Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
simbe11
Member
Posts: 2087
Joined: 23 Feb 2013, 13:02
Location: Addis Ababa

ምሳ እቃዬን ያያችሁ፡፡ (ወቀሳ ሳይሆን ለትዝታ ያህል ብቻ ነው)፡፡

Post by simbe11 » 29 Jul 2019, 19:17

አዲሳባ ትምህርት ቤት ቁጥር አንድ በቀድሞ አጠራር ከፍተኛ 8 ቀበሌ 15 በተለምዶ እንቁላል ፋብሪካ ከሚባለው ሰፈር ትንሽ እልፍ እንዳሉ እስላም መቃብር ፊት ለፊት ይገኛል፡፡
እዚህ ትምህርት ቤት በምንማርበት ወቅት ብዙ ትዝታ አሳልፈናል፡፡ ከብዙ ትዝታዎቼ መሃል ምሳ እቃዬን ያያችሁ ያስብሉ የነበሩ ወንድማማቾች መቼም አይረሰኙም፡፡ መቼም ስም መጥራት ደግ አይደለምና ለዛሬ ታላቅ እና ታናሽ ብለን እንጥራቸው፡፡ የምታውቁ ግን ስለ ማን እንደማወራ ታውቃላችሁና በትዝታ ፈገግ በሉ፡፡
አዲሳባ ትምህርት ቤት ሲገቡ በሩን እንዳለፉ የሚቀበሎት ከጠጠር ጋ የተቀላቀለው የጊቢው አዋራ ነው፡፡ በዋናው ህንፃ በስተቀኝ እና አጥሩን ታከው ከእጨት በተሰሩት የመማሪያ ክፍሎች መሃል አልፈው ከዋናው ህንፃ ጀርባ ወዳለችው አንስተኛ ክፍት ቦታ ያልፉና በጣውላ እንጨት ድርድር ብለው ወደተሰሩት ሌሎች የመማሪያ ክፍሎች ይደርሳሉ፡፡ በነዚህ ክፍሎችና ወደቀኛችሁ ትታችኋቸው በመጣችሁት ክፍሎች መሃል ላይ ባለች አነስተኛ ክፍተት መሃል ከቆርቆሮ የተሰራች አነስተኛ ክፍል አለች፡፡ ይህች ክፍል የመማሪያ ክፍል አይደለችም፤ የጥበቃ ወይም ደግሞ የመምህራን ቢሮም አይደለችም፡፡ የምሳ እቃ ክፍል እንጂ፡፡ ምሳ ተቋጥሮለት የሚመጣ ተማሪ ሁሉ የያዘውን የምሳ እቃ ጠዋት እንደመጣ (ሙሉ እንደሆነች) ደግሞም ከምሳ ኋላ ባዶዋን እዚች ክፍል ማስቀመጥ ግዴታው ነው፡፡ ወደቢት ሲሄድ የምሳ እቃውን ከዚህቹ ክፍል ይዞ ይሄዳል፡፡
ከተማሪው ባብዛኛው ምሳ ይዞ የሚመጣ ነው፡፡ አንዳንዶች ሰፈራቸው ቅርብ ከሆኑት ውጪ ሁሉም ይዞ ይመጣል ማለት ይቻላል፡፡ ስለሆነም እቺ የቆርቆሮ ክፍል በምግብና በምግብ ሽት የተሞላች ነበረች፡፡
በምሳ ሰአት አንድ የተለመደ ነገር አለ፡፡ ከተማሪው ውስጥ አንዱ ወይ ሁለቱ ሶስቱ ማልቀሳቸው አይቀርም፡፡ ምክንያቱ ደሞ ከቤት ይዘው የመጡት ምሳ የት እንደገባ አይታውቅምና ነው፡፡
“ቲቸር ምሳዬን በሉብኝ” ብሎ እዬዬ ነው፡፡
“ማነው የበላብህ?”
ተማሪው ይመልሳል “እኔ እንጃ ቲቸር” ለቅሶ ይቀጥላል፡፡
ነገር ግን ጠያቂውም ሆነ ተጠያቂው የምሳ እቃ ቀበኛውን ይውቁታል፡፡ ስም አይጠሩም እንጂ፡፡
“በቃ አታልቅስ” ብሎ ከክበብ ዳቦ ይገዛል አስተማሪው፡፡
ታናሽና ታላቁን ሁላችንም እናውቃቸዋለን፡፡ እነሱን ለማወቅ ያንድ ክፍል ተማሪ መሆን አይጠይቅም፡፡ እነሱ እዛ ጊቢ እስካሉ ድረስ ሁሉም ተማሪ ያውቃቸዋል፡፡ ምክንያቱም በህይወቱ ቢያንስ አንዴ አስለቅሰዉታልና፡፡
ታናሽና ታላቅ ወደ ምሳእቃ ክፍል ሲገቡም ሆነ ሲወጡ ያያቸው ሰው ስለመኖሩ አልሰማሁም፡፡ በትምህርት ሰአት ከክፍላቸው ተሰውረው እንደሚወጡም አልሰማሁም፡፡ በእረፍት ሰአትም እንደማንኛውም ተማሪ ጊቢው ውስጥ እናያቸዋለውን፡፡ ታዲያ በምን ሰአት ነው ምሳ እቃችንን የሚያራግፉት? እንጃ!!
ከሁሉም በላይ ግርም የሚለው ደግሞ የምሳ እቃ ክፍላችን በር ቁልፍ ያለው መሆኑ ነው። ቁልፉ ሳይሰበር ፤ በሩ ሳይገነጠል እንዴት አድርገው እንደሚገቡ እግዜር ይወቀው።
ስንቱን አስለቅሰው እነሱ ምሳ ሳይዙ ግን ጠግበው ይውሉ ነበር። ከሁሉ ከሁሉ ደሞ ግርም የሚለኝ በታላቅና ታናሽ ማንም ሰው ቂም አይዝም ምሳውን በልተው ያስለቀሱት እንኳን ሳይቀር።
ታናሽና ታላቅ ድንገት ይህን ፅህፍ ካያቺሁ ወቀሳ አይደለም የልጅነት ትዝታ እንጂ።