ስለ አደጋው ልታውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

ስለ አደጋው ልታውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፕሮቶኮል ሻሀድ አብዲሻኩር በአውሮፕላን አደጋው ከሞቱት መካከል አንዱ ናቸው።

ትላንት ከቦሌ ኢንተርናሽናል አየር መንገድ ተነስቶ ወደ ኬንያ በመብረር ላይ የነበረው ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ባጋጠመው የመከስከስ አደጋ ተሳፋሪዎችንና የአየር መንገዱን ሰራተኞች ጨምሮ 157 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

ከአደጋው በኋላ እስካሁን ያገኘናቸው የተረጋገጡ መረጃዎች እነዚህ ናቸው። BBC AMHARIC

የአደጋው ቦታ

• 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረው ET 302 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከጠዋቱ 2፡38 ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ተነሳ።

• ከ6 ደቂቃ በኋላ ከአብራሪዎቹ ጋር ይደረግ የነበረው ግንኙነት ተቋርጦ ቢሾፍቱ አካባቢ አውሮፕላኑ የመከስከስ አደጋ አጋጠመው።

• የአውሮፕላኑ አብራሪ ችግር ስላጋጠመው ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ጠይቆ እንዲመለስ ተነግሮት እንደነበር ታውቋል።

• ከጠዋቱ 4፡ 48 ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በደረሰው አደጋ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ ሁሉ በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ስም ኀዘኑን ገለጸ።

• የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞቹን አደጋው ወደ ደረሰበት ቦታ መላኩን ከረፋዱ 5 ሰዓት ላይ ባወጣው የአደጋ ሪፖርት አስታወቀ።

• ከቀኑ 7፡ 30 አካባቢ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም አደጋው ከደረሰበት ቦታ ተገኝተው ጉብኝት አደረጉ።

• ከቀኑ 10፡20 አካባቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ET 302 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን የተከሰከሰበትን ቦታ ጎበኙ።

• በትናንትናው ዕለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ መጋቢት 2/2011 ዓ.ም የብሔራዊ ሐዘን ቀን እንዲሆን አወጀ።

• ቦይንግ 737 ማክስ 8 ከአራት ወራት በፊት የተገዛ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዚህ አይነት ስድስት አውሮፕላኖች አሉት።

• አውሮፕላኑ እሁድ ጠዋት ከጆሃንስበርግ በረራው ሲመለስ ምንም አይነት የበረራ ችግርን የሚመለከት መረጃ እንዳልነበርና ከሶስት ሰዓት በላይም መሬት ላይ ቆይቶ እንደነበር ተገልጿል።

• ዋና አብራሪው ያሬድ ሙልጌታ ከ 8 ሺህ ሰዓት በላያ ያበረረ ፓይለት ሲሆን ረዳት አብራሪው አህመድ ኑር ሞሃመድ ደግሞ 2 መቶ ሰዓት ያበረረ ፓይለት እንደሆነ ታውቋል።

• የአውሮፕላኑ አምራች ቦይንግ በአደጋው የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ የቴክኒካል ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልክ አስታውቀዋል።

• የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ የሲቪል አቪየሽን ባለስልጣንና የኢትዯጵያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር በመተባበር አደጋውን የሚመረምር ኮሚቴ አቋቁሟል።

• የኢትዮጵያ አየር መንገድ የትናንትናው አደጋ እስኪጣራና ለበረራ ደህንነት ሲል ለጊዜው ቦይንግ 737 ማክስ 8 መጠቀም ማቆሙን ባወጣው የአደጋ ሪፖርት ገልጿል።

ስለሟቾች እስካሁን የምናውቀው

• ህይወታቸው ካለፉት ሰዎች 32 ኬንያዊያን፣ 18 ካናዳዊያን፣ 18 ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ በአጠቃላይ የ33 ሃገራት ዜጎች ይገኛሉ።

• የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፕሮቶኮል ሻሀድ አብዲሻኩር በአውሮፕላን አደጋው ከሞቱት መካከል አንዱ ናቸው።

• የስሎቫኪያ የፓርላማ አባል አንቶን ሄርንኮ ፌስቡክ ገፃቸው ላይ እንዳሰፈሩት ባለቤታቸውና ሁለት ልጆቻቸው በአደጋው ህይወታቸው አልፏል።

• በአደጋው ህይወታቸው ካለፉት ተሳፋሪዎች መካከል በኬንያ የሚደረገውን የአካባቢ ጥበቃ ኮንፈረንስ ለመካፈል የተጓዙ 19 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች ይገኙበታል።

• በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የኢስማይሊና የቲፒ ማዜምቤን በዋና ዳንነት ሊመሩ የነበሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሁሴን ስዋሌህ ከሟቾች መካከል ናቸው።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE