Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Atomsa
Member
Posts: 174
Joined: 03 Nov 2017, 06:53

የትግራይ ማህበር በአሜሪካ የአስኳይ ግዜ አዋጁንና የሰዎችን መገደል እንደሚደግፉ ገለጸ!

Post by Atomsa » 07 Mar 2018, 10:07

የትግራይ ማህበር በአሜሪካ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ማርች 4, 2018 ያወጣውን መግለጫ ከዚህ በታች አንብቡ።
Image
በአሜሪካ የትግራይ ኮምዩኒቲዎች ፎረም

በአገራችን ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

እኛ በኣሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የምንገኝ የትግራይ ኮምዩኒቲ ማህበራት መሪዎች ባቋቋምነው የጋራ ፎረም አማካኝነት ዛሬ ማርች 4, 2018 ተሰባስበን ስለ ሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በጣም አሳስቦን፥ የተጀመረውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትና ዳዴ በማለት ላይ ያለው የዲሞክራሲ ፋና ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ እንዲሁም ለዘመናት ተሳስቦና ተከባብሮ የኖረው ህዝባችን ኢትዮጵያዊ ጨዋነቱን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንዲያስረክብ ባለን ጠንካራ ፍላጎትና ሃገራዊ ሃላፊነት ተነሳስተን በጥልቀት ከተወያየን በኋላ የሚቀጥለው ባለ 11 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል።

1. የሃገራችን ኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት መጪው ትውልድ ከድህነት ተላቆ የተሻለ ህይወት እንዲመራ ያስችለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣቱ በአንዳንድ የሃገሪቱ ክልሎች የሚያወድማቸው መሰረተ-ልማቶች በወጣቱ የወደፊት እድል ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ስለሚኖራቸው በዚሁ ጉዳይ ላይ የነገው ሃገር ተረካቢ የሆነው ወጣቱን የሚጎዳ መሆኑን በቂ መረጃና ትምህርት እንዲሰጠውና ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲያስተጋባ እንዲደረግ እንጠይቃለን።

2. በትምህርት ጥራት ይሁን በስራ ፈጠራ መስክ መንግስት ያለበትን ሃላፊነት በመወጣት ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እርምጃዎች በወቅቱ እንዲወሰድ እንጠይቃለን።

3. የሃገራችን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት በማለት ኢህአዴግ የታሰሩትን የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎችና አባላት በመፍታት ብሄራዊ መግባባት እንዲሰፍን ማሰቡ እንደግፋለን። ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚ ሃይሎች ህዝብንና ሃገርን የመምራት ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ተገንዝበው በሚያገናኙዋቸው አብረው የሚሰሩበት በማያገናኙዋቸው ደግሞ ህዝቡ ነፃና ፍትሃዊ በሆነ ምርጫ በካርዱ እንዲመርጣቸው የተመቻቸ ሁኔታ እንዲፈጥሩና ከጠላትነት አባዜ ወጥተው ተፎካካሪ ድርጅቶች ለመሆን እንዲበቁ አጥብቀን እናሳስባለን።

4. የሃገራችን ሰላም እየደፈረሰ፣ በሰው ህይወትና ንብረት አደጋ እየደረሰ ባለበት በአሁኑ ጊዜ መንግስት ያወጀው ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደግፋለን። ይህ አዋጅ ስንደግፈው የሚያመጣውን ሰላም በመጠቀም መንግስትና የተቃዋሚ ሃይሎች ለተፈጠሩ ችግሮች ሰከን ብለው በማሰብ መፍትሄ ለማምጣት እንደሚጠቀሙበት በማመን ነው። ስለሆነም የሃገሪቱ መረጋጋት ሳይረጋገጥና አስፈላጊ መፍትሄዎች ሳይቀመጡ አዋጁ በችኮላ እንደበፊቱ እንዳይነሳና ሃገሪቱ እንደገና ወደ ህውከትና ብጥብጥ እንዳትመለስ አጥብቀን እናሳስባለን።

5. በጎንደር የተጀመረውና እስከ ወሎ ድረስ የዘለቀው የዘር ጥላቻ በትግራይ ተወላጆች ህይወትና ንብረት ላይ የተፈፀመው አረመኔዊና ከወገን የማይጠበቅ አፀያፊ ኋላቀር ድርጊት አጥብቀን እናወግዛለን።

በተመሳሳይም በኦሮሚያና በሶማሊያ ክልል አጎራባች መንደሮችና ከተሞች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ምክንያት የደረሰው የህይወትና የንብረት ውድመት አጥብቀን እናወግዛለን። የመርማሪ ቡድን ባልተቋቋመባቸው አካባቢዎችም ባስቸኳይ ተቋቁሞ ድርጊቱን በሚገባ ተጣርቶ ወንጀሉን በፈፀሙ አካላት ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድና ለህዝቡም ይፋ እንዲሆን አጥብቀን እንጠይቃለን። መንግስትም ዜጎች ለህይወታቸው ሳይፈሩ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል የመኖር፣ የመስራትና ሃብት የማፍራት መብታቸውን የማስከበር ሃላፊነትና ግዴታውን እንዲወጣ እንጠይቃለን። ለተፈፀሙ ወንጀሎችም ሃላፊነት በመውሰድ መንግስት ህይወታቸው ላጡና በህይወት ላሉ ተጎጂዎች የገንዘብና የንብረት ካሳ እንዲያደርግላቸውና ወደነበሩበት ቦታ ተመልሰው ደህንነታቸው ተጠብቆ በሰላም እንዲኖሩ ይደረግ ዘንድ እንጠይቃለን።

6. የተከሰተው የሃገሪቱ አለመረጋጋት፣ እጅግ አደገኛና አሳሳቢ ከመሆኑም በላይ እንዳይባባስ መንግስት፣ ተቃዋሚ ሃይሉና ህዝብ ከሁሉም በፊት ያገሪቱን ህልውና ቅድሚያ እንዲሰጡ እንጠይቃለን።

7. ዜጎች የማንም ፖለቲካና ፓርቲ ደጋፊ በመሆናቸው ይሁን በብሄር ማንነታቸው እንደጠላት የሚፈርጁ፣ አደጋ የሚያደርሱና ለማድረስ የሚሞክሩ ሰዎች የሚቀጡበት “የጥላቻ ወንጀል መቅጫ ህግ” ካለ ተግባራዊ እንዲሆን ከሌለ ደግሞ እዲደነገግ ኣጥብቀን እናሳስባለን።

8. ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈፀመ ያለው መጠነ ሰፊና በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ የስም ማጥፋትና የጥላቻ ዘመቻ መሰረተ ቢስ ከመሆኑም በላይ በሃገራችን ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅእኖ ቀላል ስለማይሆን ይህ ዘመቻ በመንግስት፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በታዋቂ ግለስቦችና ተቃዋሚ ሃይሎች በጥብቅ ተወግዞ ተከታታይ ትምህርትና እርምት እንዲሰጠው አበክረን እንጠይቃለን።

9. በኢትዮጵያ ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጪ የምንኖር የትግራይ ተወላጆች በዚሁ አሳሳቢና ፈታኝ ወቅት እንደ ወትሮው ትእግስትን እንድንመርጥ እያሳሰብን በማንኛውም ጊዜ ከህዝባችን ጎን የምንሰለፍ መሆናችንን እናረጋግጣለን።

10. በብዙ ሺህ የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ የህይወት መስዋእትነት የከፈለባቸው መሰረታዊ የዲሞክራሲ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ እንጠይቃለን። ፍትህና መልካም አስተዳደርን ያጎደሉ፣ የህዝብን ንብረትና ገንዘብ የዘረፉ፣ የመንግስትና የፓርቲ ባለስልጣናት በህግ ፊት ቀርበው እንዲቀጡ እንጠይቃለን።

11. የኢትዮጵያ ህልውናና የህዝቦቿን አንድነት የሚፈታተኑ በውስጥም ይሁን በውጭ ሃይሎች የሚዶለቱ ሴራዎችን እናወግዛለን።

እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
http://welkait.com/wp-content/uploads/2 ... 030618.pdf


Post Reply