ጋምቤላና የዘውግ ፖለቲካ ተግዳሮት
***
ቴዎድሮስ ኀይለ ማርያም (ዶ/ር)
(የታሪክና የብሔርተኝነት ጥናት ምሁር)
***
በደቡባዊ ምዕራብ ኢትዮጵያ ተንጣልላ የምትገኘው አረንጓዴዋ በረሃ ጋምቤላ በውስጧ አምስት ዋና ዋና ተወላጅ ብሔረሰቦችና፣ ቀድሞ ደገኛ የሚባሉ ዛሬ ደግሞ በመጤነት የተመደቡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይኖሩባታል። ከአገሬው ብሔረሰቦች ዋነኞቹ አኙዋ፣ ኑዌርና መጀንግር ቢሆኑም፣ ባለፉት መቶ ዓመታት የጋምቤላ ውስጣዊ ፖለቲካ ወሳኝ ጉዳይ በአኝዋና በኑዌር መካከል የነበረው ክፉም ሆነ ደግ መስተጋብር ነበር። እነዚህ ወንድማማች ብሔረሰቦች በአሰፋፈር፣ በባህል፣ በኤኮኖሚ ዘይቤና ማኅበራዊ አደረጃጀት ልዩነቶች ቢኖራቸውም፣ ለረዥም ዘመናት በጋራ ልማድ፣ በጋብቻ፣ በታሪካዊና ኤኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ተሳስረው አንዴ ሲጋጩ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲታረቁ ኖረዋል።
በአስተዳደራዊ ቅርፅ ከወረዳነት እስከ ክልላዊ መንግሥትነት የዘለቀችው ጋምቤላ፣ ከ1890ዎቹ ጀምሮ ባለፉት መቶ ምናምን ዓመታት ሦስት የኢትዮጵያ አገዛዞች ተፈራርቀውባታል። እነዚህ መንግሥታት የተከተሉት ከበርቴያዊ፣ ኅብረተሰባዊና ጎሳዊ የአስተዳደርና ፖለቲካ መርሆዎች የክልሉን ማኅበራዊ ግንኙነት ከሚዘውሩ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ነበሩ። ዛሬ በጋምቤላ የሚታየውን ግራ የሚያጋባ የደም መፋሰስ አዙሪት ለመረዳት፣ በነዚህ ዘመናት የታዩትን ታሪካዊ ሒደቶች መተንተን ያስፈልጋል። በነዚህ ዘመናት የሕዝቦች አሰፋፈርና እንቅስቃሴ እንዴት ነበር? በቡድኖች መካከል ያለውን ግንኙነት የቀየሩ ውስጣዊና ውጫዊ መንስኤዎች ምንድናቸው?
ዘውዳዊ አባታዊነት
***
ከመነሻው ታላቁ የጋምቤላ ችግር ውስጣዊና ውጫዊ የመሬት ወረራ ነው። ውስጣዊ ወረራ በክልሉ ባሉ ማኅበረሰቦች መካከል የሚደረግ መገፋፋት ሲሆን፣ ውጫዊ ወረራ ደግሞ ከክልሉ ውጭ ባሉ መንግሥታዊ የሆኑና ያልሆኑ ድርጅቶቸና ቡድኖች የሚከናወን ነው። ኢትዮጵያና እንግሊዝ የድንበር ስምምነቱን በፈረሙበት በ1895 አኙዋኮች ከሞላ ጎደል በምዕራብ