Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Thomas H
Member
Posts: 4981
Joined: 27 Jan 2007, 16:30
Location: Kaliti
Contact:

የህወሓት ኣስቸኳይ ስብሰባ የኣቋም መግለጫ ፦ ደመቀ መኮንን ልክስክስም ልፍስፍስም ነው

Post by Thomas H » 11 Jul 2019, 15:37

በፌዴራል ከፍተኛ የወታደራዊ መኮንኖች እና በኣማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የተቀነባበረ ግድያን ምክንያት ተከትሎ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ሃምሌ 2/2011 ዓ/ም ኣስቸኳይ የ 1 ቀን ስብሰባ ተቀምጧል ። ስብሰባው ባሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ተከስቶ ያለውን ሁለንተናዊ ቀውስ እና ሊከተል እሚችለው ሃገራዊ ኪሳራና ውድቀት ላይ በይበልጥ ኣተኩሮ ጥልቅ ውይይት ኣድርጓል ። ህወሓት ባስቸኳይ ስብሰባው ላይ ባሁኑ ወቅት ሃገሪቱ ከመጥፎ ወደከፋ ኣደጋ እየተዘፈቀች መሆኗን ገምግሞ ኣምኗል ።

በኣስቸኳይ ስብሰባው በተለይም ደግሞ ሃገራችን ኢትዮጵያ ካለፈው 1 ዓመት ወዲህ በታሪኳ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከፖለቲካዊ ቀውስ ወደ ሃገራዊ ቀውስ ተሸጋግራ በሃገሪቱ ከፍተኛ ኣመራሮች ደህንነት ላይ ያነጣጠረ የግድያ ዘመቻ መጀመሩንና ይህንንም የኢፌድሪ ኢታማጆር ሹም ጀነራሉን እና የኣማራ ክልል ፕሬዚደንቱን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ኣመራሮችን በመግደል ተጀምሯል ።

ህወሓት በኣስቸኳይ ስብሰባው ትናንት ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን በሽብር ለመበታተን ፥ ሃገሪቱንም ለባዕድ ኣሳልፈው ለመስጠት በውጭና በውስጥ ሆነው ሲሸርቡ የነበሩ ከሓዲዎች በተፈጠረላቸው የኣመራር ክፍተት ተጠቅመው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የስልጣን መዋቅርን ስለተቆጣጠሩ እና በተለይም ደግሞ ከያሉበት ተጠራርተው የገዢው ፓርቲ የድርጅቱን መተዳደሪያ ህግንና ደንብን በጣሰ ኣኳኋን የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ኣሰላለፍን በማይፈቅደው ኣኳኋን ኣጥፊ ኃይሎችና ገዢ ድርጅቱ የፖለቲካ ኣሰላለፍ መቀላቀል ሁኔታ እንዳለ ገምግሞ ይህንን ኣመቺ ዕድል ተጠቅመው ፀረ ሉኣላዊነታችንና ፀረ ሰላም የሆኑት ኃይሎች በመንግስት እሚወደሱበትና ያሻቸውን እሚያደርጉበትን ፥ ዕድሜ ልካቸውን ለሃገር ሉዓላዊነትና ልማት ሲታገሉና ሲለፉ የኖሩ የቁርጥ ቀን ልጆች ግን የስም ማጥፋት እና የእስር ውንጀላ ሲካሄድባቸው ባስ ብሎም ግድያ ሲፈፀምባቸው በምናይበት ወቅት ላይ መድረሳችን ህወሓት ገምግሞ ፥ ይህም ኢህኣዴግ ለሚያደርገው ፖለቲካዊ ትግል የኣሰላለፍ መቀላቀል ውስጥ ሆኖ ጎራን ባልለየ በኣደገኛ የፖለቲካዊ ኣሰላለፍ እየኳተነ መሆኑን ተገምግሟል ።

የኢትዮጵያ ዜጎች በተለይም ደግሞ ወጣቶች በስራ ኣጥነት እንዲሰቃዩ ፥ በማንነታቸው ምክንያት ዜጎች ያፈሩትን ሃብት ፥ ኣካሎቻቸውንና ህይወታቸውን እንዲያጡ ፥ እንዲሸማቀቁ ፥ በረሃብ ኣለንጋ እንዲገረፉ ፥ ዜጎች መጠለያ ኣጥተው በፀሃይና በቁር እንዲገረፉ ፥ በዚህች ሃገር በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የዜጎች በኣደባባይ ላይ መገደል ፥ የዜጎች መፈናቀል ፥ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ሕግና ሰርኣት መከበር ያልታየበት ሁኔታ መስፈኑ ፥ ኢትዮጵያ ጠባቂ ኣጥታ የፅንፈኞችና የህገወጦች መላገጫ የሆነችበት ፥ እንዲሁም ባሁኑ ሰዓት ፀረ ህገ-መንግስት እና ፀረ-የፌደራል ስርዓት የሆኑ ፅንፈኛ የሆኑ የትምክህት ኃይሎች እንዳሻቸው እሚፈነጩበት ዕድልና ሁኔታ መፈጠሩን ህወሓት በፅኑ ገምግሟል።

ህወሓት በግምገማው "የትምክህት ኃይሎች" ብሎ ሲፈርጅ የህዝቦች መሰረታዊ ፥ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ዓፍነውና ረግጠው የራሳቸው ፍላጎትን ለማሟላት እሚጥሩትን ጥቂት ቡድኖችን እንጂ ሰፊውን ህዝብ በዚህ ሓረግ ፈርጆ እንደማያውቅ እንዲሁም በማንኛውም መለኪያ ትምክህተኛ የሚባል ህዝብ እንደሌለ ያምናል። ህወሓት ሁሉም ህዝቦች ፍላጎቶቻቸውና ምኞቶቻቸው ተመሳሳይና ኣንድ እንደሆነ በፅኑ ያምናል ። ወዳጅም ጠላትም ማወቅ ያለበት ህወሓት ትናንት ፥ ዛሬም ሆነ ነገ ለህዝቦች የላቀ ክብር እሚሰጥ ፥ ህዝባዊ ዓላማና ኣቋም ኣንግቦ በቅኑ ፖለቲካዊ መስመር እሚታገል ድርጅት መሆኑን ነው።

ህወሓት ባለፉት ጊዚያት ከኣማራ ህዝብ ጋር በመሆን ፀረ ትምክህተኞችንና ፀረ የገዢ መደቦችን ኣብሮ የታገለና ትርፍ መስዋእትነት የከፈለ ድርጅት ነው። ስለሆነም ህወሓት ለኣማራ ህዝብ "ትምክህተኛ" ሊል እሚችል ድርጅት ኣይደለም ። ነገር ግን በኣማራ ህዝብ ስም እሚነግዱ ኃይሎች ሰፊውን የኣማራ ህዝብ "ትምክህተኛ ተብለሃል" በማለት ህዝቡን ለርካሽ ፖለቲካዊ ፍጆታቸው ሲያደናገሩት ቆይተዋል ። በኣማራ ስምም እየነገዱ ላልተባለውና መገለጫው ላልሆነው "እንዲህ ተብለሃል" እያሉ እላዩ እንደ መዥገር ተጣብቀው ህዝቡን በሁሉም ነገር እያማቀቁት ይገኛሉ ። ቢሆንም ግን የኣማራ ህዝብ እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ ለሰላም ፥ ለልማት ፥ ለዲሞክራሲ ብሎ መስዋእትነት ከፍሏል ፥ ኣዲሲቷን ኢትዮጵያ በመፍጠር ሂደትም እማይተካ ሚና የተጫወተ ህዝብ ነው ።

በሃገሪቱ ተጀምሮ የነበረ ተስፋ ሰጪና ብሩህ የሰላምና የልማት ስራዎች ዛሬ መሪ ኣጥተው ጨልመዋል ፥ የፀጥታና የደህንነት ተቋማት ከየትኛውም ጊዜ በላይ የሃገሪቱና የዜጎች ሰላምና ደህንነትን ማስጠበቅ በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። የተፈፀመው የከፍተኛ ኣመራሮች የተቀነባበረ ግድያ እሚያሳየን መንግስት የዜጎች ሰላምና ደህንነት ማክበር እንደተቸገረ ፥ በግፍና በጭካኔ የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት እሚፈልጉ የትምክህት ኃይሎች እንዳሻቸው እሚፈነጩበት ፥ በመንግስት የስልጣን መዋቅር ተሰግስገው የኢትዮጵያ ብ/ብ/ሰ/ህዝቦች የስምምነት ሰነድና ዋስ ጠበቃ የሆነውን ህገመንግስታዊና ፌዴራላዊ ስርዓቱን ለመናድ በጠራራ ፀሃይ እሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

እንዲህ ባለ ሁኔታ በዚህች ሃገር በየቀኑ ምን ኣዲስ ጥፋት እንደሚፈፀም ኣስቀድሞ ለማወቅ በሚያዳግትበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን ። የሃገራችን ሁኔታ ወደዚህ ዓዘቅት መውረዱን እየታወቀ በግልፅ የተፈፀመውን የከፍተኛ ኣመራሮች የተቀነባበረ ግድያ በመፈፀም የመንግስት ስልጣንን በቀላሉ ለመቆጣጠር የተደረገውን ሙከራ የፈፀሙትን ወንጀለኞች እሚኮንንም ሆነ ግልፅ ኣቋም ይዘህ ፖለቲካዊ ትግልን ለማራመድ የተደረገ ነገር እየታየ ኣይደለም። ይባስ ብሎም "ሁሉም ሟቾች ለውጡን በማምጣት ሂደት ላይ ከፍተኛ ኣስተዋፅኦ ያበረከቱ ነበሩ" በሚል ኣደገኛ የእንዝላልነት መግለጫ የተፈፀመውን እኩይ ተግባር ይበልጥ እንዲቀጥል እሚያበረታታና የከፍተኛ ኣመራሮች ግድያም እንዲቀጥል እሚያደርግ ከማስቻሉም በላይ በዚህ ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተባበሩና እጅ ያለባቸው ኣካላትንም ከተጠያቂነት ለመደበቅ ጥረት ሲደረግ እያየን ነው ። ሌላው ቀርቶ የሃገሪቱን ሰላምና ደህንነት ያስጠብቃል የተባለው የመረጃና ደህንነት ተቋም ይህንን የተቀነባበረውና በከፍተኛ ኣመራሮች ላይ የተፈፀመው ግድያ እንዲጣራም የሚጠበቅበትን እየሰራ ኣይደለም ።

ስለሆነም የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ሃገሪቱ በከፍተኛ ፖለቲካዊ ፥ ማህበራዊ ፥ ኢኮነሚያዊና በተለይም ደግሞ ሉዓላዊ ቀውስ መዘፈቋን የደመደመ ሲሆን ድርጅቱ ቀደም ሲል ተንብዮ ባስቀመጠው የመፍትሄ ነጥቦች ላይ የሚከተለውን ተጨማሪ የኣቋም መግለጫ ኣውጥቷል ፦

1) በጀግኖች ከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊት ኣመራር ኣካላት ላይ የተፈፀመውን የግድያ ወንጀል ከንድፈ ሃሳብ እስከ ተግባር በቀጥታና በተዛዋዋሪ ተሳትፎ ያደረጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች በሃገራዊ ገለልተኛ ወገን በፍጥነት እንዲጣራ ፥ የሃገሪቱ የፀጥታውና የደህንነት ተቋማት ይህንን ኣደገኛ የግድያ ወንጀል ኣስቀድመው ለመከላከል ባለመስራታቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ ፤ ይህ የማጣራት ሂደትም በየደረጃው በሚደርስበት የማጣራት ሂደት ለህዝቡ ተከታታይ መግለጫ እንዲሰጥ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ያሳስባል ።

2) ባሁኑ ሰዓት ሃገር እየበተነ ያለው ከየኣቅጣጫው የተሰባሰቡ በሃገሪቱ የመንግስት መዋቅርም ጭምር ያሉ የትምክህት ኃይሎች ናቸው ። እነዚህ የትምክህት ኃይሎች እንደፈለጉ ይፈነጩ ዘንድ ሁኔታዎችን ኣመቻችቶ ዕድል እየሰጣቸው ያለውም ብኣዴን ኣዴፓ ነው ። በተለይም ኣዴፓ በግድያ ወንጀሉ ፤ ባጠቃላይ በራሱ ድርጅት ከፍተኛ ኣመራሮች ላይ የተፈፀመውን ግድያ በዝርዝር ገምግሞ ራሱን ተጠያቂ እንዲያደርግ እና ከዚህ በመነሳትም ለኢትዮጵያ ህዝቦች በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ይጠይቃል። ከዚህ ውጭ የተፈፀመውን የግድያ ወንጀል እና የኣዴፓ ውስጣዊ የፖለቲካ ችግር ለመሸፋፈን ሲባል "ወንጀሉ 3ኛ ወገን ኣለው ፥ ረጅም እጆች ያሉት ነው ... ወዘተ" እያሉ ህዝብን ለማደናገር እሚደረግ ኣጉል መልፈስፈስ ሊቆም ይገባል ። በእንዲህ ኣይነት ልክስክስ ኣካሄድ መቀጠል እንደማይቻልም መላው ህዝብ የተገነዘበው ጉዳይ ነው። በመሆኑም ኣዴፓ ሁሉንም ውስጣዊ ችግሩን በዝርዝር ገምግሞና ኣውቆ ፖለቲካዊ ኣቋሙን እንዲያሳውቀን የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ጥሪ ያቀርባል ። ኣዴፓ ይህንን ባያደርግ ህወሓት ከእንዲህ ያለ ቅጡ የጠፋበት ኃይል ኣብሮ ለመስራት እንደሚቸገር ሊታወቅ ይገባል ።

3) እስካሁን ኣጋጥሞ ያለው መሰረታዊ ችግር በዋናነት በኢህኣዴግ ውስጥ የፖለቲካዊ ኣሰላለፍ መደባለቅ የፈጠረው ችግር ሆኖ በግልፅ የኣቋምና የፖለቲካዊ መርህ ውግንና ትግል እየተተወ ኢህኣዴግ ሁሉም ኣይነት ጥገኛና ደባል ፖለቲካዊ ኣመለካከቶችን ተሸክሞ የሚጓዝ ድርጅት እየሆነ ስለመጣ ነው ። ስለሆነም የሃገራችን ደህንነትና ሰላም ለማረጋገጥ እንዲሁም ኢህኣዴግ ወደሚታወቅበት ህዝባዊነቱና ታማኝነቱ ባህሪው በፍጥነቴ እንዲመለስ ብሎም ከቅይጥ ፖለቲካዊ ኣሰላለፍ ተላቆ የጠራና ንፁር የፖለቲካዊ መስመር ውግንናን ወዳደረገ ትግል እንዲመለስ በቀጣይ ኣመት ስለሚካሄደው ህገመንግስታዊ ስርዓቱን የጠበቀ ሃገራዊ ምርጫ ኣስመልክቶ ኢህኣዴግ ኣቋሙን እንደ ገዢ ፓርቲም እንደ መንግስትም ለኢትዮጵያ ህዝብ መግለጫ እንዲሰጥ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ያሳስባል ።

4) የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሃገሪቱ ህገመንግስት እና የፌዴራል ስርዓቱን ከየትኛውም ውስጣዊና ውጫዊ የጥፋት ኃይል ለመጠበቅ የተሰጣችሁ ህገመንግስታዊ ኃላፊነት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ኣንድነታችሁን ኣጠናክራችሁ የእናት ሃገራችሁ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ዝግጁ እንድትሆኑ ጥሪ እያስተላለፍን ይህንን ለመፈፀም በምታደርጉት ታሪካዊ ትግል ልክ እንደወትሮው ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ ከጎድናችሁ እንዳለን ልንሳውቃችሁ እንወዳለን ።

5) ህወሓት እንደ ኣንድ ህገ-መንግስታዊና ፌደራላዊ ኃይል ህዝብን እና ሃገርን ኣሁን ካለው እና ከመጪው ችግር ለማዳን ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ህገ-መንግስታዊና ፌደራላዊ ኃይሎች ጋር ሰፊ መድረክ ፈጥሮ እንዲታገልና ወደተግባርም እንዲገባ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ጥሪውን ያስተላልፋል ።

6) በደቡብ ክልል እየተነሱ ያሉት ህገመንግስታዊ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች ህገመንግስቱን መሰረት በማድረግ ህገመንግስታዊ በሆነ መልኩ ብቻ መፈታት ይኖርበታል ። ከዚህ ውጭ የህዝቦች ጥያቄ በኃይል ለመደፍጠጥ እሚደረግ የትኛውም እንቅስቃሴና ሙከራ ተቀባይነት እንደማይኖረው ህወሓት ያሳስባል ።

7) የፌዴራል መንግስት በሃገሪቱ ኣስተማማኝ ሰላም እንዲያረጋግጥ ፥ ህግና የህግ የበላይነት እንዲያከብር ፥ የዜጎች ሰብኣዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲያረጋግጥ ፥ ህገመንግስት እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ሳይሸራረፉ በጥብቅ እንዲተገብር የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ደግም ያሳስባል ።

ዝኸበርካ ህዝቢ ትግራይ ፦
================

ኣብ ዙርያ መስመርካን ውድብካን ዓሲልካ በቢእዋኑ ንዘጋጠመካ ማእለያ ዘይብሉ ተፃብኦን ውዲትን እናበጣጠስካ ንቅድሚት ትምርሽ ኣለኻ። ሳላ ፅንዓትካ፣ ትዕግስትኻን ብልሕኻን ካብ ዝሓዝካዮ መንገዲ ከይወፃኻ ኣብ ዕላማኻን መስመርካን ፀኒዕኻ ትቃለስ ኣለኻ። ተስፋ ክትቆርፅ፣ ክትስኮን ርእስኻ ክተድንን ኢሎም ኮስኺስካ ሃኒፅካን ዘዕበኻዮም ሙሩፃት ተጋደልትኻ ክትስእን ገይሮም እዮም። እንተኾነ ግን መስዋእቲ ናዓኻ ሓድሽ ኣይኮነን። ሙሩፃት ደቅኻ እናኸፊልካ ኢኻ ናብዚ በፂሕኻ። ሕዚ እውን እንተኾነ ዘጋጠመካ ፀገም በዲህኻ ንዝበለፀ ቃልስን ንዘይተርፍ ዓወትን ተዳሎ። ሓቀኛን ፍትሓውን ቃልሲ ክሳብ ዘካየድካ ኣብ ዕላማ ዝተመስረተ ፅኑዕ ሓድነትካ ክሳብ ዘረጋገፀካ መፃኢ ጉዕዞኻ መንገዲ ተደራራቢ ዓወት እዩ። ብምዃኑ እውን ሓድነትካ ኣስጢምካ ኣብ ዙርያ ውድብካን መስመርካን ዕሰል። በቢእዋኑ ንዝህሉ ኩነታት ብንቕሓትን ብትዕግስትን ተኸታተል።

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብ/ብ/ሰ/ህዝቦች ፦
==========================

ትናንት በድህነት እና በኋላ ቀርነት ችካል ተቸንክረን ፈርዶብን የነበረ የኣህዳዊው ስርዓት እና የትምክህት ኃይል በብ/ብ/ሰ/ህዝቦች የተባበረ ትግል ብዙ መስዋእትነት ተከፍሎበትተሸንፎና ተቀብሮ የነበረ ቢሆንም እነሆ ኣሁን ከግብረ ኣበሮቹ ጋር የመቃብሩን ኣፈር ኣራግፎ በማንሰራራት ላይ ይገኛል። ይባስ ብሎም በብ/ብ/ሰ/ህዝቦች ደም የተፃፈውና የህዝቦቻችን ቃል ኪዳን ሰነድ የሆነውን ህገመንግስቱንና የፌዴራል ስርዓታችን ለማፍረስ ከውስጥ እና ከደጅ ኃይሉን ኣቀናጅቶ ላይና ታች እያለ ይገኛል ። ስለሆነም እኛ ኢትዮጵያውያን ብ/ብ/ሰ/ህዝቦች ህገመንግስታችንና ፌዴራላዊ ስርዓታችንን ለመጠበቅ ፥ በይበልጥ ደግሞ የሃገራችን ኢትዮጵያን ህልውና ለማረጋገጥ ኣብረን እንድንታገል የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ጥሪውን ያስተላልፋል ።

ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለሰማእቶቻችን ‼

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማእከላይ ኮሚቴ ፥

ሓምሌ 3/2011 ዓ.ም

መቐለ ፤


Post Reply