ከ1ሺህ በላይ አውቶብሶች ቢሰማሩም የትራንስፖርት ችግሩን እየቀረፉ አይደለም ተባለ

የመንግስት አውቶብሶች የትራንስፖርት ችግሩን እየቀረፉ አይደለም ተባለ

በከተማዋ ከ1ሺህ በላይ አውቶብሶች ቢሰማሩም የትራንስፖርት ችግሩን መቅረፍ እንዳልተቻለ የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ባስልጣን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ እንደሚለው የከተማዋ ስፋትና የህዝቡ ቁጥሩ መጨመሩ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎቱን ፍላጎት ለማርካት አዳጋች አድርጎታል፡፡

የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ዘለቀ ለኢትዮጵ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንደተናገሩት በአዲስ አበባ ሁሉም አቅጣጫዎች በ10 መስመሮች ከ1ሺህ በላይ የህዝብ ማመላለሻ አዉቶብሶችን አሰማርቶ ቢሰራም ችግሩ ሊቀረፍ አልቻለም፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተገነቡባቸው አካባቢዎች ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል በልዩ ትኩረት እየተሰራም ነው ብለዋል፡፡

ለአብነት ከሜክስኮ ኃይሌ ጋርሜንት በገላን አድርጎ ቱሉድምቱ ፣ከመገናኛ አስከ የካ አባዶና ከሜክስኮ እስከ ጀሞ ባሉ እያንዳንዱ መስመር ከ60 በላይ የአምበሳና ሸገር ትራንስፖርት አዉቶብሶችን በመመደብ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ መሆኑን ባስልጣኑ አመልክቷል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻልም የስምሪት ክትትልና ቁጥጥሩ የተጠናከረ እንዲሆን ለማስቻል በ10 ቅርንጫፎች ሁለት ሁለት ተቆጣጣሪ ባለሙያዎችን ባለስልጣኑ መድቦ በሬድዮ ተግባቦት በመታገዝ ጭምር እየሰራ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

በስራ መግቢያና መውጫ የሚታዩ ረጃጅም ሰልፎችንም በአጭር ጊዜ በአግባቡ ለማስተናገድ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በዘላቂነት የትራንስፖርት ችግሩን ለመፍታት ከ3 ሺህ 5 መቶ በላይ አዉቶብሶች እንደሚያስፈልግ አስታውቋል፡፡

ከዚህ ውስጥ አስተዳደሩ በቀጣይ 500 አዉቶብሶችን ጨረታ አዉጥቶ በመግዛት ፈጣንና ዘመናዊ ትራንስፖርት ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑንም የከተማዋ ትራንስፖርት ባለስልጣን አመልክቷል፡፡

(ኢ.ፕ.ድ)


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE