Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Assegid S.
Member
Posts: 936
Joined: 11 Aug 2013, 07:11
Contact:

ብቻውን የተሻገረው "አሻጋሪ"

Post by Assegid S. » 28 Dec 2019, 19:03

https://www.eaglewingss.com/



ብቻውን የተሻገረው "አሻጋሪ"

የዘመን መሽጋገሪያ ሳምንት ነውና፥ ስለ ዘመንም ባይሆን ስለ ሽግግራችንና አሻጋሪያችን  ትንሽ እናውጋ።

በኣንድ ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ "የሽግግር መንግስት ያቋቁሙልን " ተብለው ሲጠየቁ፥ የሚቆምም የሚቀመጥም መንግስት የለም፤ እሱን እርሱትና ተቀናጁ "እኔ አሻግራቹሀለሁ " ሲሉ መልሰው እንደነበር አስታውሳለሁ። አሻጋሪው አሁን ጠቅላላውን ህዝብ አውዳሚ የሞት አውድማ ላይ ትተውት፥ ብቻቸውን ወደ ብልፅግናው ምድር … ከንአን … ተሻግረዋል።

ስልጣን - ዙፋኑ ላይ የተቀመጡት እርሳቸውና እርሳቸው ብቻ ሆነው ሳለ፣ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠብቅ ኃላፊነት ያለበት የደህንነቱም ሆነ የመከላከያው ግብረ-ሀይል የሚታዘዘው በእርሳቸውና ለእርሳቸው ብቻ ሆኖ እያለ፥ ዛሬም ነገም፦ ሰው ባለቀና ንብረት በወደመ ማግስት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ እያሉ "ሰላምህን አስከብር - ደህንነትህን ጠብቅ " ብለው ደብዛቸውን ያጠፋሉ። በቀን ኣንዴ እንኳ በልቶ ለማደር የሚቸገር ቤተሰብ ያለው ምስኪን ገበሬ፥ ኣንድ የጦር ብርጌድ የሚያሰተዳድር ይመስላቸዋል ልበል? በእርሳቸው ቅጥ ያለፈ ገፅታን የመገንባት ልክፍት፥ በትንግርትም ይሁን በታሪክ አጋጣሚ በእጃቸው ስር የወደቀው ህዝብ ሲዋከብ፣ ሲፈናቀል፣ ሲገደል፣ መሽሻ መድረሻ ሲያጣ ይኸው ሁለት ዓመት ሊደፍን ነው። በፌሮ ብረት ብቻ ሳይሆን በፌደራል ጦር ጭምር ችብችብ ብሎ በታጠረ ቤተ-መንግስት ውስጥ እየኖሩ፥ ህዝቡን ለሚያረግፈው  ፅንፈኛ-ወለድ ተስቦ ዛሬም ድረስ መልሳቸው "ራስህን ተከላከል " ነው፤ በሰፈሬ ልጆች ቋንቋ ደግሞ "ስራህ ያውጣህ !”

እርግጥ ነው ጠቅላይ ሚንስትሩና በዙሪያቸው ያሉ ሁሉ በሰላምም በንብረትም በልፅገዋል። በወታደር አጀብ ወጥተው - በወታደር አጀብ ይገባሉ፤ የመኖር ዋስትናቸው ስጋት ላይ አልወደቀም። እንጀራ ጠግበው ይተኛሉ - እንቅልፍ ጠግበው ይነቃሉ። ልጆቻቸው ሊያለቅሱ ቀርቶ በሌላው ልጅ ለቅሶ በማይረበሹበት ስፍራ፥ በብዙ ሺህ ማይልስ ርቀት በቅንጦት ያድጋሉ - ይማራሉ። ያም ቢሆን ግን፦ ሰው እንዴት የሌላውን ህመም ለመታመም ባይወድ እንኳ ለማስታመም እንዲህ ይደነድናል? ራስን በመውደድ ጩኽት ይደነቁራል?

አሁን አሁንማ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለህዝቡ የሚያደርሱት የትኛውም የፅሑፍም ሆነ የድምፅ ዲስኩር፥ ከቀይባህር ማዶ በርቀት የሚሰማ "ብትሻገር እንደ እኔ ተሻግረህ ና ባትሻገር ገደል ግባ !” የሚል ለዛ ያለው የአሻጋሪ ቁጣ እየመሰለኝ መጥቷል።

ለእርሳቸውና ለቢሮክራሲያቸው የIMF'ም ሆነ የWorld Bank ካዝና የእናት ጡት ነው … ያለ አንዳች ሐሳብ የሚጠባ። ስንቱ ዜጋ ከስራ ከኑሮው ተፈናቅሎ - የእናት ሞት - ሆኖበት እንደሚያነባ ግን በቅርብ የምናየው ሀቅ ይሆናል። በእርግጥ ለእርሳቸው ስጋት የሚሆነው የኢኮኖሚው አለመረጋጋት የሚለኩሰው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሰደድ ለስልጣን መንበራቸው የሚያቀብለው ትኩሳት እንጂ፥ በተቋማቱ አስገዳጅ ቅድመ-ሁኔታዎች የሚለበለበው ደሃ ህይወት አይደለም። ጠቅላይ ሚንስትሩ፦ ከሰው የጀርባ ቁስል ይልቅ ለክንዳቸው tattoo አብልጠው የሚጨነቁ እጅግ ሲባዛ ራስ ወዳድ ናቸው። ይኽን እንድል የሚያስገድደኝ ብዙ ትዝብት ቢኖረኝም፥ በጣም የቅርቡን እንኳ ባነሳ - የዓለም የሰላም ኖብል ተሸላሚ በሆኑ ማግስት የሸጡዋቸው ኢትዮጵያውያን እህትና ወንድሞቼ በቂ ማሰረጃዎቼ ናቸው። አስቆርቱ ይሁዳ አምላኩን በሰላሳ ዲናር እንደሸጠ፥ "ኢትዮጵያዊው ሙሴም " አስራ-ዘጠኝ እህትና ወንድሞቹን በሰላሳ ሚልዩን ብር ቸብችቦ፣ በሆቴሉ ዙሪያ ችቦ አስለኩሷሶ ወደ ሀገሩ በሯል። በሰላሳ ዲናርና በሰላሳ ሚልዩን ብር መካከል ለሚታየው ሰፊ ልዩነት መነሾ ምክንያት ደግሞ የዋጋ ግሽበት (inflation) እንዳይመስላችሁ … የሞራል ንቅዘት ነው

ሚንስትሩ ከኦስሎ ከተማ መልስ አዲስ አበባ ከገቡ ከኣንድ ሰዓት ቦኃላ … በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰዋራ ስፍራ፣ ከተጓዥ መንገደኞችና የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች እይታ ውጪ ብቻዋን ተነጥላ እንድታርፍ ስለተደረገችው አውሮፕላን ሚስጢር በቅርቡ በዝርዝር የምናነበው ነውር ይሆናል። ዛሬ ላይ ግን … ከSpanish ቋንቋ ውጪ ጆሮአቸውን ቢቆርጡዋቸው እንኳ ሌላ አፍ በማይናገሩት የበረራ ሰራተኞች አስተናጋጅነት፥ 60 ኖርዌጅያን ፖሊሶች እንዴትና ለምን ጠቅላይ ሚንስትሩን እግር-በ-እግር  ባያስብልም ክንፍ-በ-ክንፍ  ተከትለው ወደ ሀገር እንደገቡ ቢጠየቁ፥ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተንደርድረው … በለመዱት ሹክሹክታ … "የቻርተር አውሮፕላኗ ተልኮ የአሜሪካን የጦር ጀቶች ለAir-Force-One ከሚሰጡት መደበኛ የጥበቃ ሽፋን የተለየ አልነበረም በል " እንደሚሉዋቸው አልጠራጠርም። የተጋጠ አጥንት በመጋጥ የማይዘል መንጋጋ መቼም ውሽት በማውራት አይደክምም።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር - ዲሴምበር 10 / 2019 - "በዓለም መድረክ ላይ ኢትዮጵያን በክብር አስጠሩ " ተብለው የተሞካሹት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፥ 48 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፥ በነጮቹ ምድር ኢትዮጵያዊ ወንድምና እህቶቻቸውን በጥቁር ገበያ ሸጠው ዶላር ይዘው ሲመለሱም፥ የምድር ጦር ሙዚቀኛ "ጉሮ ወሽባዪ ወሽባ … ጀግናው ድል አድርጎ ሲገባ " ብሎ ሞዝቆላቸዋል። ወገኑን የሸጠ ራስ ወዳድ - ለወገኑ እንደቆሰለ ፋኖ ተቆጥሮ "ድል አድርጐ " ተባለልኛ። "ድንቄም!” አሉ ወይዘሮ ብርቄ … ገድገድ ቢያደርጋቸው አንድ ጠርሙስ አረቄ። ምነው ይህንን ጉድ እሳቸው ሰምተውልኝ ቢሆን፦ "ድንቄም ሙሴ! ቆይ ግን እንዳልሳሳት… ሙሴ ነው ያልችሁት ወይስ ሞሲሳ ?" ብለው ይጠይቁ ነበር።

ከሰላም ኖብል ሽልማታቸው ወዲህ … ጠቅላይ ሚንስትሩ እማማ ብርቄን እንዳስታውስ ሲያደርጉኝ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ባለፈው እኔ ስልጣን በሰላም ማስረከብ ስለማስብ "ደም መቃባት " አልፈልግም ሲሉ ብሰማቸው፥ ከአፌ ሳይሆን ከአንጀቴ ነው ፈገግ ያደረጉኝ።

ለአይን ያዝ ሲያደርግ፥ እንደ ወጉ ከፀጉራቸው ላይ ጣል ያደርጉት ሻርፕ፥ ዘርዘር ብሎ በተማገረ የእንጨት አጥር ላይ የተሰጣ ምንጣፍ መስሎ ከቤት ይወጣሉ … ወይዘሮ ብርቄ። አጠር ቀጠን ቢሉም፥ ኣንድ inch እንኳን ሳይዛነፉ ቀጥ ብለው ሲራመዱ የቄሮን ዱላ ያስንቃሉ። ግራ ቀኝ መንደርተኛውን ሰላምታ እየሰጡ ወጣ ያሉት እማማ ብርቄ፥ ብዙም ሳይቆዩ … በቁንዶ አረቄ አጥንታቸው እስከ መቅኔው በስብሶ ሐረግ ይሆንና፣ በእያንድኣንዷ ሰከንድ የተለያየ የአካል ቅርፅ እየሰጣቸው፣ ንፋስ በሌለብት - ቀጥ ባለ አየር እንደ ባንዲራ እየተውለበለቡ ከመንደር ይገባሉ። ይኼኔ ታዲያ ደጋፊም ተመልካቹም ሰፈርተኛ "አይይ ወይዘሮ ብርቄ ዛሬም ጠጡ ?” ሲላቸው … ሁሌም መልሳቸው "አበስክ ገበርኩ ለዚህ ሰፈር ሰው ድንቁርና ! በመቀባትና በመጠጣት መካከል ያለው ልዩነት እንኳ የማይገባው። ደርቆ የዋለ አፌን በኣንዲት ጠርሙስ አረቄ አበስ አበስ አድርጌው ብመጣ … 'ብርቄ ጠጣች ' ይላል ወሬ ፉቱ ሁላ !" ይላሉ። እማማ ብርቄ ሲጠጡ አንጀታቸው ብቻ ሳይሆን አጥንት ጥፍራቸው ጭምር [deleted] ብሎ ርሶ አሹቅ እስኪሆን ድረስ ነው። ቆሞ የዋለው ፀጉራቸው እንኳን ሳይቀር፥ ዞማ ሆኖ ለጥ ብሎ ተኝቶ ነው የሚመለሱት። በተቃራኒው ደግሞ፦ ጠጥተው ሲመጡ … ይቅርታ እንደ እርሳቸው ትርጓሜ አበስ አበስ አድርገው ተቀብተውት ሲመለሱ … ደብተራ እንደደገመበት መጫኛ ቀጥ ብሎ ደርቆ አልታጠፍ - አልዘረጋ የሚለው ምላሳቸው ብቻ ነው። እዚህ ጋር ሳይንሱን ልርሳውና … ለዛም ይመስለኛል ሲያወሩ የሚኮላተፉት።

የነገሬ ጭብጥ ያልገባው አንባቢ አሁንም በድጋሚ … "ታዲያ ጠቅላይ ሚንስትሩና ወይዘሮ ብርቄን ምን ያመሳስላቸዋል ?” ብሎ ሊጠይቅ ይችላል። ወይዘሮዋ መጠጥ ጠጣሁ - ሚንስትሩም ደም ተቃባሁ ለማለት የሚያስቀምጡት መስፈርት … ይሆናል መልሴ። ጠቅላይ ሚንስትሩ "ደም ማፍሰስ / መቃባት አልፈልግም " ሲሉ፥ ከዚህ በላይ ምን ቢያስቡልን እንደሆነ ስገምት ዘገነነኝ። እንደው የሰኔውን ሰቀቀን ብቻ እንኳ ብናወሳ … በmilitary fatigues ሽክ ብለው፣ በቴሌቭዢን መስኮት ተኮፍሰው ሲፎክሩ እኮ፦ ለልጅ አባት፣ ለሚስት ባል የነበረን ክቡር የሰው ልጅ ደም አፍስሰው እንጂ የጂማን ቡና አተላ ደፍተው አልነበረም። የሚስትና ልጅን ዋሻ አፍርሶ፣ የወንድምና እህትን ጋሻ ነጥቆ፣ ደም ጠጥቶ "ደም መቃባት አልፈልግም " ማለት በሟች ላይ ብቻ ሳይሆን በቋሚውም መዘበት ይሆናል።

ዛሬ የኣዲስ አበባን የእስር ቤት ጉድጓድ የሞላው እኮ የበሻሻ ቆሻሻና ጉድፍ አይደለም። ጠቅላይ ሚንስትሩ፦ እነ አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ ሌሎች በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ንፁሀን በሐሰት ክስ የሚያፈሱት እንባ በቀለም እንጂ ልዩነቱ፥ በክብደት ከደም እንደማይተናነስ መረዳት እንዴት ተሳናቸው?  እንባ እንደ ደም ባይቀላም፥ የሁለቱም ሚዛን መለኪያው ያው 'ሊትር ' ነው። የቀዱትን ያህል ቀን ቆጥሮ ማፍሰስ ግድ ይሆናል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ "የኣፍሪካ መሪዎች ችግር ስልጣን ሲይዙ ደም መቃባታቸው ነው " ይበሉ እንጂ፤ እንደ እኔ - እንደ እኔ ችግራቸው ትላንትናን መርሳታቸው፤ ኣዲስ ቀን እንጂ ኣዲስ ፀሐይ እንደማትወጣ፣ አዲስ ምሽት እንጂ ኣዲስ ጨረቃ ዞራ እንደማትመጣ መዘንጋታቸው ነው። በቀትርም ይሁን በውድቅት ትናንት የሰሩትን ወንጀል የዛሬዋ ፀሐይ የምታውቅ፣ የዛሬዋ ጨረቃ የምታስታውስ አይመስላቸውም። ዕለት ዕለት ንፁህ ነኝ ብለው ስለሚያስቡ፦ የትላንት ክፋታቸው ዛሬ ላይ፥ የዛሬው ደግሞ በነገው ላይ እየተደመረ … ግፋቸው በዝቶ በደም ባህር እየዋኙም ቢሆን እንኳ በጠብታውም የረጠቡ መስሎ አይሰማቸውም።

እርግጥ ነው ተማክረው ምን ያሉት አይሸትም ይባላል። ተማክረው ያፈሰሱት ደም ግን ተሸሽጐ አይከርምም። ሀጢያትና ሴራ በእህልና በመጠጥ ቁርባን የሚሰረይበት የብሉይ ዘመን አልፎአል። አይኖቹ ምድርን ሁሉ ለሚያዩ፣ ጆሮቹ ምስጢርን ሁሉ ለሚያዳመጡ፣ መድሎ ለማያውቅ ለሰማዩ ፈራጅ … በኣዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል የቀረበው የብልፅግና ፓርቲ "የስድስት ወር መታሰቢያ ገበታ" ወንድሙን እንደገደለው - እንደ ቃየል መስዋዕት ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ " I am the KEEPER of my brother" ብለው አዳራሽ ሙሉ ህዝብ ቢያስጨበጭቡም፤ የወንድማቸው KILLER እንደሆኑ በጊዜውና በቦታው አንዱ ብቻ የሚፈርደው ሐቅ ይሆናል። በወገኖቻቸው እንባ የነገዱ፣ የወንድማቸው SELLER መሆናቸውን ግን እኔና 19 ሰዎች ዛሬም እናውቃለን።

አንድ የምድር ትዝብቴን ላካፍላችሁና የዛሬው ጽሑፌን ላጠቃል። አምላክን የማያውቅ ሰው ሲከፋ ክፉ ነው፤ አምላኩን የረሳ ሰው ሲከፋ ግን በጣም በጣም እጅግ በጣም ክፉ ነው። እንደ እነዚህ አይነት ሰዎች፣ መጽሓፉ "የአምልኮ መልክ ያላቸው ሀይሉን ግን የካዱ " የሚላቸው የጥቅም ተኩላዎች በበግ ተመስለው ሲመጡ፥ ለምዱን ብቻ አይደለም የሚለብሱት፥ ምቹ አጋጣሚ አግኝተው፦ አንገት በስተው ደም እስኪመጡ ድረስ … አጎንብሰው ከበግ በላይ ሳር ይግጣሉ። ውስጣቸው ክፋት እንጂ ወተት ባያግትም … እምነትን ለማትረፍ ግልገልንም እስከማጥባት ገፍተው ይሔዳሉ። ውዮ ለአንተ ይኼ እውነት ላልገባህ አማኝና ታማኝ!
Last edited by Assegid S. on 02 Jan 2020, 11:04, edited 1 time in total.

Assegid S.
Member
Posts: 936
Joined: 11 Aug 2013, 07:11
Contact:

Re: ብቻውን የተሻገረው "አሻጋሪ"

Post by Assegid S. » 30 Dec 2019, 09:43

I just wanted to apologize for the inaccessibility of eaglewingss.com. The file transfer protocol check revealed no change to the domain's access ip; yet, for a reason, eaglewingss is down since yesterday. As you can see it here; the 'feature image' on this article is broken and the article is not currently available at eaglewingss. The only response I got from the 'server provider' is to 'wait'; and the only thing I could say for the readers is SORRY. But I got some to those who might be behind this unless the problem is out of blue :-) . Here is some of our founding mottoes at EaglewingsSociety:

[*]To edify your body as a temple: BE YOUR OWN APOSTLE and SAY what the heart urges, DO what the mind commands, VALUE brain over melanin.
[*]We don't FIT to survive, we FIGHT to revive.

Post Reply