በኩር፤ ሐምሌ 23 ቀን 2010 ዓም
አማራን የሚያገልና የሚጨቁን የፌዴራሊዝም አተገባበር ነው የነበረው!!
ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር መምህር ናቸው:: በሰብዓዊ መብት ዙሪያም የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አላቸው::
ዶክተር ሲሳይ በአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ በምክትል ሀላፊነት ያገለገሉ ሲሆን በቀድሞ ስሙ የኢህዴን (ብአዴን) ታጋይም ነበሩ:: ዶክተሩ የዚህ እትም እንግዳችን ናቸው::
መልካም ንባብ!
ስምዎ በተለየ ሁኔታ ከራያ ህዝብ ጋር ብዙ ጊዜ ይነሳል:: ምክንያቱ ምንድን ነው?
ተወልጀ ያደግሁ ራያ ውስጥ ነው:: በራያ ስማር በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት ወደ ኢህዴን ገብቸም ታግያለሁ:: ኢህዴን /ብአዴን/ በነበርኩበት ጊዜ የራያን ህዝብ መብትና ጥቅም እንዲጠበቅ እታገል ነበር:: የራያ ህዝብ ፍላጐት ሳይጠየቅ በሁለት ክልሎች እንዲተዳደር ተደርጓል:: በ2005 ዓ.ም የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ እና የማዕከላዊ መንግሥታት ምላሽ ከአፄ ዮሐንስ እስከ ኢህአዴግ የሚል መጽሀፍ ከጓደኛዬ ጋር ሆነን አዘጋጅተናል:: የራያን ህዝብ ታሪክ እና ተጋድሎም እያሳወቅሁ ነው:: የራያን ህዝብ ተጋድሎ ትግራዮች ደግሞ ቀዳማዊ ህዝብ ወያኔ ትግል የሚሉትን ታሪክ በተመለከተ በማስረጃ ሞግተናል:: ቀዳማዊ ህዝብ ወያኔ የራያ ህዝብ ታሪክ ነው:: በዚህ ጉዳይ ጽፌያለሁ፤ሞግቻለሁ:: ለዚህ ይመስለኛል ስሜ ከራያ ህዝብ ጋር ጐልቶ የሚነሳው::
የራያ ህዝብ ስነ ልቦናዊና ባህላዊ ቅርበቱ ከየትኛው ማህበረሰብ ጋር ነው?
የራያን ህዝብ ሠዎች በተለያየ መንገድ ይገልፁታል:: የራያ ህዝብ ስንል በድሮው የራያ ቆቦና አዘቦ አውራጃ የሚኖር ህዝብ ድምር ነው:: የራያነት ስነ ልቦና አለው:: ራያ የነ ጥላሁን ግዛው ሀገር ነው:: አማርኛ ይነገራል:: ትግረኛ የሚመስል