የማዕከላዊ ጎንደር ደምቢያ፣ ጭልጋና ላይ አርማጭሆ ግጭቶች አገርሽተዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ያለው የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን የዓይን ምሥክሮች ተናገሩ፡፡

በችግሩ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንም ተናግረዋል፡፡

አብመድ ያነጋገራቸው የማዕከላዊ ጎንደር ደምቢያ፣ ጭልጋና ላይ አርማጭሆ ወረዳዎች ነዋሪዎች እንዳሉት በአካባቢዎቹ ግጭቶች አገርሽተዋል፡፡ ‹‹ከትናንት በስቲያ አይምባ አካባቢ ፣ ትናንት ደግሞ አገው ሰገዴ አካባቢ ሰዎች መሞታቸውን ተመልክቻለሁ›› ያሉት የዓይን ምሥክር የክልሉ መንግሥት አፋጣኝና ጠንካራ ሕግ የማስከበር እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

ቅማንትን የማይወክሉ መለዮ የለበሱና የታጠቁ ቡድኖች ጥቃት እያደረሱ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ያለፉት ሦስት ቀናት በጣም አስቸጋሪ ነበሩ፤ በድምጽ ማጉያ ‹እልልል› እያሉ ቤት ያቃጥላሉ፤ይህንን የአካባቢው ሰዎች ሲነግሩን ወደ ቦታው ልናግዛቸው ሄደናል፤ የተባለውን ችግርም በአካል ተመልክተናል›› ብለዋል የዓይን ምሥክሮች፡፡ ወደ አይምባ እና አገው ሰገዴ አካባቢ እየሄዱ ችግር ሲፈጥሩ ከተማረኩት መካከል ‹‹የተለያዩ መታወቂያዎችን የያዙ፣ ‹ቡላ› መለዮ የለበሱ፣ መትረዬስና ስናይፐር ጭምር የታጠቁ አሉ›› ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ለሕግ አካላት ቢጠቁምና ይዞ ቢሰጥም መለቀቃቸው ለችግሩ መፈጠር አስተዋጽኦ ማበርከቱንም የዓይን ምሥክሮች ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሕዝብ ለፖሊስ ይዞ ያስረከበው ሰው መልሶ ተለቅቆ ትክል ድንጋይ ላይ አንድን ሾፌር አግቶ ‹200 ሺህ ብር ካላስመጣህ እንገድልሀለን› እያለ ነው፡፡ ስለዚህ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል፤ የፀጥታ መዋቅሩንም ይፈትሽ›› ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው መግባት አንጻራዊ ሰላም እየፈጠረ መሆኑን የገለጹት የዓይን ምሥክሮቹ ጉዳዩን ለማረጋጋት እየጣረ እንደሆነና ችግሩንም ማርገብ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሥራ ኃላፊዎች መረጃ ለማግኘት በስልክ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፤ ምላሾችን እንዳገኘን እናደርሳለን፡፡

የአማራ ክልል ሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ችግሩ ማገርሸቱንና ለማረጋጋት እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ የጸጥታ አካላት ችግር ፈጣሪዎችን የመለየትና ጉዳዩን የማረጋጋት ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE