የኢትዮጵያ አውሮፕላን ከተከሰከሰበት የሰው አካል የሚመስል ምንም ማግኘት እንዳልተቻለ ተነገረ

የኢትዮጵያ አውሮፕላን ከተከሰከሰበት ጊምቢቹ ቀበሌ ትልቅ ጉድጓድ ፈጥሯል። በቦታው የደረሱ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በጎ ፈቃደኞች የሰው አካል የሚመስል ነገር አላገኙም። ዶክተር ሰለሞን አሊ “የሰው አካል የሚመስል ምንም ማግኘት አይቻልም። ከደረሰን ሪፖርትና ከፎቶግራፎች እንዳየንው ብጥቅጣቂው ራሱ በጣም ትንንሽ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር፤ የቻይና እና የእስራኤል ባለሙያዎች ከትናንት ጀምሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 -800 ማክስ አውሮፕላን ከተከሰከሰበት ቦታ ፍለጋ ሲያካሒዱ ቆይተዋል። የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሰብዓዊ ዲፕሎማሲ፤ የገቨርናስና የዓባላት ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን አሊ “የሰው አካል ነው ብለህ የምትላቸው ነገሮች የሉም። ሕይወት ለማዳን የሚቻልበት አይነት ኹኔታ አልነበረም። ስለዚህ እዚያ አካባቢ ተበታትነው የነበሩ ቁሳቁሶችን፤ ንብረቶችን፤ አንዳንድ የሰውነት ክፍሎችን” በጎ ፈቃደኞች ከትናንት ጀምሮ መሰብሰባቸውን ለDW አስረድተዋል።

ዶክተር ሰለሞን “የሰው አካል የሚመስል ምንም ማግኘት አይቻልም። ከደረሰን ሪፖርት እና ከፎቶግራፎች እንዳየንው ብጥቅጣቂው ራሱ በጣም ትንንሽ ነው” ሲሉ አክለዋል። በጎ ፈቃደኞች በቦታው ከነሩ የጸጥታ አስከባሪዎች፤ የሕክምና ባለሙያዎች እና ከሌሎች አገራት ከተጓዙ ባለሙያዎች አጠገብ ሆነው የተቀዳደዱ መፃሕፍት፤ መታወቂያዎች፤ ፓስፖርቶች ሰብስበዋል።

 

 

 


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE