ከሰሞኑ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በባህር ዳር በተደረገ መስራች ጉባኤ የተመሰረተ ሲሆን የፓርቲውን ሊቀ መንበርና የስራ አስፈፃሚ አባላትንም መርጧል፡፡ ፓርቲውን በመመስረት ሂደት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ አሁን በሊቀ መንበርነት የተመረጡትን ጨምሮ 16 ሰዎች በኮማንድ ፖስት ታስረው መፈታታቸው የሚታወስ ሲሆን ፓርቲው ሲመሰረት የክልሉ መንግስት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ትብብር አድርጎላቸዋል፡፡
ለመሆኑ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) አላማና ግብ ምንድን ነው? የትግል ስልቱስ? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የፓርቲው ሊቀመንበር፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህሩን ዶ/ር ደሣለኝ ጫኔን፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በአጭሩ አነጋግሯቸዋል፡፡
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄን (አብን) ለመመስረት ምክንያታችሁ ምንድ ነው?
መሠረታዊ መነሻ ምክንያታችን፣ በአማራ ህዝብ ላይ ባለፉት ዓመታት እየደረሰ ያለው፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ ግፍና መከራ ነው፡፡ የአማራ ህዝብ ህልውና አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ ያንን ደግሞ በአግባቡ ይዞ መታገልና ለህልውናው መከበር የሚሠራ ድርጅት ስለሌለ፣ ክፍተቱን ለመሙላት ነው ድርጅቱን የመሰረትነው፡፡
የፓርቲያችሁ ዓላማና ግብ ምንድን ነው?
ዓላማዎቹ ብዙ ናቸው፡፡ አንደኛው፤ አሁን የአማራ ህዝብ ከኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ተገልሏል፡፡ ጥቅሞቹ እየተከበሩ አይደለም፤ ስለዚህ እነዚህን ጥቅሞቹን ማስከበር የመጀመሪያው አላማ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ማንነታቸውን እየጠየቁ ያሉ አማሮች መገለጫዎቻቸው እየተከበሩ አይደለም። የአማራን ህዝብ ሁለተንናዊ ማንነት ማስከበርና ማስጠበቅ ሌላው ነው፡፡ ሌላው አጠቃላይ በአማራ ክልልም ሆነ ከክልላችን ውጪ ያሉ ወገኖቻችን የመገደል፣ የመሠደድ፣ የመፈናቀል፣ ሃብታቸው የመውደም ችግር እየደረሰባቸው በመሆኑ፣ እነዚህን የመመከት፣ የመከላከልና እንዲቆም የማድረግ ትግል ነው፡፡ የአማራ ህዝብ ለኢትዮጵያ የሚያበረክተውን ሁለንተናዊ አስተዋፅኦና በዚህች ሃገር ሊኖረው የሚገባውን ድርሻ ማሳደግም