ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚያደርጉት ውይይት የሚሰክኑት መቼ ነው?

ከወራት በፊት ወደ አሜሪካን ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በጉብኝታች ወቅት እዚያ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከተናገሩት ንግግር መካከል የሚጠቀሰው፣ የሥልጣን ዘመናቸው የመጨረሻ ግብ በአገሪቱ ነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ ምርጫ ማድረግ እንደሆነ ነበር፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚያደርጉት ውይይት የሚሰክኑት መቼ ነው?
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስብሰባ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳና የፓርቲ ተወካዮች

ምንም እንኳን በአሜሪካ ጉዟቸው ወቅት ይህን ቃል ቢገቡምና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ካደረጉት ከመጀመርያው የበዓለ ሲመታቸው ንግግር ጀምሮ በተደጋጋሚ ሲናገሩት የነበረው፣ ሁሉንም ያሳተፈ የፖለቲካ ምኅዳር መገንባትና ለዚህም አንዱን ከአንዱ ሳይለዩ በጋራ እንደሚሠሩ መግለጽ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ይህንን ቢሉም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የፖለቲካ ተንታኞችና የተቃውሞ ጎራው አባላት፣ የተገባው ቃል ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ከሁሉም አስቀድሞ መሠራት ያለበት ነገር በአገሪቱ ያሉት አፋኝ ሕጎችን መሻር እንደሆነ ይገልጹ ነበር፡፡

ሕጎቹን ከመሻር ባለፈ ደግሞ ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች በአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አስመልክቶ፣ የተደራጀና ቀጣይነት ያለው ውይይትና ድርድር አስፈላጊነትንም እንዲሁ አበክረው ይገልጹ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በተለያዩ መልኮች ሲካሄዱ የነበሩ ድርድሮችና ውይይቶች ቀጥለዋል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ፍረጃው ተነስቶላቸው በአገሪቱ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳ ላይ ተሠልፈዋል፡፡

ከእነዚህ ድርጅቶች መካከልም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነት)፣ አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ እንዲሁም የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ከውጭ የመጡትን የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን ጨምሮ በአገሪቱ ለበርካታ ዓመታት በፖለቲካው ሲሳተፉ የነበሩ ድርጅቶች፣ አሁን ላለው የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ አዋጭ መፍትሔ ነው ብለው የሚያስቡትን የመፍትሔ ሐሳብ በየፊናቸው መሰንዘራቸውንም እንዲሁ ቀጥለዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚያደርጉት ውይይት የሚሰክኑት መቼ ነው?

አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዥው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ጋር አሉን በሚሏቸው አገራዊ ጉዳዮች ላይ ፊት ለፊት ተገናኝተው ለመወያየትም እንዲሁ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ ነበር፡፡

ምንም እንኳን የፓርቲዎች የእንደራደር ጥያቄ በዚህ መንገድ ሲቀርብ የተለየ ቢመስልም፣ አገሪቱን ለሦስት ዓመታት አካባቢ ሲያምሳት የነበረውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ኢሕአዴግ ለድርድር መቀመጡ የሚታወስ ነው፡፡

ኢሕአዴግ የሥነ ምግባር ደንብ ከፈረሙ ፓርቲዎች ጋር ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ያህል ባካሄደው የማራቶን ድርድር ወቅት በአገሪቱ ወሳኝ የሚባሉ እንደ ምርጫ ሥርዓት ማሻሻልን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅን፣ እንዲሁም የተሻሻለውን የኢትዮጵያ የምርጫ አዋጅ ለማሻሻል ተስማምተው ነበር፡፡

ምንም እንኳን ፓርቲዎቹ በጀመሩት ድርድር ብሔራዊ መግባባት የሚባለው አጀንዳ ላይ ደርሰው የነበሩ ቢሆንም፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሥልጣን በመልቀቃቸውና የአገሪቱ የፖለቲካ አሠላለፍ ለውጥ በማሳየቱ ምክንያት፣ የተጀመረውን ድርድር በእንጥልጥል እንዲቀር አድርጎታል፡፡

በዚህ መካከል በርካታ የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ የሚገለጽ ሲሆን፣ አፋኝ የነበሩትን ሕጎች የማሻሻል ጅማሮዎችና ምርጫ ቦርድን የመሳሰሉ የዴሞክራሲ ተቋማትን እንደገና የማደራጀት ሥራዎችም ተከናውነዋል፡፡

የአገሪቱን የፖለቲካ ኃይሎች የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ተሰባስበው በጋራ ቢሠሩ መልካም እንደሆነ የሚገልጹ የፖለቲካ ተንታኞችም፣ ከምንጊዜውም በላይ ድምፃቸው እየተሰማ ነው፡፡

የተወሰኑ ፓርቲዎችም በጋራ የመሥራትና የመዋሀድ ዕቅዳቸውንና ሥራቸውን በተለያዩ ወቅቶች ይፋ ሲያደርጉ ሰንብተዋል፡፡ ፓርቲዎቹ ራሳቸውን ለማጠናከር የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን በሚገልጹበት ወቅትም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱና ከውጭ አገር ከመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ኅዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ውይይት አድርገው ነበር፡፡ በውይይቱ መጨረሻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲዎች ሰብሰብ ቢሉ መልካም እንደሆነ ገልጸው ነበር፡፡

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ተካሂዶ የነበረው ውይይት አጀንዳዎች በአገሪቱ ስለተጀምረው ለውጥ፣ በመጪው ዓመት ስለሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ፣ እንዲሁም ድኅረ ምርጫ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያተኮሩ ነበር፡፡

በወቅቱ ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ተበታትነው የቀረቡ ጥያቄዎችን ያደመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከሁሉም በፊት ቀጣይ ውይይቶች የሚመሩበትን ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት በመስጠት ምርጫ ቦርድ ኃላፊነቱን በመውሰድ፣ የፓርቲዎቹን ጥያቄዎች አቀናጅቶ እንዲያቀርብና ቀጣይ የውይይትም ይሁን የድርድር ሒደቶች የሚመሩበት የውይይት መመርያ ሥርዓት እንዲያዘጋጅ የቤት ሥራውን ለቦርዱና ለፓርቲዎቹ ሰጥተው ነበር፡፡

ይህንን ውይይት ተከትሎ ፓርቲዎች ጥያቄያቸውን ለቦርዱ በጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከሁለት ሳምንታት በፊት ደግሞ 16 አንቀጾች ያሉትና በምርጫ ቦርድ አማካይነት የተዘጋጀ ቀጣይ የገዥው ፓርቲና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ውይይቶችና ድርድሮች የሚመሩበት ረቂቅ ደንብ አፅድቀዋል፡፡

ረቂቅ ደንቡን ከማፅደቅ ባለፈም በጽሑፍ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች በተደራጀ ሁኔታ ለቀጣይ ውይይት እንዲቀርቡ ተስማምተው ነበር፡፡ በስምምነታቸው መሠረት ደግሞ ረቡዕ ጥር 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በቀረቡት አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት ተገናኝተው ነበር፡፡

በዕለቱ ውይይቱ ወቅት ምንም እንኳን በቦርዱ አማካይነት ተዘጋጅተው የቀረቡ አጀንዳዎች የነበሩ ቢሆንም፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ቀደም ብለው ከደረሳቸው አጀንዳ ውጪ የተለያዩ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በማንሳት ስብሰባው ከታቀደለት ጊዜ፣ እንዲሁም አጀንዳ ውጪ እንዲሆን አድርገውታል፡፡

ስብሰባውን ሲመሩ የነበሩት የቦርዱ ሊቀመንበር ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ተወያዮች በአጀንዳው ላይ ብቻ በማተኮር አስተያየቶቻቸውን ወይም ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ በተደጋጋሚ ሲማፀኑ ተስተውለዋል፡፡

በረቡዕ ዕለት ውይይት ፓርቲዎቹ የሚቀርቡትን አጀንዳዎች አንድ በአንድ በማፅደቅ ለቀጣይ ድርድርና ውይይት ማዘጋጀት አንዱ ጉዳያቸው ቢሆንም፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች በሚያነሷቸው ጽንፍ የወጡና ከአጀንዳው ጋር ተያያዥነት በሌላቸው ጥያቄዎች ሳቢያ አጀንዳዎቹን ሙሉ በሙሉ ለማፅደቅ አልተቻለም፡፡

ከፖለቲካ ፓርቲዎች በጽሑፍ ቀርበውለት በዕለቱ ለውይይት ቀርበው እንዲፀድቁ በቦርዱ አማካይነት የቀረቡት ሰባት አጀንዳዎች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይን በተመለከተ በሚለው ሥር ውይይቶች የሚመሩበት ሥርዓትና ደንብ፣ የሥነ ምግባር ደንብ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደረግ ድጋፍ፣ የጋራ ምክር ቤትን የማቋቋም ጉዳይ፣ ስለፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት፣ ትብብርና ጥምረት፣ እንዲሁም ያልተመዘገቡ ፓርቲዎች (ከውጭ አገር የመጡና በአገር ውስጥ ያሉ) የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ምርጫ ቦርድን በተመለከተ ደግሞ ስለምርጫ ቦርድ አደረጃጀት፣ የምርጫ አፈጻጸም ሒደቱን ስለማዘመን፣ የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በሦስተኛነት የቀረበው አጀንዳ ደግሞ ምርጫ የ2012 ዓ.ም. እና የአካባቢ ምርጫን የተመለከተ ሲሆን፣ በዚህም ሥር ደግሞ የምርጫ መራዘምን፣ የ2012 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ፣ የአካባቢ ምርጫ፣ ሰላምና መረጋጋት፣ እንዲሁም ስለሰብዓዊ መብት የሚሉ ርዕሶች በአጀንዳነት ቀርበዋል፡፡

የዴሞክራሲ ተቋማትን የማሻሻል ጉዳይን በተመለከተ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ሕግ ማሻሻያ፣ የመገናኛ ብዙኃን ገለልተኝነትና አጠቃቀም፣ የዓቃቤ ሕግ፣ የፖሊስ፣ የደኅንነትና የመከላከያ ተቋማት ግንባታን ስለማሻሻል፣ እንዲሁም የዳኝነት ሥርዓቱን ስለማሻሻል የሚሉ ርዕሶች ተካተዋል፡፡

ሕገ መንግሥትና ፌዴራሊዝምን በሚመለከት ደግሞ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ፣ የሥራ ቋንቋ፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ፣ ሰንደቅ ዓላማ፣ ሚዛናዊ ውክልና ማግኘት፣ የድንበር ግጭቶችና የማንነት ጥያቄዎች፣ የፌዴራል ሥርዓቱና የሀብት ክፍፍል፣ የመንግሥት አደረጃጀት፣ የፌዴራል ክልሎች አከላለል፣ የወሰንና የማንነት ጉዳዮች፣ እንዲሁም የደቡብ ክልልን የተመለከቱ የሚሉ ርዕሶች ተዘርዝረዋል፡፡

ሌሎች ጉዳዮች በሚለው ርዕስ ሥር ደግሞ ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት፣ የሕዝብ ቆጠራ፣ እንዲሁም የፌዴራል ከተሞችና ነዋሪዎች ጉዳይ የሚሉት የተዘረዘሩ ሲሆን፣ በመጨረሻም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን በሚመለከት ከጎረቤት አገሮች ጋር ስለሚደረግ ግንኙነት የሚል ርዕስ ለአጀንዳነት ቀርቧል፡፡

ምንም እንኳን ከላይ የተዘረዘሩት በርካታ አጀንዳዎች አስቸኳይ ድርድርና ውይይት ተካሂዶባቸው፣ መጪውን ጠቅላላ ምርጫ አሳታፊ ለማድረግ ይቻል ዘንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰጥቶ መቀበል መርህ አጀንዳዎችን እየቋጩ መሄድ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም፣ በረቡዕ ዕለት ውይይት ግን የተስተዋለው ተሳታፊዎቹ ከአጀንዳ ውጪ፣ እንዲሁም ከፀደቀው ድርድሮች ከሚመሩበት ረቂቅ ደንብ ጋር የሚጣረስ ነበር፡፡

በዕለቱ ተሳታፊ የነበሩ አንዳንድ ፖለቲከኞችም ውይይቱን በትዝበት የተመለከቱት ሲሆን፣ በርካቶችም በሚቀርቡ የተዘበራረቁ ጥያቄዎች በመሰላቸት በሚመስል ስሜት በተደጋጋሚ ከአዳራሹ ሲወጡና ሲገቡ ይስተዋል ነበር፡፡

አጀንዳዎቹን ለመለየትና ውይይት ለማካሄድ መድረኩ ክፍት ሲሆን፣ ምንም እንኳን የመድረክ መሪዋ በመጀመርያ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነትና በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሠራር ቃል ኪዳን የሚል ባለ 20 አንቀጽ ሰነድ ላይ ተሳታፊዎች ቢጨመር ቢቀነስ የሚላቸውን ሐሳቦች እንዲሰነዝሩ ዕድል ቢሰጡም፣ ተሳታፊዎች ግን ከቃል ኪዳኑ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ጥያቄዎችን በመጠየቅ ሒደቱን አዝጋሚ አድርገውታል፡፡

ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር)፣ ‹‹በዚህ ዓይነት አካሄድ የተዘረዘሩት አጀንዳዎችን መጨረስና የታለመውን ግብ ማሳከት የሚቻል አይመስለኝም፤›› በማለት ትዝብታቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹በመጀመርያ ባለፈው ያፀደቅነው ረቂቅ የውይይት መመርያ መከበር አለበት፡፡ ሁለተኛ ደግሞ አስተያየት ሰጪዎችን ሊገራና በቅጡ ሊቆጣጠር የሚችል ልምድ ያለው አወያይ ሊኖር ይገባል፤›› በማለት አክለዋል፡፡

‹‹በዚህ ሁኔታ ለፖለቲካ ምኅዳሩ ወሳኝ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን፣ እንዲሁም የመጫወቻ ሜዳውን እኩል አድርገን እንሄዳለን ማለት ከባድ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ምርጫ 2012 ማሰብ አይቻልም፤›› ሲሉ ከዚህ አንፃር ምርጫው በጊዜው ይካሄዳል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ በበኩላቸው ውይይቱን፣ ‹‹አሠልቺና የተሻለ ነገር ሊገኝበት የማይችል፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡

እሳቸውም አሁን በተያዘው መንገድ የተዘረዘሩትን አጀንዳዎች ማጠናቀቅ በራሱ ሌላ ፈተና እንደሚሆን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ‹‹ውይይቱ ልምድ ባለው አካል መመራት አለበት፤›› በማለት አጀንዳዎቹ ለውይይት ቀርበው ፍፃሜ እንዲያገኙ ሌላ አካል አወያይ ቢሆን እንደሚመረጥ አስረድተዋል፡፡

ቃል ኪዳኑን በማፅደቅ ወደ ሌሎች ዓበይት ጉዳዮች ማምራት የረቡዕ ዕለት ስብሰባ አጀንዳው የነበረ ቢሆንም፣ ፓርቲዎቹ ቃል ኪዳኑ ላይ እንኳን የሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች የተለያዩና ጽንፍ የወጡ በመሆናቸው፣ ቃል ኪዳኑን አፅድቆ ወደ ሌሎች አጀንዳዎች መሻገር በራሱ ከፍተኛ የቤት ሥራ እንደሚሆን በርካቶች ገልጸዋል፡፡

እንደ ፖለቲካ ተንታኞች ዕይታ ደግሞ በዚህ ወቅት ምርጫው በጊዜው ይካሄዳል አይካሄድም የሚለው ጥያቄ ሳይሆን የሚያሳስበው፣ ምርጫው ቢካሄድ የተቃዋሚ ጎራው አማራጭ መሆን ይችላል ወይ የሚለው እንደሆነ በመግለጽ በተለያዩ ውይይቶች ወቅት የሚያራምዱዋቸውን ጽንፍ የያዙ አተያየቶችን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ፣ ይህንን ከባድ የቤት ሥራ ተቃዋሚ ጎራው ለመወጣት የመጀመርያው ሊሆን እንደሚገባ ያሳስባሉ


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE