አቶ ገብረዋሕድ በአጠቃላይ በስርዓቱ ዉስጥ አብረዋቸው ስለቆዩት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሐብት መጠን ሲዘረዝሩ ይቆዩና ‹‹እኔ መቼ ሙስና አሳሰረኝ፡፡ የማይሆን ክር ባልመዝ ኖሮ ጫፌን የሚነካኝ እንዳልነበረ ከእኔ በላይ የሚያውቅ አልነበረም፡፡›› ሲሉ በቁጭት እንደሚናገሩ ጽፏል፡፡
የዉብሸት ታዬ የግዞት ወጎች መጽሐፍ አታሚውም ሆነ አሳታሚውም በዉል አይታወቅም
‹‹ሞጋች እውነቶች››
ዋዜማ ራዲዮ– ከዛሬ አምሰት ዓመታት በፊት ሰኔ 12፣ 2003 ከሁለት ዓመት ሕጻን ልጁ ፊት በካቴና ታስሮ ወደ ማረሚያ ተወረወረ፡፡ ሽብርተኛ በሚልም የ14 ዓመት ፍርድ ተፈረደበት፡፡ በ2006 ዓ.ም. ‹‹የነጻነት ድምጾች›› የሚል መጽሐፉን ለንባብ አበቃ፡፡ ከ2 ዓመታት የእስር ቆይታ በኋላ ደግሞ ትናንት ረፋድ ላይ ‹‹ሞጋች እውነቶች›› የተሰኘውን መጽሐፍ ለአንባቢ አቀረበ፡፡ ጋዜጠኛ ዉብሸት፡፡
የመጽሐፉ ዋጋ 71 ብር መሆኑን የሚገልጽ መረጃ ከሽፋኑ ማግኘት ይቻላል፡፡ ‹‹ሞጋች እውነቶች›› የትኛው ማተሚያ ቤት እንደታተመ የሚገልጽ መረጃ ግን ፈልጎ ማግኘት አይቻልም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጠነከረ ከመጣው አፈና ጋር ተያይዞ ማተሚያ ቤቶች ስማቸው ፖለቲካዊ ይዘት ባላቸው መጽሐፎች ላይ እንዳይገለጽ አጥብቀው ይማጸናሉ፡፡
‹‹ሞጋች እውነቶች›› የቀድሞው የአውራምባ ታይመስ ምክትል ዋና አዘጋጅ የዉብሸት ታዬ የግዞት ወጎች የተሰባሰቡበት ባለ 224 ገጽ መጽሐፍ ሲሆን እንደ አታሚው ሁሉ አሳታሚውም በዉል አይታወቅም፡፡
በመጽሐፉ የሽፋን ምስል ላይ ዶሮና አንበሳ በፍጥጫ ምልክ ሲጮኹ የሚያሳይ ፎቶ የሚታይ ሲሆን ይህንኑ ለማብራራ ይመስላል በመጀመርያው የመጽሐፍ ቅጠል እንዲህ የሚል መግለጫ ሰፍሯል- ‹‹ሁለቱም ቡድናቸውን ይመራሉ፤ ሁለቱም ለቡድናቸው ይፋለማሉ፡፡ አንዱ ጥሮ አዳሪ፣ ሌላው ሰብሮ አዳሪ ናቸው፡፡››
ዉብሸት ታዬ በእስር ሳለ አባቱን