ሕብረተሰቡ ሀገር ለመበታተን ለሚዘጋጁ ኃይሎች ራሱን አሳልፎ መስጠት የለበትም- ብ/ጀኔራል አሳምነው ጽጌ

አዲስ ዘመን – ሰሞኑን በጎንደር አካባቢ ከተፈጠረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ አጀንዳውን በማራገብ ሀገር ለመበታተን ለሚዘጋጁ ኃይሎች ራሱን አሳልፎ መስጠት እንደሌለበት የአማራ ክልላዊ መንግሥት የደህንነትና ሰላም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ጽጌ ገለጹ፡፡

ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ጽጌ ከአዲስ ዘመን ጋርባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት፤ ችግሩ ሕብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ በየአካባቢው ተደራጅቶ ራሱን መጠበቅ እንዳለበት ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ የአካባቢው ባለቤት ራሱ መሆኑን አውቆ ነቅቶ ከመጠበቅ ባሻገር፤ አጀንዳውን በማራገብ ሀገር ለመበታተን ለሚዘጋጁ ኃይሎች ራሱን አሳልፎ እንዳይሰጥ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡

‹‹ሰሞኑን በማዕከላዊ ጎንደር ጥፋት ያደረሰው ኃይል በሁለት ከፍተኛ ቡድኖች የተደራጀ፤ የታጠቀና ስምሪት የተሰጠው ኃይል ነው፡፡ አንደኛው ቡድን ቤቶችን የሚያቃጥል ሲሆን፤ ሁለተኛው ቡድን ደግሞ የመጀመሪያው ቡድን እንቅፋት ቢያጋጥመው ሊከላከል በሚችልበት ሁኔታ የተዘጋጀ ነበር›› ያሉት ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው በድንገት በተፈጸመው ጥቃት ከ30 በላይ ሰው ሕይወት አልፏል፡፡ ከ300 በላይ የአርሶ አደር ቤቶች ተቃጥለዋል፤ የተፈናቀሉ ዜጎችም አሉ ብለዋል፡፡

የተቀናጀውና የተደራጀው ኃይል በሁለት አቅጣጫ መምጣቱን አመልክተው፤ አንደኛው ቡድን ከ200 በላይ ፤ሁለተኛው ከ70 እስከ 80 ሰው የሚገመት የታጠቀና የተደራጀ ኃይል እንደነበረው እንደሚገመት ገልጸዋል፡፡ ብሬንና ድሽቃ የተባሉ የቡድን ከባድ መሳሪያዎችን መጠቀማቸውን ጠቁመዋል፡፡