Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 21 Oct 2020, 04:04

የቆፍጣናውን ኤርትራዊ አባት አርበኛ የተስፋሚካኤል ትኩእን መጠሐፍ 43ኛ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። ለዛሬ ስለእንግሊዝና ጣሊያን የምስጢር ጓደኝነትና የእንግሊዝን ባንዴራ ስላቃጠሉት ስለ የአርማጭሆው ራስ ደጃዝማች ውብነህ ተሰማ በጨረፍታም ቢሆን የጠቆሙንን ሓቆች እንኮምኩም። :mrgreen:

“ጀግና ሳለ በኩራቱ ብዛት ድል ማድረግ የተለየው ሂትለራዊ የጀርመን አዋቂና ብርቱ ወታደር የእንግሊዝ ከተማ ሎንዶንን በየቀኑ በአረዮፕላን ስለደበደባትና የእንግሊዝ የምስጢር ጓደኛውና አገልጋዩም የሆነው የጣሊያን ሙሶሊኒ ስለከዳው፡ የእንግሊዝ መንግሥት ያለ ውዴታው ፊቱን ወደ የኢትዮጵያ አርበኞች አዞረ።” ገጽ 208

የኢትዮጵያ ብልህ ጥንታዊ ሕዝብ የእንግሊዝ መንግሥት ምን ኅሳብ እንዳለው እለቱን አወቀ፤ንጉሣችንን ይዘን በሰላም ሀገራችን እንግባና እንግሊዝ ሲገዛን እናያለን፤ በጀግናው አጼ ቴዎድሮስና በደፋሩ፣ በሰማእቱ በአጼ ዮሐንስ ላይ የሰራውን ግፍና ተንኮል አንዘነጋውም” ሲል የእንግሊዝ ስብከት አስታወሰው ከነከነውም።” ገጽ 208

“በዚሁም ጊዜ ሁሉ ይህን የእንግሊዝን ስብከት ያለስጋት፣ በድፍረት የተቃወሙት የትግሪው ተወላጅ የአረማጭሆው ራስ ደጃዝማች ውብነህ ተሰማና ከወንድማቸው ከደጃዝማች ሐጐስ ተሰማ ጋር ሆነው ጠባቸው እየከረረ ሄደ። በአርማጭሆ መንገድ ኢትዮጵያን እረዳለሁ ብሎ መጀር ባንቲክ የተባለ እንግሊዛዊ መስፍን ወጥቶ ባንዴራ ተከለ ማለትን ሲሰሙ አሞራው ውብነህ ተሰማ እሳት ለብሰው መጥተው፣ “ስለምን በሀገሬ ባንዴራህን ተከልክ” ብለው ጥይት አጉርሰው ባንዴራይቱን ከተተከለችበት አውርደው በቁጣ ቀደው ወረወሩለት። ልክ ኢጣሊያኖችን እንደሚገድሉዋቸው ዓይነት አድርገውም ለመግደል ተነሱ፤ ሰው ሁሉም ለምኖ የሰውዬውን መገደል አስቀረው።” ገጽ 208

በዚሁም የደነቆረ ኦሪታዊ ያረጀ ያፈጀ የማታለል ኃሳቡ የእንግሊዝ መንግሥት ጣሊያንን አስወጥቶ ኢትዮጵያን ለመግዛት የነበረውን ምኞት ለማጽደቅ ከንቱ የሆነ ስብከቱን ሰበከ፤ ካንዳንድ የሸዋ ሰዎችና እነሱንም ከመሰሉ ጥቂት ሰዎች በቀር ተቀባይ ስለአላገኘም የተመቸውን ጊዜ ፈለገ። ሱዳንን ተገዥዎቹ በሆኑት ቁጥር በሌላቸው ህንዶች ወታደሮች አለበሳት። ወደ ለቀቀው ከሰላና ጋላባት፣ ወደ መተማና ወደ አሥመራ በከረን ግንባር አሰለፋቸው። በኋላም ከረን የህንዶች መቃብር ሆነች። መስከረም ፯ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. የአርማጭሆ ራስ ደጃዝማች ውብነህ ተሰማ የእንግሊዝን ባንዴራ የቀደዱበት መስፍን የሻለቃ ባንቲክ እቤቱታውን ለመንግሥቱ ስላቀረበ በግርማዊ ጃንሆይ ቃል ተጠርተው ገዳሪፍ መጡ። ከኔም ጋር ተገናኙና ስለዚሁ የቀደዱት የባንዴራ ነገር አንስተው ጃንሆይ በዚህ ይቆጡ ይመስለዎታል ወይ ሲሉ በሰፊው አጫወቱኝ።” ገጽ 209

“እኔም “አይዞዎት ኃሳብ አይግባዎት። የኔና የመንግሥቴ ፈቃድ ወይም ማዘዣ ሳይኖረው ደርሶ በፈቃዱ ጠላታችንን ወራሪውን ጣሊያን ይመስል የእንግሊዝን ባንዴራ የሻለቃ ባንቲክ በሀገሬ ላይ ስለተከለ አውርጄ ቀድጄዋለሁ፤ ጥፋቱም የራሱ ነው ብለው እውነቱን ገልጸው ለግርማዊነታቸው ከነገሩዋቸው ይደሰታሉ እንጂ ምንም እንደማይለዎት አውቃለሁና የሚገባዎትን መልካም ትልቅ ሥራ ስለሰሩ የሚያሰጋ ነገር ስለሌለበት አያስቡ” ብዬ በማበረታታት መከርሁዋቸው፤ እውነትም ጊዜው ረዳቸው እንጂ እንኳንስ ባንዴራው ተቀዶ እንዲያውም የእንግሊዝ መንግሥት ምሕረትና ይቅርታም ባላደረገላቸው ነበር። የአርማጭሆ ራስ ደጃዝማች ውብነህ ተሰማም በዚሁ ስለ ሀገራቸው በሠሩት ሥራ በመጠየቃቸው ተናደዱና ካርቱም እንደደረሱ ታመው ወደቁ፤ በቸርነቱም ዳኑ።” ገጽ 208

“የኢትዮጵያና የጣሊያንም ጦርነት ጥቅምት ወር ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ጀምሮ እየገነነ ሄደ። ጠላታችንም አስቀድሞ ተስፋ ቆረጠ። ኢትዮጵያዊ ወጣትም በቅጽበት ወደ ንጉሡ ዞረ። ጠላቱን አሳደደ፤ በብዙ በቀል ተበቀለው። ጥቅምት ፲፰ ቀን በሻምበል ወርቁ አየለ የሚታዘዘውን ጦር ለመሸኘት የሻለቃ መስፍን ስለሺና እኔ ዶካ ሄደን ሸኝተን ተመልሰን። እነዚህም ሰዎች በቋራ፣ በበላያና ወንበራ አድርገው የምስራች ለለቀምትና ጐጃም ለግንደበረትም ሕዝብ ለመናገር ለመላላክም በፍጥነት የተላኩ ሰዎች ነበሩ። የተላኩበትን ጉዳይ ፈጸሙ። እኛም ከዶካ ገዳሪፍ ስንመለስ ወዲያው ከሰላና መተማ ተያዙ። ምንም ችግርና መከራ የማይፈታው የኢትዮጵያ አርበኛም በፈቀደው መንገድ እንደልቡ ሆኖ መሄድና መመለስም ጀመረ። ጠላቱንም ዙሪያውን ከበበ።” ገጽ 210

በቀጣዩ ክፍል የዚሁን ምዕራፍ “የተስፋሚካኤል ትኩእ ከነባለቤቱና ከነልጆቹ ተጠርቶ ካርቱም መውረድ፡ የመጀር ኖት በኔ ማዘን” ” የሚለውን አንድ ንኡስ ክፍል በመቃኘት የአርበኛውንና የሜጀር ኖትን በነገር መጎሻሸም እናያለን።

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ ቅንነትን የተላበሰ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 30 Oct 2020, 10:23

የቆፍጣናው አርበኛው የተስፋሚካኤል ትኩእን ትረካ 43ኛ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል፣ ለዛሬ “የተስፋሚካኤል ትኩእ ከነባለቤቱና ከነልጆቹ ተጠርቶ ካርቱም መውረድና ከእንግሊዛዊው የጦር መኮነን ከሻለቃ ዶናልድ ኖት ጋር ያደረጉትን የቃላት ቁሩቁስ እንመለከታለን፥ በቋረኛው ጀግና አባት ኣርበኛ ፊተውራሪ ወርቁ (የታዋቂው የእግር ኳስ ተጫዋች የመንግሥቱ ወርቁ አባት ሳይሆኑ አይቀሩም ብለን እንገምታለን) መሰዋትም እጅግ እንዳዘኑ ይገልጹልናል። ለማንኛውም ትረካውን እንቀጥል!

“የተስፋ ሚካኤል ትኩእ ከነባለቤቱና ከነልጆቹ ተጠርቶ ካርቱም መውረድ፦ ከገዳሪፍ በህዳር ፳፪ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ተነስተን በ፳፬ በምድር ባቡር ካርቱም ገባን፤ በ፳፯ ከግርማዊነታቸው ጋር ተገናኝተን አበባና ፀሐይ ተስፋ ሚካኤል በመንግሥት ሂሳብ አሜሪካን ተማሪ ቤት ገብተው እንዲማሩ ፈቅደው አቶ አንዳርጌ መሳይን አዘዙላቸው። አርበኛና የአርበኞችም መሰላል የነበሩት ቋረኛው ፊተውራሪ ወርቁ በዚሁ ሰሞን በማረፋቸው ስናዝን፣ ደጃዝማች መስፍን ገመችና ደጃዝማች በዛብህ ከጎንደር ጣሊያንን ከድተው መውጣታቸውን ሰማን።” ገጽ 210

“እኔም ከብዙ ቀን በፊት ጀምሬ ቀድሜ ወደ ኢትዮጵያ ለመውጣት በደብዳቤም፣ በቃልም ለግርማዊነታቸው ጥያቄ ጠይቄ ነበርና “ተስፋ ሚካኤል አንተ መሪዬ ነህና አትወጣም። እስክንወጣም ድረስ ከፊታውራሪ መብርሃቱ ሎረንሶ ታእዛዝ ጋር ሆነህ ሥራ እንድትሠራ ይሁን” ሲሉ ራሳቸው ግርማዊ ጃንሆይ አዘዙኝ።” ገጽ 210

በዚሁም መሥሪያ ቤት የዛሬው ምክትል ሚኒስቴሮች አቶ ሠረቀ ብርሃን ገብረ እግዚአብሄርና አቶ ምናሴ ዮሴፍ ለማ የፊታውራሪ መብራህቱ ረዳቶች ሆነው ነበር። በየቀኑም ቁጥር የሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ መተማና አግዳሪፍ እየመጣ ብረት አነሳ። ካርቱም ድረስም እየመጣ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ተገናኘ፤ ብረትና ጥይት ቢያነሳም፣ የእንግሊዝን መንግሥት የክፋትና የጭካኔ ታሪክ እያነሳ፣ በአጼ ቴዎድሮስ መንግሥት ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ ያደረገውንና በኣጼ ዮሐንስም መንግሥት ቱርክና ጣሊያንን አምጥቶ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በማስተሳሰርና ደርቡሹ ማህድትን አበራትቶ ደል(ደንገል) ማርያምና ጎንደርን አቃጥሎ በመተማ እንዲወድቁ፣ ጠላቶቻቸውን አስነስቶ የረዳ፣ የመከረ መሆኑን አንዘነጋውም” ሲል ራሱን በእንግሊዝ ላይ ነቀነቀበት።” ገጽ 210

“ይህንና ይህኑ የመሰለው ክፋቱን ያለ ማቋረጥ በኢትዮጵያ ነገሥታትና ሕዝብ ላይ ያዘወተረውን ግፍ አይበቃኝም ብሎ ዛሬም በዚሁ ወደረኛ በሌለው ክፋቱ ብዛት አጼ ኃይለ ሥላሴ አይሰሩም፤ አያሰሩምና ለኢትዮጵያ ሕዝብ መምጣቸውን አሳይተን እንዳሉም አድርገን ወደ ሎንደን እንመልሳቸዋለን ብሎ ወሰነ። በዚሁም የማስመሰል የአታላይ ሃሳቡም ኢትዮጵያን ለመግዛት ያለ ልክ ደከመ፤ ብዙ ረዳቶችም አገኘ፤ ስብከቱንም ያለ ልክ አስፋፋው፤ ቢያስፋፋውም የአካለጉዛይ ወጣትና ጀግናው አርበኛው ሊቁ ፊታውራሪ መብራህቱ ሎረንሶ ታእዛዝ “የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ ዛሬ በሐዲሱ ሕግና መንፈስ ሥራቸውን ከዱሮ አብልጠው ሊሠሩ ይችላሉና ምንም ኣይመለሱም” ብሎ በወንድነትና ከፍ ባለው ድፍረት ሲነግራቸው እንግሊዞች ከቸረናይካ ወደ ግብጽ የሚገሰግሰውን የጀርመኑን የጄኔራል ሮመልን ጦር ስለፈሩ እሺ ብለው የፊታውራሪ መብራህቱን ኅሳብ ተቀበሉት።” ገጽ 211

የእንግሊዝን ባለሥልጣኖች ኅሳብ የወደዱና በደስታም የተቀበሉት የሸዋ ሰዎችና ሌሎቹም እነሱን የመሰሉት ቢከራከሩም አይሆንም ብሎ ሕያው በሆነው አዋቂ ክርክሩ ሃሳባቸውን ፈጽሞ የሰረዘው ሊቁ ፊታውራሪ መብራህቱ ታእዛዝ ብቻ ነበር። ” ገጽ 211

“በዚሁም ጊዜ እኔ ለወዳጄ ለፊታውራሪ መብራህቱ “እንግሊዝ አጼ ኃይለሥላሴን ከካርቱም ወደ ሎንዶን እንደገና እሥር አድርጎ ሊመልሳቸው ያሰበበት ምክንያት ስለምንድር ነው?” ብዬ ስለው “ኢትዮጵያን ለመግዛት ከመመኘት አቋርጦ የማያውቀው የእንግሊዝ መንግሥት ለሕዝባቸው አሳይቶ እንግሊዝ ሀገር እንዲመልሳቸውና “አሉ” እየተባሉ በኢትዮጵያ ላይ በጫማው ሥር ነው የሚተዳደሩትን ፲፪ ደጃዝማቾች አከፋፍሎ በእነሱም ስም ኢትዮጵያን ለመግዛት በመፈለጉና እሳቸውን ባለመፍቀዱ ነው፤ የኢትዮጵያም ባንዴራ ዛሬ በትኩሱ በእኒህ ሰው ካልተተከለች በቀር ለወደፊቱ ምንም አለመተከልዋን እወቀው። እኔም ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር መከራከሬ የሀገሬ የኢትዮጵያ ነፃነትና ክብር እንዳይደመሰስ፣ ድካሜም ፍሬ ሳያፈራ ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር ብዬ ነው እንጂ አፄ ኃይለ ሥላሴ እንደማይጠቅሙ አውቃለሁ” እያለ ወደፊት የሚገጥመውን ጭንቅና መከራ ሳይቀር ዘርዝሮ በሰፊው ገለጸልኝ።” ገጽ 211

“በዚህ ጊዜ እኔ ከእንግሊዝ ንግሥት ከቪክቶሪያ ለጄነራል ሮበርቶ ናፔር በ፲፰፻፰፩ ዓ.ም. የተላለፈለት ትዕዛዝ አፄ ቴዎድሮስን በህይወታቸው ሳሉ በጥንቃቄ ይዞ እንዲያመጣላትና በስማቸው ኢትዮጵያን እንድትገዛ ነበር ያሰበችው። የዛሬም የእንግሊዝ መንግሥት ባለስልጣኖች በአፄ ቴዎድሮስ ላይ የታቀደውን በንጉሠ ነገሥት ኃይለ ስላሴ ላይ ለመፈፀም መወሰናቸውን አውቀናል። ደፋሩ ጀግናው አፄ ቴዎድሮስ ግን በጠላቴ በእንግሊዝ እጅ ተማርኬ የሀገሬን ክብርና ታሪክ ከማጥፋት፣ ነፃነትዎም ከሚሰረዝ፣ የኔው ሕይወት ቢሰረዝ ይሻላል ብለው በራሳቸው ሽጉጥ ጥይት መሞታቸውን መርጠው ራሳቸውን ገድለዋል። እሳቸው ለኢትዮጵያ መስዋዕት ባይሰዉላት ኑሮ የኢትዮጵያ ንጉሥ ነገሥት መንግሥት ስምም ተሰርዞ፣ የአፄ ቴዎድሮስም ልጅ ተማርኮ ሎንዶን ሄዶ እንደሞተው፣ ልጆቻቸው እንደ ልጅ ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ሲሞቱ በሎንዶን ለሐውልት አስቀምጦ እንግሊዝ ኢትዮጵያን በዘዴ ለመግዛት መመኘቱን ከኢትዮጵያ ጥንታዊ ሕዝብ የተሰወረ ምስጢር እንደሌለ ገልጬ መልስ ሰጠሁት።” ገጽ 212


የሻለቃ ዶናልድ ኖት በኔ ማዘን፦ ከግዳሪፍ ወደ ካርቱም ስነሳ ሳለሁ የሻለቃ ዶናልድ ኖት “በአንደኛ ክፍል ከነ ቤተሰዎችዎ እንዲሄዱ ተፈቅደለዎት ነበር፤ ዳሩ ግን ፈቃድዎ ይሁንና በ፪ኛ ክፍል እንዲሣፈሩ እለምነዎታለሁ” ኣለኝ። እኔም “እንኳንስ በ፪ኛ ክፍል በ፬ኛ ብሄድም ደስ ይለኛል” ስለው “እንዴት?” አለኝ። “እኔ የንጉሠ ነገሥቴን ትዕዛዝ ለመፈጸምና በፍጥነት ሄጄ ለመገናኘት ነው እንጂ እምፈልገው የባቡሩን ክፍል ውበት አላማርጥም” ብዬ መለስሁለት። “በዚሁ ሃገር ስንት ዓመት በስደት ተቀምጠው ኖሩ?”፤ “አራት አመት”፤ “እንዴትስ ሆነው ይኖሩ ነበር?”፤ “አንዳንድ ቀን ውሃና ማሽላም እየናፈቀኝ፣ ከነቤተሰዎቼ በብዙ ችግርና መከራ ተጨንቀን ከመኖራችን በላይ የናንተ ጠቅላይ ሚኒስትር ሻምበርሊን ለፋሺስታዊ ሙሶሊኒ ደስ ለማሰኘት ብሎ ከጣሊያን መንግሥት ጋር ተራርቃችሁ (ታርቃችሁ) ወደ ኢትዮጵያ ሀገራችሁ ባትመለሱ እኔ በግዴታ አስረክባችሁአለሁ እያለ ብዙ ቀን አስፈራርቶን ነበር፤ ዛሬ ግን የጣሊያን ሙሶሊኒ በሻምበርሊን መንግስት ላይ ጦርነት ማንሳቱ መልካም አደረገ” ስለው፥ የሻለቃ ዶናልድ ኖት በኔ ንግግር እጅግ ማዘኑን እየገለጸ የተሰወረውን የሻምበርሊንና የሙሶሊኒ ምስጢር በማውጣቴም ብዙ ተደነቀ።” ገጽ 212

ይህም እንግሊዛዊ የሻለቃ ዶናልሃድ ኖት ካርቱም በደህና መግባቴን እንድጽፍለት ለመነኝ። በኋላም ከአቶ ዮሐንስ ዓብዱና ዳዊት ዓብዱ ጋር መሪ ሆኖ በበላያ ጐጃም ከገባ በኋላ፣ ለጣሊያን ጦርነት ትሪፖሊ ታዞ ማረፉን ሰማሁ። ይህም የሻለቃ ዶናልድ ኖት እንደ ኮሎኔል ወንጌት ወንድ ስለነበረ ሁለቱም በጣሊያን ጦርነት በመሞታቸው ስለወንድነታቸው አዝናለሁ።” ገጽ 212

በቀጣዩ 44 ምዕራፍ “መሳይና ወሰን የሌለው የእግዚአብሄር ቸርነት ጀግናው የኢትዮጵያ ቆራጥ ወታደር ለዘመቻ መነሳት” በሚለው ርእስ ስር የተካተተውን ታሪክ እንደወረደ እንኮመኩማለን።

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ ቅንነትን የተላበሰ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 11 Nov 2020, 05:01

የቀደምት አርበኞችን ገድል በልበሙሉነትና በኩራት እያስኮመኮሙን፡ አርበኛው ተስፋሚካኤልት ትኩእመሳይና ወሰን የሌለው የእግዚአብሄር ቸርነት ጀግናው የኢትዮጵያ ቆራጥ ወታደር ለዘመቻ መነሳት” በሚል ርእስ ስር በመጸሓፋቸው 44ተኛ ምዕራፍ ያካተቱትን ትረካ ላይ ደርሰናል። መልካም ንባብ! :mrgreen:

ሰማያዊ እግዚአብሄር መሳይና ወሰን በሌለው ቸርነቱ በየጊዜው ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ ያደረገለትን ትአምራትና መንክራት፣ አሸናፊ ኃይልና ብርታት ሰጠው። ይህም ጥንታዊ ሃይማኖተኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉድለት በሌለበት እምነቱ የማሸነፍን እድል ማግኘቱን አስቀድሞ በመተማመኑ ባንድቃል ሆኖ ፈጣሪውን ለመነ። በጠላቱ በጣሊያን ላይም በየቀኑ ውርደትና እፍረት፣ ሽብርና ሽሽት አለበሰው፤ ተስፋ አስቆርጦም በጥቂት ሰዎች አስማረከው። ይህም የኢትዮጵያ የግል አምላክ ሥራ መሆኑን በመረዳት፣ በማድነቅ አመሰገነው፤ ያመሰግነዋልም።” ገጽ 213

“ጀግናው የኢትዮጵያ ወታደርም ገና ግርማዊ ጃንሆይ በሰኔ ወር ፲፱፻፴፪ ዓ.ም. ካርቱም እንደገቡ ጀምሮ የጣሊያንን ጦር ሠራዊት በትልቅ እምነትና በድፍረት ዙሪያውን ከበበው፤ ሞት መሞትን ኅዘን ማዘን፣ መቸገርንና መጨነቅን፣ ወደ ጥንታዊ ጠላቱ ወደ የጣሊያን መንጋ በፍጥነት አዛወረ። ካለልክ ደስታ ተደሰተ። በብዙ ለሚተማመነው አምላኩም ከልብ ምስጋናውን አቀረበለት። ስለዚህም ነው በአርእስቱ” መሳይና ወሰን የሌለው የእግዚአብሄር ቸርነት” የተባለው። ገጽ 213

ጀግናው የኢትዮጵያ ቆራጥ ወታደር ለዘመቻ መነሳት፦ መሣሪያና ስንቅ የለንም፤ ውሃ ጠማኝ፤ ረኃብ ጐዳኝ፤ መንገድ ደከመኝ፤ ችግር ቸገረኝ፤ በጦርሜዳ ቆስያለሁ ማለት የማያውቀው ወደረኛ የሌለው ባለታሪክ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግናነት ይህ ነው ተብሎ ሊነገር አይቻልም። አሞራው ደፋር የኢትዮጵያ ወታደር ለዘመቻ መነሳት መላውን የዓለም ሕዝብ በብዙ አስደነቀው። ሴቶች ሳይቀሩ እንደልማዳቸው ለጦርነት ተሰለፉ፤ ስለ ሀገር መሞታቸውንም እንደሰማዕትነት ቆጠሩት።” ገጽ 213

“የኢትዮጵያ ነገሥታት ሁሉ ከጦራቸው ጋር በጦርሜዳ መሠለፍ ልምዳቸው ስለሆነ ግርማዊነታቸውም በሊቁ በፊታውራሪ መብራህቱ ሎረንሶ ታእዛዝ መሪነት በአረዩፕላን ከካርቱም ተነስተው ሠፈራችን ሣይደርሱ በኢትዮጵያ ወሰን ኡም እድላ (ኦሜድላ) ሜዳ ላይ ወረዱ። ከኬኒያ ስደተኞች ውስጥ የአከለጕዛይ ጐዳይቲ ልጅ አለቃ ወልደ ሚካኤል ካንድ ዓመት በፊት አስቀድሞ በትንቢታዊ ጽሁፍ “ጥር ፩፪ ቀን ፩፱፻፴፫ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ባንዲራ እንደገና ተመልሳ በሀገርዋ ላይ ተተክላ ትውለበለባለች” ብሎ እንደመሰከርልን ቃል ልክ፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴም በዚሁ በጥር ፩፪ ቀን ፩፱፻፴፫ ዓ.ም. ኡም እድላ ላይ የኢትዮጵያ ባንዴራ ተክለው እንድትውለበለብ በማድረጋቸው እንኳንስ ሰዎችን ይቅርና የኢትዮጵያ አንበሳም ሳይቀር በቀኑ እያገሣ ለፈጣሪው ምስጋናውን አቀረበለት።” ገጽ 214

በነፃነታቸውና በሐዲሱ ጥበባዊው መሣሪያቸውና ወገኖቻቸው ርዳታ እጂግ ሲመኩ የነበሩት ኤውሮጶች በጠላታቸው በጀርመን ብረታዊ እጅ ወድቀው ሲያዙ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ ነፃነቱን ለበሰ። ጠላቱም በየቀኑ ጨለማ ተከናነበ። እኛም ከኡም እድላ ወንዝ ጃንሆይን ይዘን በአውቶሞቢልና በካሚዮን መንገዳችንን ቀጥለን አቡ መንድ ደረስን፤ ኣቶ ዮፍታሔ ንጕሤም ቅኔ ተቀኝተው ሰውን አስደሰቱት። ከዚያም ትንሽ እንደሔድን አውቶሞቢል የማያስኬድ የዝሆንና የአንበሳ ዱርና ገደል ስለሆነ ጃንሆይን ይዞ የመጣውን ታንክ በጠላት እጅ እንዳይገባ ብሎ እንግሊዛዊው ኮሎኔል ዊንጌት በእጅ ቦምብ አቃጠለው። ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ጂንጕላ (ያልተኮላሸ ፈረስ) ፈረሳቸውን ለራስ ካሣ ኃይሉ ሰጥተው መትሪየስ ጠበንጃቸውን ጨብጠው በእግራቸው የግስገሳ ጕዞ ሲጓዙ ሰው ሁሉ እግሩ ተመላለጠ፤ በለያ በመግባታችንም ተፈወሰ።” ገጽ 214

“ከብዙ ጊዜ በፊት ጀምሬ በጣሊያን ውስጥ ካሉት ኢትዮጵያዊ መኰንን ከባለታሪክ ከደጃዝማች ሣህሌ ኃይለ ሚካኤል ጋር ስለ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ግልጽ አድርጌ በሰፊ ስጽፍላቸው ስለነበረ ከወልቃይት ካርቱም የተላኩልኝን ደብዳቤዎች በለያ ደርሰውኝ፣ ለግርማዊነታቸው አሳይቼ በጃንሆይ ማህተም መልስ እንዳይጻፍላቸው አቶ ወልደ ጊዮርጊስ ቢቃወምም ለልጅ ጕግሣ ገብረ መድኅን፣ ባህታ ሐጐስና ለደጃዝማች ሣህሌ ኃይለ ሚካኤል ዕለቱን መልሱ ተጽፎላቸው በአረዮፕላን ተላከ። የደብዳቤዎቻቸው ቃል ይህ ነው።” ገጽ 214

“ይድረስ ከክቡር አቶ ተስፋ ሚካኤል ለጤናዎ እንደምን ይሆናሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነን። የጻፉልኝን ክቡር ደብዳቤዎ ስለ ደረሰኝና ስለ መልካም ኅሳብዎ አመሰግነዎታለሁ። የጻፉልኝን ሁሉ አንድ ሳይቀር ከልቤ ያለ ነው፤ አሁን ለጊዜው ወደርስዎ ብመጣ በኋላየ የሀገሩ ልብ ወነደሱ ይታለልና መግባቱ ይቸግራል፤ ከዚህ ሁኘ ግን ንጕሡንና ነፃነቱን ከህዝቡ ልብ እንዲሰርፀው አጥናናውአለሁ፤ ይልቁንም የሚያስፈልገንን ነገር አመለክተዎትአለሁ። በመጀመሪያ በወልቃይት ጀምሮ ወደ ትግሬና ወደ ሰሜን፣ ጠለምትም፡ ሺሬ ሁሉ በከተማ ብቻ ሳይሆነ በአገር ቤት ሁሉ በአረዮፕላን የጃንሆይ በደስታ መምጣታቸው በማህተማቸው ሁኖ ወረቀት በየሀገሩ እንዲዘረዘርለት (እንዲበተንለት) ይሁን። ይህነኑም ካየ በኋላ ርግጥ መምጣቸው መሆኑ ህዝብ ይረዳዋል፤ ህሊናውን አረጋግቶ ይረዳልና ልቡ ይጠናል። በሰው ተልኮና በሺሺግ ሲሆን ህዝቡ ሊረዳው አይችልም።”
ገጽ 215

፪ኛ ይህ ከሆነ በኋላ አከታትሎ በወልቃይትና በቃብቲያ በጸገዴ ያለ የኢጣሊያ ጦር ሠፈር በአረዮፕላን አደጋ ቦምብ ማስጣል ነው። ከዚ በኇላ ተረዳድተን እስከ ሺሬ እናባርረዋለን፤ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ግን አስቀድማችሁ ለመንግሥቱ ወልደ ኪዳን እንድትሰዱልኝና ሰው ጕዳት ሳያገኘው ለጦር ድርጅት እንይዛለን፤ ለቀንላቸው ብንወጣ ግን ይሰፋላቸዋል፤ አይመችም።” ገጽ 215

“ክቡር ሆይ ለንጕሠ ነገሥታችንና ለተዋህዶ ሃይማኖታችን ሕይወታችንን ለማሳለፍ ላደረሰን አምላክ አመሰግነዋለሁ። በህይወትና በደስታ፣ በነፃነት አገናኝቶ ለመተያየት ያብቃን እግዚአብሄር። ታህሣሥ ፮ ቀን ፩፱፻፴፫ ዓ.ም. ወልቃይት። አክባሪዎና ናፋቂዎ፤ ፊርማ ሣህሌ ኃይለ ሚካኤል” ገጽ 215

“ይድረስ ከክቡር አቶ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ። እንደምነዎት? እኔ ከጻፉልኝ ወደዚህ እግዚአብሄር ይመስገን ደህና ነኝ። በአቶ መንግሥቱ ወደ ኪዳን በኩል ጽፌልዎት ነበር። ነገር ግን ምላሹ አልመጣልኝም።” ገጽ 215

“ክቡር ሆይ የጻፍልኝ ደብዳቤ የሕይወትና የፍቅር መንገስ ስለሆነ በየጊዜው ደስ የሚያሰኝ ነው። ለወደፊቱም እንደዚሁ እንዲጽፉልኝ ብዙ ተስፋ አለኝ። ሁለተኛ ከዓድዋ ከድቶ ወደ ጃንሆይ መንገድ መድረሻ በትግሬ ስለተቸገረ ወንድሜ ነውና በኔ በኩል አድርጎ ወደጃንሆይ መጥቶዋልና የኔም አኳኋን ከሱ በኩል ያገኙታል። ወንድሜ ስለሆነ፣ ልጅ ይስሐቅ ቢተውልኝ ነፃነቱን የሚናፍቅ ስለሆነ አንድ የኢትዮጵያ ልጅ እርስዎነዎትና እንዲያደርሱልኝ ብሎ ስለተማመነኝ ወደ ጃንሆይ አቅርበው እንዲያነጋግሩልኝ በመተማመን አሳስበዎታአለሁ። ለሁሉም ነገር መልስ እንዲመጣልኝ። አቶ መንግሥቱ ወደ ኪዳን በተሎ እንዲመጣ ይሁን፤ ከእርሱ ጋር ሆኖ መልስ የሚያመጣልኝ ግራዝማች ባህታን ሰድጃለሁ። እግዚአብሔር በቸርነቱ በሕይወትና በነፃነት አቁሞ ለመገናኘት ያብቃን። ታህሣሥ ፲፩ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ወልቃይት። ፌርማ፣ ሣህሌ ኃይለ ሚካኤል።” ገጽ 215

ደጃዝማች ሣህሌ ማለት በዓዲ ሀገራ ጠረፍ ጣሊያንን ሲያሳድዱ የነበሩና በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. በሐመዶ ጦርነት ከክቡር ደጃዝማች ገብረመንድኅን ባይራዑ ጋር ሆነው በታሪካዊ ጀግንነት ጣሊያንን የወጕ ደፋር ሰው ናቸው። በዚሁም በሐመዶ ጦርነት ከክቡር ደጃዝማች ገብረ መድኅን ባይራዑ ጋር ሆነው በታሪካዊ ጀግንነት ጣሊያንን የወጕ ደፋር ሰው ናቸው። በዚሁም የሐመዶ ጦርነት ፊታውራሪ ካሣ ለኢትዮጵያ ሀገራቸው ሕይወታቸውን ስለገበሩላት ይህ ቦታ ሐመዶ መባሉ ቀርቶ ፊታውራሪ ካሣ ቢባል መልካም ነበር።” ገጽ 216

ወደ ሥር ነገራችን አንመለስ፤ በዚሁም የሚያስቸኩል የግስገሳ ዘመቻ ሰው በመንገድና በረኃብም ተጎዳ። በዚሁም በላያ ፯ የዳጉሳ ቂጣ በአንድ ብር ገዛን። ወጣቱ ፊታውራሪ ተፈራ ዘለቀ ሊቁ የግርማዊነታቸው ጐሮሮ በመቻሉ አመሰገንነው፤ ጦርነት በተነሳ ቁጥር ሀገር መራቡ የነበረም ቢሆን ጸገዴና አርማጭሆ፣ በለያም የጠላት ሠራዊት ሳይረግጠው ረኃብ በመራቡ ገረመኝ። በብዙ ድካምና ችግር በለያ እንደገባን ተስፋና ወሰን የሌለው ደስታ ተመገብን፤ የእንግሊዝም አረዮፕላን ከካርቱም ተነስቶ መሣሪያና ፓስታም ይዞልን እየመጣ በበለያ ዱር ውስጥ እያራገፉ ሲሔድ የጠላት አረዩፕላን ምንም ሳያየው በመቅረቱ ከአደጋ አምላክ ጠበቀን። ” ገጽ 216

“ወዲያው ግራዝማች ያረጋልና ፊታውራሪ ሊበን ቢሰውር ፯፻ ጀሌ ሰው ይዘው ከበጌ ምድር ሲደርሱልን፣ ልጅ ወሰን ኃይሉ ከበደ የሰቆጣ ጀግኖች ሰዎች እነ ፊታውራሪ ኃይሉ ክብረትን እንደያዘ መንገድ ጠፍቶት በመተማ ገዳሪፍ ሲወርድ፣ ከበለያ እንደተነሳን መተከል ከመድረሳችን የወሎው አልቡኮ ደጃዝማች መንገሻ አቡዬ መጥተው ለመገናኘት ቻሉ። መንገዳችንን ቀጠልንና አንጀባራ አካባቤ እንደደረስን ደጃዝማች መንገሻ ጀምበሬ ሰዎችውን አሠልፈው ተቀበሉን። ከዚያም በግስገሳ ቡሬ እንደገባን ደጃዝማች ነጋሽ ከበደ ከቡሬ ዳሞት አርበኞች ጋር ተሰልፈው ሠልፋቸውን አሳዩ፤ ወደፊት በማለፋቸው ግን አጕረመረሙ፤ በተምጫም ጦርነት ቀን በኤርትራዊው ሱልጣን ገብረመድኅን ዘአከለ ጕዛይ በወንድነትና በጀግንነት ተዋግቶ ፯ቱ በጦሎኒ በድል ባይመልሳቸው ኑሮ ትልቅ አደጋ የተደገሰልን ሰዎች ነበርን።” ገጽ 216

“በዚሁ ብርቱ ደፋር ጦረኝነቱ አቶ ሱልጣን ገብረ መድኅን አጣምሮ በ፫ት ምትሪየስ ተዋግቶ ድል ባይመታ አልቀን ነበር፤ ስለዚህ የሌተና ኮሎኔል ማዕርግ ይገባዋል ብሎ የእንግሊዝ ጦር ኣዛዥ ሻለቃ ስለመሰከረለት ዕለቱን የሻለቅነት ማዕርግ ተቀበለ። የጣሊያንን ጦር አዛዥ ራሱ ገድሎ በደረቱ ላይ የነበረውን ፱ን የጀግንነቱን መዳይ(ሜዳሊያ) ገፎ በግርማዊ ፊት አቅርቦ ሲያበረክት ሰው ሁሉ እጅግ ተደሰተ፤ አመሰገነም።” ገጽ 216

የዚሁን “መሳይና ወሰን የሌለው የእግዚአብሄር ቸርነት ጀግናው የኢትዮጵያ ቆራጥ ወታደር ለዘመቻ መነሳት” የሚል ርእስ ያለውን የ44ተኛውን ምዕራፍ ቀጣይ ክፍል በቀጣይ እንኮመኩማለን።

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ ቅንነትን የተላበሰ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 20 Nov 2020, 02:55

አያት አርበኛው ተስፋሚካኤል ትኩእ :mrgreen: የጊዜያቸውን የቦለቲካ ሁናቴ እንዲሁም ለሃገርና ለሰንደቅ ዓላማ ክብር የተሰው የአርበኛ ልጆችን መንግሥት የመንከባከብንና የመኮትኮት ኃላፊነት እንዳለበት በድፍረት በአጤ ኃይለሥላሴ የገለጡበትን የ44ኛውን ምዕራፍ የመጨረሻ ክፍል ትረካቸውን እስቲ እንኮምኩም። :mrgreen:

“በእግዚአብሄር ሰፊ ቸርነት ከዚሁም አደጋ ብንድን የእንግሊዝ አረዮፕላን በገበያና ጃንሆይም ባሉበት ቦታ ላይ ቦምብ ተኮሰብን “ነጂው ተሳስቶ ነውና አሥረነዋል” ሲሉ እንግሊዞች ምክንያት ፈልገው ነገሩን አለባበሱት። ” ገጽ 216

“እንግሊዞችም ምንም እንኳ ቅን ሥራ ቢሠሩም በኢትዮጵያውያኖች ዘንድ እምነት ሊኖራቸው አይችልም፤ ለማጥፊያ በተንኮልና በክፋት ሠሩት ከመባልም ሊድኑ አይችሉም፤ ስለምን? ጣሊያንና ቱርክን፣ ደርቡሽን በየጊዜው እያባበሉ በስጦታና በማባበል በስብከትም እያታለሉ ከኢትዮጵያ ንጕሠ ነገሥት ከአጼ ዮሐንስ ጋር ማዋጋታቸውን ስለሚያውቁ ነው። በዚሁ የተምጫ ጦርነት የደጃዝማች ነሲቡ ሰዎች እነ ግራዝማች ደበላ ከነ ልጃቸው ሲሞቱ፣ በጣሊያን የእጅ ቦምብ ያልቆሰለ ሰው አልነበረም።” ገጽ 217

“ከቡሬ ዳሞት (የዕዳ ሞት) ተነስተን በጥንታዊ የጐጃም ከተማ በደንበጫ አድርገን መንቆረር የዛሬው (ደብረ ማርቆስ) ግርማዊነታቸውን ዙሪያ ከበን በደስታ ገባን። በ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. የፋሲካ ዓመት በዓል በዚሁ መንቆረር ፈሰክን፤ ብዙ የጠላት ወታደሮች አገኘንና በወታደር ደምብ ልንቀበላቸው አስፈላጊዎቻችን ስለነበሩ ተቀበልናቸው። የቀሩት የጠላት አሽከሮች ግን ሐሰተኛ በሆነው የጣሊያን ስብከት ታውረው ሀገራቸውን ለመውጋት ፊት ፊታችን እየሸሹ ስላሴ ደረሱና የባሰውን ስሕተት ለመጨመር ወደ አዋቂው ወደ ጄኔራል ናዚ ጎንደር ለመሔድ ፊታቸውን በማዞር ታጥፈው ደራ ተሻገሩ። ደብረ ማርቆስ እንደገባንና ከዚያ በፊት፣ ከዚያም በኋላ እኔ ለግርማዊ ጃንሆይ መንገድ መሪና ሰውም አቅራቢ ስለነበርሁ፣ ከሞኝነቴ ይሁን ወይም ከደግነቴ ለኢትዮጵያ መንግሥት በብዙ መድከማቸውን ለማውቅላቸው ሰዎች በግርማዊነታቸው ፊት እያቀረብሁ በማነጋገሬ ምክንያት የጽሕፈት ሚኒስቴር ዋና ዲረክቴር አቶ ወልደ ጊዮርጊስ ወደ ዮሐንስ ተመቀኙኝ።” ገጽ 217

“እቶ ተስፋ ሚካኣኤል ትኩእ የዋህ ናቸው፤ ለራሳቸው ጃንሆይን ደጅ መጥናት ትተው ለሰው ብቻ ደጅ ያስጠናሉ” እያሉ ለፊታውራሪ መብራህቱ ሎረንሶ ታእዛዝና ለልጅ አንዳርጌ መሣይ፣ ላቶ ተፈራ ወርቅ ለባለቤቱም ሳይቀር ለመቀበሬ ብለው በሰፊው ማስጠናታቸውን ጀመሩ፤ እንዳሰቡትም እኔን ብቻ ሳይሆን ብዙ የኢትዮጵያ ወጣቶችንም ቀበሩን። አገልግሎታችንና ማዕርጋችንንም በመሰረዝ አስቀሩት። ይህነኑም ወሰን የሌው የ”ሐማ” (ሐማ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመጽሐፈ አስቴር እንደሚነበበው አይሁድን ለማስጨረስ ከፍተኛ ተንኮል የሸረበ፣ እንዲገደሉም ደብዳቤ የሰደደ የንጉሥ አርጤክስስ ባለሙዋል ነበር።) ጭካኔና ፈርዖናዊ መቃወም ያሳሰባቸው ምክንያት ለዚህ መንግሥት ከልብ ያገለገሉ ደጃዝማች አላምረውና ፊታውራሪ ኃይሉ እምሩ፣ ፊታውራሪ ደስታና ግራዝማች ኃይለ ጓንጕል፣ አቶ ፀጋዬ ባይኖሳን በሰፌው ከግርማዊነታቸው ፊት አቅርቤ በማነጋገሬ፣ ከአዋቂው ከራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ በላይነህ ጋር ዘመቻ ዘምተው በጦር ሜዳ የጀግንነት ሥራ ሠርተው ለሞቱት ኣዛዥ ስመኝና ግራዝማች መሸሻ ሐረገ ወይን፣ ሻምበል ታደስ አጎሹና ደፋሩ ጋይንቴ አቶ አስማማው ወልዴ ፪ት መትሪየስ ማርኮ ፫ኛ እጅ አደርጋለሁ ሲል የሞተ፣ ደጃዝማች ስብሃቱና ቀኛዝማች ግዛው ካሣ፣ ፊታውራሪ ዳምጠው ተሰማና ቀኛዝማች አስፋው ተሰማ፣ ፊታውራሪ ተሰማ ገብረ ሕይወትና ቀኛዝማች ናደው በጣሊያን አካፋ ተቀጥቕጠው የተገደሉ፣ ፊታውራሪ ደስታ ተበጀ የዳንግላን ምሽግ ሲያፈርሱ የሞቱ መሆናቸውንና ልጆቻቸው ከያሉበት ተፈልገው ግርማዊነታዎ ውለታቸውን ልጆቻቸውን አሳድጎ ዋጋቸውን መክፈል ይገባዋል ብዬ ሞያቸውን የሚዘረዝር ሰፊ ራፖር ለኢትዮጵያ ንጕሠ ነገሥት በማቅረቤና ጃን ሆይም “ይህ የጻፍክልኝ ደብዳቤ እጅግ መልካም ነው፤ እድሜ ይስጥህ፤ ለወደፊቱም እንደዚህ ለሀገራቸው ደማቸውን ያፈሰሱ ሰዎች እንድትጽፍልኝ አደራህን” እያሉ ሲያመሰግኑኝና የማዕርግም ስለተሰጠኝ፣ ለደብረ ማርቆስ ከተማ ሹምና ጕድሩ ተሻግሬም የጠላትን ምሽግ እንዳስለቅቅ ጃንሆይ ራሳቸው ቢመርጡኝ “አቶ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ ከፍ ያለ ሥራ አዲስ አበባ የሚይዙልን ስለሆኑ አይሆንም” ብለው ያስቀሩኝ አቶ ወልደ ጊዮርጊስ ናቸው።” ገጽ 218

“በአርእስቱም “መሳይና ወሰን የሌለው የእግዚአብሔር ቸርነት፣ ጀግናው የኢትዮጵያ ቆራጥ ወታደር ለዘመቻ መነሳት” የተባለበት ምክንያት ያለ አንዳች ስንቅ ዘመቻ ዘምቶ በእምነቱ ፀንቶና ተመክቶ፣ ወደረኛ የሌለው ሕዝብ ኢትዮጵያ በመውለድም ክብርና ከፍ ያለ ታሪክ ተጐናጥፋለች። በወዳጆችዋ ብቻ ሳይሆን በተላቶችዋም ጽሁፍ ኢትዮጵያ ተመስግናለች፤ ትመሰገናለችም።” ገጽ 218

ቀጣዩ የምዕራፍ አርባ አምስት ክፍል “ከደብረ ማርቆስ በሰላሌ የጃንሆይ አዲስ አበባ መግባት፣ ሰዎች እርስ በእርሳቸው ሹመት መሹዋሹዋም ጀመሩ፤ ከየእንግሊዝ ርዳታ ይልቅ የጣሊያን ወረራ የተመሰገነ ነው” የሚል ርእስ ያለውን ትረካ እንቀጥላለን።

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ ቅንነትን የተላበሰ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 05 Dec 2020, 05:31

ኣያት አርበኛው ተስፋሚካኤል ትኩእ ፋሺስት ጣሊያንን በደብረማርቆስ ለማጽዳት፡ የኢጦብያ መከላከያ ሠራዊት እና እነ ኣዪዋ መቐለንና ትግራይን ሹሩባ እየሰሯት እንዳሉ ሁሉ፡ ኣያት አርበኛው ተስፋሚካኤል ትኩእ እና መሰል ኣያት አርበኞችም በዚያ ዘመን ደብረማርቆስን ሽሩባና ቁንዳላ እንደሰሯትና ምን እንዳጋጠማቸውም ይተርኩልናል። በበሳሉ ፖለቲካዊ ትንተናቸውም ምክንያት ከራስ አበበ ጋር የተነጋገሩበትን ጕዳይም እንደወረደ አቅርበውልናን። መልካም ንባብ። :mrgreen:

ደብረ ማርቆስ እንደገባን እኔና የፖለቲካ ክፍል የሻለቃ ቻፕማን አንድሩስ ሆነን ኢጣሊያኖቹን በማዳን እንድንሰበስብ በጃንሆይ ስለታዘዝን፣ ከዕለታት አንድ ቀን ፩ድ የጣሊያን ማርሻሎ ከሀገሬው ሰዎች ጋራ ተመሳጥሮ ከጨሞጋ በታች አልያዝም ብሎ ብመንደር ውስጥ ገብቶ ተሸሽጐ አስቸገረን። ለሸሸጕትም ስዎች “እንዴት ከሀገራችን ነፃነት አንዱን ጣሊያን አብልጣችሁ ትወዳላችሁ። እኔም የጐጃም ጕምሩክ ዲረክተር መሆኔን እያወቅችሁ ባሶ ወረዳ በሀገራችን የጠላት ሰው የለነም ትላላችሁ” ብዬ ባባብላቸው አንሰማም አሉኝና ካንዱ ቤት ወዳንዱ ቤት ስወናጨፍ አንድ ሰው ካንድ ቤት ወጥቶ ሲሸሽ አየሁና ስገባ ማረሻሎን አገኘሁትና በክፋቱ ብዛት ስላናደደኝ ጠላት በሽጕጥ ለመግደል ደገንሁበት። በዚህ ጊዜ እንግሊዛዊው የሻለቃ ቻፕማን አንድሩስ ወገኑ የሆነው ጣሊያን እንዳይሞትበት ተንገበግቦ “ሕይወቱን እንዳታጠፋው አደራህን” ሲል በስሜ ተጣራ።” ገጽ 219

“ለማምለጥ በመሸሸግ የተጣጣረውን የጣሊያን ማርሻሎና እነዚያን የሸሸጉትን ፪ት ሰዎች ወደ እሥር ቤት ሌሊቱን አስተላለፍሁዋቸው፤ እነዚያ ሁለት ሰዎች ከቤተ ክህነት ወገን ስለነበሩ በ፫ኛቀን በዕጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ አማላጅነት ጃንሆይ ፊት ቀረቡና እኔን ግርማዊነታቸው ጠየቁ። እነዚህ ሰዎች የተደጋገመ ጥፋት ማጥፋታቸውን ከገለጥሁ በኋላ ምሕረት እንዲደረግላቸው ራሴ ለመንሁላቸውና ለጊዜው ወደ እሥርቤት ተመልሰው ገቡ።” ገጽ 219

“የዛሬው ደጃዝማች አቶ በላይ ዘለቀ አሠላለፉና ትጥቁ፣ የጠበንጃውና የምትረየሱ፣ የአንግት ዝናሩ ያማረ፣ ቁጥር የሌለው ደረቅ ጦር አምጥቶ ደብረ ማርቆስ በሠራዊቱ ስላለበሳት እንግሊዞች ዓይናቸው ደም ሞላና የተገኘው የጣሊያን መሣሪያ በስውር ሲያቃጥሉትና ሲቀብሩትም ታዩ። ልጅ አንዳርጌ መሣይን ይዘው ሔደው ሞጣ ተቆልሎ የነበረው ከ፲፭ ሚሊዮን የበለጠ የጥይት ቁልል ለኢትዮጵያ ጀግና፣ በዱላ ለሚዋጋ ሕዝብ እንዳያገለግል ብለው እንግሊዞች ቤንዝን እያርከፈከፉ በእሳት አቃጠሉት። ይህ በየሣጥኑ የተከመረው የጠላታችን የጣሊያን ጥይት ሌት ተቀን ያለ ማቋረጥ ለብዙቀን ተቃጠለ፤ በመቃጠሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ አጕረመረመ። እንግሊዞችን ጠላ፤ ንጕሡን አማ። ወጣቶቹም የእንግሊዝን ጨካኝ ሥራ በመመልከት በግፍ ከተቃጠለው ከያይነቱ ጥይት ጋር ልባቸው በኅዘን አብሮ ተቃጠለ።” ገጽ 220

ከደብረ ማርቆስ በስላሌ የጃንሆይ አዲስ አበባ መግባት፦ ከደብረ ማርቆስ ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖትን ፊት ፊታችን አስቀድመን ተነስተን ዓባይን ተሻግረን ስላሌ ገባን፤ ውለን ካደርን በኋላ በሚያዝያ ፳፮ ቀን እኔና አቶ ዮፍታሔ ንጕሤ፣ አቶ ለማ በላይነህ ወደ ፊት ቀድመን በካሚዮን እንድንሔድ ታዘን ስንሔድ ሱሉልታ ሜዳ ላይ ገና ጡዋት ከራስ አበበ ከዱሮው ባላምባራስ አበበ ጋራ ተገናኝተና በብዙ መናፈቅ ተቀበሉን። አትሔዱም ብለዉም ባንድ ሆቴል አግብተው ቁርስና ቡናም ጋበዙን። በዚሁም የግብዣ ሰዓት ደጃዝማች ዘውዱ አባ ኮራና ልጅ ሠብስቤ ሽብሩ አብረዋቸው ነበሩ። በዚሁም የደስታ ጨዋታችን መሐከል ራስ አበበ ለኔ እንደዚህ ብለው አሉኝ።” ገጽ 220

“ ‘ አቶ ተስፋ ሚካኤል እርዎ ራስዎ ከዚህ ቀደም “ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር በብዙ ትሰናዳለች፤ እኛ ግን አንድ ነገር ሣንሠራ ተቀምጠናል፤ መጠግያ የለንም።” ብለው አላሉኝም ወይ’? “አዎ በማስጠንቀቅ ነግሬዎች ነበር፤ ብነግረዎት ዋሸሁ ወይ?”፤ “አልዋሹም” ታዲያስ “እርስዎ ጠንቋይ ነዎች” ሲሉ መለሱልኝ።” ገጽ 220

“ይህ እውቀት ከጥንቆላ አይደለም የሚገኘው፤ እኔም ጥንቆላ ኣላውቅም፤ ጣሊያን ይመጣል፤ ኢትዮጵያንም ይወራል፤ መጠግያ የለንም ማለቴ መሰናዳቱን በመመልከቴና የፖለቲካውን አካሔድ በማጥናቴ ምክንያት ነው። የጋራ ጠላታችንን መምጣት አስቀድሜ ባስጠነቅቀዎት ወደ ሌላ ሊተረጐምብኝ አይቻልም” ስላቸው ባላምባራስ የዛሬው ራስ አበበ ከቁጣቸው በረዱና “ይህ ሁሉ እውነትዎ ነው፤ የጣሊያን መምጣት አስቀድመው እንደነገሩን ቃልዎ ሆኖ መምጣቱንና መጠግያ ማጣታችንን ሳስበው ስላስደነቀኝ” ነው እንጂ እርስዎን በጥንቆላ ጠርጥሬዎች አይደለም” አሉኝ።” ገጽ 220

“ከዚህ በኋላ “ግርማዊ ጃንሆይ ርግጥ መጥተዋል ወይ?” “ኣዎ” ስላቸው “ሁልጊዜ ይመጣሉ፤ ይመጣሉ ትሉናላችሁ፤ ሲመጡ ግን ምንም ኣላየነም” እያሉ በሚያሳዝን ቃል መልስ ከሰጡኝ በኋላ እኔም “ዛሬስ ጃንሆይ ይቀራሉ ብለው አይጠራጠሩ። ይልቁንስ ሠራዊትዎን ሰብስበው በደንብ አሠልፈው ነገ ጡዋት ይቀበሉዋቸው” ብዬ በማጥናናት ምክር መከርሁዋቸው። ይህን ሁሉ ስንከራከር ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ሰዎች የሁለታችንን ከፍ ያለ ክርክር ተራ አልሰጣቸውምና ተሰነባበትን። እኛም እንጦጦ ማርያም አጠገብ ባለው የጠላት ምሽግ ውስጥ በተሠሩት ቤቶች ሠፈር ሠፍረን አደርንና ጡዋት ገና ሌሊት ተነስተን በሩን ስንጠብቅ ጃንሆይ የራስ አበበን አርበኛ ጦር ሰልፍ በየመንገዱ ዓይተው መጡ።” ገጽ 221

የዚሁን “ከደብረ ማርቆስ በሰላሌ የጃንሆይ አዲስ አበባ መግባት፣ ሰዎች እርስ በእርሳቸው ሹመት መሹዋሹዋም ጀመሩ፤ ከየእንግሊዝ ርዳታ ይልቅ የጣሊያን ወረራ የተመሰገነ ነው” የሚል የምዕራፍ አርባ አምስት ቀጣይ ክፍል በቀጣዩ ትረካችን እንኮመኩማለን!

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ ቅንነትን የተላበሰ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 14 Dec 2020, 04:16

አያት አርበኛው ተስፋሚካኤል ትኩእ የያኔውን ገድል በቅጡ እየተረኩ፡ የጦቢያው ንጉሠነገሥ ከስደት ወደ አዲስ አበባ በድል የገቡበትን ሁኔታ ያስቃኙናል። እግረመንገዳቸውንም የእንግሊዝ መንግሥትን መሰሪ አቋም ገለጥለጥ አድርገው እንደ ዘመዴ “ነጭነጯን” ያንስኮመኩሙናል! መልካም ንባብ! :mrgreen:

“በሚያዝያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ንጕሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴንና ነፃነትን ይዘን አዲስ አበባ በመግባታችን ለጊዜው በብዙ ተደሰትን፤ ችግርና መከረ፣ ረኃብና ስቃይ መሰቃየታችንንም ሁሉ ረሳነው። ሰዎቹም እርስበርሳቸው ሹመት መሹዋሹዋም ጀመሩ፤ ይህን ሹመትና ርስት፣ ቤትና ንብረት ለኔ፣ ይህን ሹመትና ደመወዝ፣ ቤትና ርስት ላንተ፣ ተሰጥቶዋል እየተባባሉ እርስበርሳቸው ብቻ ወገን ለይተው እንዲጠቃቀሙ ገና በጐጃም መሬት ሳለን ጀምረው ማላ መማማላቸውን ቢገልጹልንም፣ ይህ ከፍ ያለውን ታሪክና ወንድነት ፈጽሞ የሚያጠፋ ነገር በመሆኑ፣ በትክክል እስክረዳው ድረስ በወሬ አልሰማም ብዬ በብዙ ተከራከርሁ።” ገጽ 221

“አላምንም ብዬ መልስ በመስጠቴም “አንተኮ ቶማስ ነህ፤ የሰውን ነገር ምንም አታምንም፤ ለራስህ ደጅ ከመጥናትም ሰውን ደጅ ማስጠናትን ታፈቅራለህ፤ እነሱ ግን እርስበእርሳቸው ሹመት መሹዋሹዋማቸው ይቅርና እንዳይከሰሱና እንዳይወቀሱ “ካርታ ቢያንካ” (ደረቅ ማህተም ወይም ሙሉ ፈቃድን የሚያስገኝ ይሁንታ ወይም የእርስ በእርስ ውልና ስምምነት) ተሰጣጥተዋል” ሲሉ ቢያስጠነቅቁኝም፣ ራሴ በዓይኖቼ ካላየሁና በጆሮቼ ካልሰማሁ በሰው ቃል አላምንም ብዬ ነገሩን ለማጣራት በብዙ ደከምሁ።” ገጽ 221

“የዱሮ አበሳችን ይቅርና በዚህ ፭ት ዓመት ጦርነትና አርበኝነት፣ መራራውን ስደት መሰደድ፣ ጭንቅና ስቃይ መሰቃየትን መከራ ተቀበልን። “አምላኬ ሆይ በነፃነት ሀገሬን መልሰህ ካገባኸኝ ሹመት አልሻም፣ አርሼ እበላለሁ፣ እመነኩሳለሁ፤ አንዳንዶቹም በሐዲሱ የዓለም መንግሥታት ሕግ በትክክል እንሠራለን፤ ሥዕለታችንን ለተሣልነው ታቦት እናበረክታለን፤ ሲሉ የነበሩት ታላላቆች ሰዎች ዛሬ እርስ በእርሳቸው ወገን ለይተው ተሹዋሹመዋል ብትሉኝ አላምንም” ብዬ መለስሁ።” ገጽ 221

“እኔን አጥብቆ ያከራከረኝና አላምንም ለማለት ያስደፈረኝ ፊታውራሪ መብራህቱ ሎረንሶ “በሐዲስ ደንብ እንሠራለንና የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከካርቱም ወደ ሎንዶን አይመለሱም። የኢትዮጵያ ሕዝብም ንጉሠ ነገሥቱን ካላየ በያዘው መሣሪያ ይዋጋል እንጂ ማንንም መንግሥት አይቀበልም” ብሎ እንግሊዞቹን አጥብቆ በማስፈራራት በማምጣቱና የእንግሊዞችም ባለሥልጣኖች ምን ጊዜም ቢሆን ኢትዮጵያን ለመያዝ የሚያደርጉት ወሰን የሌለው ተንኮልና ትግል ከነሱ የተሰወረ አለመሆኑን በማወቄ በብዙ ተከራከርሁ።” ገጽ 222

“ከእንግሊዝ ርዳታ ይልቅ የጣሊያን ወረራ የተመሰገነ ነው። የእንግሊዝ ቪቶሪያ ንግሥት መንግሥት ምክርና መሪነት ቅኝ ሀገር ይዞ ለመግዛት በ፲፰፻፸፰ ዓ.ም. ጣሊያንና አቅፎና ደግፎ ምጽዋዕ አስገባው፤ በኤርትራም እንዲስፋፋ አድርጎ እስከ ገዳሪፍ ድረስ አስያዘው። ካስያዘውም በኋላ የኢትዮጵያ መሬት የሆነውን ገዳሪፍንና ከሰላ እንግሊዝ ለራሱ ወስዶ ከሱዳን ጋር ቀላቀለው።” ገጽ 222

“ብዙ መሳፍንትና ልእልት ተዋበሽ ልእልት ምንትዋብ አዳል (ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት) የተዋጕበትና ሰማዕቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ስላገራቸውና ስለሃይማኖታቸው የተሰውበት ጋላባትና ሪስሪስ(ሮሴረስ)፣ ገዳሪፍና ከሰላ፣ ቃሮራ ወደ ሱዳን እንደተወሰደው ቀረ።” ገጽ 222

“ጣሊያን ኢትዮጵያን በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ሲወራት ስንቅ በያይነቱ ያስነቀውን በግና ላም፣ ግመልና አህያ፣ ቅቤና ስኳር፣ ቤንዝን ሳይቀር ከሱዳን ያቀበለውና ከዓለም መንግሥታት በፊት ጣሊያን የኢትዮጵያ ገዥ እንዲሆን የፈቀደለትና ያወቀለት፣ የሰበከለት ራሱ የእንግሊዝ መንግሥት የፖለቲካ ክፍል ነው።” ገጽ 222

“የጣሊያን መንግሥት ባላጋራነትና ወራሪነት ከ፲፰፻፸፰ እስከ ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ስለሆነ የ፶፭ ዓመት ባላጋራችን በመሆኑ የሱን ወረራና ጭካኔ፣ የሱን ክፉ ሥራና አገዳደል ምንጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘለዓለም ሊረሳው የማይችል ነው።” ገጽ 222

“ሩቅ ባልሆነ ጊዜ ጣሊያን በኢትዮጵያውያኖች እጅ ብድሩን ያለ ጥርጥር ይቀበላል። ጣሊያን ግን ሁልጊዜ ረዳቱና ጠቃሚው ለሆነው የእንግሊዝ መንግሥት ርዳታና ውለታ ትቶ እንደልማዱ በክዳት ወደ ሐዲሱ ጌታው ወደ ጀርመን መንግሥት ወደ ሂትለር ዞረ፤ በዚሁም ክዳቱ የእንግሊዝ መንግሥት በሐዘን ተከበበ፤ የሚያደርገውም ጠፋው፤ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ ሕዝብ መለሰ። ደስ ለማሰኘትም ፈለገ፤ የኢትዮጵያ ረዳትና የቃል ኪዳን ጓደኛ ነኝ እያለም እስኪይዝ ድረስ ያለ ማቋረጥ በስብከት ሰበከ። ከኛ ጋራም ጐን ለጐን በጣሊያን ላይ ለጦርነት ተሠለፈ፤ የጣሊያን ሀብትና ንብረት፣ ፋብሪካና ባንኮች ይቅርና የኢትዮጵያ ሀብትና ንብረት ሳይቀር ሰብስቦ በመውሰዱ “ከእንግሊዝ ርዳታ ይልቅ የጣሊያን ወረራ የተመሰገነ ነው” የተባለበት ምክንያት ይህ ነው።” ገጽ 223

“እንግሊዞችም በረዳትነት የቃልኪዳን ጓደኞች ነን ብለው ከኛ ጋር ከካርቱም ኢትዮጵያ እንደገቡ የጣሊያንን እሥረኞች እየሰበሰቡ ወደ ካርቱምና ኬኒያ እየወሰዱ በትልቅ ጭቆናና ረኃብ የመንገድ ሥራ ከጀርመኖች ለይተው ሲያስቆፍሩዋቸው፣ ጌጣቸውን ሁሉ ገፈው ያለ ርህራሔ የጣሊያንን ሴቶች አሥረው በሙቀታሙ በርበራ ወደ ባህር እያስነዱ በኬኒያ ጃምቦች አስነወሩዋቸው። እነዚህ የሰው ሀገር ለመያዝና ለመግዛት ልምድና ስስነት ያላቸው የእንግሊዝ ፖለቲካ ሰዎች ከአዲስ አበባ አንወጣም ብለው ተከራከሩን። የዓለምም ጦርነት ባይስፋፋ እንግሊዞች ምንጊዜም ከኢትዮጵያ አይወጡም ነበር፤ ከወጡም በኃላ ለመመለስ ተመኙ። ዛሬም ስለሚመኙ ከኢትዮጵያ ወጣቶች የተሰወረ አይመስለኝም።” ገጽ 223

በቀጣዩ ምዕራድ አርባ ስድስት “የእንግሊዝ ቋንቋ የሚያውቁ ዕለቱን ተሾሙ፤ የጣሊያንን ሀብት በሚሊዮን ያበረከቱ ሰዎችም ተማሩ” በሚል ርእስ ስር የተካተተውን የአርበኛውን እይታ እንኮመኩማለን!

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ ቅንነትን የተላበሰ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 28 Dec 2020, 10:16

የታያቸውን እውነታ የለአንዳች ማድበስበስ መግለጥ የሚወዱት ኤርትራዊው አያት አርበኛ ተስፋሚካኤል ትኩእ፡ በዛሬው ትረካቸው ባጤዎች ላይ ተረማምደዋል። :mrgreen: አጤ ዮሐንስን ሲያሞካሹ አጤ ኃይለሥላሴንም ሆነ አጤ ምኒልክን ግን አልማሯቸውም! “የሸዋ ቤተ መንግሥት” እያሉ “በክህደት” ወንጀል ወቃቅሰዋቸዋል። አያይዘውም የትግሬው መስፍን ራስ ጕግሣ ወሌ አንቺም ላይ ከአልጋወራሽ ጋር ጦርነት እንደገጠሙ፡ ጦርነቱም በእግረኛና በአረዮፕላንም ቢሆን የትግሬው መስፍን ራስ ጕግሣ ወሌ በግንባር ገብተው ሲዋጉ በጥይት በረዶ ተበጣጥሰው መጋቢት ፳፫ ቀን፲፱፻፳፪ ዓ.ም. እንደሞቱም ተርከውልናል። ለማንኛውም መልካም ንባብ!

“የእንግሊዝ ቋንቋ የሚያውቁ ሰዎች ሁሉ ወደ እንግሊዛዊ ሥራ ለመሥራት ጠጋ እዳይሉ ተብሎ ከያሉበት ቦታ ተፈልገው ተስፋ ያላደረጉበትን ሹመት ከኢትዮጵያ መንግሥት በመቀበላቸው ተኣምራት ነው ተባለ። እንኳንስ ተመልካቾቹ የተቀባዎቹም ሳይቀሩ በብዙ ተደነቁ። ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት አገልግሎትና ሹመትም ፈጽሞ ያልነበራቸው ሰዎች ዛሬ በ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. በመብራት ተፈልገው በመሾማቸው ምክንያት “የእንግሊዝ ቋንቋ የሚያውቁ ዕለቱን ተሾሙ” ተባለ።” ገጽ 224

“የጣሊያንን ሀብት በሚሊዮን ያበረከቱ ሰዎችም ተማሩ፦ የጥንታዊ ጠላታችን የጣሊያን መንግሥት ቁጥር የሌለው ሀብትና ንብረት በብድር አምጥቶ በብዙ ሚሊያርድ በየ ጕድጓዱና በየዋሻው በኢትዮጵያ መሬት ጥሎት የሔደውን ገንዘብ በያይነቱ በሚሊዮን ያበረከቱና ወይም የተቀበረበትም ጕድጓድ ያሳዩ ሰዎች ሁሉ በመብረቃዊ ቅጽበት ከኃጢያተኛነታቸው ነፃ ወጥተው ሙሉ ምሕረት ተማሩ።” ገጽ 224

“እነዚህ የጣሊያን በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያበረከቱ ሰዎች ምሕረት ሲማሩ፣ የእንግሊዝንም ቋንቋ የሚያውቁ ተፈልገው እየቀረቡ ተስፋ ያላደረጉበትን ሹመትና ደመወዝ ሲቀበሉ፣ ከረጅም ዘመናት ጀምረው በሰላሙና በጦርነቱ፣ በአርበኝነቱና በስደቱ፣ ከዚያም ወዲህ በእምነትና በባለዋጋ አገልግሎት ለኢትዮጵያ ንጕሠ ነገሥት መንግሥት ያገለግሉና ያገለገልን ሰዎች ሁሉ ተረስተንና ተሰርዘን የቀረንበት ምክንያት ሰው ሲባል ያለ “ነገ ሳልስት ማግስት በቀር” ሌላ መልስ ስላልተገኘ ለጃንሆይ ብዙ ሰዎች “አርሰን ወይም ነግደን እንኖራለንና ያሰናብቱን” ያሉትም ሰዎች “እርሻ ለማረስና ንግድም ለመነገድ የምትችሉ እኛ ስንፈቅድላችሁ ነው” ስለተባሉ፣ አንዳንዶቹም እለቱን ወደ ማረፍያ (እስር) ቤት ስለሔዱ ሰው ፈጽሞ ከድፍረትና ከወንድነት፣ ከብርታትም ተለይቶ ተከዘ። እፍረትና ውርደት ልብስ አድርጎ ተከናነበ። ችግርና ስቃይ መሰቃየትንም ተመገበ።” ገጽ 224

““ጥንታዊ የኢትዮጵያ ንጉሣዊ መንግሥት ፖለቲካ ርምጃ ጥልቀኛ ሆኖ ሳይመሠረት፣ በተቀበለው ቀብድና በሰጠው ቃል ሳይረጋ፣ በጠላቶቹ ዙሪያውን መከበቡን ረሳው። አልፎም በችግሩ ቀን ሊደርሱለት የማይችሉትን መንግሥታት ወዳጆች በማድረጉም ተሳሳተ፤ ፖለቲካውን ለማረም ሳይችል ስለቀረም ፫ቱ ጓደኞቹ መክረው አስመክረው ተነሱበት። ጣሊያንም የኢትዮጵያ መንግሥት ፲፱፻፳፯ ዓ.ም. በፊት ጀምሮ ሕዝብን በመጥፎ አገዛዝ ይገዛል” እንኳንስ ለከብት ለሰው ሐኪምና ፀጥታ፣ ነፃነትም የለዉም፤ በባርነት ይሸጣል፤ ይለወጣል እያለ በመጻሕፍት ሲሰድብና ሲሰብክ በቂ መልስ ለመስጠት ሳይችል ስለቀረ፣ ጣሊያንም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እንዳልተስማሙ ስለተረዳ ለመኳንንቱና ለካህናቱ በጁ ገባባቸው። ሴቶቹም ሳይቀሩ ተገዙ፤ ሀገራቸውንና ክብራቸውን ሸጡ። ባንዳንድ ቂምና በቀል ምክንያት ከመግዛት መገዛትን አፈቀሩ። ከዘራቸውም የወረሱትን ገንዘብ ማውረስ መስሎዋቸው የኢትዮጵያና የሸዋ መንግሥት፣ መሳፍንትና ሚኒስትሮች፣ መኳንንቶች፣ ፕረሲደንቱም ሳይቀሩ ላንዳንዱ ሰው ካንድ ሚሊዮን ብር እስከ ፶ ሺህ ብር ከጠላት መቀበላቸውን መሰከሩ። የጣሊያንም መንግሥት እነዚህ በሰጡት ተስፋና ምልክት በወንዶቹና በባለታሪኮቹ ሀገር መግባት ቻለ። ሀውልቱንም ወሰደ፤ በእግዚአብሔር ቸርነት የኢትዮጵያን ነፃነት ቢመለስ በሰዎቹ ኃይልና በንጕሡ እውቀትና ብርታት ብቻ የተመለሰ አድርገው ቆጠሩት። ይህም የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ንጕሠ ነገሥት መንግሥት መሆኑ ቀርቶ የሸዋ ቤተ መንግሥት ብቻ መሆኑ በብዙ ጽሑፎቹ ራሱ ለራሱ መሰከረ። የጥንቱ ኢትዮጵያውያንም እነማን እንደነበሩ ረሳቸው።” ገጽ 225

“ይህም ሁሉ ለማድረግ ያደፋፈረው የኢትዮጵያ ንጕሠ ነገሥት ጀግናው፣ ሰማዕቱ ግርማዊ አጼ ዮሐንስ ለኢትዮጵያ ልማትና ስፋት ብለው በጐንዳጕንዲና በጕራዕ ከቱርክ መንግሥት፣ በሰሐጢ ከጣሊያን መንግሥት ጋር ጦርነት ሲዋጕ ሳሉ፣ የሸዋ ንጕሥ ምኒልክ አስቀድመው ከቱርክ መንግሥት ጋር በክህደት የተዋዋሉትን ታሪካዊ መሳይ የሌለው ክደታቸው ቱርክ ድል ሆኖ ሲደመሰስ ከጣሊያን ጋር የቃል ኪዳን የጦር ጓደኝነት ውል የተዋዋለው የኢትዮጵያ ዘውድ ስለነጠቁ ነው። በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ መሬት ያልነበረውን ክዳትና ከሀዲነት፣ ገንዘብ መብላትም ተዘወተረ፤ መንግሥትና ሕዝብም ስምምነት አጥቶ በመለያየቱ ሀገሩን ለገንዘብ የሸጠ ደላላ ተባለ። በዚሁም መሠረት መንገዱን ስላቀጠነው ራሱን ጐድቶ ኢትዮጵያንም ለሁል ጊዜ ጐዳትና ታሪክዋንም አበላሸው።” ገጽ 225

“ዓይነተኛች ጭዎችና(ጭዋዎች) የጥንት ገዥዎች የትግሬና የጎንደር ቤተ መንግሥት ሰዎች፣ መሳፍንቶችና መኳንንቶች፣ ሕዝብም ከቁጥርና ከሥልጣን፣ ከሹመትም ስለምን ውጭ ሆኜ እቀራለሁ ብሎ ሳይል በእምነትና በትልቅ ርጋታ አንገቱን ደፍቶ እያዘነ ሲያገለግል የሐዲሱ የሸዋ ቤተ መንግሥት ሚኒስትሮችና ባለሥልጣኖች ወይዘራዝሮችም አስቀድመው ሀገራቸውንና ንጕሠ ነገሥታቸውን በመክዳት ጠላታቸውን ወዳድ አድርገው በጦርነት እንዳይወጕት ገንዘብ ተቀብለው የተስማሙት በምን ምክንያት ነው ብዬ ብጠይቅ፣ “የዛሬው ንጕሠ ነገሥት ገና በአልጋ ወራሽነታቸው ዘመን ቀን ወጥቶልኝ የኢትዮጵያን ንጉሠ ነገሥት የሆንኩ ጊዜ ራስ ብዬ ሹሜ ያባትህን፣ የአያትህን ሀገር አስገዛህ አለሁ እያሉ ከ፻ ሺህ እስከ ፫፻ ሺህ ብር ብድር ድረስ ካንዳንድ ኢትዮጵያዊ ባለጸጋ ተቀብለው በነገሡ ጊዜ እንደቃላቸው ሳይፈጽሙላቸው ስለቀሩና ስለተረሱም ነው የከዱ። አንዳንዶቹም ያባታቸውን ሀገር ማግኘታቸው ይቅርና ከያዙትም ሀገር ተሽረው መግብያ ስላጡና ስለተናቁም ነው”።” ገጽ 226

“አንዳንዶቹም የራሳቸውን አሽከሮች ከመሬት አንስተው ተስፋ ያላደረጉበትን ማዕርግ ሰጥተው ቢያነሱዋቸውም እንደ ይሁዳ ከሐዲዎች ሆነው ሀገራቸውንና ጌታቸውን ለጠላት በገንዘብ መሸጣቸው ትልቅ ኃጢያት መሆኑን ያላጤኑ፣ ንዋይን ያፈቀሩ እብዶችና ከሀዲዎች ናቸው”።” ገጽ 226

““ከሁሉም የበለጠ ንግሥት ዘውዲቱ ከጥንት ባላቸው ከትግሬው መስፍን ከራስ ጉግሣ ወሌ ብጡል ጋር ለመታረቅ በስውር አልጋ ወራሽን ለማስወጣት ተስማምተው ነበር።” ይህም ስምምነት ሳይፈጸም በመሐከሉ የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ ጦር ላኩና አንቺም ላይ ከራስ ጕግሣ ወሌ ጋር ጦርነት ገጠሙ። ጦርነቱም በእግረኛና በአረዮፕላንም ቢሆን የትግሬው መስፍን ራስ ጕግሣ ወሌ በግንባር አብተው ሲዋጉ በጥይት በረዶ ተበጣጥሰው መጋቢት ፳፫ ቀን፲፱፻፳፪ ዓ.ም. ሞቱ።” ገጽ 226

“ከሁሉም የባሰና የመረረ ክህደትና ክዳት ማለት ሀገርን ከመሸጥ የበለጠ ኃጢያትና ጥፋት እንደሌለ ሲያውቁ አጼ ምኒልክ ኤርትራንና ሶማሊያን ለጣሊያን፣ ጂቡቲን ለፈረንሣይ፣ በርበራና ቦሮና፣ ጋምቤላን ለእንግሊዝ በመሸጣቸው መኳንንቱና ሕዝቡም እንደጌታው መሸጥና መለወጥ፣ ደላላ መሆንም ስለተማረ ነው። በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ሚኒስሮችና መኳንንቶች፣ ወይዘራዝሮችና ሠራተኞች፣ ገነትዋን ሀገራቸውን ጠላታቸው ለሆነው ጣሊያን በገንዘብ ተታልለው የናታቸውን ዋጋ የተቀበሉት፣ እፍረትና ውርደት የለበሱ፣ እሥራትና ሞትም የተመገቡ፣ የይሁዳም ስም የተቀበሉ ሆኑ። ይህን ሚክድ ሰው ቢገኝ የሰዎቹንና የገንዘቡንም ዝርዝር ለልጽላችሁ እችላለሁ።” ገጽ 227

“ከዚህ በላይ የተጠቀሱትም ባለሥልጣኖች ከአጼ ምኒልክ በወረሱት ምንቀኝነትና ተንኮል በወራዳው ሽብርና ፍራት ተሞልተው፣ በትልቅ ስንፍና ዙሪያቸውን ተከበው፣ ምንጊዜም የውጭ ጠላት ደፍሮዋት እማታውቀዋን ድንግልዋን ኢትዮጵያን አስደፈርዋት።” ገጽ 227

በቀጣዩ በምእራፍ አርባ ሰባት “የሐማ ጭካኔ፣ የኔ ወደ ደሴ መታዘዝና መጕላላት፣ ከስደትና ከአርበኝነትም ወደ የባሰው ፈተናና ችግር መግባት” የሚል ርእስ የሰጡትን ትረካቸውን እንኮመኩማለን።

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ ቅንነትን የተላበሰ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 01 Feb 2021, 10:50

አያት አርበኛው ተስፋሚካኤል ትኩእ በዛሬው ትረካቸው ከጠሐፌ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ጋር ሽዅቻ እንደነበራቸው አልደበቁንም። አቶ ወልደ ጊዮርጊስንም “ጋኔናዊ የምቀኝነትና የአድልዎም ሥራቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጭቆናና ባርነት አዝንሟል” ሲሉ አልጋወራሹንም በድፍረት “እንዲህማ ከሆነ . . . ምን ዋጋ አለው!” ያሏቸው መስለዋል! ለጦቢያ ከልባቸው የደከሙት ኤርትራዊው አያት አርበኛ መጨረሻ ላይ በጠሓፊ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ የተቀነባበረ ሴራ ምክንያት ያጋጠማቸውን ልባቸውን የሰበረ ኵነት ፍንትው አድርገው አሳይተውናል። የዚህን መጠሐፍ የመጨረሻ ክፍል በቀጣዩ ትረካ እናጣጥመዋለን። መልካም ንባብ! :mrgreen:

“የሐማን ጭካኔና መኖፖላዊ ኅሳብ ያደረባቸው አቶ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ እኔን ብቻ ሳይሆን መላውን ኢትዮጵያዊ የአርበኛና ስደተኛ፣ እንደተጫወቱበት እንደዚሁም የአገልግሎቴን ዋጋ እንዳልቀበል የጐጃምና የነቀምት ጠቅላይ ግዛት ዋና ዴረክተርነት እንዳይሰጠኝ በግፍ አስከለከሉኝ። ገና ከካርቱም ተነስተን አዲስ አበባ ስንገባ ጀምረው እኔን ለመጉዳት ስለተነሱ ከንጕሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ጋር እምጣላበትን ምክንያት በመፍጠር በየእለቱ ለግርማዊነታቸው እየነገሩ ወደ ደሴ ያለ አንዳች ደመወዝ በሥራ ስም ለአሥራት እንድታዘዝ ከንጕሥ አስወሰኑብኝ። ጃንሆይም በሻለቃ መርዕድ መንገሻ አስጠርተው “ስለምን ለሥራ ወደ ታዘዝህበት ደሴ አትሔድም” አሉኝ። እንደዚህም ማለታቸው “እምቢ ብለው አሉኝ አቶ ተስፋ ሚካኤል” ብለው እንደነገሩዋቸው ዓይነት አድርገው ጠየቁኝ።” ገጽ 228

“እኔም ደመወዜን አልተቀበልሁም፤ የታዘዘልኝም ስንቅ እጅግ አነስተኛ ነው። ለዚሁም ቢሆን ማዘዣው የደረሰኝ ገና ፪ት ቀኑ ነው። ልዑል አልጋ ወራሽም አያውቁኝም፤ እኔን አደራ ይበሉልኝ” ስላቸው፣ “እኛ እናውቅህ አለን፤ አልጋ ወራሽም ያውቅሀል፤ አደራ እንለዋለን፤ ስንቅ ይጨመርልሃል፤ ደመወዝህንም ትቀበላለህ” ብለው አቶ ጌታሁን ተሰማን አዘዙልኝ። አልጋ ወራሽ ጋርም ራሳቸው አገናኙን።” ገጽ 228

“ባለቤቴና ልጆቼ ከነ ፕሮፌሰር ታአምራት አማኑኤል ጋር ከካርቱም ስደት በአሥመራ መንገድ አዲስ አበባ በደረሱ ማግስት ለኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ መስከረም ፬ ቀን ፲፱፻፫፬ ዓ.ም. በቁጥር ፮፻፩ በተጻፈልኝ ደብዳቤ መሠረት ለሥራ ወሎ ታዘዝሁ። ለወሎም የታዘዝሁት ለንግድ ሚኒስቴር ኃላፊ ሹም ነበር፤ ነገር ግን የአቶ ወልደ ጊዮርጊስ “አቶ ተስፋ ሚካኤልን አርቃችሁ አባርሩልኝ የሚል” ደብዳቤ ቀድሞኝ ለነ ባላምባራስ ማህተመ ሥላሴ ስለደረሳቸው ከደሴ ከተማ ውጭ በባላገር ውስጥ ተወስኜ ያለ አንዳች ደመወዝ እንድቀመጥ ተመከረብኝ። “ከጃንሆይ የታዘዝልህ የንግድ ሚኒስቴርነት ሥራ ትላንትና ሰው ሹመንበት ነበርና ዛሬ ሽረን ለመስጠት ስለሸገረን የየጁን ዲረክተርነት ሰጥተነሀልና ወርደህ እንድትሠራ” ሲሉ አልጋ ወራሽ በነገሩዋቸው መንገድ ነገሩኝ።” ገጽ 228

“በዚህ ጊዜ ወሰን የሌለው ኅዘን ተሰማኝ። አዲስ አበባም እንዳልመለስ እምቢተኛ ነው ብለው እንዳይጽፉብኝ ስጋት ያዘኝ። ከንዴቴም ብዛት የተነሳ “ልዑል አልጋ ወራሽ ሆይ፤ ያን ያህል በጦርነቱና በስደቱ የደከምሁትን ባለ ዋጋ አገልግሎቴ ያንዱን የጣሊያን ባንዳ ያህል ዋጋ ከሌለው ለመንግሥት ማገልገል ትልቅ ኃጢያት መሆኑን የተረዳሁት ዛሬ ነው” ብዬ ስላቸው ተናደዱ፤ አዘኑ። እውነት ስለተናገርሁም ወደ ሌላ ተርጕመው እንደ አንድ የማይታዘዝ ሰው ቆጠሩኝ። እውነት ከሚናገር፣ ሌባና ሐሰተኛ ይወደዳል ይከበራልም።” ገጽ 229

“የኢትዮጵያ ን.ነ. መን. አልጋ ወራሽ መርች አዝማች አስፋ ወሰን ኃ.ሥ.፣ ይድረስ፣ ከደጃዝማች አበበ ዳምጠው (ቁጥር ፯፻፳፰)
አቶ ተስፋሚካኤል ትኩእ የየጁ አውራጃ ሀገረ ገዥ ዲረክተርነት ተሰጥቶታልና ሥራዉን ተረክቦ እንዲሠራ ይሁን። ጥቅምት ፳፮ ቀን ፲፱፻፴፬ ዓ.ም. ደሴ። ማህተም፣ የወሎና ያውራጃዎችዋ ሀገረ ገዥ።” ገጽ 229

ከስደትና ከአርበኝነት ወደ የባሰው ፈተናና ችግር መግባት ተብሎ በአርእስቱ እንደተመከተው በየጁ መከራ ገጠመኝ። ደጃዝማች አበበ ዳምጠውም የተገኘችዋን ገንዘብ ከባለ ሀገሩ ራሳቸውና አሽከሮቻቸውም እየተቀበሉ ሥራ በደንብ እንዳይሠራና ግምጃ ቤቶቹም እንዳይቋቋሙ ብዙ እንቅፋትና ችግርም እያዘነቡብኝ ፮ ወር ከሠራሁ በኋላ ወደ አዲስ አበባ እንድመለስ ችግሬን በዶክቶር ሉረንሶ ታእዛዝ በኩል ለግርማዊነታቸ አስታወቅሁና አዲስ አበባ እንድመለስ ተፈቀደልኝ እና ተመለስሁ።” ገጽ 229

ጃንሆይም ሁሉንም ነገር በአቶ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ እጅ መቆለፉን እያወቁ በንግድ ሚኒስቴር ክፍል እንድሠራ ነጋድራስ ገብረ እግዚአብሄርን አዘዙልኝና ሥራ መስራት ጀመርሁ። አቶ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ግን ሰውን በማስማማት ፈንታ የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስበእርሱ እያጣሉ በማፋጀት፣ በማናከስ፣ ማለያየትን አፍቅረው የኢትዮጵያን መንግሥት ሥልጣን በጽሕፈት ሚኒስቴር ብቻ እንዲሆን አስወስነው፣ የፈቀዱትን ሰው ለመጥቀምና የጠልቱንም ሰው ለመጕዳት ቻሉ። ንጕሠ ነገሥቱም ባልታወቀ ምክንያት ሥልጣናቸውን ላቶ ወልደ ጊዮርጊስ አስረከቡ። በቀላሉም የሕዝብ ፍቅር ራቃቸው።” ገጽ 229

“የኢትዮጵያ ንጕሠ ነገሥት መንግሥት፣ የንግድና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ (ቁጥር ፱፻፵፱ - ግንቦት ፳፩/፲፱፻፴፬ ዓ.ም.) ለግርማዊ ንጕሠ ነገሥት። አቶ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ ለየጁና ለአውራጃዋ ሀገረ ገዥ ዲረክቴር ሁነው ከመስከረም ፩ድ ቀን እስከ ጥር ፴ ቀን አምስት ወር የሠሩበትን በወር ፪፻፳፭ ሁለት መቶ ሐያ አምስት ብር) ሂሣብ ፩ሺ ፻፩፭ አንድ ሺህ አንድ መቶ ሐያ አምስት ብር፣ ሁለተኛ በንግድ ሚኒስቴር ክፍል ለሥራ ታዘው ስለቆዩ የመጋቢትና የሚያዝያ ወር የቀለባቸውን ልክ ለመቁረጥ መደብ ስላልተገኘለት፣ የሁለቱን ወር ቀለባቸውን በግርማዊነትዎ ፈቃድ እንዲወሰን ሐሣቤን አቀርባለሁ። ማኅተም፣ ፊርማ፣ ሚኒስትር የንግድና የእንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ገብረ እግዚአብሔር” ገጽ 230

በዚሁም እውነት የሌለበት መጻጻፍና ክርክር ድካምና ከፍ ያለው መመላለስ በኋላ የቀረብኝን ደመወዜ በ፭ኛው ዓመት ለመቀበል በመቻሌም ተቀናብኝ። የዱሮ ዲረክተርነቴን ማዕረግ ሰርዘው እንደ ጓደኞቼ የድካሜ ዋጋ እንዳይሠጠኝ በጥብቅ አስከልክለው ከችግር እንዳልወጣ፣ ሰላምም እንዳላገኝ አድርገው በሩን ዘግተው አቶ ወልደ ጊዮርጊስ ቀበሩኝ።” ገጽ 230

“እንደዚህና እንደዚህም በመሰለው ጋኔናዊ የምቀኝነትና የአድልዎም ሥራቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጭቆናና ባርነት በማዝነባቸው ስቃይ አሰቃዩት፣ ዙሪያውን አስከብበው ተጫወቱበት። ለምለምዋ ኢትዮጵያም በጠላትዋ በጣሊያን ጊዜ ያወለቀችውን ሱሪዋን እንዳትታጠቅ ከመከልከላቸውም በላይ ለምለሚቱ ኢትዮጵያ ወደፊት እንዳትገፋ ከልክለው፣ በየዓመቱ ወደኋላ ብቻ፣ ቁልቁል እንድትመለስ አድርገው በማስገደድ ደመሰሱዋት።[ይህ ማጠቃለያ ሀሳብ ፕሮፌሰር መስፍን የቁልቁለት መንገድ ካሉት ጋር ይጣጣም ይመስላል- ተርጓሚዉ]” ገጽ 230

“ስለዚሁ መሳይ የሌለው የጉቦና በአድልዎ የታወረ የኢትዮጵያ ሕዝብ መደምሰስ ምክንያት በአርእስቱ የሐማ ጭካኔ ተብሎዋል።” ገጽ 230

በቀጣዩ ትረካ የአርበኛውን ፍጣሜ እናያለን። ቸር እንሰንብት!

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ ቅንነትን የተላበሰ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 19 Feb 2021, 11:14

የካቲት ፲፪ ስትዘከር፡ የጣሊያኑን ጀነራል ግራዚያኒ አዲስ አበባ ውስጥ ያርበደበዱት ጀግኖች ኤርትራዊያኖችን አብርሃም ደቦጭና ሞጎስ ኣስገዶምን እንዲሁም ፋሺስት ጣሊያን የገደለቻቸው በርካታ ንጹሐን ዜጎችን እንዘክራለን። እኛም የሰማእታቱን ቀን ስንዘክር፡ ለፋሺስት ጣልያን አልገዛም ብሎ ትንፋሹ እስክታልፍ ድረስ በአርበኛነቱ የጸናውን ጀግናው ተስፋሚካኤል ትኩእንም እያስታወስን፡ የህይወት ታሪኩን ፍጣሜ የምትገልጠውን የመጨረሻዋ ክፍል ትረካችንን በዚች በተባረኸች የሰማእታት ቀን እናቀርባለን። መልካም ንባብ!

ዜና ዕረፍት (ገጽ 250)

አቶ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ በኤርትራ ጠቅላይ ግዛት በአካለ ጉዛይ አውራጃ በሰገነይቲ ወረዳ፣ በደግራ ልባኤ ከአቶ ትኩእ ተመልሶና ከወ/ሮ ስላስ አምዱ ሰኔ ፲፪ ቀን ፲፰፻፹፬ ዓ.ም. ተወለዱ።

የኢትዮጵያን ትምህርት ከአጠናቀቁ በኋላ ከረን ከተማ በሚገኘው በስሚናር ሚሲዮን ካቶሊክ ተማሪ ቤት ገብተው ከፍተኛ ትምህርት ተምረዋል።


በ፲፱፻፲፯ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ፲፱፻፳፮ ዓ.ም. በአዲስ አበባና በደሴ በጉምሩክ ሹመት

ከ፲፱፻፳፮ ዓ.ም. ጥቅምት ወር ጀምሮ እስከ ፲፱፻፳፯ ዓ.ም. በጎጃም ጠቅላይ ግዛት የጉምሩክ ዲሬክተር ሆነው ሠርተዋል።

በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. በትልቁ ጦርነት ሽሬ ዘምተዋል። ጠላት አገራችንን በወረረ ጊዜም በጎጃም ክፍል አንድ ዓመት በአርበኝነት ተከራክረው ወደ ካርቱም ተሰደዋል።

በ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በድል አድራጊነት አዲስ አበባ ሲገቡ ተከትለው ገብተው በከፍተኛ ሹመት ወደ ወሎ ሄደው ጥቂት ጊዜ ከሠሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው የገንዘብ ሚኒስቴር ባልደረባ በመሆን እስከ ዕለተ ሞታቸው አቅራቢያ ድረስ ሠርተዋል። (የዚህ ታሪክ ጠሐፊ አርበኛው ተስፋሚካኤል ትኩእ ግን ከስራ ባለደረቦቻቸው ጋር በመሆን ከንጕሠ ነገሥቱ ቀድመው ፊት ፊት በመሄድ ማለትም ንጕሠ ነገሥቱን አስከትለው አዲስ አበባ በድል እንደገቡ መግለጣቸው ይታወሳል።)

ለመታከም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሆስፒታል ገብተው ሕመማቸው በሕክምና ሊጠገን ባለመቻሉ በተወለዱ በ፸፪ ዓመታቸው መስከረም ፳፯ ቀን ፲፱፻፶፯ ዓ.ም. ከቀኑ በ፰ ሰዓት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ዜና ሞታቸው እንደተሰማ አስከሬናቸው ከአዲስ አበባ በአይሮፕላን ተሣፍሮ አሥመራ ከጧቱ በ፪ ሰዓት ገባና በመኪና ጎዞውን ወደ ሰገነይቲ በመቀተል መስከረም ፳፱ ቀን ፲፱፻፶፯ ዓ.ም. ከቀኑ በ፱ ሰዓት ቤተ ሰቦቻቸውና ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት በቅዱስ ሚካኣኤል ቤተክርስትያን በክብር ተቀበሩ። ከኅዘን ተካፋዮች አንዱ፣ ብላታ ተስፋማርያም ንግሩ፣ (አዲስ ዘመን፤ ጥቅምት ፴ ቀን ፲፱፻፶፯ ዓ.ም.፣ ገጽ ፮)

ተፈጥሟል። አንድ ሙዚቃ ግን እንጋብዛችዋለን . . . “ተከብረሽ የኖርሽው ባያቶቻችን ደም፡ . . . !” :mrgreen:
http://www.mereb.shop/rs/?prodet=true&p ... 283&vid=88

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ ቅንነትን የተላበሰ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።

ፋሽስት ጣሊያንን በመፋለም ኣኩሪ ገድል የፈጸሙ የአፍሪካ ቀንድ አርበኞችና ሰማእታት ለዘለዓለም ይዘከሩ!!!!

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 05 May 2022, 03:27

እኛ ኤርትራዉያን የመሃልና የመስመር ዳኞች፡ የኣርበኞች ቀንን ስንዘክር፡ አርበኛውን ተስፋሚካኤል ትኩእንና ጓዶቹን በሙሉ እየዘከርን የተስፋዬ ገብሬን አርበኞችን የሚያወድስ ሙዚቃ እየኮመኮምን በኤርትራዊ ጭዋነትና ኩራት ትህትናም ጭምር ነው። :mrgreen:
Meleket wrote:
19 Feb 2021, 11:14
. . . አንድ ሙዚቃ ግን እንጋብዛችዋለን . . . “ተከብረሽ የኖርሽው ባያቶቻችን ደም፡ . . . !” :mrgreen:
http://www.mereb.shop/rs/?prodet=true&p ... 283&vid=88

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ ቅንነትን የተላበሰ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።

ፋሽስት ጣሊያንን በመፋለም ኣኩሪ ገድል የፈጸሙ የአፍሪካ ቀንድ አርበኞችና ሰማእታት ለዘለዓለም ይዘከሩ!!!!

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 06 May 2023, 04:08

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ ቅንነትን የተላበሰ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው። :mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 3057
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 06 Apr 2024, 04:38

“መጋቢት ‘28’ በያመቱ ይምጣ፡
የናንተም መሳርያ ጦርጋሻችሁ ይውጣ፡

መጋቢት 28 የነጻነት ቀን፡
ይከበር ዘላለም በሃገራችን።”

ነበር ያለው ብርቁ ድምጻዊ ተስፋዬ ገብሬ በምርጥ ዜማው አርበኞችን ሲያስታውስ፡ ዘነጋነው እኮ። እኛ ኤርትራውያን የመሃልና የመስመር ዳኞችም ይህኛውን አርበኛ ከነ ብርቅ ታሪኩ አስታወስን፡ በኤርትራዊ ጭዋነት ኩራትና ትህትና ጭምር።
:mrgreen:
Meleket wrote:
06 May 2023, 04:08
ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ ቅንነትን የተላበሰ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው። :mrgreen:

Post Reply