Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Meleket
Member
Posts: 506
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 20 Nov 2019, 03:38

የኒህን ቆፍጣና የታሪክና የስነጽሑፍ አርበኛ ተስፋሚካኤል ትኩእ ታሪክ ምዕራፍ 31 ደርሰናል፡ ስለ ድንቁ ዲፕሎማት ሎሬንሶ ታእዛዝ ገድል ከባህር በጭልፋም ያቋድሱናል። መልካም ንባብ። :mrgreen:

“የተስፋ ሚካኤል ትኩእ መጨነቅ እየተጨመረበት ሔደ። የእንግሊዝም መንግሥት ባለሥልጣኖች ከኢትዮጵያ አርበኞችና በየሀገሩም ስደት ተሰደው ካሉትም ጋር በጽሕፈት እንዳልላላክ በቁጣ ከልክለው፣ አጥብቀውም በስውር ስለተጠባበቁኝ ከፍ ያለ የማያቋርጥ ስጋት ጣለብኝ። የመረረ ንዴት መናደድና ችግርም ዙሪያየን ከበው አጠቁኝ፤ ነገ ተነገ ወዲያ ምን እመገብ ይሆን በማለትም የልብ እረፍትና እንቅልፍም አሳጥቶ ኅሳብ ቢማርከኝም ሰማያዊ አምላክ የዕለት ቁርስ ምንም አልነሳኝም ነበር” ገጽ 153

“ከኔ ይልቅ ባለቤቴ ወይዘሮ ቀደስ ባህታና ልጆቼ ወይዘሪት አበባ ተስፋ ሚካኤል፣ ወይዘሪት ፀሐይ ተስፋ ሚካኤል ጉድለት በሌለበት እምነታቸው የእግዚአብሔርን ታዳጊነት ብቻ ምግብ አድገው የጠላት ፈጣን ጥፋት አመኑ። ምልካም አብነትና መልካም አርአያም ሆኑ።” ገጽ 153

የፊተውራሪ መብራህቱ ታእዛዝ መምጣት፦ የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና አማካሪና ጠበቃ ዶክተር ሎሬንዞ ታእዛዝ ግርማዊነታቸውን ይዞ በሎንዶንና በቡሩክስለስ ከፓሪስም መንግሥት ጋር ስለ የኢትዮጵያ በግፈኛው ወረራና ወንበር መከልከልዋም ምክንያት በፖለቲካዊ ዲፕሎማሲ ጉዳይ ክርክር እየተመላለሰ ከተከራከረ በኋላ፣ የህግ ሊቁ ዶክቶር ሎሬንዞ በፊታውራሪ መብራህቱ ስም መንገድ አሳብሮ ከሎንዶን ተነስቶ በመብረቃዊ ያልታሰበ አመጣጥ በግብፅ መንገድ ገዳሪፍ ገባ። “ ገጽ 153

“አመጣጡም እንደ ህልም ሆነብኝ፤ ከጨካኙ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጠላት ከጣሊያን ፋሽስቶች የሚደርስበትን ስቃይና ውርደት፤ ጨካኝ በሆነው መጥፎ አገዳደል መገደሉንም ሳያስብ፣ ሕይወቱን ሳይቆጥብ፡ ስለ ውዲቱ ስለ ኢትዮጵያ ሀገሩ ነፃነት ወጣቱ ሊቅ ሎሬንዞ ታእዛዝ መሞቱን መረጠ። የኢትዮጵያ ሴቶች መመኪያ፣ የጀግናይቱ የትግሬ ሴት የቴጌ ጣይቱ ብጡል ኃይለ ማርያም ገብሬና የራስ አሉላን ደፋር ሕያው ተዋጊነት በመላው የአለም ነገሥታት ዘንድ በስመ ጥሩነታቸው እጅግ የተከበሩ መሆናቸውንና ከዚሁም የበለጠ አንዳች ነገር ምንም በዓለም አለመገኘቱን እየደጋገመ በሰፊው አጫወተኝ።” ገጽ 154

ስለዚህ ወታደር፣ የወታደር ልጅ የሆነው የአከለጉዛይ ሊቅ ፊታውራሪ መብራህቱ ታእዛዝ ቆራጥና ደፋር በሆነው ውሳኔው በዚሁ የመከራ ግዜዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ደሙን ለማፍሰስ፣ ያለማቋረጥ ስለነፃነታቸው በሚጋደሉትም የኢትዮጵያ አርበኞች መካከል ተገኝቶ ለማጽናናት፣ ለማበረታታትና አብሯቸው በትልቅ ሰልፍ ተሰልፎ ስእል ለመነሳትና ኢትዮጵያም በጣሊያኖች አለመገዛትዋን ሊያስፈርማቸው በአማርኛና በፈረንሳይኛ ፰፣፰ (ማመልከቻ) አሰናድቶ ቁምጣ ታጥቆ ተነሳ። ሲነሳም ሳለ ለዚሁ የረቀቀ የዲፕሎማሲ ስራው ምስክሮች የሚሆኑት ፫ት ፈረንጆች የአረብ ልብስ አልብሶ፣ ራሱን የቱርክ ቆብ ደፍቶ፣ ሀገሬውን መስሎና እነዚህን ሰዎች አስከትሎ በቅጽበት ሌሊት ተነሳ።” ገጽ 154

“አቶ ዓድሐኖም ክፍለዝጊ አብሮት እንዲነሳ አስገደደኝ። እኔ ግን “ዓድሐኖም ከዚህ ሔዶ እስከወንድሞቹ ኤርትራን አቋርጦ ከዓጋሜ ያመጣውን መሣሪያና ወንድሞቹን ከሠላ ትቶ በድንገት ስለመጣ፣ እነዚያም ልጆች ወደ ጠላት ግዛት ተመልሰው ገብተው ይጠፋሉና እነሱን እስክያመጣ ድረስ ቆይ ጠብቀው። ከዓድሐኖም ይልቅ አርማ ጭሆንና ጐንደርን ጐጃምንም ስለማውቅና አንተን ለመርዳት ስለምችል። ሰውንም ስለማውቅ አብሬህ እሄዳለሁ” ብለው “እኔ ብሞት ግድ የለንም፤ አንተ ግን እኒህን ሴትና ሕፃናት በሱዳን ጥለህ ከኔ ጋር ለመሄድ አይሆንም። አቶ ኣድሐኖም ብቻ ይበቃኛል አንድ ሰዓትም ለመጠበቅ አልችልም ሲል አጥብቆ ተከራከረኝ እና እለቱን ከዓድሐኖም ጋር ተነስቶ ሔደ።” ገጽ 155

“ዓድሐኖምም ለፊታውራሪ መብራህቶም ታእዛዝ ሕይወት በብዙ ስለሳሳ ወንድሞቹንና በወንድነቱ ከጠላት ማርኮ ያመጣውን መሣሪያውን ጥሎ አብሮት ሔደ። ጊዜው ክረምት ስለነበረ ጓንጊ ሞልቶ መሻገሪያ አጥተው በምድር ላይ እየተኙ በዝናብና በረኃብ ተጨነቁ። ከፈረንጆቹ አንዱ ዛፍ ቆርጦ በግንድ መሸጋገሪያ ለማበጀት ሲደክም ከነግንዱ ጐርፍ ይዞት ስለሄደ ፈረንጆቹ በብዙ ስለደነገጡ፣ የህግ ሊቅ ፊትውራሪ መብራህቶ “ወንድሜ ዓድሀኖም ያወጣዋል እና ኣይዟችሁ፣ አትደንግጡ” ኣላቸው። እነሱ ግን ከዚህ የጐርፍ አደጋ ይድናል ብለው ተስፋ ሳያደርጉ የዛሬው ካፒቴን አቶ ዓድሐኖም ክፍለእግዚ እመር ብሎ እንደ ጥይት ተወንጭፎ የጓንጊ ውሃ የበላውን ሰው መንጥቆ በኃይል ሲያወጣው ሳለ፣ የስፓኛ ተወላጅ የጣሊያን ጠላት የሆነው ኮሎኔል እንድሪያስ ዓድሐኖምን ሲያወጣው ሳል አነሳቸው፤ በብዙ ተጨበጨበለት። ኮሎኔል እንድራያስም ከዓድሐኖም ብርታትና ጉብዝና የፊታውራሪ መብራህቱን ትንቢት በብዙ አመሰገነ፤ ዓድሐኖምም ንዳድ ታሞ ስለወደቀ በመከራ ገዳሪፍ ተመልሶ ሆስፒታል ገብቶ ዳነ። ከእግዚአብሔርም በታች ኤርትራዊ አፈንድ ሚካኤል በኪት ሐኪሞቹን በጥብቅ አዞ ስለደከሙለት ለመዳን ተስፋ ያልነበረው ዓድሐኖም ተረፈ።” ገጽ 155

“ፊታውራሪ መብራህቱም ፫ት ፈረንጆች ይዞ ጥቂት ሰዎች አስከትሎ ወሰንና መሳይ በሌለው መከራ የፊታውራሪ ባህታ ሀገር ሐውሳ ሲገባ ሁሎቹም ንዳድ ታመው ወደቁ። ለሐውሶች አደራ ብሎ ፈረንጆቹን ትቶ ፪ ሰዎችን አስከትሎ በአርማ ጭሆ ጣቁሳና አለፋን አቋርጦ፡ በአሸፈር ጐጃም ወደ ደጃዝማች ነጋሽ ከበደና ወደ አቶ ጊላጊዮርጊስ፣ ወደ ፊታውራሪ መንገሻ ጀምበሬ ዘንድ ገብቶ በሰልፍ እየዞረ ከጐበኛቸው በኋላም፣ በሕዝብ መራጭነት በጀግናነቱም ብዛት “የኢትዮጵያ ደም መላሽ አጼ በጉልበቱ በላይ ዘለቀ” ተብሎ ብዙ ፊታውራሪዎችና ደጃዝማቾች ራስ ብሎ እየሾመ ጣሊያንን ያለልክ ያረደና ያንቀጠቀጠ ኢትዮጵያዊው ጀግና ዘንድ አቶ አማኑኤል መንገሻን ብሸና ልኮ በፕላኑ መሠረት በሠልፍ ሥዕላቸውን አንሥቶ፣ ማኅተም ማኅተማቸውን አትመውና ፈርመው እንዲልኩ አደረገ፤ በአቶ አማኑኤል መንገሻ ብሩም በቤጌምድር እና በሰሜን፣ በጐጃምና በቋራ የተፈጸሙት ቁጥር የሌላቸው የጀግንነት ሥራዎች ምንም እንኳ ግርማዊነታቸው ቢያውቋቸውም በታሪክ መሥመር ሳይጻፉ በመቅረታቸው እጅግ ያዝናል።” ገጽ 155

“የአከለጉዛይ ሊቅና የዲፕሎማሲ አርበኛም የሆነው ደፋር ፊትውራሪ መብራህቱ ታእዛዝ የጐጃምን ሥራ ከፈጸመ በኋላ በትግሬ መኮንን ኃድጉ ልጅ በፊታውራሪ አየለ ሀገር በአሸፈር አቋርጦ አርማ ጭሆ ሲመለስ፣ ኮሎኔል እንድሪያስ የጣልያን መንግሥት ፈጽሞ ኢትዮጵያን አለመያዙንና ራሱ ጣሊያን ዙሪያውንም በኢትዮጵያውያኖች ተከቦ መጨነቁን ፈርሞ ለዓለም መንግሥታት መስክሮ አስታውቆ የነበረው ሙቶ ስለቆየው ብዙ ኅዘን አዘነ። ይህ ባለ ታሪክ የሆነ ዶክቶር ሎረንሶ ታእዛዝ ከበደ ቸኮልንና ወልደ ኪዳንን አስከትሎ ወደኛ ገዳሪፍ ተመልሶ ከመድረሱ፣ ጀኔራል ናዚ በጎንደር ሆኖ “ዶክቶር ሎሬንዞ ታእዛዝ በፊታውራሪ መብራህቱ ስም ወደ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተዋልና እጃቸውን ይዞ ላመታልኝ ሰው ወረታውን ሚሊዮን ሊሬ እሰጣለሁ” ብሎ በከንቱ ለኢትዮጵያዊ ህዝብ አዋጅ አናገረ።” ገጽ 155

“ዶክቶር ሎሬንዞ ታእዛዝ ግን የዲፕሎማሲ ስራውን ሳይለቅ ከፍ ያለውን ደፋር የአርበኝነት ስራ አጣምሮ ከፈጸመ በኋላ ህዳር ፲፰ ቀን ፲፱፻፴፩ ዓ.ም. ከገዳሪፍ ተነስቶ በካርቱም፣ በግብጽ፣ ፓሪስ ሲደርስ ስለ የኢትዮጵያ ወዳጅ ስለ ኮሎኔል አንድርያስ መሞትና ኢትዮጵያ በጣሊያን አለመያዝዋን ምስክርነት ተጠይቆ ካስረዳቸው በኋላ፣ አርበኛው ዶክቶር ሎሬንዞ ኢትዮጵያ በጣሊያን ከመያዝ በእግዚአብሔር ኃይልና በአርበኞቹዋ ወሰን የሌለው ብርታትና ጀግንነት ነፃ መሆንዋን ለግርማዊ ጃንሆይ የምስራችነት አበረከተ። በዓለም ነገሥታት ፊትም ጀግናው ዶክቶር ሎሬንዞ ታእዛዝ ክብርና ምሥጋና አገኘ፤ ሀገሩንም አስከበረ። ደፋር በሆነው ብርታቱና ወንድነቱም የሊቁ ሎሬንዞ ታእዛዝ ፖለቲካ እጅግ አስደነቀ።” ገጽ 156

“የፈረንሳይና የእንግሊዝ ማንቀላፋትና ስሕተት፦ በኤውሮጳ ጦርነት እንዳይነሳ በመፍራት እሳት ጫሪ ጣልያንም በናዝስቲና በየኤሮጳ ዲሞክራሲ መንግሥታቶች መሐከል ገብቶ እንዳይበጠብጣቸው አቆላመጡት፤ ኢትዮጵያን እወራለሁ ሲላቸውም ፈቀዱለት። የሚያስፈልገው ፖለቲካና ምክር አቀበሉት፤ አበዳሪና ዋስ ሆነውም ገንዘብ አበደሩት፤ የሚያስፈልገውን ርዳታ ሁሉ አደረጉለት፤ ላፋቸው ግን ጣሊያን ኢትዮጵያን እንዳይወጋ አደረግን፣ አስወሰን ሲሉ አውርተው አስወሩ።” ገጽ 156

ወዳጃቸው የጣሊያን መንግሥት በተምቤን ድል ሆንኩ ብሎ በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ስልክ ባሳለፈላቸው ቀን የርዳታቸውን ምስክርነት ጉልህ አድርገው ሲገልጹ፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ “የጣሊያን በኢትዮጵያ ድል መሆን ለድፍን ኤውሮጳ ውርደትና እፍረትም ስለሆነ “በመረዝ” በርትታችሁ ውጉዋት” ሲሉ በቁጣ ቃል ለጣሊያን ማስተላለፋቸው ከማንም ሰው የተሰወረ አልነበረም። የኢትዮጵያ ዘር ሁሉ ምንጊዜ ሊረሳው ምንም አይችልም። የኢትዮጵያን መንግሥት መስዋእት ለጣሊያን አሳልፈውን ሰጥተን በሀገራችን ጦርነት ሳይነሳ በሰላም እንኖራለን፤ ጀርመንም ለጦርነት እንዳይነሳ ከፋፍለን፣ በጭቆናና በርኃብ ገድለን አስረነዋልና ለመነሳት አይችልም በማለታቸው ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን አሳልፈው ለጣሊያን በመስጠታቸው በአርእስቱ “የፈረንሳይና የእንግሊዝ ማንቀላፋትና ስህተት” ተባለ።” ገጽ 157

“በዚሁም የፈረንሳዊና የእንግሊዝ በማንቀላፋት መሳሳት ኢትዮጵያን በጣሊያን በማስወሰዳቸው ምክንያት የናዚስት መሪ የሆነው ጀርመናዊ አዶልፍ ሂትለር “ፍላይት ቦምብ” የተባለ ሐዲስ እሳታዊ በራሪ ዲስክ ሲያጥለቀልቃቸው ጊዜ፤ በመጸጸት እንዲህ ሲሉ ኑዛዜ ተናዘዙ። “ዙሪያውን በአረመኔዎች የተከበበቺው የኢትዮጵያ ክርስቲያናዊት ደሴት አምላክ ከባህር ዛፍ በታች ሆኖ ከጠላቶችዋ ጠበቃት” ሲሉ ራሳቸው መሰከሩላት። በብዙም እግጅ ተደነቁ።” ገጽ 157

በቀጣዩ የምዕራፍ ሠላሳ ሁለት ትረካ “ከኔ ከተስፋ ሚካኤል ለግርማዊ ጃንሆይ የተጻፉት ደብዳቤዎችና በጸሐፊያቸው ራሳቸው የሰጡኝ መልስ” በሚል ርእስ ስር የተካተተውን ታሪክ እናያለን።

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።

Meleket
Member
Posts: 506
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 29 Nov 2019, 08:56

አርበኛው ተስፋ ሚካኤል ትኩእ ያመኑበትን ጉዳይ በግልጽ በማቅረብና ከ “ሞዓ ኣንበሳ"ዉና ከጠሐፊዎቻቸው ጋር የተጣጣፏቸውን ደብዳቤዎች እንቃኛለን። መልካም ንባብ። :mrgreen:

“ለግርማዊ ጃንሆይ። ቸሩ እግዚአብሄር የልቦናዎን ኅሳብ ሰምቶ በቅጽበት እንዲፈጽምልዎ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሁሉ በትልቅ ኅዘን ፈጣሪን ከመለመን ምንም አላቋረጡም። የፍፃሜው ቀኑም ባይደርስ ነው እንጂ ደህና ከሆነ ነገሩ በቶሎ ይፈጸማል። በየምክኒያቱም ከሸዋና ከሰቆጣ፣ ከበጌምድርና ከጐጃም ተልከው የመጡ ሰዎች ጉዳያቸውን ሳይፈጽሙ ገዳሪፍ ላይ በእንግሊዝ ተይዘው ታስረው በብዙ የኦባ(ወባ) በሽታና ጨካኝ ረሃብ በመገረፋቸው ችግራቸውን ለግርማዊነትዎ እንዳስታውቅ ኅልናዬ አጥብቆ አስገድዶኛልና በቸርነትዎ የእነዚህኑ ፍጥረቶች ብርቱ ችግር እንዲያቃልሉላቸው አሳስበዎታለሁ።” ገጽ 158

ከሸዋ ልጅ ነጋ ኃይለ ሥላሴና እንግዳ ወርቅ ወልደማርያም፣ መኮንን ደስታ፣ ተስፋዬ በላቸው፣ ከሰቆጣ ፊታ. ኃይሉ ክብረት፣ አቶ ስጦታው፣ ልጅ መጐስ አሊ፣ አቶ ላቀው። ከበጌ ምድር ግራዝማች አስማረ ዘረፋና አቶ በለጠ ሣህለሚካኤል ከጐጃም አቶ መኮንን ደስታ፣ ከበደ ወልደ ሰማያት፣ አቶ ታደሰ ገብረ መድኅንና ሌሎቹም ብዙ ሰዎች ናቸው የመጡ።” ገጽ 158

“የግርማዊ ጃንሆይን ልክ ለማወቅ ከየክፍሉ የመጣ ሰው ቁጥና ወሰን የለውም። በኦባ ህመም ተሸንፎ ካልወደቀ ወይም ካልሞተ በቀር ወደዬ ሀገሩ እየተመለሰ ይሄዳል። የኢትዮጵያ ሕዝብም የተቸገረው በሕይወት መኖርዎን በብዙ እየተጠራጠረና ሃሳቡም እየተከፋፈለ፣ ተጨንቆ ተጠቦዋልና ለፈጣሪዎ አስጨንቀው እንዲለምኑትና ጉዳዩው ሁሉ በፍጥነት እንዲፈጸም እንዲያደርጉለት ህዝብዎ በብዙ ተስፋ ይጠብቅዎታል። ገዳሪፍ መስከረም ፳፮ ቀን ፲፱፻፴፩ ዓ.ም። ፊርማ፣ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ።” ገጽ 158

“ለግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ። ሎንዶን። ሐዋርያት ያልቻሉት ረሐብና ችግር አስጨንቆኛልና ጊዜ ስለማይሰጥ የገንዘብ ርዳታ እንዲሰጠኝ ለግርማዊነትዎ ቸርነት አለምናለሁ። እኔም ከነ ባለቤቴና ከነ ልጆቼ ፭ት ራሴ ሆኜ ስደት ስሰደድ ጉዳቴ ከልኩ አልፎ የተረፈ መሆኑን ለማንም ሰው ያልተሰወረ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ራሳቸው ለተሰደዱ ሰዎች ግን አስተዋሽና ዘመድም በማግኘታቸው ከግርማዊነትዎ በየጊዜው የገንዘብ ርዳታ ሲደርሳቸው እኔ ብቻ ተለይቼ በመቅረቴ በብዙ አዝናለሁ። ርዳታም እንዳይደርሰኝ ያስከለከሉኝ ትግሬ በመሆኔ ነው። ትግሬነቴም ምንም የሚያሳፍረኝ አይደለም። ገዳሪፍ፣ መስከረም ፳፮ ቀን ፲፱፻፴፩ ዓ.ም። ፊርማ፣ ታዛዥዎ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ።” ገጽ 159

“ሞዓ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ። ይድረስ ከአቶ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ። እንደምን ስንብተሃል? እኛ በእግዚአብሔር ቸርነት ደህና ነን። የላከው ደብዳቤ ደርሶናል። ድህንነታችሁን ስለሰማን ደስ የሚያሰኝ ነው። ምላሹም ተጽፎአል። በዚህ በፈተናችን ሰዓት በማናቸውም ጊዜ ሐይማኖታችንን ማጽናት ያስፈልገናል። በእርሱም ላይ የምናደርገው እምነት ከንቱ ሁኖ አይቀርም። ግንቦት ፲፱ ቀን ፲፱፻፴፩ዓ.ም ተጻፈ። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ።” ገጽ 159

“ይድረስ ለክቡር ወዳጄ አቶ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ። እጅጉን እንደምን አሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። የላኩልኝ ደብዳቤ ደረሰኝ፤ ምላሹን ከዚህ ጋር ያገኙታል። ምንም ችግርና የዚህ አለም የመከራ ኑሮ ቢታገለን የሰጠንን እድል በትዕግስት በመቀበልና ለማሸነፍም በመጣጣር መበረታት ይገባናል።” ገጽ 159

“ወሬዎን ሳልሰማ ብዙ ጊዜ አልፎ ነበር። ምንም ባይመችዎ እስከዚያው ድህንነትዎን በመስማቴ ደስ አለኝ። ደብዳቤዎ በመጥፎ አጋጣሚ ጊዜ ስለደረሰኝ ስለተመኙት ምንም ለማድረግ ባለመቻሌ ከልክ ያለፈ አዝናለሁ። ነገር ግን ተስፋ አልቆርጥም፤ የተሻለ ጊዜ እንዲገጥመኝ እለምናለሁ። የቤት አባት ጭንቅዎ ይሰማኛል፤ ሰው ለመርሳት ቢፈልግ ኢትዮጵያና ልጆቹን ታላቁ ጌታ አይረሳምና በቅርብ ብርሃን እንዲያሳየን እንለምን። ሎንዶን፡ ግንቦት ፩ ቀን ፲፱፻፴፩ ዓ.ም። የርስዎ፣ ፊርማ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ።” ገጽ 159

“ካርቱም ነሐሴ ፲፬ ቀን ፲፱፻፴፪ ዓ.ም ይድረስ ለክቡር ወንድሜ አቶ ተስፋ ሚካኤል። ባቶ በርሄ አደራነት የላከልኝ ደብዳቤዎች ትላንትና ከ፮ ሰዓት በኋላ የደረሰኝ፤ ለባለቤቱ አድርሻለሁ። የኤርትራ ልጆች በመጡ ቁጥር ወደዚህ በቶሎ እንዲላኩ ለሚካኤል ኤፈንዲ እየነገርክ እንድታግዛቸው አደራ። ለዚሁ ስራ አንድ መንገድ እስቲበጅበት ድረስ ነው። አሥፈሐ ወደ ሥላሴ እዚህ መምጣቱን ያለመምጣቱን ለማወቅ አልቻልኩም፤ ለጊዜው አሁን ማለዳ ነውና ነገር ግን አስጠይቃለሁ። ለባለቤትና ልጆችህ የናፍቆት ሰላምታ አቅርብልኝ። ትናንሾቹን ባንዲራዎች ለመጀር ኖት አስረከብከው ወይ። ያንተ ። ፊርማ ፊታውራሪ መብራህቱ ታእዛዝ ሎረንሶ።” (በዚህ ደብዳቤ ዕለቱ በመጀመርያ ተጽፏል፣ የጸሐፊው ዘመናዊ ትምህርት መቅሰምን ሊያመላክት እንደሚችል አርታዒው ገልጿል)” ገጽ 160

ለወዳጀ አቶ ተስፋ ሚካኤል፤ ገዳሪፍ። እንደምን አሉ ከነቤተሰብዎ። እኔ ደህና ነኝ። የጻፉልኝ ደብዳቤዎች ደርሰውኛል። አቶ መንግሥቱም ተመልሰው ለስራቸው መጥተዋል። ለተባባልነውም ጉዳይ ወረቀቱን ተቀብለዋል። ሌላ የምንሰማው ሁሉ ደስ የሚያሰኝ ነው። የካሣ አብርሃ መምጣት ሳይሰሙ አልቀሩም፤ ከርስዎ ተርፎ የመጣ ነው። ይህንን የመሰለ ሰው በሕይወት ቆይቶ ወደዚህ ለመድረስ መቻሉ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑን የሚያስረዳ ነው። የጠላታችን አይን ተቸፍኑዋል። ይህም የአምላክ ኃይል ነው። መልእክተኞቹ በቶሎ መነሳታችው ስለሆነ ይህን አጭር ቃል ጻፍኩልዎ። ባለቤትዎ ወይዘሮ ቀደስና ልጆችዎ ደህና ኣንዳሉ ተስፋ አለኝ። የማክበር ሰላምታ ይስጡልኝ፤ በቅርብ ያገናኘን። መስከረም ፲፭ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም። ካርቱም። ፊርማ፣ ወልደ ጊዮርጊስ ወደ ዮሐንስ።” ገጽ 160

በቀጣዩ የምዕራፍ ሠላሳ ሦስት ትረካ “ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ እኔ ተስፋ ሚካኤልና አቶ መኰንን ተጻጽፈንባቸው ከጠፉት ውስጥ የቀሩት ደብዳቤዎች ለመታሰቢያ” በሚል ርእስ ስር ያካተቱን ታሪክ እናያለን።

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።

Meleket
Member
Posts: 506
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 10 Dec 2019, 08:16

የአርበኛው የአቶ ተስፋሚካኤል ትኩእን ትረካ እየኮመኮምን ምዕራፍ ሠላሳ ሦስት ደርሰናል፤ አርበኛው ከአቶ መኮንን ጋር ከተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች መካከል ከጠፉት ውስጥ የቀሩትን ለመታሰቢያነት ያህል ለዛሬ አጋርተውናል። መልካም ንባብ። :mrgreen:

“ለክቡር አቶ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ። የጥብቅና መጣበቅ ኮሚቴ ምክትል ፕረሲደንት። ካርቱም። ግንቦት ፳፰ ና ሰኔ ፩ ቀን የጻፉልኝ ደብዳቤዎች ደርሰውኛል፤ ለግርማዊ ከእኔ ማስታወሻ ጋር ልኬዋለሁ፤ ለማናቸውም ቢሆን ምላሹ እስኪመጣ ቢታገሡ ይሻላል፤ ባይሆን ለቤተ ዘመዶችዎ እዚያው እሱዳን ውስጥ ነፋሻ ቦታ ፈልገው (እነሱን እዚያ እሱዳን ውስጥ) እርስዎ ለቢሮዎ ወደ ተመቸዎት ከተማ ብትቀመጡ ይሻላል። ስደተኞቹ ወንድሞቻችን በታላቅ ብስጭት ላይ በመሆናቸው አለአግባብ በሚያባክንዎ ሁሉ እርስዎ የሀገር ፍቅር ስላለብዎ ይታገሡ።” ገጽ 161

“ገንዘብክ አልደረሰነም ስላሉኝ፤ ገንዘብ የተላከው ባቶ ገብርኤል ወልደ ማርያም በኩል ነው። ርስርስ ባንክ የለም፤ ለብላታ ዴሬሣ አንሰጥም ስላሉኝ፣ አቶ ገብርኤል ተቀብለው ለብላታ ዴሬሣ እንዲያደርሱ ስለላክንላቸው ገንዘቡ መጥቶልናል ለብላታ ዴሬሣ አስረክባለሁ ብለው ጽፈውልናልና በትህትና አቶ ገብርኤልን ይጠየቁአቸው።” ገጽ 161

“ዳግም እንግሊዝ ኰሚቴአችን አንድ ፻፶ ጊኒ በሱዳን ገቨርኔር በኩል ተልኮላቸው ሳይነግሩአችሁ አይቀሩም። ለማናቸውም ተመካክራችሁ በየጠረፉ ያሉትን ሰዎች ቁጥር ችግር ቢገጥማችሁ በትልቅ ትህትናና ብልሃት ለሀገር ገዥው ጸሐፊ ብታመለክቱአቸው መልካም ነው። አለዚያም እስኪያስታውቁዋችሁ ጥቂት ጠብቃችሁ ምላሹን አስታውቁን። ፓሪስ፣ ሰኔ ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም። ፊርማ መኰንን ሀብተ ወልድ።” ገጽ 161

“ይድረስ ለአቶ ተስፋ ሚካኤል፣ ጤናህን እንደምን ሰንብተሃል? ወንድሜ እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። በደህና ከነልጆችህ ካርቱም መድረስህን ብሰማ በጣም ደስ አለኝ። እንኳን አምላክ ከአደጋ ያተረፈህ። የአቶ መኰንን ሀብተ ወልድ ደብዳቤ ገና ዛሬ ከወረቀትህ ጋር ደረሰኝ። ሁሉንም በዝርዝር አድርጌ ቶሎ እሰዳለሁ። አስበህ ስለጻፍህልኝ እግዚአብሔር ይስጥልኝ። ባላምባራስ አሸብርም መጥቶ እዚህ ነው ያለው፤ እንዲጽፍላችሁ አድራሻችሁን እሰጠዋለሁ። የካቲት ፪ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. ርስሪስ፣ ፊርማ ብላታ ዴሬሣ አመንቴ።” ገጽ 162

“ይድረስ ለክቡር አቶ መኰንን ሀብተ ወልድ፣ ፓሪስ። እንደምን ሰንብተዋል? እግዚአብሔር ይመስገን እኔ ደህና ነኝ። ለጻፍሁለዎት መልስና ለሰጡኝ ብዙ ተስፋ እጠባበቃለሁ። ክቡር ሆይ የስደተኞች ቁጥርና ችግር በየቀኑ በዝትዋል፤ የግርማዊ ጃንሆይን ልክ ለማወቅ ብለው በበጌምድር አቋርጠው ጋላባት መጥተው የነበሩት ፊታውራሪ ኃይሉ ክብረት ተመልሰው ዳግም በጋላባት ገዳሪፍ ጠረፍ ለጠረፈ ከነጓዛቸው ከሀገራቸው ተነቅለው መጥተው መጉላላታቸውንና በብዙ መጨነቃቸውን ስለሰማሁ በሀገር ገዥው በኩል ተፈልገው እንዲረዱ ለግርማዊ ጃንሆይ እንዲያመለክቱላቸው አስታውሰዎታለሁ።” ገጽ 162

“፪ኛ ግራዝማች ፍስሐዬ ዘሚካኤል የሚባሉ አርበኛ ከሰሜን ራሳቸው መጥተው ኃደሊያ ካሉት ቀኛዝማች ዓምደማርያም ተስፋ ጽዮን ጋራ ተቀላቅለዋል፤ ሥዕላቸውን ግን ለማግኘት አልተቻለም።” ገጽ 162

“፫ኛ ግራዝማች ውብነህ ተሰማ የተባሉ በእውነተኛው ውብነታቸው በሀገር ፍቅር የተነደፉ አርበኛም ጓዛቸውን አስቀድመው በፊት ገዳሪፍ አስገብተው ራሳቸው ግን የአርማ ጭሆን ሰው ሁሉ አሳብረው ብርቱ የወንድ ሥራ ሠሩ፤ ጠላትን በብዙ ማረኩ። በማባረርም እጅግ አስቸገሩት። ያስቸግሩታልም። ስለዚህ ሞያቸው ለግራዝማች ውብነህ ተሰማ ደብዳቤ ቢጻፍላቸው እጅግ መልካም ነገር ነበር።” ገጽ 162

“፬ኛ ስዩ የፊታውራሪ ዮሐንስ ጆቴ አጋፋሪ የነበረው ቀኛዝማች ወልደ አማኑኤል ፲፫ ራሱ ሆኖ ሐምሌ ፲፱ ቀን ካርቱም ገባ። ከሞት የተረፈ ሰው ሁሉ እየበረረ ፈጽሞ መምጣቱ አልቀረምና ለባለቤቱ አስታውቀው አስቀድሞ እካርቱም ለኋላ የሚሆነውን ነገር ሁሉ አሁኑኑ ጀምረው እንዲያዘጋጁት አሳስበዎትለሁ። የኢትዮጵያ ሰው ሁሉ ዛሬ በግልጽ የሚያወጋው ጃንሆይ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ሱዳን ደርሰዋል፤ ጣሊያን ግን ቀኑ ስላለቀ አይኖርም፤ አልቆ ይቀራል እያለ ሌት ተቀን እግዚአብሔርን መለመን ይዞዋል ይሉናል። ልመናችንም እግዚአብሔር ፈጥኖ እንደሚሰማን የተረጋገጠ ነገር ነው እና እስከዚያው ድረስ ለስደተኛው ሁሉ መሠረት ያለው ተስፋ እንዲሠጡት።” ገጽ 162

“፭ኛ ላባ ገብረ ሥላሴ ተብሎ ወጥቶ ባቶ ገብረ መስቀል እጅ የተቀመጠውን ፲ ጊኒ እሳቸው ግብፅ ወርደው ስለጠፉ ሱዳን ካሉት ሰዎች ችግር ለበዛበት አይተው ቢሰጡት መልካም ይመስለኛልና ከባለቤቱ እንዲያስፈቅዱ።” ገጽ 162

ክቡር ሆይ፤ ክፉ ቀን ያልፋል፤ ስም ግን አያልፍምና ነዋሪ ሆኖ በታሪክ ለሚጻፈው ስምዎት እንዲጣጣሩ በብዙ አስታውስዎትአለሁ። ካርቱም፣ ሐምሌ ፳፫ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ምሕረት። ፊርማ፣ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ።” ገጽ 163

በቀጣዩ የምዕራፍ ሠላሳ አራት ትረካ “ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኅበ እግዚአብሔር፤ በፓሪስ የቆመ ማኅበር” የሚል ርእስ የሰጡትን ትረካቸውን እንቃኛለን።

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው። :mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 506
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 30 Dec 2019, 04:22

ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኅበ እግዚአብሔር፤ በፓሪስ የቆመ ማኅበር” በሚል በመጸሓፋቸው ሠላሳ አራተኛ ምእራፍ ውስጥ አርበኛው ተስፋሚካኤል ትኩእ ከኢትዮጵያ ማኅበር ፕሬዘዳንት ካቶ መኰንን ሀብተወልድ ጋር የተጻጻፏቸውን ቅልብጭብጭ ያለ ይዞታ ያላቸውን ደብዳቤዎች እንጋራለን። የአርበኛውን ሃሳብ የማፍለቅና ሃሳባቸውን በቅንነት የመግለጽ ባህሪም ይህ ደብዳቤያቸው አሁንም ፍንትው አድርጎ ያሳየናል። መልካም ንባብ። :mrgreen:

“ይድረስ ለክቡር ወዳጄ አቶ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ። የወዳጅነት ሰላምታዬን ለርስዎና ለተወደዱ ቤተ ዘመዶችዎ አቀርባለሁ። ወዳጄ ሆይ ለጤናዎ እንደምን ሰንብተዋል? ሐምሌ ፩ ቀን የጻፉልኝ ደብዳቤ ሐምሌ ፯ ቀን ደረሰኝ፤ አመሰግንዎታለሁ። ሌላ ፕሬሲደንት በመለወጡ ለርስዎ እረፍትና ጥቅም ነው፤ ቀድሞውንም ቢሆን የመረጥንዎ ለስደተኞቹ ወንድሞቻችን ጥቅም ነው እንጂ ለርስዎማ ድካም አይደለምን? አሁንም በሚቻለዎ ወንድሞቻችንን መርዳትዎን እንዳያቋርጡ እንለምንዎታለን፤ በሰላም ያገናኘን። ሐምሌ ፲፫ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም ፓሪስ። የኢትዮጵያ ማኅበር ፕሬዘዳንት፤ ፌርማ፣ መኰንን ሀብተ ወልድ።” ገጽ 164

“ይድረስ ለክቡር መኰንን ሀብተ ወልድ፣ ፓሪስ። እንደምን ሰንብተዋል? ለጤናዎ ቸሩ እግዚአብሔር ይመስገን እኔ ደህና ነኝ፤ በሐምሌ ፲፫ ቀን የጻፉልኝ ክቡር ደብዳቤዎ ደረሰኝ፤ ስለ የሥራ መለዋወጥ ምክንያትም ደስ ብሎኛል፤ ወንድሞቻችንንም ለመርዳት አላቋርጥም፤ በዚሁ ነገር ተስፋ ሚካኤል ይከፋዋል ብለው ምንም እንዳያስቡ። ይልቁንስ የስደተኞቹ ጥቅም አብልጦ ደስ ይለኛል እንጂ አይከፋኝም።” ገጽ 164

“፪ኛ ራፓር በረኰማንዴ እንዳልጽፍለዎ የጊዜው ችግር አልፈቀደልኝም፤ ለጊዜው የሚያስፈልገውን በገዳሪፍና በከሰላ ለሰው እንዳይታዩ ፈርተው በድብቅ ገብተው በብዙ ችግር የተለወሱትን ስደተኞች በፍጥነት መርዳት ነው። ከሁሉ የበለጠ ነገር ለመጡና ለተቀመጡ በሌላ ሰው ስም አዙሮ ለመላክም የሰውዬውን ስም ይስጡን፤ አይስጉ።” ገጽ 164

“፫ኛ ክቡር ሆይ ከዚህ ቀደም የጻፍሁለዎትን ትንንሽ ኅሳቦቼን ከ፫ቱ አንዱን ተቀብለው ቢፈጽሙት ኑሮ እጅግ መልካም ነበር። አሁንም አለብርታት መፈጸም ምንም መዳኛ እንደሌለን ይወቁት፤ ለወደፊቱም ፲፱፻፴ ዓመተ ምሕረት ካለፈች በኋላ ተስፋችን በመቆረጡ ያለቀ የተፈጸመ ነው። ስለዚህ ዛሬውን መሥራት የመሰለ የለም። በሕይወት ያገናኘን እግዚአብሔር፤ አሜን። ሐምሌ ፳፬ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. ካርቱም። ፊርማ፣ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ።” ገጽ 164

በቀጣዩ የምዕራፍ ሠላሳ አምስት ትረካ “እኔ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ በየጊዜው ለጻፍሁላቸው የማነቃቃት ደብዳቤዎች ሲመሰክሩ አርበኞች የሰጡኝ መልሶች” የሚል ርእስ የሰጡትን ትረካቸውን እንቃኛለን።

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ ቅንነትን የተላበሰ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።

Meleket
Member
Posts: 506
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ተስፋሚካኤል ትኩእ (1892 – 1964)] - ወለዶና ክነቦ ዝግባእ መኽዘን ታሪኽ

Post by Meleket » 13 Jan 2020, 10:26

ለዛሬ ኤርትራዊው አርበኛ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ‘የእውቁ የቦለቲካ ተንታኝ’ የታምራት አባት አያ ነገራም ሆኑ አያቱ አያ 'እንቶኔ' ንፍጣቸው ባፍንጫቸው ይዝረከረክባቸው በነበረ በዚያን ቀውጢ ሰዓት :mrgreen: ፡ እኒህ ኤርትራዊ አርበኛ ለኢትዮጵያውያን አርበኞች የጻፏቸውን የማነቃቃት ደብዳቤዎች፡ አርበኞቹም እማኝነታቸውን የሰጡባቸውን ደብዳቤዎች ለናሙናነት ጥቂቶቹን እናያለን፣ መልካም ንባብ። :mrgreen:

“ይድረስ ከአቶ ተስፋ ሚካኤል ጤናህን እንደምን ከርመሃል? እግዚአብሔር ይመስገን እኔ ደህና ነኝ፤ የጻፍህልኝ ደብዳቤ ደርሶኛል፤ ያንተንም ከጣሊያን አደጋ አምልጠህ ካርቱም መድረስህን ብሰማ በጣም ደስ አለኝ፤ ለወደፊቱም እንደዚሁ ብትጽፍልኝ መልካም ነው። የኢትዮጵያን ባንዲራ አቁም ፊት ለፊት ተገናኝተን ለመጨዋወት ያብቃን። ሐምሌ ፮ ቀን ፲፱፻፴ ዓ.ም. ዝማኅተም፣ ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ። መተማ ስለ አስሽከሮቻቸውና ባለቤታቸው እስከመጨረሻ ተዋጉ።” ገጽ 165

“ይድረስ ለአቶ ተስፋ ሚካኤል፣ ጤናኽን እንደምን ሰንብተሃል? እኔ አምላክ ይመስገን ደህና ነኝ፤ የላክህልንም ደብዳቤ ደረሰልኝ። እኛም በሥላሴ ቸርነት ከጠላታችን ከኢጣሊያን መዋጋት ከጀመርን እስካሁን ድል ከማድረግ በተቀር ድል ሆነን አናውቅም። ብዙ መትረየስና መድፍም ማርከናል፤ እስከ ዛሬ እንታገላለን። የኢትዮጵያ ልጅ የሆነ ሁሉ መርዳት ለዚህ ጊዜ ነው። ይኸው ለሁሉም ነገር ልጅ ታደሰን ልከነዋልና በየተቻላችሁ መርዳት ነው። የኢትዮጵያ አምላክ ለነፃነት አብቅቶ፣ ግርማዊ ጃንሆይንም አሰንብቶ፣ እኛንም አቆይቶ በሰላም ለመገናኘት ያብቃን። ሐምሌ ፴ ቀን ፲፱፻፴ ዓ.ም. ተጻፈ። ፊርማ ደጃዝማች መንገሻ ጀመሬ(ጀምበሬ)።” ገጽ 165

“ይድረስ ለክቡር ወንድሜ አቶ ተስፋ ሚካኤል። በመክበር ሰላምታዬን አቀርባለሁ፤ እኔ ቤተሰዎቼም ደህና ነን፤ አምላክ ይመስገን። የላኩልኝ ደብዳቤ ደረሰኝ። ይኸውና በዚህ በኩል ባለፈው መስከረም የጀመርን እስከ ግንቦት ድረስ አልቦዘንንም፤ ብርታቱም ወደኛ ነበር። ባላባቶች በሀገር እየተቀያየሙ ከግንቦት ወዲህ ለጠላት ጉልበት ሰጡት። ፭ት ካምቦ የነበረው ፩ ተከለበት፤ ተከቦ በያለበት ተቀምጦዋል። በጌምድር ባሁኑ ጊዜ በጣም ጠንክሮዋል፤ እስከ መስከረም ድረስ ካለ ጎንደር ከተማው የሚቀረው አይመስልም።” ገጽ 166

“የጐጃም ሕዝብ ሳያውቁት አይቀሩም፤ ገንዘብ ወዳጅ ነውና ጠላታችን ጭካኔውን ትቶ በማታለል መስበክ ጀምሮዋል። ባላገርን በገበያ ሲሰቅል የነበረው ጣሊያን አሁን ግን እየገባችሁ ብረት አንሱ እያለ እርስ በርሳችን ሊያፋጀን አስቦዋል። እነ አቶ ገብረ መስቀል ሳይደርሱ መላላት ጀምሮ ነበር፤ አሁን ግን ዳር እስከ ዳር ተጽናንተዋል። አንድ ዋና ቢሆን ለወደፊቱ ደግ ነበር፤ በእውነት ለሀገራችው ነፃነት ብቻ አስበው የተነሱ ያለ ደጃች መንገሻ በጐጃም በኩል ያገኘ አይመስለንም። እኔ ቤቴን ለቅቄ ከርሳቸው ጋራ ነኝ ያለሁ። በሕይወት ያገናኘን ቤተሰዎቼ ለቤተሰዎችም ጭምር ሰላምታቸውን ያቀርባሉ። ሰኔ ፫ ቀን ፲፱፻፴ ዓ.ም. ጐጃም ፊርማ፣ ጊላጊዮርጊስ (የዛሬው ፊታውራሪ)” ገጽ 166

“ይድረስ ለክቡር ወንድሜ፣ ወዳጄ ካቶ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ፤ ከተለያየን እስካሁን ጤናዎን እጅጉን እንደምን ሰንብተዋል። እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ፤ የርስዎንና የልጆችዎን ደህንነት በሰማሁ ጊዜ እጅግ ደስ አለኝ። አሁንም የሚመጣ ሰው ሲገኝ እደጃዝማች ነጋሽ ድረስ ይጻፉልኝ፤ ይደርሰኛል። ይኸ መኰነን ደስታ የኔ ወንድም ነውና በማናቸው በሚቸገርበት ነገር ሁሉ እንዲረዱት ስል አጥብቄ እለምንዎታለሁ፤ በዚያ ሀገር ዘመድ የለውም። አደራ። ነሐሴ ፭ ቀን ፲፱፻፴ ዓ.ም. ጐጃም። ፊርማ አለማየሁ ቦጋለ።” ገጽ 166

“ይድረስ ለክቡር አቶ ተስፋ ሚካኤል፣ እጅጉን ለጤናዎ እንደምን ከርመዋል? እኔ አምላክ ይመስገን ደህና ነኝ፤ እንኳን ዘመን ከዘመን አሸጋገረዎ፤ ይኸው ከዚህ ቀደም ፲፱፻፴፪ ዓ.ም. በሐምሌ በገዳሪፍ መኖርዎን ሰምቼ ጽፌለዎት ነበር። ይህም ደብዳቤ ሣይደርስዎት በመቅረቱ በጣም አዘንሁ። አሁንም ከዚህ ቀደም ከመጣው መሣሪያ ለአርበኛ አንድ አልደረሰልንም፤ እና ስለዚህ ኅሳብ እንዲያስታውቁልኝ። የኢትዮጵያ አምላክ ረድቶ በሕይወት ለመገናኘት ያብቃን። ፊታውራሪ ካሣ ኪዳነ ማርያም የጃንሆይን ድምጽ ስለሰሙ እኔም ስለላኩባቸው ፶ ራሳቸው ሆነው ከነ መሣሪያቸው ከጠላት ወደኔ መጥተው መግባታቸውን አስታውቀዎታለሁ። ጥቅምት ፳፩ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ጸገደ። ፊርማ፣ ደጃዝማች አዳነ መኰነን።” ገጽ 167

“ገዳሪፍ፣ መስከረም ፲ ቀን ፲፱፻፴፩ ዓ.ም. ይድረስ ለክቡር ደጃዝማች ሕይወት መሸሻ፣ ትግሬ። እንደምን ከርመዋል ለጤናዎ? እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን እኔ ደህና ነኝ። የእርስዎ ብርታትና ትልቅ ጀግንነት በዓለም ሁሉ በመሰማቱ እድልዎ ከሁሉ ያማረና ታሪኩዎም የበለጠ መሆኑን አስቀድሜ አረጋግጥለዎታለሁ። ግርማዊ ጃንሆይም ብዙ ጊዜ ድህንነትዎን ጠይቀው ጽፈውልኛል፤ ስለዚህ በሕይወት የመኖርዎን ምልክት ደብዳቤ ይጠብቃሉና በቶሎ የሁሉን ነገር ገዳሪፍ ድረስ በኔው ስም ቢልኩት ይደርሳቸዋል።” ገጽ 167

በድፍን ኢትዮጵያ ያለውን ጣሊያን በያለበት መከበቡን፣ መሞቱን፣ በከንቱ ማለቁን የዓለም ሕዝብ በብዙ ያደንቃል። በአውሮጳም ታላላቆች መንግሥታት ጋራ በቅረብ ቀን ለጦርነት ውጊያ ለመግጠም ተፈራርሟል። አስቀድሞም በሀገሩ በረኃብና በእስፓኛም ጦርነት ብዙ ሺህ ሰው ሲሞትበት መሣሪያም አልቆበታል። ስለዚህ ጣሊያን ከኢትዮጵያ ፈጽሞ በፍጥነት መውጣቱንና የነፃነታችን ቀን በርግጥ መድረሱን አይጠረጠርምና ለሕዝባችን አስተካክለው ያስረዱት። በሞኝነቱ የጠላቱ ረዳትና ደም ከፋይ እንዳይሆን ያበረታቱት፤ ይምከሩትም።” ገጽ 167

“፪ኛ ጀርመንና ቺኮስሎቫኪያ ጦርነት ገጥመው ኤውሮጳ በነሱ ምክንያት ብርቱ ፍራትና መንቀጥቀጥ፣ ሞትና መደበላለቅ ተነስቶበታል። በበጌምድርና በጐጃም፣ በሸዋና በሐረር፣ በለቀምትና በጅማ፣ በሲዳማ፣ በወሎና በሰቆጣ፣ በሺረ፣ በአድያቦና በሰቲትም በያለበት ጣሊያን ተከቦዋል። ከብዙውም ቦታ ለቆዋል። የቀረው በምሽጉ ውስጥ ብቻ ነው ይባላል። ሁሉም ነገር አጣርተው በፍጥነት ደብዳቤዎን ይላኩልን። በሕይወት፣ በደስታ በእግዚአብሔር ያገናኘን፤ አሜን። ፊርማ፣ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ። ገዳሪፍ፣ መስከረም ፲ ቀን ፲፱፻፴፩ ዓ.ም.።” ገጽ 168

“ለክቡር ካህና ኣባ ጨርቆስ፤ ሐውሣ። ዛሬ የመጣልኝ ሐዲስ የምስራች። የጄኔራል ባዶሊዮ ወንድም የ፲፮ በጦሎኒ አለቃ ሆኖ የዘመተ በባህር ዳር ዘጌ ሲሄድ በጥይት ቆስሎ ሞተ፤ ሰዎቹም አለቁ፤ ሱዳኖች ግን አምልጠው ኣየበረሩ እብድ ሆነው አገራቸው ገብተዋል። እንግሊዝና ፈረንሣዊ፣ መስኮብና አመሪካን የኢትዮጵያን መንግሥት ረዳቶች ሆነዋል፤ የጉባኤው ስብሰባ መስከረም ፲፪ ቀን ነው- የኢትዮጵያ ጉዳይ ነገር የሚፈጸምበት።” ገጽ 168

ክቡር ሆይ፣ ባጭሩ ቃል ጠላታችን ጣሊያን አልቆዋል፤ ከሀገሩም ጦር መጨመር ምንም አይችልም። በኤውሮጳ ትልቅ የጦርነት ቃጠሎና ድብልቅልቅ ያለ ብርቱ ውጊያና ልቅሶ ደርሶበታል። የኛ የኢትዮጵያውያን ደስታ ግን ቀርቦዋልና ሕዝቡን ያጥናኑት፤ ይምከሩት። ፊርማ፣ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ።” ገጽ 168

“ይድረስ ለክቡር አቶ ተስፋሚካኤል። እጅጉን እንደምን ሰንብተዋል? ባለቤትና ልጆችዎስ እንደምን ሰንብተዋል። እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። እስከ ዛሬ ድረስ እዚህ መኖርዎን ሳላውቅ ወደ ካርቱም ወረቀት ጽፌለዎ ነበር፤ መድረሱን አለመድረሱን አላውቅም። ኃጢያታችን ቢበዛ ለአረመኔ አሳልፎ ሰጠን፤ አሁን ግን ይቅር ሊለን ነውና ለሀገርዎ ምሕረት ያብቃዎት። ሰላመ እግዚአብሔር ከነቤተሰዎችዎ ይጠብቍዎት አውሳ ጥር ፲፩ ቀን ፲፱፻፴፩ ዓ.ም. ፊርማ፣ ኣባ ጨቆስ።” ገጽ 168

ይድረስ ለክቡር ርእሰ መኳንንት አቶ ተስፋ ሚካኤል እንደምን ሰንብተዋል ለጤናዎ? እግዚአብሄር ይመስገን እኔ ደህና ነኝ፤ ደብዳቤዎም ደረሰኝ፤ እግዚኣአብሔር ይስጥልኝ፤ ስለ የ፲፫ ት ሰዎች ነገር ስለጻፉልኝ። ሰው ለሃይማኖቱ ብሉ የደከመ እንደሆነ ከሰው ባያገኘው ከእግዚኣብሔር ያገኛል። አሁንም እርስዎ ለስደተኞች ብለው የለፉት፣ የደከሙ እንደሆነ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያገኙታል። እኔም እንደ አቅሜ ስለ ሃይማኖትና ስለ ስደተኞች ብዬ የላኩኝን ሁሉ እፈጽማለሁ። በደህና ለመውጣቴ ለጃንሆይ ቢያመለክቱዋቸው ደግ ነው፤ ይቤ ታዛጅዎ። ኃደሊያ ሚያዝያ ፰ ቀን ፲፱፻፴ ዓ.ም. ፊርማ፣ ቀኛዝማች ዓምደ ማርያም ተስፋ ጽዮን።” ገጽ 169

“ካርቱም መጋቢት ፳፩ ቀን ፲፱፻፴፩ ዓ.ም. ይድረስ ለክቡር አቶ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ። እጅጉን እንደምን ሰንብተዋል? እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። ባለቤትዎ በደህና ካርቱም ደርሰዋል። ያመጡትም ደብዳቤ ደርሷል፥፡ ወደ ባለቤቱ አስተላልፌ መላኬ ነው። ከወገራ የመጣው ደብዳቤ ደርሶኛል። ነገር ግን በፖስታ የማይላክ ዋና ፖስታ አለ ብለው በደብዳቤ ያስታወቁኝ ገና አልመጣልኝም። የታመነ ሰው ሲገኝ እልክልሀለሁ ብለውኝ ነበርና እጠብቃለሁ። ለባለቤትዎ ቢልኩልኝ ኖሮ ደግ ነበር። ለወደፊት ግን አቶ እሸቴ የመጣ እንደሆነ ለርሱ ይላኩልኝ። እርሱ ግን ካልመጣ እኔ ከዚህ ሰው መላኬ አይቀርም። ይህ ነገር በጣም ጥንቃቄ የሚያስፈልግ ነው። ላቶ አብርሃ ሰላምታዬን እንዲነግሩልኝ እለምነዎታለሁ። ጤና ይስጥዎ። ፊርማ ወዳጅዎ ዳባ ብሩ።” ገጽ 169

በቀጣዩ የምዕራፍ ሠላሳ ስድስተኛ ምዕራፍ ትረካቸው፡ አርበኛው ተስፋ ሚካኣኤል ትኩእ ኬኒያ ከነበሩ አርበኞችና ስደተኞች ጋር የተጻጻፏቸውን ደብዳቤዎች ለመታሰቢያነት እንቃኛቸዋለን።

ይህን ታሪክ ብርቅ የሚያደርገው አሁን ያለው አዛውንት ትውልድ ንፍጡ ባፍንጫው ይዝረከረክበት በነበረ ወቅት ለነጻነቱ ሲል ብርቱ ገድልን ባከናወነ ኤርትራዊ አባት አርበኛ የዓይን እማኝነት የተጻፈ ቅንነትን የተላበሰ በሳል ፖለቲካዊ ትንታኔ መሆኑ ነው።

Post Reply