ከተማ የሚገነባው የግድ ሰፈርን በማፍረስና ሕዝብን ለጎዳና በመዳረግ አይደለም – መላኩ አላምረው


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ

ከመላኩ አላምረው – የግል አስተያየት

እንደዚህ አይደለም!

ሕግ ይከበር፤ ነገር ግን ሕግ የሚከበረው ሰዎችን በተለይም አቅመ ደካሞችን በማዋረድ አይደለም፡፡

የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ፤ ነገር ግን የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠው የሰውን ልጅ ተፈጥሯዊ መብት በመረጋገጥ አይደለም፡፡

ከተሞች ተውበው ይገንቡ፤ ነገር ግን ከተማ የሚገነባው የግድ ሰፈርን በማፍረስና ሕዝብን ለጎዳና በመዳረግ አይደለም፡፡

በሥርዓት እንመራ፤ ነገር ግን ዘመናዊ ሥርዓትን የምናሰፍነው እዚህ ያደረሰንን ማኅበረሰባዊ ትውፊት በመናቅና በመጣል አይደለም፡፡

ሀገር የምናሳድገው ሕዝብን በማማረርና በማስለቀስ አይደለም፡፡

የተበላሸ ሥርዓት የተጣሰም ሕግ ቢኖር እንኳን መሰተካከል የሚችለው በአግባብና በሥርዓት ቀስ በቀስ እንጅ ንቀትና ትዕቢትን ባስቀደመ ማናለብኝት አይደለም፡፡

ልዩነቶች በበዙባት ሀገር ውስጥ መግባባት የሚፈጠረው ልዩ ጥንቃቄ በተሞላበትና ቅንነት በታከለበት ሰዋዊና የሰከነ አካሄድ እንጅ በስሜት በሚመራና ለሰዎች በማይራራ የጭካኔ እርምጃ አይደለም፡፡

ሀገርን መምራትም ሆነ መገንባት የምንችለው ሁሉንም በእኩል ዓይን በመመልከት እና ፍትሕና ርትዕን በማስፈን እንጅ በራስ ወዳድነት፣ ለይቶ በማቀፍና ለይቶ በማግለል፣ በአድሏዊነት አይደለም፡፡

በታሪክ አጋጣሚ አንድንመራት ዕድል እጃችን ላይ የጣላትን ሀገር ወደተሻለ ከፍታ የምናሸጋግራት ሕዝቦቿን በእኩልነት እጆቻችን በፍቅር አቅፈን፣ የተጣሉትን አስታቀን፣ የተራራቁትን አቀራርበን፣ ስጋትን እያስወገደን ተስፋን በማለምለም እንጅ የተለመደን ጥላቻና በቀል እየሰበክን፣ በመካከላቸው ልዩነትን እያሰፋን፣ አንዱን አቅፈን ሌላውን እየገፋን፣ ለአንዱ አለኝታ ለለላው በሽታ እየሆንን…. ከችግር ወደ ችግር፣ ከአንዱ አዙሪት ወደ ሌላኛው አዙሪት በማሽከርከር አይደለም፡፡

እንደዚህም አይደለም!

የሕዝብ ጠበቆች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ የሥርዓት መሪዎች ነን የምንል ሁሉ ሕዝቡን ልንጠቅም የምንችለው የሕዝቡን ፍላጎት በትክክል ስንረዳና በዚሁ መሠረት ስንንቀሳቀስ እንጅ የእኛን ፍላጎትና ምኞት ሕዝባዊ በማስመሰልና ይህንኑ ለመጫን ሌት ተቀን ስለደከምን አይደለም፡፡

ሀገር የምትመራውና ሕዝብ የሚተዳደረው በሁሉም ሐሳብ መዋጮ ከሚመጣና የአብዛኛውን ፍላጎት በሚያሟላ አማካይ ሐሳብ እንጅ በአንዱ ወይም በሌላው የግል ሐሳብና ፍላጎት ብቻ አይደለም፡፡

የሀገር አንድነትና የሕዝብ አብሮነት ቀጣይነትና ዘላቂነት የሚኖረው በሁላችንም ደርሻ ሁላችንንም የሚያስማማ ለሁላችንም የሚሆን ሥርዓት ስንገነባ ብቻ እንጅ በአንዳችን ፍላጎት ለአንዳችን ጥቅም የሚሆንበትን ሴራ በመተብተብ አይደለም፡፡