Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

የሴት ታጋዮቻችንና የ‘ገልጠም - አሶሳ - ገልጠም - ምጽዋ’ ገድል በፊዮሪ መሓሪ፡ ገነት ስዩም (ሽጎም) እንደተረከችው

Post by Meleket » 06 Feb 2020, 08:18

ይህ ጽሑፍ “ፈንቅል” በሚል ርእስ የትግሉን ዘመን ገድል ከሚተርከው 3ኛ ቅጽ መጸሐፍ ውስጥ የታጋይ ፊዮሪ መሓሪ የትግል ዘመን ታሪክን የዳሰሰ ታጋይ ነገት ስዩም (ሽጎም) የጻፈችው እ.አ.አ. በ1990 ምጽዋን ነጻ ለማውጣት የተደረገው “ኦፕሬሽን ፈንቅል” ወይ “ዘመቻ ፈንቅል” የሚባለውን ፈንቃይና ደምሳሽ የጦርነት ውሎ ዙርያ ያጠነጥናል። ታጋይ ፊዮሪ እግረኛ ሰራዊትን በመምራት “በቀጭኗ ጎዳና” ወይም “ስጋለት ቀጣን” በተባለችው መንገድ፡ ስፍር ቁጥር ያልነበረውን የጠላት አፈሙዝ የጥይት ውርጅብኝ ያቀናበትን ጎዳና ኣልፋ፡ ምጽዋን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ካስቻሉት ብርቅና ድንቅ እንስት ታጋዮቻችን አንዷ ናት። በዚህ “የቀጭኗ ጎዳና” ውጊያ ወቅት ጀብዱ ፈጽመው የተሰው ታንከኞችም ምጽዋ በተነሳች ቁጥር ሁሌም ይወሳሉ፣ ታንኮቻቸውም ምጽዋ ውስጥ የትግሉን ዘመን ታሪክ ይተርኩ ዘንድ ህያው ሃወልቶች ሆነው ተቀምጠው ይገኛሉ። ታሪኩ እንደወረደ በገነት ሽጎም አተራረክ ቀርቧል። ኮምኩሙ!

ሰምሃር የተባለው የቀይባሕር ዳርቻና ሜዳዎቹ ከረዢም ዘመናት ጀምሮ ብዙ ዕጹብ ድንቅ ፍጻሜዎች የተከናወኑበት ስፍራ ነው። የአካባቢውን የቅርብ ግዜ ታሪክን ስንቃኝ እንኳን፡ ዓይለትና ገምሆት የተባሉት የሰምሃር ቀየዎች፡ እ.አ.አ. በ1967 በኢትዮጵያ ሠራዊት በእሳት እንዲጋዩ ተደርገዋል። የምጽዋ ወደብንም ያለ አንዳች የነዋሪዎቿና የተወላጆቿ ተቃውሞ እንዳሻው ሊንፈላሰስባት ስለፈለገም ሕርጊጎ፣ እምበረሚንና ወቒሮ የተባሉትን ቀዬዎች ከነ ህንጻዎቻቸው በእሳት በማጋየት ነዋሪዎቻቸውንም በካራና በጥይት እያሳደደ ቁም ስቅላቸውን በማሳየት አመናምኗቸዋል።

ይህ የሰምሃር የቀይባሕር ዳርቻ በኤርትራ ህዝብ የነጻነት ትግል ታሪክ ውስጥ፡ እ.አ.አ. በ1977 ምጽዋን የማጥቃትና የስልታዊ ማፈግፈግ የተደረገበት እንዲሁም፡ እ.አ.አ. በ1990 የግፈኞቹ ባዕዳን ገዢዎች እድሜ ያጥርበት በነበረ ወቅትም፡ ለማመንና ለመተረኽ የሚያስቸግር በርካታ ተአምራዊ ገድላዊ ፍጻሜዎችን አስተናግዷል። ያም ሆኖ “እኔነት፡ ትምክህትና አጉል ኩፈሳ” እንዳይጎለብት በትግሉ ወቅት በተላበስነው የትግል ባህል አኳያ፡ እገሌ ወይ እገሊት እንዲህ እንዲህ አይነት ድንቅ ጀብዱ ፈጸመ ወይ ፈጸመች ይባላል ነበር እንጂ፡ ‘እኔ’ እያሉ መተረክ በኤርትራ ህዝብ የነጻነት ትግል ውስጥ ቦታ ያልነበረው መሆኑ የታወቀ ነው።

እስቲ የትግል አጋጣሚዎቻችንንና የገድል ታሪካችንን እንተርክ ስትባል፡ “ወታደራዊ ታሪክ መች የግለሰብ ታሪክ ሆነና!” ብላ ትጀምራለች ኤርትራዊቷ የነጻነት ታጋይ ፊዮሪ መሓሪ። ታጋይ ፊዮሪ መሓሪ እ.አ.አ. በ1977 ወደ ትግሉ ጎራ የተቀላቀለችና በበርካታ ጦርነቶችም የተካፈለች ተዋጊና አዋጊ ጀግና ነች። ወደ ትግሉ ከተቀላቀለችበት ግዜ ጀምሮ እስከ የኤርትራ ነጻነት ድረስ በተዋጊ የሰራዊት ክፍል ውስጥ ነበረች። ትግል የጀመረችበት ወቅት ‘ምዝላቕ’ ተብሎ በሚታወቀው፡ የኤርትራ የነጻነት ተዋጊዎች እስከ አፍንጫው ድረስ በሶቭየት ህብረትና በሌሎች ሃገሮች ብዙ ድጋፍ የተደረገለትን ግዙፍ የኢትዮጵያ የደርግ ሰራዊት በጥበብ ለማደባየት፡ ‘ስልታዊ ማፈግፈግ’ ባደረጉበት ወቅት ነበር። ፊዮሪም የደፈጣ ተዋጊ ምድብ ውስጥ ተመድባ፡ በጠላት ወረዳ ውስጥ ጥቃት ፈጽሞ፡ በመሸበት እየተሽለኮለከ የሚያድር የደፈጣ ጦር ውስጥ ‘አሃዱ’ ብላ የገድል ህይወቷን ጀመረች። በስንት ውትወታና ጥያቄ ገድላዊ ታሪዃን ልትነግረኝ የታሪኽ መዘክሮቿን እያገላበጠች ከብዙ ይሉኝታ ጋር ጥልቅ ትዝታ ውስጥ በመግባትም ገድላዊ ታሪኳን ከባህር በጭልፋ በተለይም ምጽዋን ለማጥቃት እ.አ.አ. በ1990 ስለተካሄደው ‘ኦፕሬሽን ፈንቅል’ እርሷ የተካፈለችበትን ውሎዋን እንዲህ አጫወተችኝ።

ኦፕሬሽን ፈንቅል ወይም በታጋዮች አሰያየም ‘ስርሒት ፈንቅል’ የተለኮሰው የካቲት 8 1990 ነው። ክፍለሰራዊታችን ማለትም 70ኛው ክ/ሰራዊት ግን ከወር በላይ ከአራምባ ቆቦ አራምባ ማለትም ‘ከገልጠም ወደ ገልጠም’ ነው የተወናጨፈው። እ.አ.አ. ሕዳር 11 1989 ክፍለሰራዊታችን ከዕጫይ ደብራይና ከአካባቢው ወደ ኋላ ማለትም ከምሽግ በኋላ ወዳለ ስፍራ ለልምምድና ቀጣይ ስልጠና እንዲወርድ ከተደረገ በኋላ፡ የመገናኛ ሬዲዮናችን በሙሉ ወሩን ሙሉ እንዲዘጋ ተደርጎ ነበር። ማንኛውም መልእክት በእግረኛ አማካኝነት ብቻ እንዲተላለፍም ተደረገ።

ተራ ታጋይ ይሁን ሃላፊም ወዴት እንደምንሄድ? ቀጣይ ስራችን ምን ማድረግ እንደሆነ፣ ምን እንደተወጠነ፣ በጭራሽ የሚያውቅና ለማወቅ የሚጨነቅ አንድም አልነበረንም። ነባሮቹ የሰሜናዊ ሳሕልና የናቕፋ ግንባሮችን ካፈራርስን በኋላ፡ ኑሯችን ቋሚና የተደላደለ አልነበረም። በከረን ግንባር ይሁን ማንኛውም የኛ ክፍለሰራዊት የነበረችበት ቦታ ሁሉ ጊዜያዊ ይዞታ ብቻ ነው የነበረን። በደንቡና በቅጡ አደልድለን ከሰራናቸው ምሽጎቻችን ወጥተን ጊዜያዊ መጠለያዎች እየሰራን ጠላትን እግር እግሩን እየተከተልን እንቅልፍ እንነሳው የነበር።

ገልጠም፡ ሃበሮ በተባለው ወረዳ ፡ ማለትም ከዛራ በስተምስራቅ የሚገኝ ከብዙ ትንንሽ ጅረቶችና ሸለቆዎች እየሰበሰበ ከምስራቕ ወደ ምዕራብ ወደ ዓንሰባ ወንዝ የሚቀላቀል ጠባብና ጥልቅ ወንዝ ነው። ገልጠም እንደ ስሙ በሁለት ትልልቅ ተራሮች መካከል የታቀፈ በመሆኑ፡ ድምጽ ሲፈጠር በቀላሉ አጋንኖና አግዝፎ የገደል ማሚቶው በጣም የሚያስተጋባበትና የሚያጉረመርምበት ወንዝ ነው። በገልጠም ወንዝ ውስጥ የሚገኙት ድንጋዮችና አለቶች እጅግ ትልልቅ አይደሉም። ሻካራዎችና ስለታማ በመሆናቸው ግን በገድል ላይ ገድል የሚጨምሩ አስቸጋሪዎችና ለመራመድ አሰናካዮችም ናቸው። ይህ ስፍራ የናቅፋው ግንባር ከመፍረሱ በፊት የመሸግንበት ሲኦል የሆነ ቦታ ነው። ከገልጠም በስተደቡብ ታጋዮች “ሃገር-ግኒ!” ብለው የሰየሙት በስተጀርባው የሚመታው አዳጋች ስፍራ፡ ይህ የገልጠም አካባቢ ነው።

ክፍለሰራዊታችን ከምሽግ ጀርባ ቆይታ ካደረግን በኋላ፡ ስልጠና ወደ ምናደርግበት ወደ ገልጠም ታሕሳስ እ.ኣ.ኣ. 13 1989 ተመለስን። ጠንካሮቹ ትልልቅ ማርቸዲሶቻችን በምርጥ ሹፌሮቻቸው እየተመሩ፡ ሳዋ ገባን። ከሳዋም በዒላ ኣብደላ በኩል ወደ ሱዳን መሬት ገባን። ሌት ተቀን ያለ አንዳች እረፍት ተጉዘንም አባይን ወይም ኒልን(ናይልን) አቋርጠን፡ የኢትዮጵያ መሬት ውስጥ ገባን። ታሕሳስ 30 በገስ በተባለ ስፍራ፡ የጉዟችንን ዓላማና ተልእኾ በተመለከተ በ70ኛው ክፍለ ሰራዊታችን አዛዥ በፊሊጶስ ወልደዮሃንስ (የአሁኑ ጄነራል) ኣማካኝነት ገለጻ ተደረገልን። ከወር በኋላ ገደማም ጊዛኒ ላይ በከፈትነው የማጥቃት እርምጃ ተዘግተው የነበሩት የክፍለሰራዊታችን የመገናኛ ሬዲዮኖች ተከፈቱ። ጠላትም ጠፍቶበት የነበረው የኛን ድምጽ ጊዛኒ ማለትም ምዕራብ ኢትዮጵያ ላይ ሰማ። ወደ አዲስ አበባ የሚወስደውን ዳውስ ላይ የሚገኘውን ድልድይም እ.አ.አ. ጥር 8 1990 በፈንጅ አፍርሰን፡ የጠላትን ቀልብ ስበን ወዲያውኑ ተመለስን።

ጊዛኒ ወደ ዳውስ የተጓዝነው ብርቱ በሆኑት የስለያ ክፍሎቻችን አባላት እየተመራን ባይሆን ኖሮ እጅግ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ወይ ዱር በመሆኑ እጅግ አዳጋች በሆነብን ነበር። የምትረግጠው መሬት ሁሉ ረግረግ ጭቃ ነው። የሰው ሳይሆን የአራዊት ስፍራ ነው፡ ምንም ያልተዳሰሰ ድንግል መሬት፡ ሰው ሆነ ከብት ያልረገጠውን ስፍራ ተረማመድንበት ተጎማለልንበትም። ያኔ አዲስ የሃይል አመራር የሆንኩበት ግዜ ነበር። በዚያ ጭልጥ ባለ ዱር ወይ ጫካ ውስጥ የመገናኛ ሬዲዮዬ፡ ወዲህ ብላት ወዲያ ብላት ድምጿ ጥልቅም ብሎ ጠፋ! እንደዚያ ጊዜ ሆኜ ተጫንቄ አላውቅም። የሚነኩትን የሬዲዮ ክፍሎች ሁሉ ብነካካ ድምጽ የለ ምንም የለ ጥልቅም ብላ “ሹሽ” ብላ ድምጿን ማሰማት አሻፈረኝ አለችኝ! ከጊዛኒ ማለትም ከአሶሳ አካባቢ አይደለም የሬዲዮ ግንኙነት አቋርጠህ ይቅርና፡ በእግር እንኳ ስትሄድ እጅ ለእጅ ተያይዘህ ከመሄድ ከተሳነፍክ፡ አለቀልህ ነው! ብልህና ጀግና የኮማንዶ ስለያ አባላት ስለነበሩን ግን በነሱ ጥበብና የሬዲዮ ሞገድ ችግራችን ተፈታ።

ጥቃት ወደምንፈጽምበት ወደ ተልዕዃችን ስፍራ ስናመራም፡ ትንሽ ገላጣ ቦታ ስላገኘሁ ለማወሃሃድ ከግራ ወደ ቀኝ ሳማትር፡ ወደ ቤቱ ወይ ስፍራው የገባሁበት፡ ጆሮ ይሁን ቀንድ እንደነበረው በውል ያላጤንኩት ዘንዶ፡ ግማሽ ሜትር የሚሆን አካሉን ከሳሩ መሀል አቅንቶና ቀጥ አድርጎ፡ በሚያጉረጠርጥ ዓይኖቹ አፈጠጠብኝ! ዳግም ተመልሶም ለጥ ብሎ ለመንቀሳቀስ ሞከረ፡ ከግዝፈቱ የተነሳም እንደልቡና እንዳሻው ለመንቀሳቀስ ያዳግተው ነበር። እንዲያው እንዲህ አይነት ነገር አየሁ ሳልል እየተጣደፍኩ ወደ መሪዎቻችንና አባሎቻችን ተቀላቀልኩ። ከአሶሳው ተልዕኳችን በኋላ፡ ሌትና ቀን በማርቸዲስ ተጉዘን ግምሩክ(‘ኩርሙክ’ ይሆንን? ተርጓሚው ያከለው) ወደሚባል የሱዳን መሬት ተመለስን፡ ቁስለኞቻችንና ሠራዊታችን ባጠቃላይ ለሳልስትም እረፍት አደረግን።

ያኔም በሳህል ይሁን ባርካ ውስጥ አይተናቸው የማናውቅ፡ በጥፍሮችና በእግር ጣቶች መካከል ቆዳ ፈልቅቀው የሚገቡ ትላትል ፍጥረቶች፡ እጆቻችንና እግሮቻችንን አቆሳሰሉን። ይህን ቦታ የሚያውቁት የስለያ አባሎቻችንም እነዚህ ትሎች “ሙጀሌ ወይ ቦጀሌ” እንደሚባሉ ነገሩን። በመርፌም ነቅሰን እንድናወጣቸው ነገሩን። እርስ በርሳችን በመርፌ ሙጀሌዎቹን ነቃቅሰን ካወጣን በኋላ፡ የዳውስን ድልድይ በፈንጅ አፍርሰን፡ በምዕራብ ኢትዮጵያ ለጠላት ድምጻችንን አሰምተን፡ የመገናኛ ሬዲዮኖቻችንን አጥፍተን፡ ያለ እረፍት ሌተቀን ተጉዘን ወደ ተነሳንባት ገልጠም ተመለስን። ከበገስ ወደ ዒላ ዓብደላ፡ ከዒላ ዓብደላ ዓዳይት፡ ከዓዳይት መዝረት፡ ከመዝረትም የማደናገሪያ ስልታችንን ጨርሰን ወደ ተነሳንባት ገልጠም እ.አ.አ ጥር 26 1990. ተመለስን። ይህ ደግሞ ኦፕሬሽን ፈንቅል ከመጀመሩ ሁለት ሳምንታት በፊት ነው።

ይህ ሁሉ ከሁለት ወራት በላይ ከገልጠም ወደ ገልጠም ማለትም ከአራምባ ቆቦ አራምባ እንወናጨፍና እንጥበለበል የነበረው፡ ወደ ዋንኛው የሰምሃር ስርሒት ፈንቅል ማለትም ኦፕሬሽን ፈንቅል ጥቃት ለመፈጸም፡ ጠላትን ለማደናገርና ለማደነጋገር ነበር። በገልጠም ለሳልስት አደረጃጀታችንን በቅጡ ከፈተሽንና ካስተካከልን በኋላ፡ እጅግ ጥንቃቄና ምስጢራዊነት በተሞላበት እንቅስቃሴ በእግር ከገልጠም ታንከኞቻችን ወደሚገኙበት ሃበሮ፡ ከሃበሮም ወደ አፍዓበት፡ ከዚያም በሌሊት አፍዓበትን በስተግራ በመተው በረሃ ለበረሃ የእግር ጉዞ በማድረግ ዒን ወደ ተባለው ወንዝ አካባቢ ገባን፡ እዚያም ተደብቀን ዋልን። (በማግስቱ ምን እንዳደረግን በቀጣዩ ክፍል ትረካችን ይጠብቁን!) :mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: የሴት ታጋዮቻችንና የ‘ገልጠም - አሶሳ - ገልጠም - ምጽዋ’ ገድል በፊዮሪ መሓሪ፡ ገነት ስዩም (ሽጎም) እንደተረከችው

Post by Meleket » 07 Feb 2020, 04:20

የጀግናይቱን ትረካ እንቀጥልላችኋ!

ከዚያማ በማግስቱ ከዒን ወደ ማይ-ኡለ አመራን። ከማይ-ኡለም የሰሜንናዊ ባሕሪ ክፍሎች ተሰባስበው ወደሚፈሱበትና ሚደባለቁበት ስፍራ ማለትም የሰለሙና፡ የግርግር፡ የማይ-ላባና ማይ-ኡለ ወንዞች ተደባልቀው ወደ ቀይባሕር ወደሚፈሱበት አስቸጋሪ የወንዝ ዳርቻዎች የሚገኙበት ስፍራ በስለያ አባላቶች ተመርተን በመሻገር፡ ዋንኛ ተልዕኳችን ወዳነጣጠረበት የሰምሃር ሜዳዎች ገባን። እዚህ ለመድረስ ለስድስት ቀናት ያህል ያለ በቂ ውሃና ምግብ ተጉዘናል። ከዚያም በኋላ አይናቸውን አፍጥጠው የሚጠብቁን ብርቱ የሞት የሽረት ውጊያ፡ ድካም፡ መቁሰልና መሰዋእትነት ናቸው። ሁሉንም በእምነት ስለተቀበልነው ግና ግዜውና ሁኔታው እንዲያው ዝም ብሎ ጣፋጭ ነበር። በዚህ አይነት ሁኔታ ላይ የሚፈጠር ድፍረት የሚፈጥርልህ ነገር ቢኖር ለህይወት ዘመንህ በሙሉ ሊያኖርህ የሚችል በራስ የመተማመን ስንቅን ነው። 70ኛ ክፍለሰራዊታችን በዋነኝነት ከ44ኛ ብርጌድና ከ23ኛ ብርጌድ የደፈጣ ስልት ጋር የተቆራኘ የደፈጣ ስልት ባህርይ የነበረው የጦር ክፍል ስለነበረ፡ በሜዳማው ክፍል ወደ ውጊያ ለመግባት የተመረጠበት አንዱ ምክንያት ይሆናል።

በስድስተኛው ቀናችን፡ ከማይ-ኡለ ተነስተን ስንጓዝ አድረን፡ ማለዳ ሩባ ዘነብ በተባለው፡ ውጊያ ወደሚጀመርበት ስፍራ ደረስን። የዘነብ ወንዝ ዓድ-ዕለ ከተባለችው ኮረብታ በስተሰሜናዊ ምስራቅ ትገኛለች። የመጀመሪያዋ ሻምበል(ቦጦሎኒ 70-1) የሰራዊታችን ክፍሎች በስተ ግራችን በእምበረሚ በኩል የባህር ዳርቻዎች ተመድበው ነበር። የካቲት 8 ማለዳም፡ የሰምሃሩ የማጥቃት እርምጃ በይፋ ተጀመረ። እኛ ግን ለጥ ባለው ሜዳ - አሁን የምጽዋ አየር ማረፊያ በታነጸበት ስፍራ - እንድንገባ ስለተመደብን፡ የዓድ-ዕለ ውጊያ ሂደትን ሳናረጋግጥ መንቀሳቀስ አንችልም ነበር። ጠላት በዓድ-ዕለ ጥርሱን ነክሶ ሲዋጋ ዋለ። ዓድ-ዕለ ከባህሩ ዳርቻ አካባቢው ያለ የተለቀው የኮረብታ ከፍታ ነው። ከረፋዱ 4፡00 ሰዓትም ጠላት ያለ የለሌ ሠራዊቱንና ታንኮቹን ይዞ ዓዲ-ዕለን ከበስተጀርባ በእንትልፋፍ ሜዳዎች በኩል ዞሮ ለማጥቃት እኛ አድፍጠንበት ወደነበረው ስፍራ ቀጥ ብሎ መጣብን። ፋጎት(ጸረ ታንክ) መሳሪያ የታጠቁ አባሎቻችን ተዘጋጅተው ስለነበረ፡ የመጀመሪያዋን የጠላት ታንክ አጋዩዋት። ጠላት ተቀላጥፎ ወደኋላ አላፈገፈገም፡ ነገር ግን መደናገጡን ሲመሰክር ትንሽ እንደመቅረት ብሎ ከፈጣኑ ጉዞው ተገታ። እኛ ማጥቃታችንን ስንቀጥል ግን ጠላት አሁንም ጥርሱን ነክሶ መዋጋት ጀመረ። ታንከኞቻችን በምን ቅጽበት እንደደረሱልን ባናውቅም፡ ሰው ከሰው ጋር መዋጋት ቀርቶ ታንክ ለታንክ በዚያ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ እኔ ነኛ ያለ ውጊያ ቀጠለ። ጠላት ሆን ብሎ ስልታዊ ማፈግፈግ አድርጎ፡ ወደ ውስጥ ይዞታው ስቦ ሊደቁሰን አስቦ ይሁን ወይም የእዝ ሰንሰለቱ ተፈረካክሶበት ልናውቅ ባንችልም፡ ሲሸሽ ዋለ። ሸሽቶ ሸሽቶ መጨረሻ ላይ የባህሩ ዳርቻ ስለሚቀበለው ሌላ መፈናፈኛ መከላከያ ዕድልም አልነበረውም፣ እኛ ግን ተልዕዃችን በስሚንቶ ፋብሪካ በኩል አድርገን ወደ ናቫል -በይዝ ነበር። አሁን ስታዪው አጭር ይመስላል፣ ያኔ ግን . . . !

የካቲት 8 እዛ ሜዳው ላይ ስንዋጋ ውለን ጸሃይዋም ጠለቀች። እንደመሸም በኛ በኩል ሆነ በጠላት በኩል የቆሰሉብንን ስናወጣና ስንደራጅ አመሸን። ጠላት ከሌሊቱ 4 ሰዓት እኔነኝ ያለ፡ ብርቱ የከባድ መሳሪያ ድብደባ ያጀበው ሃያል የመልሶ ማጥቃት ሞከረ። ቦታው ካለ አንዳንድ ትንንሽ ሰርጦች በስተቀር ምንም ዓይነት ከለላ ልታገኝበት የማትችል ገላጣ ሜዳ ነው። ባገኘነው ስፍራም መሬት ላይ ለጥ አልን። ውጊያው አልቀጠለም፡ ጠላትም አልገሰገሰም በነበረበት አደረ። ጠላት የካቲት 8 በአየር ማረፊያው አካባቢ ሜዳማ ስፍራ ማደሩና መቆየቱ በማግስቱ ለሚደረገው ውጊያ ብርቱ ዕንቅፋት ሆኖን ዋለ። ሌሊቱን ሙሉ በዶዘሮች እየቆፈሩ ታንኮቻቸውን ሲቀብሩ አደሩ። በማለዳ ውጊያ ጀመረ። አፈሙዛቸው ብቻ የሚታይ ምሽግ ውስጥ የተቀበሩ ታንኮች ፍንክች እንዳንል አድገው መላወሻ መፈናፈኛና መንቀሳቀሻ ነሱን።

እግረኛ ሰራዊታችንም እነሱን እየተጠጋና እየታከከ በርካታ ግዜ የመልሶ ማጥቃትን ሲያደርግ፡ እኔ ነኝ ያለ ውጊያንና የውጊያን አስጠሊታነት በዓይናችን አየን። የካቲት 10 በማለዳ በተደረገ የተወሃሃደ ማጥቃጥ፡ ማለትም ከፎርቶ የተነሳው ሰራዊታችን ወደ ዕዳጋ ስለገሰገሰ፡ በጋራ እኛም ለመገስገስ ቻልን። የጠላት ሰራዊት በባህር ሆነ በምድር ሙሉ በሙሉ ቀጭኗን መንገድ ማለትም ስጋለት ቀጣንን አልተሻገረም ነበር። (ስጋለት ቀጣን በባህር ላይ ያለች 1 ኪሜትር የምትሆን ምጽዋን ከርእሲ ምድሪ ጋር የምታገናኝ መንገድና ድልድይ ነች፡ በእድሳት ላይ ነበረበችበት ወቅት በከፊል ይህን ትመስላለች፡ ተርጓሚው)

ይህችም ከታደሰች በኋላ የተነሳችው ሲሆን ከእድሳት በፊት በጦርነቱ ወቅት መንገዲቱ እጅግ ጠባብ እንደነበረች አይዘነጋም።

የሰው ልጅ “በቃኝ ተሸንፊያለው! ኣይልም እንጂ፣ ያን ዕለት ማለዳ የሞተውና የተማረከው የጠላት ሰራዊት ስፍር ቁጥር አልነበረውም። ከሞት ያመለጡ ወታደሮችና ምጽዋ ውስጥ የቆዩት ተደርበዋቸው ባንድላይ በመሆን ‘ማን ጀግና ነው ስጋለት ቀጣንን የሚያልፍ’ በማለት፡ አለ የተባለ ከባድና ቀላል መሳሪያዎቻቸውን በአጠቃላይ ‘ቀጭኗ መንገድ’ ስጋለት ቀጣን ላይ ኣቀኑ። የካቲት 10 ስጋለት ቀጣንን ለማለፍና ለመጣስ በእግረኛና ታንከኛ ሰራዊታችን በኩል ተሞክሮ ነበር። የተከፈለው መስዋእትነት ከተገመተው ስለበዛ ግን ወዲያውኑ ተቋረጠ። እነዚህ ታሪክ ይመሰክሩ ዘንድ ነባሪ ሃውልት ሆነው ምጽዋ ውስጥ የተቀመጡት ታንኮች የካቲት 10 ምጽዋ የገቡ የኤርትራ ህዝብ የነጻነት ታጋዮች ታንኮች ናቸው።

(እንደ https://en.wikipedia.org/wiki/Battle_of_Massawa_(1990) አገላለጽ በኤርትራ ነጻነት ተዋጊዎችን በኩል ውጊያዉን ይመራ የነበረው ታጋይ ስብሃት ኤፍሬም (የአሁኑ ጀነራል) ሲሆን በኢትዮጵያ ሰራዊት በኩል ደግሞ መንግስቱ ሃይለማርያም እንደሆነ ይገልጻል። እንደሚታወቀው ታጋይ ስብሃት ኤፍሬም በአንድ ወቅት በኤርትራ ቴሌቭዥን በሰጠው የውጊያውን ሂደት የሚመለከት መግለጫ፡ ፈንቅል የሚለውን ስያሜ የተሰየመው፡ የጠላትን ኃይል ለመፈንቀል የታለመ ቁርጠኝነትን ለማመልከት ብቻ ሳይሆን በትግሉ ወቅት እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉት የተሰው ታጋዮች አንዱ የሆነውን ወዲ-ፈንቅልን ለመዘከር የተደረገ አሰያየምም መሆኑን ቁልጭ አድርጎ እንደገለጸ ተርጓሚው ያስታውሳል።) ወደ ትረካዋ እንመለስ፦

የካቲት 11 የስጋለት ቀጣንን አፎች የመጠበቅ ተልእኮ ለኛ ሃይል (የመቶ) ተሰጠ። ያ ከገልጠም እስከ ስጋለት ቀጣን ለሁለት ወራት የተወናጨፍንበት የማደናገር ጉዞና ውጊያም የመጀመሪያ ምዕራፉ ላይ ደረሰ።

የካቲት 13 ቀን እኔ ከሶስት ጓዶቼ ጋር ‘በቀጭኗ መንገድ’ ዘብ ቆመን እያለን፡ የጦር አውሮፕላኖች መጡብን። ኪሳራችንን ለማጉደል በማለምም፡ አሁን አዳዲስ ፎቆች በተሰሩበት አካባቢ ድልድዮች ስለነበሩ፡ ሰራዊታችን ጥበቃን ትቶ በነዚያ ድልድዮች ውስጥ ይደበቅ ነበር። ተዋጊ አውሮፕላኖቹ ጭነው የመጡት፡ አስፋልቱን ደረማምሶ መሬቱን ሁሉ ብትንትን ለማድረግ የሚችሉ ቦንቦችን ነው። ከነዚህ መካከል አንዷ ወደኛ ቦንቧን ብትወረውርም የአስፋልት ጥርጊያውን ስቶ በባህሩ ዳርቻ ባለው መሬት ላይ ወደቀ። እኛ ይህ ቦምብ በፈጠረው የጭቃ ፍንጥቅጣቂ ፊታችን ሁሉ ተሸፍኖ ሰው አንመስልም ነበር። ጀሮዎቻችን በምን ተአምር ከመደንቆር እንደተረፉ አይገባኝም! ተዋጊ አውሮፕላኖች እንደሄዱ፡ አባሎቻችን እኛ በህይወት የተረፍን አልመሰላቸውም። እኛ ወደ ነበርንበት ሲመጡም አንድም ሊቀብሩን አሊያም ከተበታተንበት አስከሬናችንን ለመሰብሰብ ብለው እንጂ በህይወት እናገኛችዋለን ብለው ተስፋ አልነበራቸውም።

አጋጥሞን በነበረው የቁስለኛና የተሰው ጓዶች ምክንያት ቁጥራችን ተጓድሎ ስለነበረ፡ እ.አ.አ. 1977 ጠላት ከምጽዋ ውስጥ ዳግም ሃይሉን አስተባብሮ የሰምሃርን ሜዳዎች እንደተመለሰባቸው ሁሉ፡ አሁንም ከ 13 ዓመታት በኋላ ያን የመሰለ ብርቱ መስዋእትነት እንዳይደገም፡ ተራ ታጋዮች ሆኑ አመራሮች በእልህ ተሞልተን ነበር። ለአራት ቀናት ያህል ሁሉንም ያስደመመ፡ ጠላትንም ያስገረመ ዝምታ ሰፈነ! የካቲት 13 ሁለት ምርኮኛ ወታደሮች ነጭ የሰላም ጨርቅ እያወዛወዙና እያርገበገቡ፡ የሰላም መልእኽት ተሰጥቷቸው፡ ወደ ምጽዋ ውስጥ እንዲገቡ ተላኩ። “ሞኝ የገበጣ ጠጠሩ እስኪያልቅ ይጫወታል!” እንዲሉ ጠላት የመረጠው የገበጣ ጠጠሮቹ እንስኪያልቁ መዋጋትን ነው። የካቲት 14 ምሽትም፡ በራሳቸው ምርጫ፡ ከራሳቸው በማረክነው ከባድ መሳርያ፡ ለኛ የተመኙትን ስቃይና መከራ፡ የከባድ መሳርያ ድብደባ ምጽዋ ውስጥ ወደ ነበረው እጄን አልሰጥም ወዳለው የጠላት ሰራዊት በማቅናት፡ ምጽዋ ስትናወጥና ናላዋ ሲዞር ዋለች። ምንም እንኳ ውጊያ ሁሌም አስጠሊታ ቢሆንም ቅሉ፡ ያን ዕለት የነበረው ግን እጅግ ሰቕጣጭ ነበር! ትንሿ ደሴት ምን ሆና ነው ባህሩ ውስጥ ያልሰጠመች ያስብላል?! ህንጻዎቿስ ምን ሆነው ነው ወደ አሸዋነት ያልተቀየሩትም ያስብላል፣ ሳስበው እስከ ዛሬ ድረስ ይገርመኛል።

የቀጭኗን መንገድ የስጋለትን አስፋል ወይ ድልድይ የመሻገር ተልእኮ የተሰጠው ለኛዋ ሻምበል ነው። መሪዎቻችን ሃይለ ጠዓመና ምሕረተአብ (ሃይወይ) ነበሩ። ማታ የማጥቃት እርምጃውን አካሄድ ውጥን ወይ ንድፍ ለመግለጽ ጠሩኝ። “ቀጭኗ መንገድ” ወይ “ስጋለት ቀጣንን” መቆጣጠር ያንቺ ሃይል ወይ የመቶ ተልዕኾ ነው! ወደ ምጽዋ ውስጥም መግባት ያንቺ ተልዕኾ ነው!” በማለት ትእዛዝ አስተላለፉልኝ። ሁሌም ለመስዋእትነት ዝግጁዎች ስለነበርንም የተሰጠንን ተልዕኾ በፍላጎትና በወኔ መተግበር ብቸኛው ምርጫችን ነበር።

ከዚያ ምድረሰማዩን ጨለማ ካለበሰው ጠላት ላይ ካዘነብነው የከባድ መሳርያ ድብደባችን በኋላ፡ መሬት ወገግ ሲል የማጥቃት እርምጃችንን ጀመርን። ወዲ-ሓውሲ ብለን የምንጠራው አባላችን የሚመራትን ጋንታ ተከትለን፡ ከሁለተኛዋ ጋንታ ውስጥ ፍስሃየ እኔና የኔ የራዲዮ ቴክኒሻን ብርሃነ ማንጅስ እና፡ ሶስተኛም ጓል-ሓድጉ የምትመራት ጋንታ ተመራርተን ማጥቃቱን ለመፈጸም ተነሳን። ቀይባሕር ጎደል ብሎ ስለነበረ አንዳንዶቻችን በአቅራቢያው ባለ ዳርቻ ወይ ምድር፡ አንዳንዶቻችን ደግሞ ቀጭናኡን አስፋልት ተከትለን ዚግዛግ እየሰራን በመሮጥ መግባት ጀመርን። መጀመርያ ለማጥቃት የገሰገሰው ሰራዊት መሪ ወዲ-ሓውሲ አስፋልቱ መሃል ተመቶ ቆስሎ ቆየኝ። ያኔ ምንም የማወሃሃደውና በሬዲዮ ሞገድ የምገናኘው አካል ስላልነበረ፡ ወደ ተዋጊነት ተቀይሬ ሬዲዮኔን ዘግቸ ከአባላቶቸ ጋር እየተኮስን ወደ የጠላት የመጀመርያ ምሽግ ገባሁ። ያኔ መሽቶ ስለነበረም እንዲያው በደፈናው በእሩምታ ለመተኮስ እንጂ አነጣጥሮ ለመተኮስ አይመችም ነበር። ቀጭኗን ጎዳና ስጋለት ቀጣንን አልፈን ከድልድዩ ማዶ ባለው መሬት እግራችንን እንዳሳረፍን በጆኒያ ሙሉ እህል በተገነባ ምሽግ ውስጥ የነበሩ ወታደሮች አስፋልቱ ላይ ቆዩን። በድፍረት ቀጥ ብለን በመግባት ቦንቦቻችንን እንደወረወርንባቸውም፡ በረዶ ወደሚሰራበት ስፍራ በኩል ሸሹ። ስጋለት ቀጭኗን መንገድ ተሻግረን ይበልጥ በጠላት ወረዳ ውስጥ እንደገባን፡ የመገናኛ ራዲዮዬን ድምጽ ሰምተው እንዳይመቱኝ የመገናኛ ራዲዮዬን ጥርቅም አድርጌ ዘግቻት ነበር። ስጋለት ቀጣንን ተሻግሬም መሬት ላይ አደልድየ መርገጤን አረጋገጥኩ። የመገናኛ ሬዲዮዬን ዘግቻት ነው እንጂ “የስለያ አባላት ቀድመዋችሁ ከፊት ከፊታችሁ አሉ፡ እናንተ ከነሱ በኋላ ነው የምትገቡት!” ተብለን ነበር። የሌሊት ማለት የጨለማና የከተማ ውጊያ ላይ ማን እንደሚመታህ ለማየትና ለማወቅ አስቸጋሪና አዳጋች ነው። አንተ የት እንዳለህ አያዩህም፣ እነሱ የት እንዳሉም አታያቸውም። እኛ በነሱ በጠላቶቻችን ቦታ ውስጥ ስለገባን ግን፡ እነሱ ባሻቸው መሸጎጫ ሲደበቁና ሲወሸቁ፡ እኛ ደግሞ ከለላ ሊሆነን ይችላል ባልነው ስፍራ እንጠጋ ነበር።

ይህች አስቸጋሪዋን ጠባቧን መንገድ ስጋት ቀጣንን እንደተሻገርኩና አስተማማኝ መዋጊያ ከለላ ማግኘቴን ካረጋገጥኩ በኋላ፡ የመገናኛ ራዲዮዬን ከፈትኩ። “ተሻግሪያለሁ፣ ሁነኛ መቆናጠጫ ይዣለሁ፣ በአፋጣኝ ረዳት ኃይል ደርብልኝ፡ አዎን ባፋጣኝ ላክልኝ!” የሚል የምሥራችን በወታደራዊ ኮድ አማካኝነት ለአለቃየ አስተላለፍኩ። ይህቺ የምስራች ለአለቃየ ለወዲ ጠዓመ ብቻም አልነበረችም፤ የምስራቿ ለሁሉም በኔ የመገናኛ ሞገድ ውስጥ ይከታተሉኝ ለነበሩት የግንባሩ አመራሮችን ባጠቃላይ ያበሠረች ነበረች። ከዚች የራዲዮ ምሥራች በኋላ፡ ከመቅጽበት ደጋፊና ረዳት ኃይል ተላከልኝ። በስተባህሩ ደግሞ ከባሕር ወደ ምጽዋ በጀልባዎች አድርገው የገቡ የሠራዊታችን ክፍሎችም፡ የጠላት ሰራዊት ከበስተጀርባው ጥቃት መፈጸም ጀምረውበት ነበር። የካቲት 11 እንዳጋጠመው ዓይነት አደጋ፣ ታንኮቻችን ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ስለተሰጋ ለግዜው እንዲያደፍጡ ብቻ ተደርጎ ነበር። በዚህ ቅጽበት ግን እየተንፈላሰሱ አለን ብለው በያሉበት ወደኛ አቅጣጫ እያጓሩና አይምሬ ክንዳቸውን በጠላት ላይ ለማሳረፍ እየተቀላጠፉ ተከተሉን። ከዚያም ምጽዋ ውስጥ ስለገባን የጠላትን ድምጽ በሰማንበት አቅጣጫ እያራወጥን እንደፍቀውና እንጨፈልቀው ጀመርን - የምጽዋው ውስጥ ውጊያ እንዲህ ጀመረ። (ምጽዋ ውስጥ የነበረው ውጊያ እንዴት እንደቀጠለ በቀጣይ ክፍል ይጠብቁን) :mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: የሴት ታጋዮቻችንና የ‘ገልጠም - አሶሳ - ገልጠም - ምጽዋ’ ገድል በፊዮሪ መሓሪ፡ ገነት ስዩም (ሽጎም) እንደተረከችው

Post by Meleket » 08 Feb 2020, 04:55

ከባለፈው የቀጠለውን፡ የምጽዋ ውስጥ ውጊያ እንዴት እንደቀጠለ ነው ዛሬ የምተርክላችሁ አይደል? :lol:

ማታ 3 ሰዓት ገደማ፡ አንድ ቤት አጠገብ ሆኜ በመገናኛ ሬዲዮዬ ውጊያ ሳወሃህድ፡ ቤቱ ውስጥ የጠላት ኃይሎች እንዳይኖሩና ጥቃት እንዳይፈጽሙብኝ ስለተጠራጠርኩ፡ ትንሽ ፈቀቅ ብየ ከአንዲት ዛፍ ጋር ተጣብቄ ውጊያ ማወሃሃዴን ቀጠልኩ። አሁን የተቃጠሉት ታንኮቻችን ታሪክ ይነግሩ ዘንድ ሃውልት አድርገን ባቆምንበት አደባባይ አካባቢ አንዲት እግሯ ሰንሰለት ሳይሆን ጎማ የሆነ ታንክ በድንገት መጣች፡ ያቺ ከለላ ተጠቅሜባት የነበርኳት ዛፍ ስላገዘችኝ ግን አልታየሁም፡ እኔም ራዲዮ ይዤ የነበርኩባትን እጄን ከዛፏ ጋር አገናኝቼ ወደላይ ሁለተኛዋን እጄንም ከዛፏ ጋር አቆራኝቸ ልጥፍ አልኩባት። ከዛፏ ጋር በደንብ ስለተመሳሰልኩ ታንኳ ሳታየኝ አለፈች። እኔን እንዳለፈች ‘ዶሽካ’ የተባለውን መሳርያ ይዘው የነበሩ አባሎቻችን አይታ፡ ጥይቶቿን አርከፈከፈችባቸው። ያኔም ‘ዶሽካ’ የተባለውን መሳሪያ ይዘው ከገቡት አባላቶቻችን ጣቡስ የምንለው መሪያቸው ተሰዋ። ታንኪቷም ሳትመለስ በዛው ሄደች። ቀጭኗን መንገድ ስጋለት ቀጣንን ለጉድ ተርፌ እንዳልተሻገርኳት፡ በዚች ትንሽ ዛፍ ላይ ተጣብቄ ለረዢም ግዜ ቆየሁ። በኋላማ በየፈራረሱ ቤቶችና በየ እህል ጆንያዎች በተሰሩ ምሽጎች ውስጥ የነበሩ ወታደሮችን “ንዓ ውጻእ!” ማለት “ና ውጣ!” ስንል ሌሊቱን ሙሉ ጠላትን ስንለቃቅም በድካም አሳለፍነው።

አንድ ለመጥቀስ የምሻው ነገር ቢኖር፡ ቀጭኗን መንገድ ማለትም ስጋለት ቀጣንን የተሻገርኳት ሴት እኔ ብቻ አይደለሁም። በሃላፊነት ደረጃ ከነበሩት መካከል መብራት ሓድጉ (ጓል-ሓድጉ) የመጀመሪያዋ ጋንታ መሪ፡ ፍዮሪ ታረቀ የመስርዕ መሪ፡ የጋንታ ሓኪሟ አበባ ጎሮዶ የሚገኙ ሲሆኑ ተራ ሴት ታጋዮች ደግሞ እጹብ ድንቅ ጀብዱ የፈጸሙ በርካታዎች ነበሩ።

“በከተማው ውጊያ ወቅት ከመስታውት ጋር ሳይቀር የሚዋጉ አባላቶች ነበሩ” ሲባልን የኋላ ኋላ ሰምቻለሁ። ከመስታውት ጋር መዋጋት ሳይሻል ይቀራልን?! አሁንም ድረስ ቦታው እዚህ ነበር ለማለት እማልችለው ስፍራ ግን ደግማ የተዋጋሁበት ስፍራ አለ። እናትና ልጅ ናቸው እስክንባል ድረስ ከጓል-ሓድጉ ጋር በራዲዮ ሞገድ በቀጣይ እንገናኝ ነበር። ወደሷ ለመሄድ ከአንዲት የቤት ግድግዳ ወደ አንዲት የባሕሩ ዳርቻ ክፍል ልሄድ ስል፡ አንድ ወታደር “እዚ አለሁኝ” በማለት ድምጹን አሰማኝ። ለጠላት ጥይት ገላጣ ቦታ ላይ እያለሁ በድፍረት እጅ ወደላይ በማለት አፈጠጥኩበት። ወደ ኋላ ተመልሼ፡ ወታደሩ ከነመሳሪያው እጁን ሊሰጠኝ ወደኔ ሲጠጋ፣ “እኔም አለሁ” እኔም አለሁ” “ኣብዚ እኔሄኩ” እያሉ ስምንት ነጭለባሽ በስንዴ ተገዝተው ለጠላት የወገኑ የትግራይ ሚሊሻዎችና ኤርትራውያን ሚሊሻዎችም እጃቸውን ለመስጠት በፊቴ ተርመሰመሱ። መሳርያችሁን ጣሉ ስላቸውም ሁሉም መሳርያቸውን ጥለው እጃቸውን ወደላይ በማንሳት ተባበሩ። ምርኮኞቹን እየነዳሁ ወደ ጓዶቼ እንዳላደርሳቸው ጠላት መስያቸው በጥይት እንዳይቀልቡኝ ሰጋሁ። ሽጉጤን መዝርጨ ተከተሉኝ ብዬ እየመራኋቸው በሩጫ ወደኋላ ተመለስኩ። እነሱም ነፍሳቸውን ለማትረፍ እየሮጡ ተከተሉኝ። ምርኮኛ ተጸጸቶ ዳግም እንዳይተናኩልህና እንዳያጠቃህ ሁሌም በኋላው ሆነህ ልትነዳው እንደሚገባ ይታወቃል። የጦርነትና የውጊያ ነገር ግን ሁሌም እንደምትማረውና በመጸሐፍ እንደሰፈረው ሆኖ አይቆይህም። ውጊያ ውስጥ ምርኮኛን መርተህ ፊት ፊቱ የምትሮጥበት የሚገርም አጋጣሚ እኔው ራሴን እንኳ አጋጥሞኛልና!

ሰገነይቲን ተወለድኩባት እንጂ አልቦረቅኩባትም አልፈነጨሁባትምም።
[ሰገነይቲን ከተነሳች አይቀር እግረመንገዳችንን ትንሽ ስለ ሰገነይቲና የታሪክ ፈርጦቿ በጥቂቱ ብናስተዋውቃችሁስ ምን ይላችኋል። እንደ https://en.wikipedia.org/wiki/Segeneiti አገላለጽ ደጃዝማች ባህታ ሓጎስ የትግራዩን ያጤ ዮሃንስ የእህት ልጅን የራስ አርአያ ልጅን ልጅ አምባየን በውጊያ መሃል በጦር ሆዱን የቦደሱትና እስከ ወዲያኛው የሸኙት ከጣልያንም ጋር ፊት ለፊት ሲፋለሙ ‘ሓላይ’ በተባለ ስፍራ የተሰው፣ ራስ ተሰማ አስበሮም (ኤርትራ ለኤርትራዉያን በሚል የፖለቲካ እምነታቸው የሚታወቁ)፣ ሙሴ ተስፋሚካኤል (ከአአዩ ወደ የኤርትራ ህዝብ ትግል የተቀላቀለና ለዲሞክራሲ ባለው አመለካከቱ የታወቀ)፣ አብርሃም ተወልደ (የነጻነት ሰልፍ ወይም ሰልፊ ናጽነት የመጀመሪያ መሪ)፣ ኢሳያስ ተወልደመድኅን (ወዲ ፍላንሳ)በራኺ ንጉሠ (ፈንቅል)ወልደንኪኤል ሃይለ (ወዲ ሃይለ)፣ ሃይለ ወልደንስኤ (ድሩዕ)፣ አየለ ትኩእ (ፊዳ) የተባሉ በኤርትራ ህዝብ ትግል የነጻነት ገድል ውስጥ ብርቅና ድንቅ ሚና ያበረከቱና ደማቅ ታሪክ የጻፉ ታጋዮችን ጠቅሳለች። በእንግሊዝ የሞግዚትነት ዘመን “ማኅበር ፍቕሪ ሃገር” ማለትም ‘ያገር ፍቅር ማህበርየመጀመሪያው ፕረዚደንት በመሆን፣ በዚያ ዘመን የኮንፌደሬሽንና ፌደሬሽን ምንነት በሚገባ በመተንተን ያስረዱት ፊተውራሪ ገብረመስቀል ወልዱ፡ በፌዴሬሽን ግዜም ከኢትዮጵያ ጋር አንድነት ይበጀናል ብለው በመሞገት ሳያሰልሱ የሰሩት ቢትወደድ አስፍሃ ወልደሚካኤል እንዲሁም ከዚያ ዘመን በፊት ጣልያንን በኤርትራ፣ በሱማሊያ በኢትዮጵያና በሱዳን ሆነው ከኢትዮጵያዉያን አርበኞች ጋር በጣምራነት በማርበድበድ ታሪካቸውን ለመጪው ትውልድ ጽፈው የሰነዱት ተስፋሚካኤል ትኩእና ቀደምት የኤርትራ ነጻነት ታጋዮችን የኋላኋላ ታጋይ አብርሃም ተወልደን የተካውን ታጋይ ኢሳይያስ አፈወርቂንም ጭምር በቃኘው እስቴሽን ከሲአኤ ጋር እንዳገናኘ የሚነገርለት፡አዲስ አበባ ውስጥ በድል ገበያ ገብርኤል ቤተክርስትያን አካባቢ በወያኔዎች ዘመን ባልታወቁ ኃይሎች የተገደለው፡ ተስፋሚካኤል ጆርጆ (ወዲ ጆርጆ) ወዘተ ከብዙ በጥቂቱ የሰገነይቲ አካባቢ የኤርትራችን ፍሬዎች መሆናቸው ይታወቃል።]

ይህ የሰገነይቲ አካባቢ ከሚታወቅባቸው የዳዕሮ (ዋርካ) ዛፎች አንዱ ነው። በአካባቢው የቱሪስት መስህብ የሆኑ እድሜ ጠገብ በርካታ የተንሰራፉ የዋርካ ዛፎች እንደሚገኙ ይታወቃል። ይህ ዋርካም በኤርትራው ገንዘብ ማለት በ5 ናቅፋ ላይ ሰፍሮም ይታያል።

ይህ ደግሞ ለኤርትራ ነጻነት እንደሻማ ለቀለጡትና ነጻነትን አሁን ላለው ትውልድ ህይወታችውን በመክፈል ያስረከቡ ሰማእታት ያረፉበት ለመታሰቢያነትም የተሰራላቸው የሰገነይቲ መካነ መቃብራቸው ነው። ኤርትራ ውስጥ ትልቁ የሰማእታት ሓውልት በዜጎች ልብ ውስጥ እንደሆነም ይታወቃል።

የእህታችንን ትረካ እንቀጥል በሉ!

ሰገነይቲን ተወለድኩባት እንጂ አልቦረቅኩባትም አልፈነጨሁባትምም። ጦርነት ውስጥ በውጊያ ነው ያደግኩት። ገና የ12 ዓመት ልጅ እያለሁ ነው የሸመገሉ አያቶቼን ለማገዝና ለመርዳት ከቤተሰቦቸ እንደተለየሁ ታጋዮች አግኝተው ትምህርት ሰጥተው ያነቁኝ። ከዚያ ግዜ ወዲህ እንደ ሴት ልጅ ሳልፈራ ተልእኮየን ተወጥቻለሁ፡ ተማሪ ሆኜም መጻሕፍትና ደብተር ይዤ ወደ ቤተ መጽሓፍት አልተመላለስኩም። የአካዳሚው ዓለም ዕዳ ስለቆየኝ ግን፡ ከእርግዝና ከወሊድ ጋር ጎን ለጎን እየታገልኩ በማታ ትምህርት 12ኛ ክፍል ደረስኩ። እኔ ራሴን ካወቅኩበት ግዜ ጀምሮ ያደኩት፡ ስለ ጦርነትና ውጊያ ወሬዎችን እየሰማሁና ጦርነትና ውጊያን እየተለማመድኩና ከዕለት ዕለት እየሰለጠንኩ ነው። ይህ ነው የምለው የምናፍቀው የቤተሰብ ፍቅር አልነበረኝም። ያደኩት፡ ገድል፣ ምሽግ፣ ውጊያና ተመሳሳይ ወታደራዊ ቋንቋዎችን እየሰማሁና እያጣጣምኩ ነው። በኦፕሬሽን ፈንቅል ምጽዋን ለማጥቃት በተነሳንበት ወቅት የሓይሊ (የመቶ) አዛዥ ሆኜ፡ ዕድሜየ 29 ነበር። ከማንኛውም እኔ ነኝ ካለ ታጋይ የማይተናነስ ድፍረት ወኔና ሞራልም ነበረኝ። ሰነፍ እንዳልባል እረፍት ልረፍ ሳልል፡ ለትርኪምርኪ የአኗኗር ዘይቤ ጀሮየን ሳልሰጥ፡ በሆነው ባልሆነው ምክንያት ከውጊያ ለመቅረት ሳላቅማማ፡ ይኸው ጦርነቱ ሁሉ ተገባደደ። በኦፕሬሽን ፈንቅልም እኔም እንደ ሌሎች ታጋዮች እጣየ ደርሶኝ፡ ቆስየ አባላቶቻችን ተሸክመው አወጡኝ። ከቅርብ እርቀት ነው አንዱ ተኩሶ እግሬን የጨራረፈኝ! ይህኛው ቁስሌ በጦር ሜዳ ላይ ዘጠነኛው ቁስሌ ነው፡ ዘጠኝ ግዜ ቆስያለው። ከዚያ በኋላም ሁለቴ ቆስያለው። ለነገሩ ቶሎ ቶሎ ስለማልቆስል ነው እንጂ ከውጊያ ውጭ ሌላ ምን ስራ ነበረንና ነው! አንዳንዶቹ ጓዶቻችን በየገባንበት ውጊያ የሚቆስሉ ነበሩ። እኔ ደህና ነኝ!

በጋራ ጥረት፡ የጾታ ሁኔታን ወደጎን ትተን በእኩል ተሳታፊነትን፡ ቀጭኗን መንገድ ማለትም ስጋለት ቀጣንን እየታዘዝንና እያዘዝን በዚህ መልኩ አለፍነው። የክፍለሰራዊታችን አባል የሆነው ዓንደብርሃን ፍስሃየ (ቀሺ) በጀልባ በባሕሩ በኩል፡ እኔም በቀጭኗ መንገድ በስጋለት ቀጣን፡ እኔ በእግር እሱ በባህር ወደ ጦርነቱ ገብተን፡ ለአንድ አላማ በመወሃሃድ በአንድ ላይ ተዋጋን። በኋላም ተዛምደን ባልና ሚስት ሆነናል። ዓወት የተባለ የበኹር ልጃችንን ወልደናል፡ ቀጥለንም አንድ ወንድ ከዚያም አንዲት ሴት ልጆችን ወልደናል። ሁለታችንም ከብስል ጥሬ እንዲሉ ከስንት መከራና እሳት የተረፍን “እንደወርቅ በእሳት” ተፈትነን የወጣን ነን። እነዚህ ከነጻነት በኋላ የወለድናቸውን ልጆቻችን ይዘንም ልክ እንደኛው “ከብስል ጥሬ” ሆነው “እንደወርቅ በእሳት” ከተፈተኑ ጓደኞቻችን ጋር ሆነን ዓመት ዓመት ምጽዋን እየነገድን እንገኛለን።

በስርሒት ፈንቅል ከተሳተፉትና መስዋእትነትና ጀብዱ ከተፈጸመባቸው ታንኮች አንዷ


ዘልዓለማዊ ክብሪን ዝኽሪን ንሰማእታት ኤርትራና!ሞጎስ ንህዝቢ ኤርትራ!
:mrgreen:


molover
Member
Posts: 2327
Joined: 26 Apr 2013, 05:16

Re: የሴት ታጋዮቻችንና የ‘ገልጠም - አሶሳ - ገልጠም - ምጽዋ’ ገድል በፊዮሪ መሓሪ፡ ገነት ስዩም (ሽጎም) እንደተረከችው

Post by molover » 07 Mar 2020, 12:57

Meleket wrote:
07 Mar 2020, 11:41
ክብር ለዓለማችን ሴቶች በሙሉ!!! :mrgreen:
Dinki Tsuhuf Kbur haw Meleket Ketsilo .

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: የሴት ታጋዮቻችንና የ‘ገልጠም - አሶሳ - ገልጠም - ምጽዋ’ ገድል በፊዮሪ መሓሪ፡ ገነት ስዩም (ሽጎም) እንደተረከችው

Post by Meleket » 21 May 2020, 08:42


ኣብ ኣሰር ፊዮሪን ሽጎምን!
ኣብ ኣሰር ጓል ሓጂን ጓል ቀሺን!
ኣብ ኣሰር ማርያን መሬምን!
ኣብ ኣሰር አቦታተንን ኣሕዋተንን!
ኣብ ኣሰር አዴታተንን ኣሓተንን!
ኣብ ኣሰር ሰማእታት ኤርትራ!
ዝተጠምራ!



Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: የሴት ታጋዮቻችንና የ‘ገልጠም - አሶሳ - ገልጠም - ምጽዋ’ ገድል በፊዮሪ መሓሪ፡ ገነት ስዩም (ሽጎም) እንደተረከችው

Post by Meleket » 07 Mar 2022, 10:52

Meleket wrote:
07 Mar 2022, 05:08
ዮሃና ኣዴታት ኤርትራ፡ መምህራን ኤርትራዊ ጭዉነትን ጅግንነትን! :mrgreen:

ዮሃና ኤርትራዉያት ኣሓትና፡ መምህራን ኤርትራዊ ጭዉነትን ተወፋዪነትን! :lol:

ዮሃና ኤርትራዉያን ደቅና፡ መምህራን ኤርትራዊ ግርህነትን ንጽህናን! :lol:

ዮሃና ደቀንስትዮ ዓለምና ንዓለምና ኣብ ማህጸንክንን እንግዳዓኽንን ዚጾርክን ዋዕሮታት! ንብለክን ብምኽንያት ኣህጉራዊ መዓልቲ ደቀንስትዮ መጋቢት 8! ኤርትራዉያን ደያኑ ማእከልን መስመርን፡ ሎሚዉን ከምትማል ንኩሉ ጠርባሽ ጸለመታት 'ቀናኣት ጃጀውቲ' ብዘይክማሕ ጽንዓትና እናፍሸልና።
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: የሴት ታጋዮቻችንና የ‘ገልጠም - አሶሳ - ገልጠም - ምጽዋ’ ገድል በፊዮሪ መሓሪ፡ ገነት ስዩም (ሽጎም) እንደተረከችው

Post by Meleket » 08 Feb 2023, 02:44

ኤርትራውያን የራሻን ታንኮች እንዲህ ማርከን ሃወልት ያደረግን፡ ማንኛውንም ወራሪና ተስፋፊ ኃይል በመቃወም በፍትሃዊው ትግላችን ድባቅ ዬመታን ኩሩ የኣፍሪካ ቀንድ ህዝብ ነን ብንል ማነው ጉራ ነው ዬሚለው? :mrgreen: ምን ይሄ ብቻ፡ ደርጉንም ያማክሩ ዬነበሩ የራሻ የጦር መኮንኖችንም ኣፍዓበት ላይ ማርከናቸዋል እኮ! :mrgreen:



ምጽዋ ላይ ልክ የዛሬዋ ዕለት በ1990 ነበር "ስርሒት ፈንቅል" የተባለው ምጽዋን ከኢትዮጵያ የደርጉ ሰራዊት ነጻ ዬማድረግ ኦፕሬሽን የጀመረው። እናማ በመስዋእትነት ዬተለዩንን የኤርትራ ጀግኖች በሙሉ ብንዘክር ታሪካቸውንም ብንገልጽ ያንሳቸዋል እንጂ ኣይበዛባቸውም። ይህንንም ስናደርግ "ለፊዚካል ዲማርኬሽንም" እየተጋን ኤርትራ መጪው ትውልዷ በሰላም የሚኖርበትን ዘመን ለማመቻቸት በመጣርም ነው። :mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: የሴት ታጋዮቻችንና የ‘ገልጠም - አሶሳ - ገልጠም - ምጽዋ’ ገድል በፊዮሪ መሓሪ፡ ገነት ስዩም (ሽጎም) እንደተረከችው

Post by Meleket » 09 Feb 2023, 11:03

"ውጥን ናይ ክሬምሊን ጌርካዮ ኪነሚን :mrgreen: ፡ . . . ተጋዳላይ ዝብሉኻስ እንታይ ኢዩ ፍጥረትካ " በለ ጅግና ወዲ ትኹል :mrgreen:


Post Reply