የፈጣን አውቶብስ መስመር ግንባታ ምክንያት በአዲስ አበባ ከስድስት መቶ ቤቶች በላይ ይፈርሳሉ ተባለ፡፡

በአዲስ አበባ በቅርቡ ስራ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው የፈጣን አውቶብስ መስመር ግንባታ ምክንያት ከስድስት መቶ ቤቶች በላይ ይፈርሳሉ ተባለ፡፡

ቢ2 ተብሎ የሚጠራው የፈጣን አውቶብስ መስመር ከዊንጌት ተነስቶ በአውቶብስ ተራ አድርጎ በተክለሃይማኖት ሜክሲኮ፣ ከሜክሲኮ በቄራ አድርጎ ወደ ጎፋ፣ ከዚያም በጀርመን አደባባይ ጀሞ የሚደርስ መሆኑን ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ሰምተናል፡፡

አጠቃላይ ርዝመቱም 17.4 ኪሎ ሜትር ነው ተብሏል፡፡

አውቶብሶች ብቻ እንዲጓዙበት ለሚገነባው መንገድ 127 ሚሊዮን ዩሮ ወይንም ዛሬ በዋለው ምንዛሬ አራት ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

ከሚያስፈልገው 4 ቢሊየን ብር ውስጥም 2.7 ቢሊዮን ብሩ ከፈረንሳይ መንግስት በብድር መገኘቱን ከመንገዶች ባለስልጣን ሰምተናል፡፡

ቀሪው ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚሸፈን ነው ተብሏል፡፡

17.4 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውንና ከዌንጌት ተነስቶ በአውቶብስ ተራ፣ በሜክሲኮ፣ ቄራ፣ ጀርመን አደባባይ፣ ጆሞ የሚደርሰውን የፈጣን አውቶቡስ መስመር ግንባታ ለመጀመር መንገዱ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ተነሺዎች ጋር ውይይት ተጀምሯል ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመንገዶች ባለስልጣን ለይቶ የያዛቸው የልማት ተነሺዎች 665 ቤቶች፣ 396 የቤት አጥሮች 935 የመብራትና 90 የቴሌ ምሰሶዎች መሆናቸውን ሰምተናል፡፡

የነዚህ የወሰን ማስከበር ስራዎች እንደተጠናቀቁ የመንገዱ ግንባታ በ2012 በጀት አመት ለመጀመር ታቅዷል ተብሏል፡፡

የፈጣን አውቶብስ መስመሩን መገንባት በአዲስ አበባ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ለማቃለልና የብዙሃን ትራንስፖርትን ለማስፋፋት ትልቅ እገዛ ያደርጋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

ከዚህ በኋላ የሚገነቡና የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደባቸው ያሉ መስመሮች መኖራቸውም ተነግሯል፡፡

እነዚህም ከጦር ሀይሎች ቦሌ፣ ከቦሌ ለገሃር፣ ከሽሮ ሜዳ መገናኛ እና ከዊንጌት አየር ጤና መሆናቸውን ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሰምተናል፡፡