በአማራ ክልል ሀሰተኛ ምስክርነት ለፍትህ ስርዓቱ ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን የህግ አካላትና ነዋሪዎች አመለከቱ

በአማራ ክልል ሀሰተኛ ምስክርነት ለፍትህ ስርዓቱ ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን የህግ አካላትና ነዋሪዎች አመለከቱ፣ ችግሩን ለመከላከል የንቃተ ህግ ትምህርትን ለመስጠት ማቀዱን የአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አመልክቷል፡፡

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሀሰተኛ ምስክር በዜጎች ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሆነ ነው የፍትህ አካላትና ነዋሪዎቹ የሚገልፁት፡፡ችግሩ በክልሉ ምክር ቤት ጉባዔዎች ሳይቀር በተደጋጋሚ እየቀረበ ውይይት ቢደረግበትም መሻሻል እንዳልታየበት ነው የአነጋገርናቸው አካላት የሚናገሩት፡፡

አቶ ላንተይደሩ ተስፋዬ በባህር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአንድ ጉዳይ ለምስክርነት ተጠርተው ነበር ያገኘኋቸው ሀሰተኛ ምስክርነት በክልሉ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ነው ያሉኝ፡፡ የአማራ ክልል ምክር ቤት የህግና ፍትህ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ ሰጤ ችግሩን የክልሉ ምክር ቤት በየወቅቱ የተወያየበት ቢሆንም አሁንም ግን በአንዳንድ አካባቢዎች፣ በተለይም ከመሬት ባለቤትነት ጋር በተያያዘ በስፋት እንደሚታይ አብራርተዋል፡

የችግሩ የስፋት መጠን ሰፊ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አማረ ይህን ለማወቅ ጥናት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ፍርዴ ቸሩ በችግሩ ሴቶች፣ ህፃናትና እገዛ የሚፈልጉ የህብረሰብ ክፍሎች ተጠቂ መሆናቸውን ጠቅሰው የመንግስት ተቋማት ሳይቀር የተጣራ መረጃ ስለማይሰጡ ሀሰተኛ ምስክርነት ሰፊ ነው ብለዋል፡፡ እየሰፋ የመጣውን የሀሰተኛ ምስክርነት ለመከላከል የሰው ምስክርነትን የሚያስቀር አሰራር ለመዘርጋትና የንቃተ ህግ ትምህርት ለህብረተሰቡ ለመስጠት እቅድ መያዙን ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ለ«DW» ተናግረዋል፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE