==============================
በኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ብዙነሽ መሰረት የሚመራና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ቲያትር፣ ከታዋቂ ድምጻዊያንና የጃኖ ባንድ የተካተቱበት ከ60 በላይ አባላትን የያዘ የኢትዮጵያ የባህል ቡድን ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የሙዚቃ ዝግጅት ለማቅረብ ከሰኞ ታህሳስ 6 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ ወደ ኤርትራ ይጓዛል።
የባህል ቡድኑ የኤርትራ ጉዞ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የተፈጠረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው።
የባህል ቡድኑ በኤርትራ ቆይታው በአስመራ፣ ከረን እና ምጽዋ ከተማዎች የተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶችን እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።
የኤርትራ የባህል ቡድን ባለፈው የካቲት ወር 2011 ዓም በአገራችን በመገኘት ተመሳሳይ ዝግጅቱን በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በባህርዳር እና በሀዋሳ ከተማዎች ማቅረቡ ይታወሳል።