የአምልኮ ቦታዎችን ማጥቃት ውጉዝ አገር አጥፊ ወንጀል ነው! – ድምፃችን ይሰማ

ድምፃችን ይሰማ

የአምልኮ ቦታዎችን ማጥቃት ውጉዝ አገር አጥፊ ወንጀል ነው!
የመንግስት እንዝህላልነት ህዝበ ሙስሊሙን ለተጨማሪ ጥቃት እያጋለጠ ነው!

ህዝበ ሙስሊሙ እየተካሄደ ያለውን ከህገ ወጥነት ተቆጥቦ በሰከነ መንፈስ ይመለከታል!

ሰሞኑን የተደራጁ የአምልኮ ቦታ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ይገኛሉ። ከሳምንት በፊት በደቡብ ጎንደር እስቴ ሁለት መስጊዶች ተቃጥለው ነበር። ከቀናት በፊትም በሐላባ የፕሮቴስታንት ቤተ አምልኮዎች ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት ጥቃት የደረሰ ሲሆን ትናንት ምሽት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን በአንዳቤት ወረዳ ጃራገዶ ቀበሌ ሌላ ሶስተኛ መስጊድ ተቃጥሏል። ይህ የተደራጀ የሽብር ተግባር አገሪቱ እየተከተለች ያለችውን አቅጣጫ እጅጉን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው።

የሁለቱን መስጊዶች ቃጠሎ ተከትሎ የአማራ ክልል መንግስት በቂ እርምጃ አለመውሰዱ፣ የህዝብ ሚዲያዎችም ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ሰጥተው አለመዘገባቸው ለሶስተኛ መስጊድ መቃጠል ሰበብ እንደሆነ ግልጽ ነው። እናም የፌደራል መንግስት፣ በተለይም የሰላም ሚኒስትር ጉዳዩን ታች ወርዶ መከታተል አለበት። አድሎአዊ ዘገባዎች እና ኢ-ፍትሀዊ እርምጃዎች ይህንን ችግር እንደሚያባብሱ እየታወቀ የመንግስት ሚዲያዎች ሳቀይር አድሏዊ ዘገባ ይዘው መቅረባቸው በእጅጉ የሚያስተዛዝብ እና ተቀባይነት የሌለው ነው።

ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ይህን መሰል ትንኮሳዎችን በሰከነ መንፈስ ማጤን እና ከስሜታዊነት መቆጠብ ይኖርበታል። ስሜታዊ እርምጃውን የሚፈልጉ ሴረኞችን ተንኮልም እንደተለመደው ሁሉ አጥብቆ መጠንቀቅ ይኖርበታል። መስሊሙ የተደራጀ ትንኮሳ ሲፈጸምበት በስሜት ተነሳስቶ ጸረ ህዝብ አካላት የሚፈልጉትን የህገወጥ እርምጃ አቅጣጫ እንደማይከተል ካሁን ቀደምም በተደጋጋሚ ያስመሰከረ ህዝብ ነውና በሰከነ መንፈስ ለመፍትሄ በመንቀሳቀስ የእምነት ቦታዎቹ ላይ እየተሰነዘረ ያለውን ጥቃት ድባቅ እንደሚመታ ጥርጥር የለውም።

የየትኛውም እምነት የአምልኮ ቦታዎች ሊደፈሩ አይገባም! የአምልኮ ቦታዎችን ለፖለቲካዊ ጥቅም ጭዳ ማድረግ አገር አጥፊ ውጉዝ አካሄድ ነው! በመሆኑም መንግስት ሚዛናዊነት ባልተለየው አኳኋን በአስቸኳይ ከወንጀሎቹ ጀርባ ያለውን የሽብር ቡድን ሊያስቆም ይገባል!

አላሁ አክበር!