በሃላባ በተከሰተ ግጭት በፕሮቴስታንት ቤተክርቲያኖች ላይ ጉዳት ደረሰ

በሃላባ በተከሰተ ግጭት በፕሮቴስታንት ቤተክርቲያኖች ላይ ጉዳት ደረሰ

በደቡብ ክልል ሃላባ ቁሊቶ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት 7 የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያኖች ላይ ጉዳት መድረሱን የሃላባ ዞን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ኑር እንደገለጹት ጉዳቱ የደረሰው “በዱራሜ አካባቢ መስጊዶች ላይ ጥቃት ደርሷል” በሚል በተሰራጨ የተሳሳተ የማህበራዊ ድረ-ገጾች መረጃ አማካኝነት ነው።

በዚህ ምክንያትም እስከ ትናንት ቀትር ድረስ በከተማዋ በሚገኙ የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖችና የማምለኪያ ስፍራዎች ላይ በተደራጁ ህገ-ወጥ ወጣቶች ጥቃት መፈጸሙን አስረድተዋል።

ጥቃቱ ቅጥር ግቢያቸውን ከማፍረስና ከማቃጠል ጀምሮ የመገልገያ ቁሳቁሶችን እስከ መሰባበር እንደሚደርስ ተናግረዋል።
በጥቃቱ የሞተ ሰው እንደሌለ የገለጹት ምክትል ኃላፊው እሳት ለማጥፋት የተንቀሳቀሰ አንድ የማዘጋጃ ቤት አሽከርካሪና የዞኑ የኮሙኒኬሽን ባልደረባ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው በሀላባ ሆስፒታል ህክምና እንደተደረገላቸው ገልጸዋል።

ግጭቱን ለመቆጣጠር ፖሊስና የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ግጭቱን ማረጋጋታቸውንና አጥፊዎቹን በቁጥጥር ሥር ማዋል መጀመሩን ጠቁመዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው በአካባቢው የተከሰተው ግጭት የከተማውን ሕዝብ የማይወክልና የኅብረተሰቡን አብሮ የመኖር ባህል የጣሰ መሆኑን አስረድተዋል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE