ህሙማን መድኃኒት ማግኘት አልቻልንም፤ መድኃኒት አስመጪዎችም እንደልብ ወደ ሀገር ውስጥ መድኃኒት ማስገባት ተቸግረናል ይላሉ።

DW : ህሙማን መድኃኒት ማግኘት አልቻልንም፤ መድኃኒት አስመጪዎችም እንደልብ ወደ ሀገር ውስጥ መድኃኒት ማስገባት ተቸግረናል ይላሉ። ችግሩ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት እንደሆነም ይነገራል።

Image result for የመድኃኒት እጥረት

ኢትዮጵያ ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ችግር አሁንም እንዳልተፈታ እየተነገረ ነው። ህሙማን መድኃኒት ማግኘት አልቻልንም፤ መድኃኒት አስመጪዎችም እንደልብ ወደ ሀገር ውስጥ መድኃኒት ማስገባት ተቸግረናል ይላሉ። የመድኃኒቶች እጥረት በገበያው ላይ እንዳለ DW ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጭዎች ገልጸዋል።

የመድኃኒት አስመጭዎች በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት መድኃኒቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት አዳጋች እንደሆነባቸው ይናገራሉ። ተከታታይ የሚወሰዱ መድኃኒቶች መቋረጣቸው ለአንድ ታማሚ የጤና እክል መባባስ ምክንያት ከመሆኑ በተጨማሪ፤ ለሕይወት አስጊ የሚሆንበት አጋጣሚም አለ። መድኃኒቶች በገበያው ላይ እንደልብ አለመገኘት ሕመምተኞችን አደጋ ላይ ጥሏል። በተለይም የደም ግፊት፣ የስኳር ፣ የአስም ፣ እንዲሁም የህክምና ዕቃዎችም ጭምር እጥረት አለ ይላሉ። ኬሪያ ሽኩር የስኳር ህመምተኛ ለሆኑት እናትዋ መድኃኒት ፈልጋ የምታጣበት ጊዜ እንዳለ እንዲህ ነግራናለች። «የኢንሱሊን መድኃኒት ሀገሪቷ ላይ እጅግ ከሚባለው በላይ እጥረት አለ።

አለበት የተባለ መድኃኒት ቤቶች ሄጃለሁ መድኃኒቱ የለም።» የፋርማሲ ባለሙያ የሆኑት አቶ እስማኤል አብደአ ብዙ መድኃኒቶች በበቂ ሁኔታ ገበያው ላይ እንደሌሉ ይገልጻሉ። በዚህም ህመምተኛው መድኃኒት ለማግኘት እንደሚቸገር ያስረዳሉ። ችግሩም የሕገ ወጥ የመድኃኒት ንግድ እንዲፈጠር መንስኤ እየሆነ ነውም ይላሉ። «ሀገሪቷ ላይ ብዙ መድኃኒቶች በበቂ ሁኔታ በገበያ ላይ አሉ ለማለት ያስቸግራል። የደም ግፊት፣ የስኳር መድኃኒቶች በበቂ ሁኔታ የሉም። መድኃኒቶች ብቻ ሳይሆን የህክምና ዕቃ መገልገያዎችም እጥረት አለ።» የህክምና ባለሙያዎች ለህመምተኞች የሚታዘዝላቸውን ሳይሆን በሀገር ውስጥ ያለውን መድኃኒት እንደአማራጭ እንዲጠቀሙ ለማድረግ እንደሚገደዱ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ገመቺስ ማሞ ይገልጻሉ። የመድኃኒትና የህክምና ዕቃ እጥረት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተባባሰ መሆሄዱንም ይስማማሉ።

አቅርቦትና ፍላጎቱ እየተመጣጠነ ባይሆንም፤ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እየታየ እንዳልሆነ ወ/ሮ አድና በርሄ የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ከDW ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል። «በኛ በኩል የመድኃኒት አቅርቦት ክፍተቶች እየታዮ አይደለም። ፍላጎትና አቅርቦት ያለመሟላት ችግሮች ይኖራሉ። ለምሳሌ ኢንሱሊን ከጠቀስን ችግር የለብንም። ምላሽ ለመስጠት ምን አይነት የሚለውን በምርት ስሙ ቢታወቅ ችግሩን ማግኘት እንችል ይሆናል።» ሊተኩ የማይችሉ መድኃኒቶች በመኖራቸው የህሙማኑ ሕይወት ዛሬም አደጋ ላይ ነው፤ የጤና ጉዳይ እንደመሆኑ መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ያሳስባሉ አስተያየት የሰጡን።