Blog Archives

ለውጡ እንዳይቀለበስ! ብርሃኑ አበጋዝ

ዶ/ር ብርሃኑ አበጋዝ – አዲስ አበባ አብዮታዊ ሁኔታ ላይ ነን፡፡ የአብዮቱ ፍጻሜ ግን ገና አልለየለትም፡፡ እንደማንኛውም አብዮት፣ ሒደቱን የሚደግፉ ኀይሎች አሉ፤ አምርረው የሚቃወሙ አሉ፤ መሃል ሰፋሪ የሆኑና ከአሸናፊው ኀይል ጋር ለመሰለፍ አድፍጠው የሚጠብቁ ወገኖችም አሉ፡፡ አብዮቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመመሥረት የሚያስችሉ ምሰሶዎችን በማቆም ፍጻሜ የሚያገኝ ከሆነ ሁሉም ተቀናቃኝ ኀይሎች ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አይሆኑም፡፡ አብዮቱ ከተቀለበሰ ግን የአገሪቱ እጣ ፈንታም አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም፡፡ በአንድ በኩል የታየውን እጅግ ጣፋጭ የለውጥ አየር ለማስቀጠል በሚታገለው እና ለውጡን ለማዳፈንና አገሪቱን ወደባሰ አዘቅት ለመመለስ በሚፈልጉ ወገኖች መሀከል የሚነሳው ግጭት ለብዙ ዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት ይሆናል፤ የአገሪቱ ህልውናም ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል “የለውጥ ኀይል” እየተባለ የሚጠራው ወገን አብዮቱን ከቅልበሳ ለመከላከል በሚል ሰበብ በሕዝብ ግፊት ዜጎችን በገፍ ማሰርና መግድል የጀመረ እንደሆነም ፍጻሜው ያማረ አይሆንም፡፡ ከዚህ ለውጥ አገርና ሕዝብ ሊጠቀሙ የሚችሉት ለውጡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ወደ መገንባት የሚሄድና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የሚጥል ከሆነ ብቻ ነው፡፡ የየካቲት 66ቱ አብዮት አጀማመር ብሩህ ነበር፡፡ መጨረሻው ግን አላማረም፡፡ የግንቦት 1983ቱ ለውጥም ቢሆን ብዙዎች ከፍ ያለ ተስፋ የጣሉበት ነበር፡፡ ሆኖም እሱም የአንድ ቡድንን አምባገነንነትን በማስፈን ነው የተጠናቀቀው፡፡ የአሁኑ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ የሚደግፈውና ብዙ ተስፋ የሰነቀበት ለውጥ እንደቀደሙት ለውጦች አገርና ሕዝብን በሚጎዳ መልኩ እንዳይቋጭ ከዜጎች ብዙ ይጠበቃል፡፡ ከታሪካችን መማር ይኖርብናል፡፡ መድኅናችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ ሁላችንም በሕግ ፊት እኩል የምንሆንበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው እኛንም አገራችንም የሚያድነን፡፡
Tagged with: , ,
Posted in Amharic News, Ethiopian News