ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬም ስኬታማ ነው

BBC Amharic : የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምንም እንኳ ከትናንት ወዲያ በደረሰው የቦይንግ 737-8 ማክስ ET302 አደጋ ችግር ውስጥ ቢሆንም አየር መንገዱ ዛሬም የአፍሪካው ምርጥ በመሆኑ ነው የሚታወቀው።

አየር መንገዱ አፍሪካ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ጥቂት አየር መንገዶች ተልቁም ነው።

በ2017/2018 በጀት ዓመት አየር መንገዱ 245 ሚሊዮን ዶላር ሲያተርፍ 10.6 ሚሊዮን ሰዎችን አመላልሷል።

በአፄ ሃይለ ስላሴ አገሪቷን የማዘመን እርምጃ እንደ አውሮፓውያኑ በ1945 የተቋቋመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚያው ዓመት ማብቂያ የመጀመሪያ በረራውን ወደ ካይሮ አድርጓል።

ኢትዮጵያ አየር መንገድ በቁጥሮች

  • 74 ዓመቱ ነው
  • 111 ፕሌኖች
  • 127 መዳረሻዎች አሉት በአጠቃላይ
  • 10.6 መንገደኞችን አጓጉዟል እንደ አውሮፓውያኑ 2017/2018
  • 3.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መሰብሰብ ችሏል በ 2017/2018
  • 245 ሚሊዮን ዶላር አትረፏል በተመሳሳይ ዓመት

አየር መንገዱ ማስፋፊያ ማድረጉን ተከትሎ 111 ፕሌኖች ያሉት ሲሆን አለም ዓቀፍ መዳረሻውን ወደ 106 የአገር ውስጡን ደግሞ 23 አድርሷል።

ኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 787 ድሪምላይነርና 757 ትልልቅ ጫኝ አውሮፕላኖችን ለመጠቀም የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር መንገድ ሲሆን በዚህም አዳዲስ አውሮፕላኖችን የሚጠቀም አየር መንገድ ሆኗል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አማካይ እድሜ 5.4 ዓመት ሲሆን በብሪቲሽ አየር መንገድ የአንድ አውሮፕላን አማካይ እድሜ 13.5 ዓመት፣ በዩናይትድ አየር መንገድ 15 ዓመት እንዲሁም በአሜሪካ አየር መንገድ 10.7 ዓመት ነው።

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ለደህንነት አስተማማኙ የአፍሪካ አየር መንገድም ነው። ቢሆንም እስከ አሁን አራት ከባድ አደጋዎችን አስተናግዷል።

Ethiopian airlines cargo plane

ከአሁኑ አደጋ በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ያጋጠመው እንደ አውሮፓውያኑ በ2010 ET409 ከቤሩት አውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ነድዶ ሜዲትራኒያን ላይ በመውደቁ ነበር።

በአደጋው 89 መንገደኞችና የአውሮፕላኑ ሰራተኞች ሞተዋል።

የሊባኖች የምርመራ ቡድን የበረራ ስህተት ለአደጋው ምክንያት ነው ቢልም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን አውሮፕላኑን ያጋጠመው ፍንዳታ ነው በማለት የቡድኑን ሪፖርት ውድቅ አድርጎታል።

አውሮፕላኑ አደጋው እንዲያጋጥመው የተሰራ ሴራ ፣ መብረቅ ወይም እንዲወድቅ ተመትቷል የሚሉ ግምቶችም በኤክስፐርቶች ተቀምጠዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1988 ደግሞ በባህር ዳር የአየር መንገዱ አውሮፕላን በማረፍ ላይ ሳለ ኤንጅኑ ውስጥ እርግቦች በመግባታቸው በተነሳ እሳት 35 ሰዎች ሞተዋል።

በ1996 ደግሞ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ይበር በነበረው ቦይንግ 767 ላይ ጠለፋ በመደረጉ አውሮፕላኑ በኮሞሮስ ደሴት አቅራቢያ ህንድ ውቅያኖስ ላይ መውደቁ ይታወሳል። በዚህ አደጋ ከ 175 መንገደኞች 125ቱ ሞተዋል።

የአፍሪካ መሪ

አየር መንገዱ ከራሱ አለፎ የሌሎች አፍሪካ አገራት አየር መንገዶችን ይረዳል።

በዚህ እርምጃው በማላዊ አየር መንገድ 49 በመቶ ፣ በዛምቢያ 45 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ያለው ሲሆን በሞዛምቢክም በአዲስ መልክ አየር መንገድ ስራ የማስጀመር ፕላን እንዳለው ቀደም ብሎ አስታውቋል።

በተመሳሳይ ትንንሽ አካባቢያዊ ጣቢያዎችን በጅቡቲ፣ ቻድ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ለመክፈት ንግግር ላይ ነው። እንደ ማላዊና ቶጎ ባሉ አገራት አሁንም ማእከላት አሉት።

በዚህ መልኩ ችግር ውስጥ የገቡ የአፍሪካ አየር መንገዶችን መታደግ ኢትዮጵያ አየር መንገድን በኢንዱስትሪው ትልቅ አድርጎል።

ኢትዮጵያ አየር መንገድ በጥሩ የንግድ ስትራቴጂውም ይታወቃል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እየተደረገ ያለው ማስፋፊያ በአፍሪካ አቬሽን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ ሌላ ከፍታ ይወስደዋል ተብሎም ይታመናል።

ምንም እንኳ የአሁኑ አደጋ አየር መንገዱን ቡያንገጫግጨውም የረዥም ጊዜ ራዩን እንደሚያሳካ ይታመናል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE