አዲስ አበባ የማናት ? በማትፈርስ ሀገር የሚፈርስ ምኞት (ስናፍቅሽ አዲስ)

አዲስ አበባ የማናት ?
በማትፈርስ ሀገር የሚፈርስ ምኞት
ከስናፍቅሽ አዲስ

አዲስ አበባ የኔ ናት የአንተ አይደለችም ለመባባል እኛስ ማን ነን ከተማችንስ ምንድን ናት? አዲስ አበባ የሀብታሞች ናት።

መድኃኒቱ ተገኘ እንጂ አልዳንም። ታመናል በአዲስ አበባ ጉዳይ ብቻ አይደለም የታመምንው። የከረመው ደዌ ጦስ ነው። ጉዳዩ የትም አለ። ሀዋሳን የሚያተራምሳት ምንድን ነው? የእኛናት የሚለው ልዩ ጥቅም አገኙ ከሚለው ጋር የተፈጠረው ትርምስ ነው። ከአንድ በላይ ብሔር መዲና ያደረጋቸው ከተሞች የይገባኛል በሽታ ላይ ወድቀዋል።

አርባ ምንጭን ያክል የፍቅር ከተማ ጋሞ ነህ? ጎፋ ነህ? መባባያ ነበረች። ሚዛን አማን በአምስት ብሔር ሽኩቻ ስትታመስ ኖራለች።

የሰው ፍቅር ምልክት ናት የምትባለው ሀረር የመጠላለፍ መዲና የሆነችው በይገባኛል እና በእበልጣለሁ ባዩ ብሔር ትርምስ ነው።

የቱ ጋ ነን ጤነኛ? ስለምንስ እንዲህ ባለው በሽታ አዲስ አበባ እንደ ልዩ መቼት ትታያለች።

ከብሔር አልፎ ጎጥ ከተሞቻችንን በይገባኛል ምኞት ተብትቧቸው የለ እንዴ? መቀሌ ከውልዋሎ ኳስ ተጫውቶ ከውጤት በኋላ አጋመ ይውጣ ያሉ አንደርታዎች የአጋመ ቤት ሲደበድቡ መቀሌ የእኛ ናት ባይነት እኮ ነው። ደብረ ብርሃንን መንዝ ሞላት የሚላችሁ ቡልጌ እኮ የወንዝ እንጂ የብሔር ልዩነት ሳይኖረው ነው።

በማትፈርስ ሀገር የሚፈርስ ምኞት የሚያፈርሰን በሽታው ስላልዳነ ነው። አሁን አዲስ አበባ የኔ ናት የሚለው ተደባዳቢ ምናልባት የአጭር ርቀት የታክሲ ሂሳብ መክፈያ የሌለው የወገን ባዳ ይሆናል። አዲስ አበባ የእሱ የሆነች ኑሮውን አጣጥሞ ይኖርባታል እንጂ የእሱ መሆኗን መፈክር ጽፎ አያሳምነንም።

እርግጥ ነው በሽታው መንጋ ውስጥ ካልገባን የምንድን በማይመስል ደረጃ ቡድናዊ ፀጋ ተላብሷል። አንድ የመሆን ስሜት ያለው ስብስብ ሌላውን ለማሸነፍ ስልቱ የሚያዋጣ መስሎት እንጂ መች አንድ ነው? አንድ ነን የሚሉ የኦሮሞ መብት ተሟጋቾች እኮ አርሴናል ወለጋ ከመባባል አላለፍም። ደሴን ቦረና ተጠቀጠቀባት የሚል ሰው ደሴ እንደገባችሁ አታጡም። ባህር ዳርስ በእነማን እንደምትታማ ጠፍቶን ነው።

ይልቁንስ አዲስ አበባ የአዲስ አበቤው ናት። አዲስ አበቤ የሚባለው ራሱ አዲስ አበባ እምብርት የተወለደው ማለት ብቻ መሆኑ እያበቃ ነው። የከተሜነት ዘይቤዋ ገብቶት ተወዳድሮ የሚኖር አቅም ኖሮት የሚከትም ማለት ነው። በአዲስ አበባ ላይ የሚታየው ሽኩቻ የታመመች ሀገር ካልዳነች የሚያጋጥማት የደዌ ማገርሸት ነው። ያን ያወቀ ትውልድ በከፋ ስለመታመም ሳይሆን ጨርሶ ስለመዳን ካላሰበ ዋጋ የለውም። አፍሪካ ውስጥ ፈርሶ የሚኖር ሀገር ብዙ ነው። ኢትዮጵያ እናፍርስሽ ብንላት አትፈርስም የፈረሰ ትውልድ ከመሆን የሚታደገን ግን የለም።

ከተሜነት በምሪት አይመጣም። ከተሜነት በአትምጣብኝ ባይነት ምሬትም አይፀናም። ኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ላይ ብዙ ችግር አይታየኝም። ጤፍ የሚሸጥልኝ ጎመን ቀንጥሶ የሚያበላኝ ዙሪያዬ ያለው ገበሬ ወገኔ ነው። እሱ ያለ እኔ አራሽ እንጂ ጎራሽ እንደማይሆነው እኔም ያ እሱ ፎቅ እንጂ ቀለብ አይኖረኝም። ልዩ ጥቅም ልዩ ጉዳት ሳይሆን የሚሰራውን ስራ እደግፋለሁ። ግን ደግሞ አዲስ አበባ የኔ ናት የኔ የሚለውን የከሸፈ ትውልድ ሀሳብ እኮንናለሁ።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE