ሚዲያው ለአገራችን አንድነት የምንወያይበት እንጂ እርስ በርስ የምንናቆርበት ሊሆን አይገባም – አንጋፋው ጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉ

«ሚዲያው ለአገራችን አንድነት የምንወያይበት እንጂ እርስ በርስ የምንናቆርበት ሊሆን አይገባም» – አንጋፋው ጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉ
አዲስ ዘመን

“… በኛ ጊዜ ከአለቆቻችን ጋር ቅርቦች ነበርን፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ አለቆቻችን ሠርተው የሚያሠሩ፤ የሚያነቡና የሙያው ሰው በመሆናቸው…”

…በደርግ ዘመንም ፈፅሞ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት እንዳልነበራቸውም በሚገለፀው ሃሳብ አልስማማም። ሁላችንም እንደምናውቀው ደርግ አፋኝና ወታደራዊ መንግሥት ነው። ነገር ግን አሁን በሚባለው ልክ የመናገርና የመፃፍን ነፃነት አያፍንም።

… ኢህአዴግ ትልቁ የሚፈራው ጉዳይ ሃሳብን ነው። ባለፉት ዓመታት እንደልባቸው መናገር መፃፍ የሚችሉት በሱ ዙሪያ ያሉ ሰዎች ብቻ ነበሩ። ያው ቢፅፉም ስለ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ብቻ ነበር። በተቃራኒው ሌላው ሲፅፍ ይገንበታል፣ ይታገዳል፣ ይታሰራል። ኢህአዴግ መሳሪያ ይዞ ታግሎ መጥቶ ፕሬስን ለምንድን ነው የሚፈራው? ይኸው አሁን እኮ ፍርክስክሱ ወጣ አይደል እንዴ? ለነገሩ እኛ ይህ ሁኔታ እንደሚከሰት አስቀድመን እናውቅ ነበር። ለዚህ ደግሞ ትንቢት ተናጋሪ መሆን አያስፈልግም።

አ ራት ኪሎ በዓታ ለማርያም ገዳም አካባቢ በ1941 ዓ.ም ሰኔ 18 ቀን የተወለደው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በመንፈሳዊ ትምህርት ነው የጀመረው፡፡ ፊደል የቆጠረው፣ ዳዊት የደገመው፣ ወንጌል ያነበበው በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ የመምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ዜማ ቤት ገብቶ ድጓውን፣ ጾመ ድጓውን በሚገባ ተምሮ አጠናቋል፡፡ የአባቱን የአፈ-ሊቅ አክሊሉን ፈለግ በመከተል የጋዜጠኝነት ህይወቱን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ልዩ ልዩ ጽሑፎችን በማቅረብ 1958 ዓ.ም ጀመረ፡፡ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 50 ዓመታት በጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮና በአሜሪካ ድምፅ ሠርቷል፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ሬዲዮ ይተላለፍ በነበረው የእሑድ ጠዋት ፕሮግራም ላይ በሚያቀርባቸው ፕሮግራሞች በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን አግኝቷል፡፡ በግሉም እንቁጣጣሽ፣ ልደትና ፋሲካ የሚሉ የማስታወቂያ ጋዜጦች ያሳትምም ነበር፡፡ የዛሬው የዘመን እንግዳችን አንጋፋው ጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉ፡፡ መልካም ንባብ!

አዲስ ዘመን፡- የአባትህ ጋዜጠኛ መሆን አሁን ላለህበት የጋዜጠኝነት ህይወት አስተዋፅኦ አበርክቶልኛል ብለህ ታምናለህ? አባትህስ የእርሳቸውን ፈለግ እንድትከተል ግፊት ያደርጉብህ ነበር?

ጋዜጠኛ ንጉሴ፡- እውነት ነው፤ የአፈ-ሊቅ አክሊሉ ልጅ በመሆኔ ዳዊቱን፣ ጾመ ድጓውና ዜማውን ለመማር ችያለሁ። ከዚያ በኋላ ደግሞ ቅኔ ቤት ገብቼ ቅኔም ተቀኝቻለሁ። እንዳልሽው አባቴ ጋዜጠኛ በመሆናቸው ደግሞ በየቀኑ ጋዜጣ ይዘው ሲመጡ አነባለሁ። በየሊቃውንቱ ቤት እየሄድኩም እንዳነብላቸው ያደርጉኝ ነበር። ሊቃውንቶቹም ጉብዝናዬን አይተው ወደ ፊት ጋዜጠኛ ትሆናለህ ይሉኝ ነበር። አንድ ጊዜ አባቴ «አንድ ባህታዊ ስምህን የሚያስጠራ ልጅ ይወለዳል አለኝ» ብለው ከዚያ በኋላ እኔም የእርሳቸውን ፈለግ እንድከተል ከፍተኛ ግፊት ያደርጉብኝ ነበር። ግን እዚህ ለመድረሴ ዋናው ጉዳይ የእኔ ጥረት ማድረግ ነው ብዬ አምናለሁ። የማይካደው ነገር ግን አዲስ ዘመን ጋዜጣን ሳነብ ማደጌ ትልቅ ተፅዕኖ የፈጠረብኝ መሆኑ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በዚያ ወቅት አዲስ ዘመን ላይ ይፃፉ ከነበሩ ፅሁፎች ውስጥ የማትረሳቸውና የምትወዳቸው የትኞቹን አምዶች ነበር?

ጋዜጠኛ ንጉሴ፡- በዋናነት አባቴ የሚያነቡት ርዕሰ አንቀፁን ስለነበር እኔም ርዕሰ አንቀፁን አነባለው። እነጋሽ ጳውሎስ ኞኞ የሚፅፏቸው፤ ደብዳቤዎች እና ጥያቄና መልስ አምዶች ትኩረቴን ይስቡት ነበር። እንዲሁም መርስዔሀዘን፣ ሙሉጌታ ሉሌና በዓሉ ግርማ ይፅፏቸው የነበሩ ጥሩ ጥሩ ቁምነገር አዘል ፅሁፎች፣ሂሶች፣ የሚያስተምሩ፣ የሚያዝናኑ መጣጥፎችንም መርጬ አነብ ነበር። እንዲሁም የዓለም አቀፍ ዜናንም የምከታተለው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ነበር።

አዲስ ዘመን፡- ያሳለፍካቸውን የሦስት መንግሥታት የጋዜጠኝነት ህይወት ልታነፃፅርልን ትችላለህ?

ጋዜጠኛ ንጉሴ፡- እንዳልሽው በሦስቱም መንግሥታት በጋዜጠኝነት አገልግያለሁ። አሁንም በማገልገል ላይ ነኝ። ከ1965 ዓ.ም ጀምሮ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እፅፍ ነበር። በንጉሡ ዘመን ለሁለት ዓመት ያህል ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዜና ክፍል ተቀባይና ኃላፊ ሆኜ ሠርቼያለሁ። በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች በኃይለ ሥላሴ ዘመን ዘውዳዊ አገዛዝና ፊውዳላዊ ሥርዓት ስለሆነ ምንም መናገር እንደማይቻልና ፕሬስ ጨርሶ ታፍኖ እንደነበር ሲናገሩ በጣም አዝናለሁ። ምክንያቱም ትክክል ባለመሆኑ ነው። ይህንን ብታሰምሪበት ደስ ይለኛል። እርግጥ ነው ሳንሱር ነበር፤ ይኸውም በዋናነት ንጉሡንና ንግሥቲቱን የሚሳደብ፣ ሃይማኖትን የሚነካና የአገርን ክብር ዝቅ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ነው። ይሁንና «ኢትዮጵያ አልሠለጠነችም፤ መሪዎቹም በትክክል አይሠሩም» ብሎ መተቸት፣ መዝለፍ በሚገባ ይቻል ነበር።

እንዳውም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በነበረው ነፃ አምድ ላይ ‹‹በዚህ ፅሑፍ ፀሐፊው እንጂ ድርጅቱ አይጠየቅበትም›› ተብሎ የህዝብ አስተያየት ያለገደብ ይስተናገድ ነበር። አንጋፋዎቹን ጋዜጠኞች እነ ከበደ አኒሳን ብትጠይቂ በደንብ ይፃፍ እንደነበር ሊነግሩሽ ይችላሉ። ለምሳሌ መጥቀስ ካስፈለገ ከበደ አኒሳ አንድ አርቲክል ፅፎ በዚያ ምክንያት ከሥራ ተባሮ ጃንሆይ ፅሑፉን አንበውት ስለነበር ጠርተውት «ምን አደረገ እርሱ በትክክል ነው የፃፈው» ብለው ሚኒስትሩን ተቆጥተውት ወደ ሥራ መልሰውታል። እንዳውም በዚያ ጊዜ ምንም ብትፅፊ መታሰር ከሥራ መታገድ የለም። መጠንና ልክ ይኑር፤ ንጉሡንና ሃይማኖትን አትንካ ነበር የሚባለው። እነዚህ ነገሮች ደግሞ አንቺም እንደምታውቂው አደገኛ እና የአገር ሉዓላዊነት የሚነኩ ጉዳዮች ናቸው። ስለዚህ ዴሞክራሲ ጭራሽ እንደሌለ ተደርጎ የሚጠቀሰው ስህተት መሆኑን መግለፅ እወዳለሁ።

በተመሳሳይ በደርግ ዘመንም ፈፅሞ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት እንዳልነበራቸውም በሚገለፀው ሃሳብ አልስማማም። ሁላችንም እንደምናውቀው ደርግ አፋኝና ወታደራዊ መንግሥት ነው። ነገር ግን አሁን በሚባለው ልክ የመናገርና የመፃፍን ነፃነት አያፍንም። ምሳሌ ማንሳት ካስፈለገ ዶክተር ንጉሴ ተፈራ የሚባል ሰው ‹‹ከምናየውና ከምንሰማው›› እያለ ጥሩ ጥሩ ሥራዎችን ያቀርብ ነበር። እኔ ራሴ በደርግ ጊዜ «ገቢ በማንኪያ ወጪ በጭልፋ» እያልኩ ስለ ሙስና ጉዳይ በሬዲዮ ፕሮግራም አቀርብ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የደርግ ሰዎች ይቆጣሉ። ግን አለቆቻችን ያስረዳሉ። አንጋፋ ጋዜጠኞች ስለሆኑ ስለተማሩ፣ እነርሱም ፅፈው የሚያስፅፉ በመሆናቸው ምክንያት እኛን ይከላከሉልን ነበር። ስለዚህ በግሌ በደርግ ጊዜ በደንብ እሠራ ነበር ብዬ ነው ምስክርነት የምሰጠው። እንደውም አሁን ካለው ለውጥ በፊት ከነበረው ጊዜና ከደርግ ጊዜ ምረጥ ብባል እኔ የምመርጠው የደርግን ጊዜ ነው። ለዚህም ብዙ ምሳሌዎችን ማሳየት እችላለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ደፈር ባሉ ሥራዎችህ ከሥራ መታገድና ሌሎች ቅጣቶች አጋጥሞህ አያውቅም?

ጋዜጠኛ ንጉሴ፡- ያውቃል! አንድ ቅዳሜ እለት ከአዲስ ዘመን አምደኛ ከሆነው ከአሸናፊ ዘደቡብ ጋር በስልክ እያወራን ሳለ ሌላ ስልክ ተጠልፎ ይገባል። እናም ከአንዱ የስልኩ ጫፍ «ኮሎኔል ጫላ አሉ?» ይላል። ከሌላኛውም ጫፍ «የሉም» እያለ ይቀጥላል። ወዲያው ሌላ ስልክ ይደገማል። ይህንን ተመርኩዤ ‹‹የዘንድሮ ስልክ ጥራ ያሉትን ትቶ ጥራ ያላሉትን ይጠራል›› ብዬ ፕሮግራም ሠራሁ። በቀጣይም ከወጋየሁ ንጋቱ ጋር የስልክ ጭውውት መሰል ድራማ ሠራን። በኋላም እንዴት ቴሌ ይሳሳታል? ተብሎ በዚያ ሥራ ምክንያት ደርግ ፅህፈት ቤት ተከሰስኩ። ይህም ቢሆን ግን በደርግ ጊዜ በአሽሙር እየተናገርን መንግሥትንና አሰራሩን የምንነቅፍበት እድል ነበር። የእናንተ ጋዜጠኞች አሁን ይህን ያህል አይደፍሩም። አሁን አንቺም እዚህ የመጣሽው ነፃነት ስለተሰጠሽ ነው እንጂ በቀደሙ ዓመታት መንግሥትና ባለሥልጣናቱን እንድትተች አይፈቀድም ነበር። ነፃነት ሲባል ግን የሰውን መብት ሳይነኩ ነው መፃፍ የሚገባው። የድሮ ጋዜጠኞች ቢተቹም የተተቹበትንም ጭምር ያስተናግዱ ነበር። እንደዛም ሆኖ አንዳንድ ጊዜ በምንሠራው ሥራ ግሳፄ ይደርስብን ነበር።

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ጊዜ ስላለው የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትና አተገባበሩ ምን ታዘብክ?

ጋዜጠኛ ንጉሴ፡- በአሁኑ ጊዜ ያለውን ካለፈው 27 ዓመታት ጋር ለማነፃፀር ያስቸግረኛል። ምንአልባት ከስምንት ወራት ወዲህ ያለውን የምናውቀው ነው። እናንተ ሁሉ ነፃ የወጣችሁበት ነው። እውነቱን ለመናገር በኢህአዴግ የመጀመሪያ ዓመታት ላይ ጥሩ ነበር። ጥሩ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ፈጥሮ እያለ ቀስ በቀስ ሁኔታዎችን እያዳከመ መጣ። ውሎ ሲያድርም ጋዜጠኝነትን በህግ እያሰረው፣ እየጠፈረው፣ ሰዎችን ፈሪ እያደረጋቸው ደፍሮ የሚፅፍ እንዲጠፋ እያደረገው ሄደ።

ኢህአዴግ ትልቁ የሚፈራው ጉዳይ ሃሳብን ነው። ባለፉት ዓመታት እንደልባቸው መናገር መፃፍ የሚችሉት በሱ ዙሪያ ያሉ ሰዎች ብቻ ነበሩ። ያው ቢፅፉም ስለ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ብቻ ነበር። በተቃራኒው ሌላው ሲፅፍ ይገንበታል፣ ይታገዳል፣ ይታሰራል። ኢህአዴግ መሳሪያ ይዞ ታግሎ መጥቶ ፕሬስን ለምንድን ነው የሚፈራው? ይኸው አሁን እኮ ፍርክስክሱ ወጣ አይደል እንዴ? ለነገሩ እኛ ይህ ሁኔታ እንደሚከሰት አስቀድመን እናውቅ ነበር። ለዚህ ደግሞ ትንቢት ተናጋሪ መሆን አያስፈልግም።

እኔ ያጋጠመኝን እንደ ምሳሌ ማንሳት ካስፈለገ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት የእርዳታ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተዘጋጀና ያንን መድረክ እኔና ደበበ እሸቱ እንድንመራ የሼህ መሃመድ አሊ አላሙዲን የቅርብ ሰው በሆነው አቶ አብነት ገብረመስቀል ትዕዛዝ ተሰጥቶን ነበር።

በዕለቱ የክብር እንግዳው ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፤ የትምህርት ሚኒስትር የነበሩት ወይዘሮ ገነት ዘውዴ፣ ጀኔራል ፃድቃን ገብረተንሳይና ሌሎችም ትላልቅ ባለሥልጣናት ቀድመው ተገኝተው ነበር። ሼህ መሃመድ ግን ከአንድ ሰዓት በላይ ቢጠበቁም ሳይመጡ ይቆያሉ። ከአንድ ሰዓት በኋላ ግን ሼሁ መጥተው ፕሮግራሙ ይካሄዳል። ያን ጊዜ ውስጤ ቢበሽቅም የፕሮግራሙ ባለቤት ሌላ አካል በመሆኑ ምንም መናገር አልቻልኩም። እኔ ወንድምሽ ግን ይህንን ብስጭቴን በወቅቱ አሳትመው በነበረው የማስታወቂያ ጋዜጣ ላይ ‹‹እንዴት ኢትዮጵያ የምትባል ትልቅ አገር ርዕሰ ብሄር አስቀምጠው ሼሁ ይዘገያሉ?›› የሚል ትችት አዘል ቆንጆ አርቲክል ፃፍኩ። በአንድ የፕሬስ ሰውና በሌሎችም ደህንነቶች አማካኝነት ‹‹ንጉሴ ተዳፈርክ? እንዴት እንዲህ ብለህ ትፅፋለህ›› የሚል ተግሳፅ ደርሶብኝ ነበር። ግን ይህን ያህል ደፍሬ መፃፍ የቻልኩት የራሴ ጋዜጣ ስለነበረኝ ነው። የእናንተ ጋዜጦች አልደፈሩም። እርግጥ ነው በዚያ ምክንያት ምንም አልመጣብኝም። ነገሩ ግን በባለሥልጣናቱ ዘንድ መነቃነቁ ግን አልቀረም።

ሌላው ትዝ የሚለኝ ከ11ዓመት በፊት ለቪኦኤ ፍሪላንስ ሠራተኛ ሆኜ እሥራ ነበር። በወቅቱ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ይከበር ስለነበር በዚያ ዙሪያ የቀድሞውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ መዝሙር ታሪክ ፈልጌ አምስት ኪሎ ሙዚየም ሄጄ ብጠይቅ፤ እንኳን መዝሙሩ ባንዲራውም ‹‹የለም›› ተባልኩ። ጊዮርጊስ ሄጄ የኢትዮጵያ ወሰንና ግዛት ባንዲራችንን የሚያሳይ መረጃ አግኝቼ ያንን ፕሮግራም ሠራሁ። ይህ ፕሮግራም ለምን? ማን ነው የሠራው? ተብሎ ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት ያሉ ሰዎች አለቆቼ ላይ ጮሁባቸው። በተለይ አቶ በረከት ስምዖን ባሳደረው ጫና ምክንያት ለሦስት ዓመት ከሥራ ታግጄያለሁ። እንዳውም ካነሳነው አይቀር መጀመሪያውኑ ከብሄራዊ ሎተሪ የተባረርኩት አማራ ነህ ተብዬ ነው። ስሙ ይቅር ግዴለም የብሄራዊ ሎተሪ የቦርድ ሊቀመንበር ሆኖ ይሠራ በነበረ የህወሓት ሰው ነው ተገፍቼ ብዙ ልሠራ በምችልበት በ41ዓመቴ የተባረርኩት። በጣም የሚያሳዝነው ጉዳይ ደግሞ 22 ዓመት ባገለግልም እድሜዬ 55 ባለመሙላቱ ጡረታዬንም እንኳ ማስከበር አልቻልኩም ነበር።

እኔ ወንድምሽ ግን ከኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ ስንት ሥራ የሠራሁ ሰው እንዲሁ መባረሬ ስላበሳጨኝ ኢህአዴግን ለመበቀል ቶሎ ብዬ የማስታወቂያ ድርጅት አቋቋምኩና ከአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ጋር መሥራት ጀመርኩ። ለ17 ዓመታት ጡረታዬን ሳላስከብር በራሴ ጥረት ልጆቼን ማሳደግ ችያለሁ። ስለዚህ በአጠቃላይ በኢህአዴግ ዘመን ስለነበረው የፕሬስ ነፃነት ጉዳይ ማንሳት የምፈልገው በተለይ አንድ የአገር መሪ መጪውን ጊዜ አሸጋግሮ ማየት አለበት። ሃሳብን ስለገደብን ብቻ የምንፈራውን ነገር ማምለጥ አንችልም። ያኔ እኛ እንፈራቸው፣ እንንቀጠቀጥላቸው የነበሩት ሰዎች ዛሬ ለመታሰር ይፈለጋሉ። ይህም የእግዚአብሔርን ተዓምር ለማድነቅ ያስገድደኛል። አሁን ያሉት መሪዎችም ቢሆኑ ሁለተኛ እንዲህ አይነት ነገር እንዳይደገም ከልባቸው ሊሠሩ ይገባል።

ይህንን ስታነሺ አንድ ነገር ትዝ አለኝ። በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ህዝብ የማያውቃቸው ግን እውነት የሆኑ የታፈኑ ድምፆች አሉ። ለምሳሌ ሕገ መንግሥት እንዴት እንደፀደቀ፣ በዚህ ሕገ መንግሥት ላይ ፓርላማ ውስጥ ኢትዮጵያውያን የነበራቸው አስተያየት ምን እንደሚመስል የሚናገሩ ሰነዶች በላይብረሪ ውስጥ ታስረው ይገኛሉ። የታሰሩ ሰዎች ሲፈቱ፤ ብዙ እውነታን የያዙት ድምፆች ግን አሁንም ታስረው ነው የሚገኙት። እነዚህ ድምፆች መፈታትና ማስተማሪያ መሆን አለባቸው። አሁን የጠፋውን ለማስተካከል የተቸገርነው እውነታው በመደበቁ ነው። በተለይ በአንቀፅ 39 ላይ፣ በኤርትራ ጉዳይ ላይ እነፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ትልቅ ተቃውሞ ያደርጉ ነበር። በዚያ ወቅት ግን በመሪ ደረጃ ሰውን ቆሻሻ ብሎ እስከመሳደብ ድረስ ንትርክ እንደነበር እነዚያ ድምፆች ምስክር ናቸው። ስለዚህ ለትውልዱ ከመስመር መውጣት አመራሩ ያበረከተውን አሉታዊ ተፅእኖ በግልፅ ተማምነን ከዚያ መማር የምንችልበት እድል መፈጠር አለበት የሚል እምነት አለኝ። የሰውን መብት አትንካ፤ የራስን መብት እንዲከበር እንደምትፈልገው ሁሉ ማለት አለብን። ሚዲያው ለአገራችን አንድነት የምንወያይበት እንጂ እርስ በርስ የምንተቻችበት ሊሆን አይገባም። መስመር መልቀቅ የለበትም።

ሌሎችም በርካታ ድምፆች ታፍነዋል። ለምሳሌ የብዙነሽ በቀለና ጥላሁን ገሰሰ ዘፈን «ኩኩሉ አለ ዶሮ፤ ምን ይሰማ ይሆን ጆሮ ዘንድሮ» የሚል ዘፈን በእኛ ጊዜ የወቅቱን ፖለቲካ ማመላከት ከሚችሉ ሥራዎች ጋር እናቀርበው ነበር። አሁን ግን አልሰማውም። በእኔ እምነት ይህ ዘፈን መደመጫው ጊዜ አሁን ነው። በተመሳሳይ ሱዳንና ኢትዮጵያ እንደዛሬው በቁርባን ሳይጋቡ በፊት፤ ተጣልተው በነበረበት ወቅት የሙሉቀን መለሰ «ነይ ነይ ወዳጄ» የሚለው ዘፈን ስናሰማ የደርግ ባለሥልጣናት ይሄ ሰውዬ ማንነው ‹‹ነይ ነይ›› የሚለው ብለው የሳንሱር ክፍል አለቃ ላይ የጮኹበትን አጋጣሚም አረሳውም። እናም እባክሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ እነዚህን ድምፆች ፍቱልን በይልኝ።

አዲስ ዘመን፡-አሁን የተፈጠረውን ነፃነት በመጠቀም ከባህላችን፣ ከሥነምግባርም ፈር የሳተ ነገር እየተስፋፋ መሆኑ ይነገራል። አንተ ይህንን ማስተዋል ችለህ ይሆን?

ጋዜጠኛ ንጉሴ፡- ይሄ እኮ ያለፉት 27 ዓመታት ቱሩፋት ነው። በዓይኔ ምክንያት የሚፃፉ ፅሑፎችን ብዙ ማንበብ ባልችልም በቤተሰቦቼ ድጋፍ ወቅታዊ ጉዳዮችን እከታተላለሁ። እናም እንዳልሽው ጫፍ የወጡ ጉዳዮችን ለማስተዋል ችያለሁ። አብዛኛው ወጣት ትውልድ ስላለፈው ታሪክ አያውቅም። እንዲማርም አልተደረገም። ለዚህም ነው ትንሽ ነፃነቱ ሲለቀቅለት ሕገወጥ የሆኑ ተግባራትን የሚፈፅመው። በእርግጥ እርስ በርስ መተቻቸት ጥሩ ነው። ግን እስከ መዘላለፍ መድረስ የለበትም።ከምንም በላይ ለዚህች አገር የሚያስፈልጋት ሰላም ነው። እርስ በርስ ሊያጋጨን ከሚችል ጉዳይ ራሳችንን ማራቅ መጠንቀቅ ይገባናል። ሥርዓት መበጀት አለበት። የሚያስፈልገው እንዲህ ተጣልተን ተበታትነን አንቀርም፤ አሁንም ሰላም ይግባ፤ አጥፊውም ከጥፋቱ ይመለስ። ዛሬ ያጠፋ ካልተጠየቀ ለነገ ምንም ዋስትና የለንም። ያጠፉት ምሽግ ሠርተው ከሚደበቁ ይልቅ እንዳውም ራሳቸው በፈቃዳቸው እጅ መስጠት ነበረባቸው የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- በአገራችን የጋዜጠኝነት ታሪክ መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር ለመንግሥቱ የማደርና ሙያው የሚጠይቀውን የገለልተኝነት ሥነምግባር ችግር በስፋት ይታያል ይባላል። ከዚህ አንፃር ከአንተ ተሞክሮ አሁን ላለው የዘርፉ ባለሙያ ምን ትመክራለህ?

ጋዜጠኛ ንጉሴ፡- መቼም አንቺም ይጠፋሻል ብዬ አላስብም። ሚዛናዊነት በጋዜጠኝነት ሙያ ወሳኙና ዋነኛው ጉዳይ ነው። በኛ ጊዜ ከአለቆቻችን ጋር ቅርቦች ነበርን። በመጀመሪያ ደረጃ አለቆቻችን ሠርተው የሚያሠሩ፤ የሚያነቡና የሙያው ሰው በመሆናቸው በቀላሉ ይይዙታል። ለእኛም ስህተታችን የሚነግሩን እንደቀልድ ነበር። እነዚህ አለቆቻችን ታዲያ ቀደም ብለውም ከኃይለሥላሴ ጊዜ ጀምሮ የሠሩ በመሆኑ አካሄዱን ያውቁታል። ስለዚህ አንድ ነገር ከመሥራታችን በፊት እናማክራቸዋለን።

ዛሬ ላይ ግን ትልቁ ችግር የሚመስለኝ ቦታው ላይ የተቀመጠው ባለሙያ ያልሆነ ሰው መሆኑ ነው። ዋናው ዓላማ ፖለቲካውን ማስፈፀም ስለሆነ ጋዜጠኛውን ሊያማክረውም የተሻለ ፅፎ ሊያፅፈው አይችልም። ይህ ባለበት ሁኔታ ጋዜጠኛው መንግሥትን በሚተች ሁኔታ ለመፃፍ ይከብደዋል። ወደፊት እርግጠኛ ነኝ። ይሄ ሁሉ ነገር ይስተካከላል ብዬ አምናለሁ። ፕሬሱ ከመንግሥት ወጥቶ ራሱን በራሱ ያስተዳድር የሚልም እምነት አለኝ። እስከዛው ድረስ ግን መንግሥትም የአገርንና የህዝብን አደራ የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለበት ያስከፋ ነገር ካለ ለምን? እንዴት? ቢል ብዙም የሚጎዳ ነገር አይሆንም። በተቻለ መጠን ጋዜጠኛው ራሱ አንድ ነገር ሲሠራ፤ እዚህ ያለውን ሰው ወይም የጠቆመውን ሰው ካነጋገረ ሌላኛውንም ወገን እኩል አነጋግሮ ማስተናገድ አለበት። ባይሆን እንኳ «ፈልጌ አጣኋቸው» ማለት እንኳ ጥሩ ማምለጫ ነው። መንግሥትም ወደ ህዝብ ጆሮ ከመድረሱ በፊት ስህተቱን ቢያርመው ጥሩ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ንጉሴ አክሊሉ ጋዜጠኛና የማስታወቂያ ባለሙያ ብቻ ሳይሆን የዜማ ደራሲ ነው። እስቲ ስለዚህ የተለየ ተሰጥኦ ትንሽ አጫውተን?

ጋዜጠኛ ንጉሴ፡- ልክ ነሽ፤ እኔ ሁሉንም ነገር እሞክራለሁ። በእኔ እምነት ጥሩ ዜና አንባቢ ጥሩ ድምፅ ያለው፤ ጥሩ ቅላፄ ያለው ሰው ነው። ዝም ብሎ ማንበብ ስለቻለ ብቻ ጥሩ አንባቢ ነው ልንለው አንችልም። ለምሳሌ መጥቀስ እፈልጋለሁ ስፖርት ጋዜጠኞች ላይ ብዙ የምታዘበው ነገር አለ። ምን እንደሚያነቡ እንኳ ሳይገባቸውና አድማጩ ምን እንዳነበቡ ሳይገባው አነብንበው የስፖርት ዜና አነበብን ይላሉ። ይህ ሁኔታ ትክክል አይደለም፤ መስተካከል ይገባዋል። ወደፊት በሌላ አርዕስት እናወራዋለን ብዬ አምናለሁ። እናም ወደ ጥያቄሽ ስመለስ እንዳልሽው ከመንፈሳዊው እንዲሁም ከዘመናዊውም ሙዚቃ እሞክራለሁ። በትምህርት ቤትም ቴአትር እሠራ ነበር። በድምፄም ብፈልግ ትዝታን አንጎራጉራለሁ።

ለምሳሌ በቅርቡ «ገጣሚ ቢታጣ የሚያንጎራጉር ጋዜጣኛው መጣሁ ዝምታን ልሰብር ዝምታ ወርቅ ነው፤ መልካም ነው ካላችሁ እድል ለእኔ ስጡኝ ልግባ በሥራችሁ» አልኩ። ለምን መሰለሽ ይህንን ያልኩት ድሮ በየምሽት ቤቱ የባህል ሙዚቀኞች ግጥም እየሰጠናቸው ያንን ያዜሙ ነበር። አሁን ያ ጠፍቷል። በየምሽት ቤቱም የሉም። ይህም የሆነው የፕሬሱ መታፈን ያመጣው ጣጣ ነው። እናም ይህ ጉዳይ ስላሳሰበኝ ይህንን ግጥም በዜማ የሠራሁት።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሜሪካ ሄደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አባቶችን ሲያስታርቁና ሊያመጡ ነው ቢባል የሰራኋቸው ዜማዎች አሉ። ለምሳሌ ብጠቅስልሽ «ነብይ በአገሩ አይከበርም፣ እንዴት አይከበርም በአገሩ፤ ይከበር ይከበር ነብይ በአገሩ» እያልኩ የሠራሁት ዜማ አለኝ። ለዚህ መነሻ የሆነኝ ዶክተር ዐብይ ወደ ሥልጣን ሲመጡ እናታቸው በሰባት ዓመታቸው ‹‹የአገር መሪ ትሆናለህ ብላኛለች›› በማለታቸው አንዳንድ ጋዜጠኞች ለምን እንዲህ ይላሉ ብለው ሲተቿቸው በመስማቴና አባባሉ በጣም ቅር ስላሰኘኝ ነው ይህንን ዜማ የሠራሁት። እንዲሁም ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ሦስት አራት ዜማዎች አሉኝ። አራዳን፣ አዲስ አበባ ከተማን የሚመለከቱ 11 ዜማዎች ይሳቅ ባንጃው በሚባል ታዋቂ የሙዚቃ ባለሙያ አማካይነት በሚገባ ተቀርፆ ተዘጋጅቶ ተቀምጧል። ያንን ይዤ ገበያ አልወጣም ብዬ ተቀምጧል፤ ወደፊት እንግዲህ እንዴት እንደሚሆን አላውቅም። የሚገርምሽ ዘንድሮ ልጄን «አዲስ ነገር ታየ ሙሽራዬ ብሎ አባት ልጁን ሲድር» ብዬ በራሴ ድምፅ ዘፍኜ ነው የዳርኩት።ይህም የሠርጉን ታዳሚ ሁሉ አስገርሟል።

አዲስ ዘመን፦ በቴዲ አፍሮ አልበም ሰብልዬ ዜማ ላይ ያለው ድምጽ እንዴት እንደተሠራ ንገረን?

ጋዜጠኛ ንጉሴ፦ ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ ፍቅር እስከመቃብር ሲተረክ በ1972 ዓ.ም ይመስለኛል አንድ ቀን እንደልማዴ ዜና ላነብ ሁለት ሰዓት ላይ ስገባ ወጋየሁ ንጋቱ ፍቅር እስከ መቃብርን ሊተርክ ይቀረፃል። ሲያነብ «ዝ ጠላ» ሲል ሰማሁት ‹‹ተው ዘነጠልክ›› አልኩና ይህንን ነገር ዘንጥሎታል ትክክል አይደለም ብዬ ዜናዬን ከጨረስኩ በኋላ መጽሐፉ ላይ እንደተፃፈው በዜማ አዜምኩለት። ያን ጊዜ ሚኒስትሩ ሻለቃ ግርማ ጉድ አሉ፤ ማነው ይህንን ያዜመው ብለው ጠይቀው ተነገራቸው። እናም ያ ታሪክ ሆኖ ተቀምጦ ኖሮ ቴዲም ለዘፈኑ ማጀቢያ ተጠቀመበት። እኔ ግን ጊዜው ስለቆየ ረስቼው ነበር፤ አንድ ቀን በአድዋ ጎዳና ላይ ቆሜ አንድ ወዳጄ አግኝቼ ድምፄን በዘፈኑ ላይ መስማቱን ነገረኝ፤ እኔም ሰማሁት። ክሊፑ ላይ ስሜ መካተቱንም አይቻለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ግን ምን አገኘህበት?

ጋዜጠኛ ንጉሴ፡-አይ ምንም አላገኘሁበትም። ግዴለም ይሄ ይቅር። እኔም እንደቁምነገር አልቆጥረውም። ደግሞም የእኔ ድምፅ ያለው ክሊፑ ላይ ብቻ ነው። በእርግጥ ክሊፑን ያዘጋጀው ያሬድ ሹመቴ የተባለው ሰው አነጋግሮኛል። እኔም ክፋት እንደሌለው ስለተገነዘብኩ ችግር የለም ብዬ ፈቅጄለታለሁ። እንዳልሽው ግን ብዙ ሰው የአንቺን አይነት ጥያቄ ይጠይቀኛል። ቴዲን በአካል ብዙም ባላውቀውም አባቱ ወዳጄ ስለነበር አስተዋፅኦ በማድረጌ ብቻ ደስተኛ ነኝ። ለእኔ እንዳውም ክብር ሰጠኝ። አድናቆት እንዳገኝ አደረገኝ። ይህንን ብትነግሪልኝ ደስ ይለኛል።

አዲስ ዘመን፡- መጽሐፍ እንደ ጻፍክ ሰምቻለሁ ከምን ደረሰ?

ጋዜጠኛ ንጉሴ፡- አንዱ በፍርሃት የቀረ ነው። ከዚህ ካለንበት ወቅት በፊት በእኔ የኮምፒውተር ፅሑፍ 700 ገፅ ገደማ ይሆናል። በተለይ በ1997ዓ.ም እንዲሁም በ2002ዓ.ም ምርጫ ጋር ተያይዞና የፕሬስ ሹመኛውን ከሌሎቹ በተለየ መልኩ አጻጻፍና በሰምና በወርቅ አድርጌ ነገ መውረዱ አይቀርም ብዬ የጻፍኩት ሥራ አለ። ርዕሱ «መርገመ በረከት» ይላል። አልቋል ግን አልታተመም። ሌላው የራሴ የህይወት ታሪክ አለ ሰፊ ነው። ግን ብዙ አልገፋሁበትም፤ አሁን ግን ጊዜ ስላለኝ እሄድበታለው ብዬ አስቤያለሁ። ሌላው የአባቴንም መጽሐፍ አሳትሜያለሁ።

አዲስ ዘመን፡-ወደ ቤተሰባዊ ህይወትህ ስንመጣ የአንተን ሙያ የተከተለ ልጅ አለህ? ድጋፍስ ያደርጉልሃል?

ጋዜጠኛ ንጉሴ፡- እኔ ከሥራ ከተባረርኩ በኋላ ስለሆነ የተወለዱት ስለ ጋዜጠኝነት ህይወቴ ብዙም አያውቁም። እኔም ስለማልጫናቸው የእኔን ሙያ የያዘ ልጅ የለም። ስለዚህ ሦስቱ ልጆቼ በተለያየ ሙያ ላይ ናቸው። አንዱ ጋና እየተማረ ነው። ባለቤቴ ጥሩ ሰው ነች፤ በተለይ በጤንነቴ በኩል ትደግፈኛለች።

አዲስ ዘመን፡- ስለ በጎ ሰው ሽልማት ትንሽ ብናወጋ ምን ይመስልሃል?

ጋዜጠኛ ንጉሴ፡- ደስ ይለኛል። በእውነት እኔ ራሴ ስለሽልማቱ አላውቅም ነበር፤ ‹‹ሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት ይፈልግሃል›› ብለው በመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ ነው የነገሩኝ። ምክንያቱም ከእኔ በፊት የነበሩ አንጋፋ ጋዜጠኞች በመኖራቸው አልጠበኩም ነበር። የበጎ ሰው ሽልማት 50ዓመት በማገልገሌ እውቅና እንዲሰጠኝ በማድረጉ አመሰግናለሁ። እኛ ብዙውን ጊዜ ውለታ አንመልስም፣ ሰው አናደንቅም፣ ሰው ማውጣት አናውቅም። ይህንን አስቦ በማድረጉ ላመሰግነው እወዳለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ሰዎችን መደገፍና ማገዝ እንደምትወድ ከቅርብ ጓደኞችህ ሰምቻለሁ። ምን ያህል እውነት ነው?

ጋዜጠኛ ንጉሴ፡- እውነት ነው። እኔ በተፈጥሮዬ በእኛ ሙያ ያለን ሰው መደገፍ እወዳለሁ። ለምሳሌ በኛ ጊዜ ተመሳሳይ ፕሮግራም ስንሠራ እንደጋገፋለን፤ እንከባበራለን። አሁን ይህ ባህል ቀርቷል፤ አሁን አንዱ የሠራውን ሥራ እንዳታገኚበት ደብቆ ነው የሚሠራው። መደጋገፍ የለም። ሌላውም ለእያንዳንዱ በጎ ሥራው እንዲከፈለው ይፈልጋል። ግን ለኛ ሙያም ሆነ በሌላው ዘርፍ ቅንነት ያስፈልጋል። ከእኔ አንተ ትብስ ስንባባል ነው የምናድገው።

አዲስ ዘመን፡- ጊዜህን ሰውተህ ከህይወት ልምድህ ስላካፈልከን በአንባቢዎቼ ስም ከልቤ አመሰግናለሁ።

ጋዜጠኛ ንጉሴ፡- እኔም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አስታውሶ ካለሁበት ስፍራ ድረስ በመምጣት ቃለመጠይቅ ስላደረገልኝ በጣም ላመሰግን እወዳለሁ።

አዲስ ዘመን –  https://www.press.et/Ama/?p=6442


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE