በመንግስት በኩል በቂ ምግብ እና ቁሳቁስ እንዳልቀረበላቸው የማዕከላዊ ጎንደር ተፈናቃዮች ተናገሩ

‹‹በአንድ ላይ ተሰብስበን በመገኘታችን ምክንያት ለተለያዩ በሽታዎች ተዳርገናል›› የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተፈናቃዮች

‹‹በአንድ ላይ ተሰብስበን በመገኘታችን ምክንያት ለተለያዮ በሽታዎች ተዳርገናል›› ሲሉ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚገኙ ተፈናቃዮች ገለፁ፡፡ ተፈናቃዮቹ ጨምረው በመንግስት በኩል በቂ ምግብ እና ቁሳቁስ እየቀረበላቸው አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በተፈጠረ ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ የሰዎች ቁጥር 45ሺህ 900 ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 2ሺህ 700 ተፈናቃዮች ምንም እርዳታ ያልቀረበላቸው ናቸው፡፡

አብዘኛቹ ተፈናቃዮች በጭልጋ ቁጥር 1 ፣በጭልጋ ቁጥር 2 ፣ምዕራብ ደምቢያ፣ ምስራቅ ደምቢያ እና ላይ አርማጭሆ አካባቢ የተፈናቀሉት ናቸው፡፡ ተፈናቃዮቹ በላይ አርማጭሆ ትክል ድንጋይ ከተማ አቅራቢያ እና በምዕራብ ደምቢያ ዓይምባ ቀበሌዎች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

የማዓከላዊ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽቤት ኃላፊ አቶ መንበሩ አውደው ተፈናቃዮች ያቀረቡት ጥያቄ ተገቢ መሆኑን አስረድተው ጽህፈት ቤቱ ለአንድ ሰው በወር 15 ኪሎ ግራም ምግብ ለማከፋፈል ጥረት እያደረገ ነው፤ ግን ደግሞ የተፈናቃዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ አስፈላጊውን ቁሳቁስ እና ምግብ ለማዳረስ መቸገራቸውን አስረድተዋል፡፡

እስከ አሁን ከ2ሺህ 500 ኩንታል በላይ ስንዴ እና 300 ሺህ ኩንታል አልሚ ምግብ መሰራጨቱን ገልጸዋል፡፡

አቶ አማረ ክንዴ ችግሩን ለመቅረፍ በማዕከላዊ ጎንደር ከሚገኙት የእህል መጋዘኖች 200 ኩንታል እህል ለተጠቃሚዎች ለማድረስ እየተጓጓዘ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ ከንዴ ገለፃ ከፌዴራል መንግስትም በተጠየቀው የድጋፍ እርዳታ 600 ኩንታል እህል እየተጓጓዘ ነው::

አብመድ እንደዘገበው ተጎጂዎች አስፈላጊውን የምግብ እና የቁሳቁስ እርዳታ እንዲያገኙ ከክልል እና ከፌዴራል መንግስት ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE