Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum

Revelations
Senior Member+
Posts: 33975
Joined: 06 Jan 2007, 15:44

Re: [Wazema Radio] አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በገፍ እየሰጠ ያለው ብድር እያወዛገበ ነው

Post by Revelations » 29 Jul 2019, 13:23

አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በገፍ እየሰጠ ያለው ብድር እያወዛገበ ነው
ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ከ200 ሚሊየን ብር የበለጠ ብድር ሰጥቷል።


ዋዜማ ራዲዮ- በአብዛኛው በአዲስ አበባ አስተዳደር እንደሚተዳደር የሚነገርለት የአዲስ ብድርና ቁጠባ ከቅርብ ወራት ወዲህ እየሰጠ ያለው በዘመቻ መልክ እየተካሄደ ያለ ብድር በፋይናንስ ተቋሙና በከተማው አስተዳደር ውስጥ መደናገርና ጥርጣሬ አስከትሏል። ከዚህ ቀደም ይህ አክስዮን ማህበር ብድርን ሲሰጥ ተያዥን ጨምሮ የሚጠይቃቸው የተለያዩ ያሉ መስፈቶች ነበሩ። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ተያዥ አያስፈልግም” በሚያስብል ደረጃ ብድር እየሰጠ እንዳለ እየታየ ነው።ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ከ200 ሚሊየን ብር የበለጠ ብድር ሰጥቷል።

ቀለል ያለ ብድር ለስራ ፈጠራ መልካም መሆኑ ይነሳል።ነገር ግን ብድር ሲሰጥ ብድር የሚሰራበት ፕሮጀክት አዋጭ ነው ወይ? ፕሮጀክቱ ተሳክቶ ብድሩ ይመለሳል ወይ? የሚሉ ግምገማዎች ይደረጋሉ።

አሁን በአዲስ ብድርና ቁጠባ እየተሰጡ ያሉ ብድሮች እነዚህ መስፈርቶች ከቁብ ሳይገቡ ሶስት-ሶስት ሁነው የተደራጁ ወጣቶች አንዱ ለአንዱ ተያዥ እየሆኑ ከ300 ሺህ እስከ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር እየሰጠ እንደሆነም ሰምተናል። ይህን ብድር በአዲስ አበባ ባሉ ወረዳዎችና በአዲስ አበባ ዙርያ ባሉ ከተሞች እየሰጠ መሆኑን ራሱ ተቋሙ በመገናኛ ብዙሀን በማስታወቂያ እያስነገረ ይገኛል። ለብድርም ሲባል የፕሮጀክት እቅድ ሽያጭ የተለመደ ስራ እየሆነ መጥቷል።

ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው ደግሞ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የአዲስ ብድርና ቁጠባ ሀላፊ አቶ አሸብር ብርሀኑን ማገዳቸውን ገልጿል። ሀላፊው የብድር አሰጣጡ ላይ ተቃውሞ እንደነበራቸውም የሰራ ባልደረቦቻቸው ለዋዜማ አረጋግጠዋል።

ከወትሮ በተለየ መልኩ የከተማ አስተዳደሩ በአዲስ ብድርና ቁጠባ በኩል እንዲህ ብድር ማሰራጨት ለምን ፈለገ ? በሚል ለአንድ የአክስዮን ማህበሩ የዘርፍ ሀላፊ ላነሳነው ጥያቄ ፣ ብድሩ እየተሰጠ ያለው የከተማ አስተዳደሩ በመደበው ገንዘብና ብድሩንም ቀለል ባለ ሁኔታ እንድንሰጥ ታዘን ነው የሚል ምላሽ አግኝተናል። በዚህም ሳብያ ባንኮች በተለይም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአዲስ አበባ ቅንጫፎች ከየወረዳው የአዲስ ብድርና ቁጠባ አክስዮን ማህበር ጽህፈት ቤቶች የባንክ ሂሳብ እንዲከፈትላቸው ደብዳቤ በተጻፈላቸው ወጣቶች የአገልግሎት ጥያቄ መጨናነቃቸውን ከባንኩ ምንጮቻችን ሰምተናል።

ይህ ክስተት የከተማው አስተዳደር ፖለቲካዊ ቅቡልነት ለማግኘት የዘየደው ስትራቴጂ መሆኑን ተደጋጋሚ አስተያየቶች ይሰማሉ።ታከለ ኡማ ምክትል ከንቲባ ሆነው ከተማውን ማስተዳደር ከጀመሩ ጊዜ ጀምሮ ወደ ስልጣን የመጡበት መንገድ ለሳቸው ሲባል ህግ ተስተካክሎ በመሆኑ ውግዘት የገጠማቸው ቢሆንም ቀላል የማይባል ነዋሪ ደግሞ ጊዜ ሰጥተን በስራቸው እንመዝናቸው በሚል ይሁንታን ቸሯቸዋል። የወሰዷቸው መልካም እርምጃዎች እንዳሉ ሁሉ በየተቋማቱ ባሉ የአመራር ቦታዎች ላይ ማንነት ተኮር የሆነ ምደባ ተደርጓል ተብሎ በመታመኑ ግን ከባድ ትችት ውስጥ ወድቀዋል።

አሁን እየታየ ያለው የብድር አስጣጥ በ1997 ምርጫ የደነገጠው የቀድሞው የኢህአዴግ አስተዳደር እስከ 2002 አ.ም ምርጫ ድረስ ከሶስት ሺህ ጀምሮ የተለያየ መጠን ያለው ብር እንደማይመለስ እየታወቀ በገፍ በከተማው ሲረጭ መቆየቱ ይታወሳል። በ100 ሺዎች የወሰዱት ብድር አልተመለሰም። በከተማውም በዚህ መልኩ በቂ ስራ መፍጠር አልተቻለም።አሁን እየታየ ያለው የብድር መስፈርት ልልነትም ከከዚህ ቀደሙ ጋር ተመሳሳይነት አለው። ለስራ ፈጠራ ብድር መቅረቡ የሚደገፍ ቢሆንም ገንዘቡ ስራ መፍጠሩ እና መመለሱ መረጋገጡ እጅጉን ተገቢ ነው።

የከተማ አስተዳደሩ በሁለት ቢሊየን ብር ተንቀሳቃሽ ገንዘብ በነዳጅ ማደያ እና በፈጣን ምግቦች ሽያጭ ዘርፍ ለአስር ሺዎች ስራ እፈጥራለሁ ብሎ በከተማው ምክትል ከንቲባ ታከለ በኩል በቅርብ ጊዜ ይፋ ያደረገውን እቅድ የት አድርሶት ነው? ዛሬ እንዲህ መጣደፍ ውስጥ የገባው የሚል ጥያቄን ማስነሳቱ ነው። በሁለት ቢሊየን ብር የወጣው እቅድም አተገባበሩ መልካም ከሆነ በመልካም ተወስዶ ነበር።

እንደ አዲስ ብድርና ቁጠባ አይነት ተቋማት ገንዘብ የሚያገኙት ከአለም አቀፍ ለጋሾችና ውጭ የኢትዮጵያ ንግድ በትንሽ ወለድ የሚሰጣቸውን ብድር ነው መልሰው የሚያበድሩት። አዲስ ብድርና ቁጠባ ለስሙ ከአስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ተመደበ እንጂ ካፒታሉ ከአራት ቢሊየን በልጦ በአመትም ከስምንት ቢሊየን ብር በላይ አበድራለሁ ብሎ የሚያቅድ በኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ ከተቋቋሙ የግል ባንኮች በሀብት የሚስተካከል ነው።[ዋዜማ ራዲዮ]

http://wazemaradio.com/%e1%8a%a0%e1%8b% ... %e1%8b%ab/

Post Reply