Blog Archives

ሰበር ዜና:- የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አዲሱን የጸረ-ሽብር ሕግ አጸደቀ

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ጉባኤው በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፤ የሕግ ማሻሻያ ም/ቤት ተሻሽሎ የቀረበለትንና ለመንግስታዊ አፈና ውሏል በሚል ከፍተኛ ነቀፌታ ሲቀርብበት የነበረውን የጸረ ሽብርተኝነት ሕግ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ፡፡ የኢፌዴሪ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001 ተብሎ የሚታወቀው የአፈና ሕግ ከወጣ በኋላ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሲቪክ ማሕበረሰብ አባላት፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ሌሎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የዚህ ክስ ሰለባ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በተለይ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ነፃነትን ለማፈን በሚል የአዋጁ አንቀጽ 6 ቁጥር 3 ላይ የጸሐፊዎቹ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን በአንባቢው ላይ ሊፈጥር ይችላል ብሎ በሚገምተው በማንኛውም የተለጠጠ ትርጓሜ ሲያስቀምጠው ‹‹አንባቢዎቹ የሚያነቡት ነገር ድርጊቱን እንዲፈጽሙ፣ ወይም ለመፈጸም እንዲዘጋጁ፣ ወይም በማናቸውም ሌላ ሁኔታ የሚገፋፋቸው እንደሆነ አድርገው ይረዱታል ተብሎ ሊገመት የሚችል መልዕክት እስከ 20 ዓመት ጽኑ እስራት ያስቀጣል›› ማለቱ በሕጉ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቶ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በዛሬው ዕለት በጸደቀው በዚህ ሕግ ላይ አቶ አበበ ጎዴቦ ስለሽር ሕጉ አስፈላጊነት ሲዘረዝሩ የሽብር ድርጊት በሰው ህይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ የሚፈጥረውን ምስቅልቅል አስቀምጠዋል፡፡ በዚህም ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መሰጠቱን እና ለረቂቅ አዋጁ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች መገኘታቸውን አውስተዋል። በመጨረሻም አዋጅ ቁጥር 652/2001 በ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ ብቻ መጽደቁን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል፡፡ —
Tagged with: ,
Posted in Amharic News