳየን ኢዜማም ሆነ ሌላ ፓርቲ በነጻ በመላ ኦሮሞ በነጻ መወዳደር እንዲችሉ ሲፈቅድ ነው እንጂ ጉራጌን በኦቢኤን ሚዲያ በመደለና በማታለል አይደለም።
ስለዚህ አቢይ የጉራጌን ድምጽ ባዲስ አበባም ሆነ ባላገር ማግኘት ከፈለገው ይህን ከመሰለ ሽወዳ መውጣት አለበት። ያው እንደነ ካሱና ሬድዋን ያሉ ተለጣፊ የግል ጥቅም አሳዳጅ አድር ባይ ጥቂት የጉራጌ ግለሰቦች በትላልቅ ሆቴል ቤት ሰብስቦ ቪዲዮ መልቀቅ ቀላል ነገር ነው። ነገሩ ከዚያ አያልፍም ።
ሁለት፣ ኦሮሞ ጉራጌን ካማራ ለይተው የነሱ አጋር ወይም ተለጣፊ ወይም የጉዲፈቻ ልጅ ሊያደርጉ ያስቡ ይሆናል ። ይህን ካሰቡ ትልቅ ስህተት ይሰራሉ። ጉራጌ በፍጹም ኦሮሞና አማራ በሚያደርጉት የበላይነት ፉክቻ ውስጥ የሚፈድል ባለጌ ሕዝብ አይደለም ።
ጉራጌ ላማራ ሕዝብ ያለው ፍቅር የሚመነጨው ከአማራ ኢትዮጵያዊነት ነው። ጉራጌ ለኦሮሞ ሕዝብ ያለው ፍቅር የሚመነጨው ከኦሮሞ ኢትዮጵያዊነት ነው።
ኦሮሞ የጉራጌን አጋርነት ለማግኘት ኦቢኤን ቅብጥርስ ሳይሆን የጎሳ ፌዴሬሽን አፍርሶ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማራመድ ብቻ ነው ያለበት ።
ግን በፍጹም ለኦሮሞ የበላይነትና ሄጂሞኒ ቅዠት ጉራጌ ከአቢይም ሆነ ሺመልስ አይለጠፍም።
ሶስት፣ በአሁን ወቅት ኦሮሞ ከሚዋሰናቸው ጎሳዎች እዚህም እዚያ ጦርነትና ቀውስ ውስጥ ነው ያለው፤ አፋር፣ ሱማሌ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ሲዳማ፣ ወለጋ፣ ሌላም ሌላም ... እነዚህን ወደ ፊት እየበዙ የሚሄዱ ጦርነቶች መሰረታቸው የኦሮሞ ክልል ድንበሮች ስለሆኑ ችግሩ ሚፈታው የክልል ጽንሰ ሃስብ በመለወጥ እንጂ በ17 ቋንቋዎች በመስበክ አይደለም። ይህም ዘዴ የተበላ እቁብ ነው።
በአንድ ቃል በኦሮሞ እና ጉራጌ ሕዝብ መሃል ፍቅር ሰላም መረዳዳት መከባበር የሚኖረው የሚያድገው ኢትዮጵያን ኦሮሞአዊ ለማድረግ በመቃዠት ሳይሆን ኦሮሞን እውነተኛ ታማኝ ኢትዮጵያዊ በማድረግ፣ ያን የሚያደርግ የኦሮሞ ካልቸር በመገንባት ነው።
ጉራጌ በታሪኩ በመንግስት ቢሮክራሲ ደሞዝና በጉቦ የከበረ ያደገ ሕዝብ ሳይሆን በሚገፉትና በሚሰድቡት ገዥዎች አፍንጫ ስር፣ በራሱ ጥረት እና ብልህነት እዚህ የደረሰ ሕዝብ ነው።
በኦቢኤን ሚዲያ ላይ መለጠፍ ለጉራጌ የሚያመጣው ቅንጣት ፋይዳ የለም ። በራሱ ግዜ፣ ሃብትና እውቀት ጉራጌ የራሱን ሚዲያ ያቆማል ።
ዛሬ መሆን ያለበት የጉራጌ አጀንዳ የውስጡን አንድነት ማጠንከር፣ የራሱን ጉልበት መገንባት ፣ አገሩን ማልማት፣ በኢንዱስትሪ፣ ቴክኖሎጂ፣ ንግድ፣ ሳይንስ፣ በፍልስፍና፣ ትምህርት፣ በአርት፣ በስነ እምነትና በስነ ህይወት ለመመጠቅ ልክ እንደ ሁልግዜ ሌት ተቀን መስራት ነው ።
ኬር ለጉራጌ! ኬር ለኢትዮጵያ!
ሆረስ ዐይነ ኩሉ ነኝ