Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Meleket
Member
Posts: 309
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 26 Jun 2019, 10:48

እኒህ ቆፍጣናና ከዓላማቸው ዝንፍ የማይሉት አርበኛ ለዛሬ፣ አልፋረዶ ካርሎ ሲቪል ለብሶ የመጣው ኮሎኔሉ የጣሊያን ሰላይ ማን ነው? እንዴትስ በጎንደር መንገድ ዘጌ ባህር ሲሰልል ህይወቱ አለፈች? ማንስ ገደለው? ለምን? ጣልያን ምን ዓይነት ሴራ ጎነጎነች? የሱን ወይንስ የባንዳዎችን ሞት እንደ ሰበብ ቆጥራ ነውን በኢትዮጵያ ላይ ጦርነቱን ያፋፋመችው? የጎንደሩ ከንቲባ ደስታ ምትኬ ጣሊያንን ለማብረድ ከአዲስ አበባ ምን እንዲያደርግ ታዘዘ? "ረቂቁ ዲፕሎማት" የተባሉት ባሻይ ዑቁባ ሚካኤል ገብረ ምን ሚና ነበራቸው? ለቀምት ላይስ ከኮሎኔል በላይ ኃይለኣብና ከአጋሮቹ ጋር ሆነው ፫ የጣሊያን አውሮፕላኖችን ምን አደረጓቸው? “ነፃነት ከሌለበት ሀገር ሚኒስትርነት ከመሾም ነፃነት ባለበት ሀገር ገበሬ መሆኔን እመርጣለሁ” እያሉ የነ አቶ መኮንን ሃብተወልድንና ቀኛዝማች ተኽለ ማርቆስን ድርጊት ለምን አብጠለጠሉት? እነዚህንና ተያያዥ ጉዳዮቹን ታሪከኛዉ አርበኛ ያስኮመኩሙናል። መልካም ንባብ።

“የጣሊያን መንግሥት ካለፉት ዓመታቶች ሁሉ የበለጠ ስለላ፣ በኢትዮጵያ በ፲፱፻፳፮ ዓ.ም. በቆንሱሎቹ ስለላውን ፈጸመ፤ ለጦርነት ተዘጋጀ። ለ፫ቱ መንግሥታት ለመካፈል ሲመኙዋት የነበሩትን ገነትዋ ኢትዮጵያ በጣሊያን ስም ብቻ እንድትያዝ፣ መብታቸው እንዲጠበቅ በፖለቲካና በገንዘብ፣ በመብልና በዕቃም እንዲረዱዋት ተስማሙ። በጣሊያን ስም ብቻ ኢትዮጵያ እንድትያዝ ወደው አልነበረም የተስማሙ። ሙሶሊኒ ከሂትለራዊ ጀርመን ጋር እንዳይስማማባቸውና ጣሊያንና ኢትዮጵያም መንግሥት በጦርነት ሲዳከሙ ከሁለቱ ጥቅም እናገኛለን ብለው ነው እንጂ ጣሊያን ኢትዮጵያን ድል መታ ትይዛለች አላሉም ነበር። ጣሊያንም ከፈረንሣይና ከእንግሊዝ ባገኙቹ ተስፋ የዶጋሊና የኣድዋን ድልና በቀል ለመመለስ፣ ኢትዮጵያንም አንድ ቀን እንኳ ይሁን ለመያዝዋ፤ የምታፈሰው ደምና የምታጠፋውም ገንዘብ ሳትቆጥብ መነሳትዋን ያልፈቀዱ ልጆችዋ ሰሚ አጥተው ስደት ተሰደዱ።” ገጽ77

“ስለዚሁም አስጨናቂ የሆነውን የኢትዮጵያ ወታደር ጦርነትና ወሰንና መሳይ የሌለውን ድፍረት ምንም እንኳ ጣሊያን ሓዳዲስ መሣሪያና አረዩጵላን ቦምብና የጋዝ መርዝ ጢስና ኢፕሪት በያይነቱ ፋሺስቶች በአረማዊነታቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ቢጥሉበትም፣ ምን ጊዜም ደሙ አለመቀዝቀዙን ስለሚያውቁት በትንሹ አልተገመተም። ስለዚህ ሁሉ የጣሊያን መንግሥት የስለላና የፖለቲካ ክፍል ሰዎቹን “በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ በየስሙ ሲልክ በትሪፓሊ በ፲፱፻፫ ዓ.ም. ብዙ ጥቅም ያስገኘውን ካርሎ የተባለ ባለ ታሪክ ኮሎኔል፣ ሲቪል ለብሶ ተራ ነጋዴ መስሎ፣ በጎንደር መንገድ ዘጌ ባህር ገብቶ ሲሰልል ሳለ ኮሎኔል ካርሎ በጣሊያን አሽከር በአየለ ተገደለ። አየለም ሰላማዊ ሰው መስሎ ካርሎን ገደለና የኢትዮጵያ ሺፍቶች እድንዃኑ ውስጥ ገብተው ሌሊት ገደሉት ብሎም አስወራና ጎንደር እንደገባ በጣሊያን ቆንሱል ግቢ ታሠረ። የጣሊያንም መንግሥት ለኢትዮጵያ መንግሥት አስጨንቆ ከፍ ያለውን የገንዘብ ካሣ ወይም ዘጌ እንዲሠጠው ጠየቀ። የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሎኔል ካርሎ መሞትና የጣሊያን መንግሥት ኢትዮጵያን ካሣ መጠየቅ እንግዳ ነገር ስለሆነበት ገንዘብ የተበደሩትንና ከሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን እነ ቀኛዝማች በላይ መሸሻን ለማሳለፍ በጥብቅ አሰራቸው። የሚያደርገውም ጠፋው። እነሱም መግደላቸውን ፈጽመው ካዱ።” ገጽ 78

“በዚሁ መካከል ከሁለቱ መንግሥታት መልእክተኞች ተልከው ነገሩ ሲመረመር ፪ቱ ሐማሴኖች (የዛሬው አርበኛ ፊታውራሪ) አቶ ጊላጊዮርጊስና ባሻይ ዑቁባሚካኤል ገብረ የጣሊያን አነጋጋሪ አቶ ጊላጊዮርጊስ በኢትዮጵያ በኩል አባሎች ሆነው ስለተገኙ፣ ኢትዮጵያን በተሰወረ ፖለቲካ በመደገፋቸው የጣሊያን መንግሥት ኢትዮጵያን ካሣ ከመጠየቅ አስጣሉት። የሠገነይቲ ባሻይ ዑቁባሚካኤል ገብረ ለአቶ ጊላጊዮርጊስ ኮሎኔል ካርሎን ያስገደለው ኮመንዳቶረ ፖለራ ነው፤ ያስገደለውም የጎንደር ቆንሱል አሽከር የሆነ አየለ የተባለ ልኮ በራሱ በግል ቂሙና የዘጌንም መሬት ወይም ካሣ ለመንግሥቱ ለማሰጠት፣ ኢትዮጵያንም ለመጕዳት ባሰበው ኅሳብ መሠረት ነው፤ እና ተጠንቀቁ፣ ይህም የጎንደር ቆንሱል የካርሎ ገዳይ ነህ ብሎ አየለን አስሮ ሰንብቶ መልሶ ኢትዮጵያን ለመክሰስ ፈትቶ ለቀቀው ብለው ሲያስጠነቅቁዋቸው፣ አቶ ጊላጊዮርጊስም ለጐጃም ሕዝብ አስጠነቀቁትና የራሱ አሽከር አየለ የተባለ ካርሎን መግደሉን ድምፁን ከፍ አድርጎ መሰከረ። የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚሁ ጥልቀኛው ፖለቲካ በባሻይ ዑቁባሚካኤል ገብረና በአቶ ጊላጊዮርጊስ ትጋትና ብርታት ከመጠየቅ ሲድኑ፣ በድፍን ኢትዮጵያ ጣሊያን መርዝ በተነ፤ ኤውሮጳም አረዮፕላኖች በኢትዮጵያ ጀግኖች ሲቃጠሉና ፲፪ የጦር መሪዎች ጄኔራሎችና ነጂዎች ሲገደሉ ባሻይ ዑቁባ ሚካኤል ገብረም ከገዳዎች ጋር አብረው ነበሩ።” ገጽ 78

“በጌራም በ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. በታህሣሥ ወር በሆነው ጦርነት ከክቡር ራስ እምሩ ጋር ስለነበሩ በጄኔራል ማልታ ተማረኩ፤ በወላሞ ሶዶም ሲታሠሩና ሲፈቱ ቆይተው ባሻይ ዑቁባ ሚካኤል ገብረ በአሥመራና በጎንደር፣ ባዲስ አበባም በስውር የምስጢር ፖለቲካ ለኢትዮጵያ መንግሥት ከመሥራታቸው በላይ፣ በኢትዮጵያ ቀርተው ሥራ በመያዛቸውና በጦር ሜዳም በመገኘታቸው ቂመኛው የፋሽት መንግሥት ያለ አንዳች ኅዘኔታና ሰብአዊ ርህራሔ ጂማ ላይ መጋቢት ፬ት ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ባሻይ ዑቁባ ሚካኤል ገብረን ገደላቸው።” ገጽ 79

“በፓለራ ቆንሱልነት ጊዜ የተነሳው የካርሎ መገደል በዮሴፍ ዲ ላውሮ ጊዜ ተፋለሰ፤ ዬሴፍም የአጼ ቴዎድሮስ ስም ዓለማየሁ ልጅ ነኝ ብሎ ሰበከ፤ የኢትዮጵያ ልብስ ለበሰ። የራስ ካሣን እና የልጅ ደጃዝማች ካሣ መሸሻን ወዳጆች አደረገ፤ ግብርም ያበላና መሣሪያና ጥይት፣ ብርም መስጠቱን አዘወተረ። የሀገሩ ገዢዎች ደጃዝማች ወንድወሰን ካሣና ደጃዝማች ካሣ መሸሻም የሱን ግብር በመብላታቸው የጣሊያን ተገዢዎች መሰሉ።” ገጽ 79

“በጎንደር ቆንሱል ተሹሞ የመጣው ፋሽስታዊ ሻምበል ዮሴፍ ዲ ላውር መንግሥቱ ያዘዘውን አንባጓሮ በማንሳት በሰላማዊ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ባንዶቹ ተኩስ እንዲተኩሱበት የጠበቀ ትእዛዝ ሠጠ። የሱ ባንዶችም ሲተኩሱ የኢትዮጵያ ሰዎች ለተኩሱ መልስ ሰጡትና አንድ ሰው ስለገደሉበት ”የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች የቆንሱል ቤታችንን ዙሪያ ከበው ተኮሱብን የሞተና የቆሰለም ሆነናል” ብሎ ለሮማ ሙሲሉኒ በራዲዮ ዕለቱን አስታወቀ። የጣሊያንም መንግሥት ክብራችንን የኢትዮጵያ መንግሥት በወረራ ገፈፈን፤ ዘረፈን፤ ተገፋልን ሲል አስመስሎ በሐሰት ለማሳጣት ለዓለም መንግሥታት አስታወቀ። ለኢትዮጵያ መንግሥትም “ባንዳ በመግደላችሁ ለጣሊያን ባንዴራ ስገዱላት፤ ይቅርታም ጠይቁን ያለዚያ ጦርነት አነሳባችሁ አለሁ” ሲል ጊዜ ኢትዮጵያ ከጠብ ለመዳን ብሎ ከጎንደር ከንቲባ ደስታ ምትኬ ሰዎቹን አሠልፎ ለጣሊያን ባንደራ ይቅርታ ጠይቅ፣ ሰላምታም ስጣት ተብሎ ታዘዘ። የጎንደርም ከንቲባ ደስታ በአዲስ አበባ ትእዛዝ መሠረት ሊያደርገው የማይገባው በውርደት የተሞላ ሰላምታ ለጠላት ባንዴራ ሰጠ። በዚህ ጊዜ ኤርትራዊ የተባለ ወጣት ሁሉ ተስፋ ቆረጠ፤ ሞቱን መረጠ፤ ሰሚ ሰው ጠፋ እንጂ ብዙም ተናገረ። የጣሊያንም ሙሶሊኒ በዚህ በቃኝ አላለምና በየቀኑ መጣሁ እያለ ያስፈራራ ጀመር። ይህነኑም ጨካኝ፣ የጣሊያን መንግሥት ጭከና መጻፌ ለመጭው ኢትዮጵያዊ ትውልድ ጠቃሚና ሕያው ታሪክ ሆኖ እንዲያገለግለው ብዬ ነው።” ገጽ 79

ኢትዮጵያኖች ሆይ! ነፃነት ከሌለበት ሀገር ሚኒስትርነት ከመሾም ነፃነት ባለበት ሀገር ገበሬ መሆኔን እመርጣለሁ። ነፃነት ከሌለ ክብርና ጽድቅም የለም። ለጋ ለስላሳው የአኩሩር ከንቲባ አንዱ የልጅ ልጅ ባሻይ ዑቀባ ሚካኤል ገብረ የተሰወሩ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ረቂቅ ፖለቲካ መሪ መሆናቸውን ሳይገነዘብ የጣሊያን መንግሥት ከጎንደር አነጋጋሪነታቸው ወደ አዲስ አበባ ለጋሲዮን አዞራቸውና በ ፲፱፻፳፭ ዓ.ም. መጨረሻ መጥተው እንኳ የጎንደርና የአዲስ አበባ ፓለቲካቸው፣ የሮማም ሳይቀር አካፍለው በሰፊዉ የነ ኮሎኔል ካርሎን ምስጢራዊ የጠበቀ ስለላና መገደሉንም ከባሻይ ዑቁባ ሚካኤል ለማጥናት ቻልን።” ገጽ 80

“የጣሊያንም መንግሥት ከኢትዮጵያ ጥንታዊ ንጕሠ ነገሥት መንግሥት ጋር ጦርንት ለማድረግ ተሰናድቶ ሚኒስትሩን አዲስ አበባ ሲያስወጣ የሚኒስትሩ ዋና አነጋጋሪ ባሻይ ዕቁባ ሚካኤል ገብረ ከድተው ቀሩና የኢትዮጵያ መንግሥት ሥራ በውጭ ጕዳይ ሚኒስቴር ያዙ። ባሻይ ዑቁባ ሚካኤል ገብረ አዲስ አበባ በሚያዝያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ጠላት እንደገባ በደፋሩ ያንበሳ ግልገል በኤርትራዊው ኮሎኔል በላይ ኃይልኣብ ከሚታዘዙት የሁለታ (አበባዎችን) ተማሪዎች ጋር ሆነው በለቀምት ያረፉትን ፫ት የጣሊያን አረዮፕላኖች አቃጥለዋል።” ገጽ 80

“በዚሁም፣ የኔው ከጃንሆይ የጐጃም ጕምሩክ ዲረክተር መሾሜ ከጽሕፈት ሚኒስቴር ለንግድ ሚኒስቴር ትእዛዝ እንደ ደረሰ የንግድ ሚኒስቴር ዋና ዲረክቴር አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ ወደ ጃንሆይ ቀርበው “እኛ ሳንሰማው እንዴት አቶ ተስፋ ሚካኤል የጐጃም ጕምሩክ ይሾማሉ” ብለው ለማስቀረት ሲከራከሩ “ወይድ” ብለው መለሱዋቸው። ቢመልሱዋቸውም በጣሊያን ሚኒስቴር በጥብቅ አደራ ተብለው ኤርትራዊያኖችን ለማጕላላት ራስ ራሳችውን የተሳሙ አቶ መኰንን ሀብተ ወልድና የጽሕፈት ሚኒስቴር ዋና ዲራክቴር ቀኛዝማች ተክለ ማርቆስ የሀገራቸው በጠላት መከበብ ሳያሳዝናቸው የደመወዜ ፻፮ ብር ከጃንሆይ ለተቆረጠልኝ ማዘዣና ስንቅም ከልክለው ለማሰንበቴና አልሄደም ብለው፤ ነጋሪና መስካሪም ሆነው ንጕሠ ነገሥት ዘንድ ለማሳጣት ያለልክ መቅበዝበዛቸውንና ለማስቀረት መስማማታቸውን በንግግራቸው ስለተረዳሁት በቅጽበት ተነስቼ ደብረ ማርቆስ በ፮ ቀን ገባሁ።” ገጽ 80

እነዚህ ሁለት የኢትዮጵያ መንግሥት ዲረክተሮች ከመባላቸው ይልቅ የኢትዮጵያ እናታቸው ጠላቶችና ባለጋሮች ተብለው መጠራት የሚገባቸው ከነፃነት ባርነት፣ ከመግዛት መገዛትን የመረጡ፣ የጣሊያን ሚኒስቴር አደራና ፍቅርን የጠበቁ ውሸትና ማታለልን የታጠቁ (እንጂ) እፍረት የሌላቸው ዲረክተሮች ተብለው መጠራታቸው ኢትዮጵያን ኣያስመሰግናትም። ይህም የሆነበት ምክንያት ከአጼ ምኒልክ ጀምሮ በዚህ ቦታ የቆመው የአስተዳደር የታወረውን ደንብ “ፈረንጆቹን አክብሩ ታዘዙ” የሚል ስለሆነ ለፈረንጅ ያላከበረና ያልታዘዝ ሰው የሚሻርና የሚታሠር ብቻ እየመሠላቸውና ሆድ አምላኩ ሆነው፣ የራሳቸውን የግል ጥቅማቸውን እንዳይቀርባችው ሲሉ ነው እንጂ ከነሱ ጋር ጥልና በቀል እኛ ኤርትራዊያኖች ምንም የለነም ነበር።” ገጽ 81

"ዱሮም ከወሎ ጕምሩክ ዲረክተርነቴ አዲስ አበባ የተዛወርሁበትም ምክንያቱ የጣሊያን ቆንሱል አቶ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ ዕቃችንን በድፍረት ፈተሸብን፣ ጨቆነን፣ በዲስኩር ሰደበን እያሉ ሲሉኝ የነበሩትን የጣሊያን የፖለቲካ ሰዎች ዛሬም ደብረ ማርቆስ ቢሾም የጣሊያንን ቆንሱል አያሠራዉም ብለው ነው አቶ መኰንንና ቀኛዝማች ተክለ ማርቆስ የተጨነቁት። ከእንደዚህ የመሰለው ስሕተትና ውርደት ይሠውረን፤ ኣሜን። ገጽ 81

በቀጣዩ ክፍል አርበኛው ጎጃም ደብረማርቆስ እንደገቡና ሥራቸውን እንደተረከቡ ያጋጠማቸውን ጉዳይ፣ የአቶ መኰንን በሠራተኞች መጫወትና የጣሊያን ቆንሱል ባሮነ ሙዝ በዘበናይነቱ ማበጥ መጀመር በሚሉ ሃሳቦች ዙሪያ የጊዚያቸውን ቦለቲካ እየተነተኑ ታሪካቸውን ይቀጥሉልናል።

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።

Meleket
Member
Posts: 309
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 02 Jul 2019, 09:07

የዛሬው ትርክት አሁን ያለው ትውልድ የመንግሥት አካሄድና ቢሮክራሲን ከዛሬ 100 ዓመት በፊት ከነበሩት ወላጆቹ መማር እንደሚገባው ይገልጽልናል። ያኔ ማንኛውም መንግሥታዊ ሥራና ትእዛዝ በጽሑፍ ይተላለፍ ነበር፡ አሁን በሰለጠነው ዓለም ደግሞ በቃል ብቻ ምስክርየለሽ ሥራ ለመሥራት የሚያነፈንፉትን መሰሪዎች እያየን እንገኛለን። በአሥተዳደር ረገድም ይህኛው ትውልድ ከቅድመ አያቶቹ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደቀረ እንገነዘባለን። ባለታሪኩ አርበኛ በደብረማርቆስ ከጣልያን ቆንስሉ ጋር ያደረጉትን እሰጥ አገባም በዛሬው ትረካ አካተነዋል። መልካም ንባብ።

"ባለታሪኩ ከታላላቅ ባለሥልጣኖችና ግለሰቦች ጋር የተጻጻፉዋቸውን ደብዳቤዎች ናሙናዎች ከዚህ መጽሐፍ ገጾች ላይ በአባሪነት አስገብተናቸዋል። የተገኙትን ሁሉ ብናስገባቸው እጅግ ጠቃሚ በሆኑ ነበር፤ ነገር ግን ገጹ ስለሚባዛና የኅትመት ዋጋውን ከአቅም በላይ ስለሚያደርገው ተውናቸው።" ገጽ82

“ስለ የኔ የጐጃም ጕምሩክ ዳረክተር መሾም የተጻፉት ደብዳቤዎች - ራስ እምሩ -ይድረስ ካቶ ተስፋ ሚካኤል - እንደምን ሰንብተሃል እግዚአብሄር ይመስገን እኛ ደህና ነን። የጻፍከው ደብዳቤ ደረሰኝ። እስካሁን የበቃ ሥራ ባለመያዝህ እደነቃለሁ። አሁንም ወደዚሁ መጥተህ ሥራ እንድትይዝ ማሰቤ አልቀረም፤ የሁሉንም እንድትጽፍልኝ። ጥቅምት ፳፱ ቀን ፲፱፻፳፮ ዓ.ም. ደብረ ማርቆስ ፌርማ እምሩ ኃ. ሥ.” ገጽ 82

“የኢትዮጵያ መንግሥት - የጽሕፈት ሚኒስቶር - ለክቡር የንግድ ሚኒስቴር - ነጋድራስ ሠርፀ ወልድና አቶ መሸሻ ገብረ ማርያም ስላልተስማሙ አቶ መሸሻ ወደዚህ እንዲመጣ። አቶ ተስፋሚካኤል ትኩእ የጐጃምን ጕምሩክ ዲረክተርነት ሥራ ተረክቦ እንዲሠራ ይሁን ብለዋል፤ የኢት.ን.ነ. መንግሥት ማህተም - ፊርማ ጸ፡ት ወልደ መስቀል (ገጽ 82)

“የኢት. ን ነገሥት መንግሥት - የንግድ ሚኒስቴር - ቁጥር ፫ሺ ፮፻፶፰ -ይድረስ ካቶ ተስፋሚካኤል - የጐጃም ጕምሩክ ዲረክተርነት ስለተሾምክ ለነጋ ድራስ ሠርፀ ወልድና ላቶ መሸሻ ገብረ ማርያም የጻፍነውን ማዘዣ ከዚህ ደብዳቤ ጋር ልከንልሃልና እዚህ ትሰራ የነበረውን ሥራ አስረክበህ በቶሎ ወደ ሥራህ እንድትሄድ ይሁን። ይህንኑም ላቶ ኃይለ ፀጋዬ አስታውቀነዋል። መጋቢት ፳፯ ቀን ፲፱፻፳፮ - የኢትዮጵያ ን.ነ.መን. ንግድ ሚኒስቴር ማህተም - ፊርማ መኰንን ሀብተ ወልድ (ገጽ 83)

“በቂ ሠራተኞች እንዲሠጡኝ ደመወዝ እንዲወሰንልኝ ብጽፍ የተሰጠኝ የክርክር የደነቆረ መልስ። የኢትዮጵያ ን.ነገሥት መንግሥት የንግድ ሚኒስቴር - ቁጥር ፫ሺህ ፯፻፵ - ይድረስ ካቶ ተስፋ ሚካኤል - ስለሠራተኞችና ስለቀለብህ ሚያዝያ ፮ ቀን የጻፍክልን ደብዳቤ ደረሰን፤ የጐጃም ጕምሩክ አሁን አዲስ የቆመ ጕምሩክ ስላልሆነ ከዚህ ቀደም ጕምሩክ ሲቆም የሚያስፈልጕትን ሠራተኞች ልከናልና እዚያው ሄደህ ሥራውን መርምረህ በጐደለ ስትጽፍልን የሚያስፈልገውን እናደርጋለን። ቀለብህም እንዲቆረጥልህ እናመለክትልሃለን፤ እስከዚያ ድረስ ግን ወደ ሥራህ እንድትሄድ የሚያስፈልግ ስለሆነ በ፫ሺ፮፻፶፰ ቁጥር እንደጻፍንልህ ትእዛዝ በቶሎ ወደ ሥራህ እንድትሄድ ይሁን። ሚያዝያ ፲ ቀን ፲፱፻፳፮ ዓ.ም. ። ቀዳማዊ ኃ.ሥ.ን.ነ. ዘኢትዮጵያ የንግድ ሚኒስቴር - ፊርማ መኰንን ሀብተ ወልድ ” ገጽ 83

“በሚያዝያ ፲፮ ቀን ፲፱፻፳፮ ዓ.ም. በበቅሎ ኪራይ ከነ ቤተ ሰዎቼ ደብረ ማርቆስ ገና እንደገባሁ የደጕ ክቡር ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ አባይነህ ያጌጠ በያይነቱ መስተንግዶ የተሸከሙ የግቢ አሽከሮችና ገረዶች ከመግባታችን አለበሱን። ወደ ግቢ ገብቼም አዋቂው ራስ እምሩን እጅ ለመንሳት መጣሁና እጅ ስነሳቸው “ስንቅ ተቀብለሐል?” ጃንሆይ ፻፮ ብር ደመወዝ ቆርጠውልህ ነበር፣ ሲቆርጡልህም ቀኛዝማች ተክለ ማርቆስ ቃላቸውን ሰምቶዋል፤ ማዘዣ ተቀብለሐልን” ብለው ጠየቁኝ። “ስንቅ ከለከሉኝ፤ ስለ ደመወዝህም ለወደፊቱ እንዲቆረጥልህ እናመለክትልሃለን። እስከዚያ ድረስ ግን ወደሥራህ እንድትሄድ” ብለው እንዳልሄድና እንዳልቀርም ስላደረጕኝ ዝም ብዬ መጣሁ” ስላቸው በብዙ አዘኑ። ወዲያውኑ ግምጃ ቤት ቀኛዝማች ከበደ ብሩን ሠፈሬ ድረስ መጥቶ ፻ ብር እንዲሠጠኝ አስይዘው ላኩልኝ።” ገጽ 83

አማካሪዎቾ እኛ ነን” ብለው በመመካት ለደመወዜ ማዘዣና እንደ የመንግሥት ሠራተኞችም ሁሉ ስንቅ ከልክለው፣ ስውል ሳድር ነጋሪና መስካሪ ሆነው “ተስፋ ሚካኤል ግርማዊነትዎ መልካም ሰው መስሎት የጐጃም ዲረክቴርነት ቢሾመውና ወደ ሥራህ እንድትሄድ ብለን ብናዘው ከተማ ተቀምጦዋል” ብለው በማሳጣት ለማስቀረት የተሰናዱትን ቀኛዝማች ተክለ ማርቆስና አቶ መኮንን ሀብተወልድ በግስገሳ ደብረማርቆስ (መንቆረር) መግባቴን በራስ እምሩ በኔም ስም ቴሌግራም በመቀበላቸው ወሰን በሌለው ኅዘን ተቃጠሉ፤ ሥራው በደንብ እንዳይካሔድም በብዙ ደከሙ፤ ድካማቸውም ሁሉ የጣሊያን ቆንሱል ተቆጣጣሪ ሰው ሳይኖረው በነፃነት በጐጃም እንዲሠራ ብለው ነው።” ገጽ 84

“በማግስቱም የጐጃም ሠራተኞች ወደኔ መጥተው “በየጊዜው አዲስ አበባ ሔደን ለንግድ ሚኒስቴር ዲረክተር ላቶ መኰንን ብናመለክታቸው ነጋድራሱና ዲረክተሩ ቀለባችሁን ይወስኑላችሁላ ብለዉን ነበር። ያለ ደመወዝም ካንድ ዓመት በላይ ሠራን፤ ደመወዝም የማይሠጠን ከሆነ አሰናብቱን” ብለው ሲሉኝ ደመወዝ ለመስጠታቸው ባለመቻሌ እያዘንሁ ባቶ መኰንን ሀብተ ወልድ ከእውነት መንገድ የራቀ ንግግራቸው ተደነቅሁ። እማደርገውም ጠፋኝ። ስለዚህ እኔም ለክቡር ራስ እምሩ በግልጽ “የሠራተኞች ደመወዝ ተወስኖ ካልተሰጣቸው በቀር ሥራ መሥራት ችግር ስለሆነ ከሁሉም ሥራ በፊት የሠራተኞቹን ደመወዝ ይወስኑልኝ” ስላቸው፣ አዋቂው ኢትዮጵያዊም “ደልድለህ አምጣልኝ፤ እሽ” አሉን። እኔም የሰዎቹን ዝርዝርና የገንዘቡንም ልክ ሰንጠረጅ አሰናድቼ ፈርሜና ነጋድ ራሥ ሠርፀ ወልድን አስፈርሜ ሳቀርብላቸው በደቂቅ ፈርመው በየወሩ ሠራተኞች ደመወዝ፣ ደመወዛቸውን እንዲቀበሉ ማዘዣ ሰጡን። ሠራተኛም ራስ እምሩን አመሰገነ፤ ለኔ ከኅሊና የማይስማማውን መጥፎ ክርክርና አድልዎም ከመጨነቅ አሳረፉኝ።” ገጽ 84

“እኔም ከመድረሴ በፊት ላንድ የደብረ ማርቆስ የመደብ ሠራተኛ ልጅ ፩ዲት ቤሣ ከገቢው የቀን ሂሳብ ቢጐድልበት በጅራፍ እንዲገረፍ ሲሉ ነጋድ ራስ ሠርፀወልድ በራስ እምሩ ችሎት ቢያቀርቡት በብዙ ተቆጥተው ነፃ ለቀቁት። ይህና ከዚህም የባሰው የባለሥልጣኖቹ መጥፎ ሥራ ከዚህ የመረረውን የጣሊያንን ግፍ ጐተተ። አመጣም።” ገጽ 84

“በጐጃም አገው ምድር በዳንግላ ተቀምጦ የጻና ባህር ሀብትና የዳንግላን የባሮች መሸጫ ገበያ መርምሮ የተረዳና ለመንግሥቱም በሰፊው ያስረዳ የእንግሊዝ መንግሥት ቆንሱል ሥራውን ፈጽሞ ለጣሊያን መንግሥት ቁንሱል ስብከቱን ለቆለት ሔደ። በራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት መሻርና መታሠር ብቻ ሳይሆን በጣሊያንም የማያቋርጥ ብርቱ የፕሮፓጋንድ መጥፎ ስብከት በጐጃም ሕዝብ ልዩ ሃሳብ ተወለደ። ምንም እንኳ ቢገፉትና ቢበድሉት የጐጃም ሕዝብ በመታሠራቸው አዘነ እንጂ በደላቸውን አላስታወሰም። የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑል ራስ ኃይሉን ልጅ ኢያሱን አቀፉ ከጣሊያን ጋራም ተስማሙ ብሎ አሠራቸው እንጂ ሕዝብን በድለዋል፣ በሳቸውም መጥፎ አገዛዝ ጐበዝ ወደ ትራፓሊ ለገንዘብ ብሎ እየሔደ አልቆዋል፣ ብሎ መንግሥት አላሠራቸው ነበርና ወጣት የተባሉ ሁሉ በሕዝብ ጉዳት አጥብቆ አዘነ።” ገጽ 85

የጣሊያን ቆንሱል ባሮነ ሙዝ በዘበናይነቱ ማበጥ ጀመረ። ይህ ባሮነ ሙዝ የተባለ ወጣት በአዲስ አበባ የሚቀመጥ የእንግሊዝ ሚኒስተር ልጅ አግብቶ ስለነበረ፣ በማበጡ ላይ የበለጠ ማበጥን መበጥበጥም ጨመረበት፤ ኢትዮጵያንም በእጁ የጨበጠ መሰለው። ኤርትራዊያን ከሆኑት አነጋጋሪው ብላት ወልደ ሚካኤልና ጸሐፊው ከአቶ ሰሎሞን ወልደ ኪዳን፣ ከአቶ ተክሌ ኃይሉ የራዲዮ ሠራተኛው ጋር ስምምነት ፈጽሞ አጣ። እነሱም ከዱትና መልካም አድርገው ራስ እምሩ ስላስቀመጡዋቸው ሙዝ በእግርና በፈረስ እስከ ዓባይ ድረስ ቢፍልግና ቢያስፈልጋቸውም ሳያገኛቸው ስለቀረ በጐጃም ብጥብጥ ተነሳ። በኔ ወደ ጐጃም መምጣትም በበለጠ ኅዘን አዘነ። ስለምን? በደሴ የነበሩትን የጣሊያን ቆንሱሎች ብሪዬሊና ካርሎ እናራቶነ በሰፊው ለአዲስ አበባ ሚኒስትራቸው አቶ ተስፋ ሚካኤል በመቃወምና በዲስኩር፣ በስድብም አላሠራም አለን ብለው በየጊዜው ስላመለከቱት የጣሊያን ጠላት መሆኔን ስለሚያውቅ ነው።” ገጽ 85

“ እንዲሁም በ ፲፱፻፳፭ ዓ.ም. የሐረር ቆንሱል አነጋጋሪዎች ባሻይ ተስፋ ማርያም ገደላና ባሻይ ገብረ እግዚአብሄር ወልደ ሚካኤልም የምስጢር ደብዳቤዎቹን ሰብስበው ስለከዱት የኤርትራዊያንና የጣሊያንን መንግሥት ጠብና ጥል እየገነነ ሲሄድ፣ በዚያን ጊዜ አታሽ ሚሊተሪ ተብሎ ተሹሞ የመጣው ኮሎኔል ሩጀሮ ለብዙ ባለሥልጣኖች በብዙ ሽህ የሚቆጠር ብር ሲያድላቸው እነ አቶ “በልተን እንሞት” መሸከም እስክያቅታቸው ድረስ ብር በሣጥን፣ በሣጥን ሞልቶ ሲሰጣቸው ያልተቀበለ አልነበረም። ከመቀበላቸውም የበለጠ “ጣሊያንን እናደኸየዋለን ዝም ብለህ ተቀበልልኝ Aየተባባሉ” ማለታቸውን ነበር የሚያናድደን። ስለምን ብራቸው ጨምሮ መወሰዱንና ዘውዳቸውና ሀገራቸውን መቀማቱ፣ ርስታቸውና ምሽቶቻቸውን መወሰዱን፣ ያለ ብር መቀበላቸው በቀር መታሠራቸውና በዶማና በአካፋ Aንደ እባብ Aየተቀጠቀጡ መገደላቸውን ባለማሰባቸውን ነው - ለኤርትራ ልጆች የበለጠ ኅዘንና ስቃይ ሲሰማን የነበረ።” ገጽ 86

“እንደዚሁም በጐጃም ለማንም ሰው ሳይቀር እንደየማዕረጕ ብር እየሰጠ “የጣሊያን መንግሥት በሸዋ ላይ ጦርነት ያነሳል፤ ጐጃምም ለሸዋ ኣይረዳም” እያለ ስብከት አሰበከ። ከሰባክዮቹና ከብር አቀባዎቹም ስዎች ተያዙ። በክቡር ራስ እምሩም ጥበባዊ የእውቀት ሥራ ብዛት ተይዘውና ብር ለየሰዎቹ ሌት እየሄዱ መሥጠታቸውንና በየገበያው ስብከት መስበካቸውን አምነው እንደየጥፋታቸው መጠን እሥራትና ግርፋት በችሎት ተፈረደባቸው። በዚህ ጊዘ ባሮነ ሙዝ አበደ፤ የሚያደርገውም ጠፋው። የኢትዮጵያም የውጭ ጕዳይ ሚኒስቴር በጐጃም የጣሊያን ቆንሱል ራዲዮ እንዲያቆም በመፍቀዱ እየወቀስሁ፣ ባንዴራውን በመኖሪያ ቤቱ ይሥቀለው እንጂ ያለ ደንቡ በመሬት ላይ ስለምን ይተክላል ብዬ ለራስ ብጠይቅ፣ ራስም በተቆርቋሪው ኢትዮጵያዊ ስም እንዲከለከል ጥያቄ ቢያሳልፉ በገንዘብ የተገዛው ሚኒስትር ከክብሩ እንዳይወርድ፣ ከሹመቱም እንዳይሻር የጣሊያን መንግሥት ወዳጅነትና በሚሊዮን የሚሰጠውም ብር እንዳይቀርበት ብሎ “ጠብ ያነሳብናልና የፈቀደውን ሥራም ቢሠራ ኣንዳትቃወሙት” የሚል መልስ ልኮ አሳፈረን። እኔም በበለጠ ኅዘን አዘንኩ፤ ተስፋም ቆረጥሁ፤ ያለ ልክ ጣሊያንን መፍራታቸውንና መገዛታቸውንም ተረዳሁት። በዚሁም መሳይ የሌለው ኅዘንና ስቃይ ታምሜ ወደቅሁ። ኅዘን እማዝነውና እምሰቃየው ስለሀገሬ ብቻ ሳይሆን ከኤርትራ ስላስመጣሁዋቸው ልጆቼና ባለቤትም ነበር። ” ገጽ 86

“እንግሊዛዊት የሙዝ ባለቤትም በጽሞና በጐጃም መኖርን አጥብቃ ጠላችና አዲስ አበባ ለመሔድ ስላስቸገረች፣ በመጨነቅ ተጠበበ፤ በሥራውም አልተደሰተም ነበር። ስለምን አዋቂው ራስ እምሩ በጥበባዊ ሥራቸው ዙሪያውን አስከብበው በቤቱ ውስጥ የሚሠራውን ሥራ ሳይቀር ዕለቱን ስለሚያውቁበት ኅሳቡን ሁሉ በመሠረዙ እሥረኛቸው መሆኑን ስለተረድው ተጨነቀ። እንዳይሠራ በራስ እምሩ እውቀት በመታሠሩና ባንድ በኩልም በምሽቱ በጽሞና መኖርን በመጥላትዋም በመታወኩ ምክንያት ባሮነ ሙዝ ባለቤቱን ይዞ ከጐጃም ወደ አዲስ አበባ ለመሔድ ተነሳ። የደብረ ማርቆስ ጕምሩክ ሠራተኞች በበር ከልክለው በባለቤቴ ላይ ሳቁባት፣ ሰደቡዋትም፣ እያለ አምባጓሮ ለማንሳት በ፲፱፻፳፯ ዓ.ም. በግንቦት ወር ባሮነ ሙዝ እንደ አንድ ዕብድ መለሎ በቢሮዬ ተንደርድሮ ገባ። ከገባም በኋላ እነዚህ በባለቤቴ ሳቅ የሳቁና ስድብም የተሣደቡ ሠራተኞች ቀጥተህ ከሥራቸው ማስወገድ አለብህ፣ አለዚያም ባለቤቴን ያሰደብካትና ያሳቅባት አንተነህ አለኝ፤ እኔም ትነጣጠራቸው እንደሆነ ሥራቱን ልይልህ፣ ካለዚያ ባንተው ቃል የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራተኞች ማንም ሰው ሊቀጣቸው ዓይችልም፤ ስለው በበለጠ ተናደደና በቁጣ እየጋለበ ወደ ግቢ ወደ ክቡር ራስ እምሩ ሔዶ ከሰሰኝ። እኔንም ከልካይ በፍጥነት መጥቶ ራስ ይጠሩዎታል ይድረሱ አለኝና በበቅሎ ወደ ግቢ ወጣሁ፤ ባሮነ ሙዝም በብላታ ንግሩ አነጋጋሪነት አቶ ተስፋ ሚካኤል የጕምሩክ ሠራጠኞች አዞ ባለቤቴን አሰደባት፣ መሳቅያም አስደረጋት እያለ ሲናገር ደረስሁበትና ከዚህ በላይ እንደተመለከተው ቃል ለክቡር ራስ እምሩ አስረዳሁዋቸው።” ገጽ 87

ባሮነ ሙዝ ግን ላመጣው የሐሰት አስመሳይ የማታለል ቃሉ በክርክር ስላቸነፍሁት ራስ ፊት የማስፈራራትና የፉከራ ቃል ሲያነሳ በደንብ ሆነህ ተናገር ብዬ ባባቱ ቋንቋ ልኩን ብነግረው፣” አቶ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ የኤርትራ ተወላጅ ስለሆነ ከኔ ጋራ ተቋቁሞ እኩል ሊነጋገር ዓይችልምና፤ የሚገባውን ቅጣት ባለቤቴን ስላሰደባትና ስላሳቀባት ቅጣት ይቅጡልኝ፤ የተሰደብነውም እኔና እግሊዛዊት ባለቤቴ ነን” ሲል ነገሩን ለማነካካት ብሎ መነሳቱን ማስረጃ ተገኘለት። እኔም እንደዚህ መለስሁለት “ባሮነ ሙዝ እጅግ ተሳስተሀል፤ ሕጋችሁም ሕግ ለሁሉ እኩል ነው ሲል አንተው መፋቅህ። እኔም እውነተኛው ኤርትራዊ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ኤርትራዊ የሆነው ሰው ሁሉ በኤርትራና በሶማሊያ ከሕግ ውጭ በሆነው በአድልዎ የተሞላ ደንባችሁ በሚገዛው ቅኝ ሀገራችሁ በቀር በማንም መንግሥት ዘንድ የታወቀና ለመነጋገርም የሚችል ነፃ ሕዝብ ነውና አንተ ተሰውረህ እንደምትሠራውና እንደምታስበው ዓይምሠልህ፤ ተሳስተሐል። የኔም ኤርትራዊነቴ እጅግ አድርጎ የሚያኮራኝ ነው እንጂ የሚያሳፍረኝ ዓይምሰልህ” ስለው የሚያደርገው ጠፋው። “እናንተ ኤርትራዊያኖች ብትከዱና ብትሸፍቱም የጣሊያን ተገዥዎች ናችሁ፤” እያለ ጠቡን በብዙ አከረረውና እኔንም እፊትዎ ሰደበኝ ሲላቸው፣ ክቡር ራስ እምሩም “በቂ መርቻ ያለበት ነገር አንጣ፤ ካለዚያ ባንተ ቃል ማንንም ሰው ለማሰርና ለመቅጣትም አልችልም” ሲሉት ጊዜ ባሮነ ሙዝ በትልቅ ቁጣ ተነስቶ እየፎከረ መንገዱን ቀጠለ።” ገጽ 87

ብቀጣዩ ክፍል “የባሮነ ሙዝ አዲስ አበባ መግባትና ጎሐ ጽዮን ደርሶ በፍራት መመለስ፣ ሙስ በግዴታ እንዲመልስ ቢታዘዝ በፊቼ ራሱን መምታቱና ኢትዮጵያኖች ገደሉኝ ብሎ በሐሰት መመስከሩ” የሚለውን ክፍል እንቃኛለን ቀጥለንም ወደ አይቀሬው የኢትዮጵያና ጣልያን ጦርነት ታሪክ እንዲህ እንዲህ የታሪከኛውን አርበኛ ታሪክ እየኮመኮምን እናዘግማለን።  

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 309
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 05 Jul 2019, 11:02

አርበኛው ተስፋሚካኤል ትኩእ ዛሬ ስለ በደብረ ማርቆስ የጣሊያኑ ቆንሱል ባሮነ ሙዝ፣ ስለሸረበው ሸፍጥ፣ ስለ ቅሌቱ መዋረዱና ማፈሩ እንዲሁም ጣልያን በምን መላ የኢትዮጵያውያንን ምስጢር ታገኝ እንደነበረችም ሆድ አደሮችን እየወረፉ ይገልጹልናል። መልካም ንባብ።

“የጣሊያን ቆንሱል ባሮነ ሙዝ በጐጃም ሕዝብ ላይ የጣሊያንን የስብከት መንፈስ ለማስፋፋት በሚያስበው ኅሳብ ሁሉ አስተዋይ የራስ እምሩ እውቀት በቅጽበት በማፍረስ ስለሚሰርዝበትና ያለ ፍቃዳቸውም እንዳይወጣ፣ ቢወጣም ፍቃድ ጠይቆ አብሮት የሚሄድ ሰው ስለሚሰጡት መሥራቱ ቀርቶ ኅሳቡን በመመርመር ቤቱ ዘግቶ እንዲቀመጥም አደረጉት። ባለቤቱም ያዲስ አበባ ፍቅር ስለያዛት ከደብረ ማርቆስ ተነስቶ አዲስ አበባ ደረሰ፤ ከመግባቱም የጣሊያን ሚኒስትር ተቆጣውና ባለቤቱ ጐጃም አልመለስም ብላ ስላለችው፣ በፍቅርዋ እያለቀሰ ጎሐ ጽዮን ብቅ ብሎ ዓባይን ሲመለከት፣ “የባሮነ ሙዝ አዲስ አበባ መግባትና ጎሐ ጽዮን ደርሶ በፍራት መመለስ” እንደተባለው፣ በመመለሱ ዓለም ሳቀበት። የጣሊያ ሚኒስትርም ሰድቦና ተቆጥቶ ተመልሶ ወደ ጐጃም እንዲመለስ ቢያዘው “ኣለ ባለቤቴ አልሄድም” ቢል፣ ባለቤቱም ካዲስ አበባ ፈረስ ግልብያ አልወጣም ብትል፣ በግድ ከባለቤትዋ ጋር እንድትሔድ ተደረገና አብረው እያጕረመረሙ ፊቼ ሲደርሱ የጣሊያንም ሚኒስትር ወዳጅ ስለነበረች በመለየትዋ ኅዘን ገብቶባት “ባልሽ ከዓባይ ሓፋፍ የተመለሰ ፈርቶ ነው ብሎ የጣሊያን ሚኒስትር ነገረኝ። እውነትም ፈሪ ነህ፤ አላንቺ ጐጃም ብቻዬን አልሔድም ብለህ አብርዬህ እንድሔድ አድርገህ ያስገደድኸኝ ብላ ስትለው፣ “ሞኝ የነገሩትን አይረሳም” እንደተባለው ተረት ከባለቤቱ ጋር “እኔ ፈሪ አይደለሁም” እያለ ፎከረ። ተጣላት፤ ለብቻውም ተለየ።” ገጽ 88

“ብርቱና ጀግና ወንድ የመሰለውን የጣሊያን ቆንሱል ባሮነ ሙዝ እንግሊዛዊት ባለቤቱ ከወዳጅዋ ለይቶ በግድ ስላመጣትና አዲስ አበባም ለመመለስ ስለተመኘች። “ባልሽ ከዓባይ ሐፋፍ የተመለሰ ፈርቶ ነው ብሎ የጣሊያን ሚኒስትር ነገረኝ” ብላ ስትለው ወንድ መስሎ ሽጉጡን መዞ በራሱ ላይ እንደማይገድለው አድርጎ ተኮሰ። ሽጕጡንም ለማስመሰል ወርውሮ ጣለው። በዚህ ጊዜ አሽከሮቹ ረዱ፤ ባለቤቱም ደንግጣ ካኮረፈችበት በሩጫ መጣችና ስትጠይቀው “የኢትዮጵያ ሽፍቶች ገደሉኝ፤ ያስገደለንም ራሱ መንግስታቸው ነው” ብሎ አላት። በዚሁም መካከል ከአሽከሮቹ አንዱ ከበደ ቸኮል የተባለና ሀገሩን የሚያፈቅር፣ ትሮፓሊ የኖረ የቡሬ ዳሞት ሰው ሙዝ የጣላትን ሽጕጥ በስውር አንስቶ አዲስ አበባ ሙዝን ተሸክመውት ሲገቡ ሆስፒታል ገባ። የደብረ ማርቆስ ቆንሱላችን ባሮነ ሙዝ በየኢትዮጵያ መንግሥት ሰዎች ስለቆሰለ ለመሞት ያጣጥራል፤ የጣሊያንም መንግሥት ክብር ተዋረደ፤ የሚል ያዲስ አበባ ሚኒስትሩ ቃል የደረሰለትን ሙሶሊኒ በሞላው የዓለም መንግሥታት ፊት ኢትዮጵያን ኃጢያተኛ ናት ብሎ ለመውጋትም የሚመኘውን ሙሶሊኒ ደስ ብሎት አፉን ከፍቶ አሰማ፤ በሐሰትም ለመውጋትዋ ተነሳ።” ገጽ 89

“ባሮነ ሙዝና ባለቤቱም በጕባዔ ተመርምረው የኢትዮጵያ ሰዎች ናቸው ያቆሰሉኝ ብሎ በሐሰት የሰጠውን ቃሉንና የባለቤቱም ቃል አንድ ሆነ፤ በጕባዔው የተሰበሰቡትም ሰዎች አመኑ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም በነገሩ እጅግ ተጨንቆበት ሳለ ከበደ ቸኮል በሀገሩ በኢትዮጵያ አንዳች ጕዳት እንዳይደርስባት በማሰቡ ሙዝ ራሱን የመታበትን ሽጕጥ በስውር አንስቶ ከጣሊያንም ለጋሲዮን ባጥር ተሾልኮ ወጥቶ ሌሊት ላይ ለዶክቶር ሎረንሶ መብራህቱ ታእዛዝ ለየኢትዮጵያ መንግሥት አማካሪ አስረከበ። ዶክቶር ሎረንስ መብራህቱ ታእዛዝም አቶ ከበደንና ሽጕጢቱን ይዘው ወዲያውን ወደ ግርማዊ ንጕሠ ነገሥት ፊት አቅርበው ካሳዩ በኋላ ሽጕጢቱ ከነ ቀልሀዋ ለዚሁ ኮሚሲዮን ለተሰበሰቡቱ ሰዎች አሳይተው፣ ይህ ሽጕጥ ሙዝ ራሱን የመታበት መሆኑን በቀለሁ ታወቀና ተመሰከረበት። በዚሁ ጊዜም የሙዝ ቃል ብቻ ሳይሆን የሙሶሊኒና የጣሊያን ቃል በመረታቱ አፈረ፤ ተዋረደ። በዓለም ሕዝብ ፊትም ዋጋ አጣ። አታላይ፣ የሐሰት ፖለቲካ ስብከት መስበኩን በማንም ዘንድ ግልጽ ሆኖ ተነገረ፤ ተሳቀባቸውም።” ገጽ 89

በአርእስቱም ባሮነ ሙዝ በግዴታ ወደ ጐጃም እንዲመልስ ዚታዘዝ በፍቼ ራሱ መምታቱንና ኢትዮጵያውያኖች ገደሉኝ ብሎ በሐሰት መመስከሩን የተባለበት ምክንያት በዚሁ ወሰንና መሳይ የሌለው የጣሊያን መንግሥት ወራሪነት በኢትዮጵያ ላይ ለማስከተል የታሰበ መሠረትና እውነት የሌለበት በኅሰት የታወረ ምኞት ብቻ መሆኑን ተመሰከረባቸው። አሥር ጊዜ በሐሰተኛነታቸው ቢመሰከርባቸውና በሐማሴነው የአከለጕዛይ ቡቺላ ወይ ታማኝ ጠባቂ በዶክቶር ሎረንሶ ታእዛዝ ቢረቱም፣ ሙሶሊኒና ወገኖቹ የሆኑት የጣሊያን ፋሺስቶች መረታታቸውን ቢያምኑትም የኢትዮጵያ መንግሥት በሰቲትና በጎንደር፣ በዘጌና በወልወል ከ፲፱፻፳፭ ጀምሮ እስከ ፲፱፻፳፯ ዓ.ም. ድረስ እውነተኞች ለመምሰል አቤቱታቸውን ከፍ ባለው ድምፅ ለዓለም መንግሥታት አሰሙ።” ገጽ 89

“ሙሶሊኒ በየጊዜው በኢትዮጵያ ላይ ያስነሳውን የሌብነት ልዩ ልዩ ልምድ ስራ ያላቸውን ሰዎች እየመረጠ በተሸከመው ነውር አለማፈሩ እጅግ የሚያሳዝንም ቢሆን፣ እንደ ካፒታኖ ቺማሩታ የመሰለ በወልወል፣ እንደ ግራሲያኒ የመሰለውን የቸረናይካን ሕዝብ የጨረሰውን ለመቃድሾ ጦር ኣዛዥ አድርጎ መላኩን ቀጠለ። ባሮነ ሙዝም ከሆስፒታል ወጥቶ በመረታቱ ወርደቱንና ሐሰቱን ለብሶ ወደ ሀገሩ ተሣፈረ። ጨክኖ ባለመሞቱም ለኢትዮጵያ መልካም ሆነ፤ በዘመዶቹ ዘንድ ግን ፈሪነቱ ተመስክሮበት አንዳች ምስጋና ሳያገኝ ቀረ።” ገጽ 90

“በጣሊያንም ፖለቲካዊ ዘዴ ከኣስያ የምሥራቅ ሰዎች በስተቀር፣ በኤውሮጳ ሰዎች በልዩ ልዩ የሥራ ስም አድርጎ ለሰለላና ለምርመራም ያለ ማቋረጥ ወደ ኢትዮጵያ እየቀጠረ ላከ። ራሳቸው በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያን መንግሥት ከፍተኛው ሥልጣን በእጃቸው ጨብጠው የነበሩት ሰዎችም ወደ ጠላት በመሆናቸው ምክንያት በቀላሉ የኢትዮጵያ ምስጢር ሊያገኝ ቻለ። የኢትዮጵያ አፍቃሪዎች እንደ ጠላቶች፣ ጠላቶችም እንደ ወዳጆችዋ አድርገው እየደለደሉና መጥፎ ቦታና መጥፎ ግምትም ለጀግኖችዋ እየሰጡቱ፣ ኢትዮጵያ ድል እንድትሆን ያስደረጕዋት አንዳንድ የተረገሙ፣ ህሊና ቢሶች የሆኑት ሐሞት የሌላቸው ሰዎች በነገሩ ተጨምረው የጣሊያን ወገን በመሆናቸውና ሥራው ሁሉ እንዳይሠራ በመቃወማቸው፣ ምስጢርን ሁሉ ለጠላት በማቀበላቸው ነው።” ገጽ 90

በቀጣይ ክፍል መንግሥትን መሰሪ ምክር ስለሚመክሩ የመንግሥት አማካሪዎች ከአጤዉና ለራስ እምሩ ከራስ ካሳም ከራስ ሥዩምና ከፊተውራሪ ብሩ የዝውውር ሃሳብ አኳያ የጣሊያንን መሰሪ አላማ ለማሳካት የተሸረበውን ሴራ ያብጠለጥሉታል፣ ሆድ አደሮችንም ይወርዱባቸዋል። አርበኛው ከራስ እምሩ ጋር ከጎጃም ወዴት እንዳቀኑም ይገልጹልናል። በቡሬና በገነትዋ የአንጃባራ አበቤ ዳንግላ አድርገው ደንገል በር እንደደረሱ ከዚያም ከአቶ ዮሐንስ ዓብዱ ጋር ፊታውራሪዎች ሆነው ወደ ጎንደር አርማጭሆን አቋርጠው ጸገደ ወልቃይት ወደ ደጃዝማች አያለው ብሩ ታዘው እንደተላኩ በመግለጽ እዛ ያጋጣማቸውን የግዜውን ፖለቲካዊ ትኩሳትም በብስለት እየተነተኑ ያስኮመኩሙናል፣ ስለ ደፋሩ ጋይንቴው ፊተውራሪ ሺፈራዉም ያወጉናል አርበኛው ተስፋሚካኤል ትኩእ!

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 309
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 11 Jul 2019, 10:37

ለፋሺስት ጣሊያን ያደሩ ባንዳዎችን የሚጠየፉት አርበኛው ተስፋሚካኤል ትኩእ ትረካቸው 20ኛ ምእራፍ ላይ ደርሷል፣ ለዛሬም እንደወረደ አቅርበነዋል። ታሪክ መስታውትም አይደል በጥንቃቄ ስናነበው ብዙ ነገሮችን እናስተውልበታለን እናይበታለን! እንዳባጉና የዛሬ ምናምን ዓመት ጋይንቴው ፊተውራሪ ሺፈራው ፋሺስት ጣልያንን ያርበደበዱበት ቦታ መሆኑንም እንረዳለን።

ከአዋቂው ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ጀምሮ በአቶ ገብረ እግዚአብሔር ደስታም ጊዜ የንግድ ሚኒስቴር ሥራ እየተቻቻለ በመሔዱ በበርና በገበያ፣ በየ ሀገሩም ውስጥ የአዛዥነቱን ሥልጣን በማሳየቱም ስሙ ተነሳ፤ አስተዳደሩም ከሁሎቹ ሚኒስቴሮች የበለጠ ስለነበረ ተመሰገነ። በየ ጠቅላይ ግዛትም ነጋድራስ እያለ ሹም ሲልክ የሥራ ርምጃ መራመዱን ሲጀምር ከፍ ያለ የወገንና የአድልዎ ሰዎች ተነስተው ራሳቸውን ንጹሕ ለማድረግ ሲሉ የንግድ ሚኒስቴርን ሥራና ሥልጣን ዕለቱን እንዲደመስስ በስውር አስፈረዱበት።” ገጽ 91

ከልብ ሣይሆን በአፋዊ ስብከት ለጦርነት መሰናዳ ተጀመረ፤ መጀመሩንም የወደዱት ሰዎች ለራሳቸው ክብርና ጥቅም ለማግኘት የሚሹ፣ ዛሬ ክብርና ደረጃ ሀብትና ጥቅም ያልተለያቸው ሰዎች፣ ክብር ላይ ክብር፣ ሀብት ላይ የበለጠውን ሀብትና ጥቅም እንጨምራለን የሚሉ ሰዎች ነበሩ። ታማኞች መስለው በደላላነታቸው ያባትና የናት ሀገራቸውን ለጠላታቸው ለጣሊያን አሳልፈው ለመስጠት ተጣደፉ፤ በፉከራቸውም ብዛት የሰውን ጆሮ አደነቆሩ። የሰውን ስም አጠፉት፤ በሰው ትከሻና በሰው ሀብትም ጋለቡ፤ ሲናገሩም እውነተኞች መሰሉ፤ ምስጢርን ሰብሰቡት፤ ይሁዳ በከሐድነቱ ጌታውን እንደሸጠም ሆኑ።” ገጽ 91

“ከ፲፱፻፳፭ ዓ.ም. እስከ ፲፱፻፳፮ ድረስ ከጣሊያን ለጋሲዮን ቆንሱሎች፣ ከኤርትራ ሀገረ ገዥና ከመቃድሾም ሀገረ ገዥ እየከዱ በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ሰዎች፣ ከጣሊያን ፊት ለመሰወር ስንደክም፣ ስንከራከርም ያዩን ሰዎች ኢትዮጵያ ለኛ ለኤርትራዊያን የግላችን የሚመስላቸው ሰዎች ነበሩ። ይህም ለመሆን የተቻለበት ሌላ አልነበረም፤ ሕዝብ ከሕዝብ፣ ወገን ከወገኑ፣ በቋንቋና በወንዝ እየለያዩ የተጠቀሙት ኢጣሊያኖችና ጓደኞቻቸው የኢትዮጵያን አንድነት ለመደምሰስ በሚያደርጕት ሐሰተኛው የማታለል ስብከታቸው ያመኑ ሰዎች ናቸው። ያስገቡዋቸው ኣንጂ፣ ጣሊያኖች እስከ ዛሬ ድረስ አዋቂዉ አጼ ዮሐንስና ደፋሩ ራስ አሉላ በህይወታቸው እንዳሉ አድርገው በሽብር ሲባንኑ ይታዩ ነበር።” ገጽ 92

“እነዚ የራሳቸው የግል ጥቅማቸውን ፈላጊዎች የሆኑትም፣ ለኢትዮጵያ መንግሥት እድገትና ስፋት ማሰባቸው ትተው፣ በጠላት ፕላን ተመርተው በ፲፱፻፳፮ ዓ.ም. በህዳር ወር የኢትዮጵያ ራሶች እንዲዛወሩ አድርገው፣ ለሹም ሺር መክረው የወሰኑትን ውሳኔ ራስ እምሩና እኔ ከጐጃም ወደ ጎንደር፣ ራስ ሥዩም ዳር ሀገር፣ ራስ ካሣ ከጎንደር ወደ ጐጃም፣ ፊታውራሪ ብሩ ወደ ትግሬ ሹምሽር እንዲደረግ ብለው መክረው የወሰኑ ሰዎች ተሳስተዋል። ዛሬ በያለንበት ለወረራ ለመጣብን ጥንታዊ ጠላታችን ጣሊያንን ተሠልፈንና ጦራችንን አደርጅተን መዝመትን ነው እንጂ ሹም ሺር ማድረግ ፈጽሞ የማይገባ ነው ብለው ራስ ኣምሩ ኃይለሥላሴ ባያሰርዙት ኑሮ፤ የኢትዮጵያ ራሶች በሹም ሺር ሲዘዋወሩ የጠላታችን ጦር በመካከሉ ሰተት ብሎ ገብቶ ጥይት ሳይተኩስ ለመግባቱ ያሰቡለት ረዳቶቹ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ወዳጆችና ኅሳቢዎች መስለው ያልሆነውን ምክር የሚመክሩት ሰዎች ስለነበሩት ሥራው ሁሉ ምንም ሊቃና አልተቻለም።” ገጽ 92

“የኢትዮጵያ ጥንታዊ ብርቱ፣ ደፋርና ጀግናው ባለ ታሪክ ሕዝብ በዚህ ጊዜ በነበሩ ባለ ሥልጣኖች ስሕተተኛው ጕድለትና በጠላታቸውም ንዋይ በመታወራቸው ምክንያት ጨዋው የኢትዮጵያ ወጣትና አዋቂ፣ ጀግኖችና ሊቃውንት ሁሉ በእነዚህ የጣሊያን ረዳቶችና ደላሎች በሆኑ ሰዎች ላይ በብዙ ዓዘን አዘንን። ሰሚም አጣን፤ ሐሰተኞች እውነተኞች ፣ እውነተኖች እንደ ሐሰተኖች ተቆጠሩ፤ በየጊዜው ከደረጃ ወደ በለጠው ደረጃና ክብር በቅጽበት ሲተላለፉ የነበሩትም መኰንኖች ሀገራቸውን ለመክዳት እረፍትና ኣንቅልፍ አጡ።” ገጽ 92

“ኢትዮጵያም ለ፫ይ መከፈልዋ ቀርቶ ለፋሺስታዊ ጣሊያን ብቻ ሆነች። ስለምን በስውር የጀርመናዊ ሂትለር ጓደኞች ስለሆነች በጣሊያን ስም ብቻ ኢትዮጵያ ተወራ እንድትያዝ ውስጣዊ ፖለቲካዊ ውሳኔ ተወሰነባት። በዤኔብ ጉባኤ ግን ለይምሰለው “የኢትዮጵያ ጥንታዊ ንጕሠ ነገሥት መንግሥት በጣሊያን መንግሥት ሊወረር ዓይገባዉም” ተባለ። ሲወረር ግን “በጣሊያን ለተወረረው ኢትዮጵያ ብለን ወደ እሳታዊ ጦርነት አንገባም” ብለው አመካኙ። የእስያ ሀገሮች ግን ስለ ኢትዮጵያ በጣሊያን ቦምብና የጢስ መርዝ በጭካኔ መደብደብና መወረር በብዙ ኅዘን አዘኑ። ራሩ፥፡ ስለ ኢትዮጵያም በብዙ ተጨነቁ።” ገጽ 93

አዋቂው ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ አባይነህም አያታቸው ቀኛዝማች አባይነህና አጐታቸው ቀኛዝማች ታደሰ አባይነህ በታሪካዊ ጀግናነት የሞቱበትን የዓድዋን መድኃኔ ዓለም ለማየት በደስታ ተነሱ። ከመነሳታቸውም በፌት የጐጃምን ሕዝብ በመስከረም ወር ለምክር ሰበሰቡት፤ ገልጸውም “ለምለምዋ ኢትዮጵያ ሀገራችንን በአጭበርባሪነት ለመንጠቃችን ጥንታዊ ጠላታችን ጣሊያን ፵ ዓመት ተሰናድቶ ለጦርነት መጥቶብናልና ለሀገራችንና ለክብራችን ብለን ትግሬ ዘምተን ጦርነት እንዋጋለንና በወንድነትና በድፍረት በርትተን እንነሳ” ሲሉ አማከሩት። የጐጃምም ሕዝብ በብዙ ነገር ደስ ባይለውም በራስ እምሩ አንድነት መውደድና ፍቅር ብሎ ከሽማግሎቹ እስከ ሕፃናት የጭብጦ ስንቅ ሰንቆ በመዝመቱ በብዙ አስደነቀ፤ በዚሁም ጊዜ ራስ እምሩ “ዘመቻ ዘምተህ ከምትሠራው ሥራ ቀርተህ የምትሠራው ሥራና የምትሰጠው ምክር ይበልጣልና ከዘመቻ ቀሪ አድርገንሀል” ስላሉኝ በብዙ አዘንሁ፤ ፈጽሜ ዘመቻ ከመዝመት ለመቅረት አለመቻሌን ገልጨ ስነግራቸው ፈቀዱልኝና ተሰናድቼ ተነሳሁ።” ገጽ 93

“ክቡር ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴም በጥቅምት ፭ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ከደብረ ማርቆስ ወደ ትግሬ ዘመቻ መዝመታቸውን አዋጅ አወጁ። ታዛዥና ታማኝ የሆነውም የኢትዮጵያ ሕዝብ በደስታ በገዛ ብረቱ፣ በገዛ ስንቁም ሰንቆ፣ ስንቅና ከብት የሌለው ጭብጦ ብቻ ስንቅ ሰንቆ፣ እግዚአብሄርን አምኖ በመዝመቱ ደፋርና ጀግና ሕዝብ አሰኘው። የጥንት የጐጃም ከተማ ደምበጫም ስንደርስ የባሮነ ሙዝን ሽጕጥ በዶክቶር ሎረንሶ መብራህቱ ታእዛዝ በኩል ገብቶ ሽጕጡን ለግርማዊነታቸው ያስረከበ አቶ ከበደ ቸኮል ከጃንሆይ ወደ ራስ እምሩ የተላከው ደረሰብንና ባልደረባነቱን ለኔ ሰጡኝ። የቀረውም የሙዝ እፍረተኛው ታሪክ ሁሉ ከሥሩ ነገረን፤ ራስም ከዘመቻ እንዲቀር አድርገው መለሱትና ዘመቻችንን ቀጠልን፤ በቡሬና በገነትዋ የአንጃባራ አበቤ ዳንግላን አድርገን ደንገል በር ስንደርስ እኔና አቶ ዮሐንስ ዓብዱ ፊታውራሪዎች ሆነን በጎንደር አርማጭሆን አቋርጠን ወልቃይት ወደ ደጃዝማች አያለው ብሩ ታዘን ተልከን ሔድን።” ገጽ 94

“ጎንደር ስንደርስ በጎንደር ከንቲባ በኩል በደብረ ታቦር ሥልክ አዲስ አበባ ለጃንሆይ ስለ የኛ ወደ ወልቃይት መሔድና ስለ ራስ እምሩ መድረስ አሥታወቅንና በቅጽበትም ገስግሰን ጸገዴ ሐፋፍ ስንደርስ በቅሎዬ ደነበረና ቁልቁል ወደ ገደል ወርውሮ ስለጣለኝ የግራ ጐኔ ሁለት አጥንቴ ተሰበሩ። የሽጕጤ ማደርያ ተበሳ። እኔም ለመነሳት ስላልቻልኩ ሽጕጤን ስተኩስ በፊትና በኋላም ያሉት ሰዎች ደርሰው ከወደቅሁበት አደገኛና መጥፎ አወዳደቅ አንስተው ሠፈር አደረሱን። በማግስቱም እኔና አቶ ዮሐንስ ወደ ደጃዝማች አያሌው ብሩ ዘንድ በደጋፊ ሕጄ ስንገናኛቸው ደጃዝማች አያሌው ብሩ ደነገጡ፤ የደነገጡበትም በኔ ጐን መሰባበር ብቻ አልነበረምና ወዲያው ሐኪም ሠፈሬ እየተመላለሰ እንዲያክመኝ አዘዙልኝ፤ ፍሪዳና መስተንግዶም ላኩልን። የወደቅሁትም ህዳር ፯ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ስለሆነ በጸገዴ ሥልክ ቤት እንድታመም ከክቡር ራስ እምሩ ትእዛዝ መጣ፤ ቢመጣም ከዘመቻ ለመቅረት ሕልናዬ ምንም እረፍት ሊሰጠኝ ስላልቻለ በብዙ ታወክሁ፤ ሞት መሞቴ ላይቀር በጦር ሜዳ ደርሼ መሞቴን ተመኘሁ።” ገጽ 94

“የጠላትም ፴፪ አረዮፕላኖች በህዳር ወር በራስ እምሩ ሠፈር ዳባት የቦምብ በሮዶ ስላፈሰሱበት ደጃዝማች ገሰሰ በለውና የሞጣው ፊታውራሪ ታምራት በየበኩላቸው እየከዱ ተመለሱ ማለትን ሰማን፤ በብዙም ኅዘን አዘንን። ራስ ኣምሩም እግዚአብሄርን አማኝ ስለሆኑ “ሀገሬን እረዳለሁ የሚል ሰው ይዝመት፤ ፍቃድ የሌለው ሰው አስገድዶ ማዘመት ጉዳትን ያስከትላል እንጂ ጥቅም ኣይሰጥምና ሰው ከዳን ብላችሁ ማስገደድና ማሠር መታኮስም የለባችሁም ብለው “ ከለከሉ። እኔም ከጸገዴ በጠልእሎ ማርያም በህዳር ፳፭ ቀን ተንስቼ በ፴ ጠለምት ደጃዝማች አያሌው ሠፈር ስደርስ በበለጠ ደነገጡ፤ ወድቀዋል ብለው የተዉኝን ተነስቼ ስደርስባቸው በብዙ ጠየቁኝ።” ገጽ 94

“ “ዛሬ እነ ክቡር ራስ አሉላ በነበሩ ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለማንሳት ባላሰበ ነበር” ስላቸው፤ “እኛን ራስ ቢሉን የበለጠ አድርገን በሠራን ነበር” አሉኝ። “የራስ አሉላን ሩብ ሥራ ቢሠሩም መልካም ነበር፤ ዳሩ ግን አይችሉም” ስላቸው በብዙ ተናደዱ። “የሁለት ራስ ሀገር እየገዙም ዓነሰኝ ማለት ዓይገባዎትም፤” ስላቸው ደጃዝማች አያሌው ብሩም እንዲህ ብለው አሉን። “ራስ ተብለው የበጌምድርን ጠቅላይ ገዢነት ማዕረግ ተሰጥተዎታል ተብዬ የግርማዊ ንጕሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴን ጫማ ከሳምሁ በኋላ ራስ መባሌ ቀርቶ ሀገሩንም ለራስ ካሣ ኃይሉ ስለተሰጠብኝ፣ አጐቴ ራስ ጕግሣ ወሌን ገድዬ መንግሥትን ብረዳ ራስነቱና ሀገርነቱንም ሳላገኝ ከንቱ ሁኜ ቀረሁ። እንደኔስ ለመንግሥት ያገለገለና የተሞኘ የተጐዳስ ማን አለ?” እያሉ እንደ አንድ ዕብድ ሂነው ምስጢራቸውን ገልጸው ነገሩኝ።” ገጽ 95

“እኔም ወሰን የሌለው ኅዘን ማዘናቸውን በመመልከት ከድንኳናቸው ወጥቼ ወደ የጠላትም ማይ አንበሳ ስሔድ የሺሬ ባላባትና ገዥ የሆኑትን ደጃዝማች ገብረ መድኅንን አገኘሁና ሰላምታ ከሰጠሁዋቸው በኋላ “ትግሮችም ከጦርነት ይሻሻሉ ወይ ስላቸው” በብዙ ሳቁ። ስለ የጦርነቱም እቅድና ሁናቴም በለማልሞ በኩል ለሚመጡ ራስ እምሩ እንዲጽፉ ምክር ረጠብሁዋቸው። እኔም ማይ አንበሳ ላይ ጋይንትየው ፊታውራሪ ሺፈራው ሠፈር ሠፍረው አገኘሁዋቸውና አብሬ ሠፈርሁ በህዳር ፴ ቀ። ደጃዝማች ገብረ መድኅን ባይርዑ ማለትም በመጀመሪያ ሐመዶ ላይ ጣሊያን መረብ ተሻግሮ ሲመጣ ወግተው ብዙ ገድለው መሳሪያ የማረኩ ጀግና የጀግናው ራስ ባይርዑ ቱርክን በጕራዕ ያረዱ ልጅ ናቸው።” ገጽ 95

“ታህሣሥ ፩ ቀን የጋይንት ደፋር ፊታውራሪ ሺፈራው ከሠፈርንበት ማይ አንበሳ ተነስተው በታህሣሥ ፭ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. በዳባ ጕና ጣሊያንን በወንድነት ድል መተው ከፈጁት በኋላ ማታ በአረዮጵላን መትረየስ በጀግናነት ሞቱ። ሀገራቸውን አስከበሩ። በዚህ በላይ ለተነገሩት ምስክርነት፤ ከራስ እምሩ ለኔ ተጽፈው በጸገዴና በጸለምት የደረሱኝ ሁለት ደብዳቤዎች ከዚህ በታ እጽፋቸዋለሁ።” ገጽ 95

“ራስ እምሩ - ይድረስ ካቶ ተስፋ ሚካኤል - ለጤናህ እንደምን ሰንብተሃል፤ እግዚአብሔር ይመስገን እኛ ደህና ነን፤ ወድቀህ ጐንህን አሞሃል ማለትን ሰምተን አስበናል፤ አሁንሳ በጣም አልተሻለህም ወይ። እኛም ወደዚያው መቃረባችን ነውና ስለእህል ነገር በጣም የሚያሳስበን ስለሆነ በርትታችሁ እንድታስቡበት ይሁን። ህዳር ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ፌርማ፣ እምሩ ኃይለ ሥላሴ” ገጽ 96

“ራስ እምሩ- ይድረስ ካቶ ተስፋ ሚካኤል - ለጤናህ እንደምን ሰንብተሃል፤ እግዚአብሄር ይመስገን እኛ ደህና ነን በ ፯ ታህሣሥ የጻፍከው ደብዳቤ ደርሰኝ። ሕመምህንስ በጣም አልተሻለህም ወይ? እኛም ሰው እስኪሰበሰብልን አንድ ነገን ብቻ እንውላለን እንጂ ወደዚያው በፍጥነት መምጣታችን ነው፤ አንተም እዚያው እንድትቆየን። ታህሣሥ ፯ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ቦያ ፊርማ፣ እምሩ ኃይለ ሥላሴ” ገጽ 96

በቀጣይ ክፍል በምዕራፍ 21 ስለ የራስ እምሩ በሺሬ በጀግንነት ጦርነት መዋጋት በሚል ርእስ ከቀረበው ታሪኽ እንየዀመኾምን፤ በእንዳባጉናዉ ጦርነት የጣሊያን ኪሳራ ዝርዝርን እንዲሁም ጣሊያን በራስ እምሩ ሰራዊት ተከዜ ላይ በአውሮፕላን የጣለዉን በዓለም መንግሥታት ሕግ የተከለከለዉን “የጢስ መርዝ ጋዝ የብረት ጋን” ማስረጃ ይሆን ዘንድ ከተጣልበት ከተከዜ ዳባት ከዳባትም አዲስ አበባ አርበኛው ተስፋሚካኤል ትኩእ እንዴት እንደላኩት እንኰመኩማለን። አርበኛው ተስፋሚካኤል ትኩእም ልብ ለልብ ከሚናበቧቸው ከራስ እምሩ ጋር የተጻጻፏዋቸውን መልእክቶችም አለፍ አለፍ ብለን እናያቸዋለን፣ የወቅቱን ወታደራዊ ሁኔታም ለመረዳት ያስችሉናል።

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።
:mrgreen:

Post Reply