የመንግሥት ተቋማት ጣልቃ ገብነት የፍርድ ቤቶችን ነፃነት እየነፈገ መሆኑ ተጠቆመ

Reporter : የፍትሕ ሥርዓቱን በጅምላ ፈርጆ መውቀስ ተገቢ አይደለም ተብሏል

የደኅንነት አባላት ጣልቃ ገብነት ዳኞችን እስከ ማሾምና እስከ ማሻር ይደርሳል 

የሕዝቡንና የአገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ በተቋቋሙ የመንግሥት ተቋማት ጣልቃ ገብነት፣ የፍርድ ቤቶችን ነፃነት እየነፈገና ተዓማኒነታቸውንም እያሳጣ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተዘጋጀው የሕግ ባለሙያዎች የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸው ፍርድ ቤቶች በደኅንነት አባላት፣ በፖሊስ፣ በዓቃቤ ሕግና በሌሎች የሥራ አስፈጻሚው አካላት ጣልቃ ገብነት ምክንያት ገለልተኛ ፍርድ ለመስጠት እንደሚቸገሩና ፍትሕ እየተጓደለ መሆኑ፡፡

ሥራ አስፈጻሚው አካል በግልጽ በፍርድ ቤት ጉዳዮች ጣልቃ ይገባል ያሉት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ደበበ ኃይለ ገብርኤል፣ በተለይ የደኅንነት አካላት ተፅዕኖ ብርቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የደኅንነት አባላት ጣልቃ ገብነት ዳኞችን እስከ ማሾምና እስከ ማሻር ይደርሳል ብለዋል፡፡ ጉዳይ ማስፈጸም ድርጊት ውስጥ እንደሚሰማሩ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ችሎት በሚካሄድበት ክፍል ተገኝተው የዳኞችን ሁኔታ እስከ ማጥናት እንደሚደርሱ ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል፡፡

አቶ ደበበ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚታዩትን ክፍተቶች ግለሰባዊ፣ ተቋማዊ፣ ውጫዊና ውስጣዊ በሚል ለአራት ከፍለው ባቀረቡት መነሻ ሐሳብ የፍርድ ቤትን ተዓማኒነት አደጋ ላይ እየጣለ የሚገኘው የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ‹‹እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የደኅንነት ተቋሙ ጓዙን ጠቅልሎ የገባው ፍርድ ቤት ነው፡፡ በዳኞች ሹመት፣ ጉዳይ በማስፈጸም፣ በማስፈራራትና በማንኛውም ነገር ፍርድ ቤት ገብቷል፡፡ ይህ ፍርድ ቤቶቻችን ተዓማኒነት እንዳይኖራቸው አድርጓል፤›› ብለዋል፡፡

የፍርድ ቤትን ተዓማኒነት በማሳጣት ረገድ ዓቃቤ ሕግም የራሱን ሚና ተጫውቷል ተብሏል፡፡ አንዳንድ ዓቃቤ ሕጎች ዳኞችን እስከ ማስፈራራት እንደሚደርሱ፣ በከሳሽና በተከሳሽ መካከል ያለውን እኩል የመዳኘት መብት ጥሰው ዓቃቤ ሕጎችን ተክተው ተከሳሾችን የሚጠይቁ ዳኞችም መኖራቸው ፍርድን እያጓደለ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃ ሲያቀርብ ተቆጥተው ተከሳሽን ‘ጠብ እርግፍ’ አድርገው የሚጠይቁ ዳኞችም እንደሚያጋጥሙ ተጠቁሟል፡፡፡ ‹‹ይህ የሁለቱን አካላት እኩልነት የሚፃረር ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ችሎቶችን የሚታደሙም ከፍርድ ቤት ፍትሕ አገኛለሁ የሚል እምነታቸውን ያጣሉ፤›› ሲሉ አቶ ደበበ አስረድተዋል፡፡

የፍርድ ቤትን ተዓማኒነት የሚያሳጡት በተለያዩ ጊዜያት የሚነግሡ የዓቃቤ ሕግ አካላት ናቸው ሲሉ አቶ ደበበ አስታውቀዋል፡፡ በአንድ ወቅት ልዩ ዓቃቤ ሕግ፣ በሌላ ጊዜ የገቢዎች ዓቃቤ ሕግ፣ እንዲሁም የፀረ ሙስና ዓቃቤ ሕግ አባላት ነግሠው ዳኞችን አስጨንቀዋል ብለዋል፡፡

‹‹እነሱ ለአስፈጻሚው አካል ቅርብ ናቸው፡፡ ደመወዛቸውም ዳኞች ከሚያገኙት የበለጠ ነው፡፡ ዳኞችን ለማስፈራራት ያላቸው አቅም ትልቅ ነው፡፡ ስለዚህ ላለፉት 20 ዓመታት የዓቃቤ ሕግ ጡንቻ ከዳኞች በላይ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ፖሊስም እንዲሁ ለፍርድ ቤቶች ተዓማኒነት ማጣት የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል ሲባል ትችት ቀርቦበታል፡፡ በተለይ በምርመራ ወቅት ፖሊሶች ዘንድ ያለው ችግር ፍርድ ቤቶች ተዓማኒነት እንዲያጡ አድርጓል ተብሏል፡፡ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን ‘እንደፈለገ አድርጎ’ ፍርድ ቤት ሲወስዳቸው፣ ተጠርጣሪዎች የደረሰባቸውን ለፍርድ ቤት ሲያስረዱ ዳኛው አያስጥላቸውም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹በነገራችን ላይ አሁን የምናያቸው በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዳኞች ቡራኬ ጭምር የተከሰቱ ናቸው፡፡ ተገርፌያለሁ ብሎ ልብሱን አውልቆ የተጎዳ አካሉን ሲያሳያቸው መልስ የማይሰጡ፣ ምንም ዓይነት ዕርምጃ የማይወስዱ፣ በእነሱ ትዕዛዝ ፖሊስ ጣቢያና ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ በተደረጉ ተጠርጣሪዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ምንም ግድ የማይሰጣቸው አሉ፤›› ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ያሉትን ችግሮች ለማሳየት እንጂ ሁሉም ዳኞች ተመሳሳይ ድርጊት ይፈጽማሉ ማለት አለመሆኑን አስምረውበታል፡፡

በሥልጠናው ወቅት ሐሳባቸውን የሰጡ ሌሎች የሕግ ባለሙያዎችም የፍትሕ ሥርዓቱን በጅምላ ፈርጆ መውቀስ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ በፍትሕ ሥርዓቱ የሚታዩ ጉድለቶች ቢኖሩም በአጠቃላይ ግን የዳኝነት ሥርዓቱን መውቀስ ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዳኞች ሰብዕና ጋር በተያያዘም ጎልቶ የሚታይ የዕውቀት ማነስ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ‹‹እንዲህ ያለ ሰው አይደለም ዳኛ የሠፈር ሽማግሌ መሆንስ ይችላል ወይ የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ፣ የአቅም ውስንነት ያለባቸው ሰዎች ዳኛ ሆነው ሲሾሙ ይታያል፤›› ብለዋል፡፡ አንዳንድ ዳኞች ተብለው የሚሾሙ ካለባቸው የአቅም ውስንነት አንፃር ጉዳዩን ወይም ነገሩን ለመረዳት ይቸግራቸዋልም ተብሏል፡፡

ከዳኞች አቅም ጋር ተያይዞም የሚሾሙ ዳኞችን በደፈናው ከመውቀስ ይልቅ የዳኞችን አቅም ለመገንባት ጥረት እንደማይደረግ የሕግ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ የዳኞችን አቅም በማጎልበት ረገድ ከፍተኛ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ፖለቲካ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይም በነፃነት ለመወሰን የሚቸገሩ እንዳሉ ተነግሯል፡፡ ‘እንዲህ ብዬ ብወስን ምን እሆናለሁ?’ በሚል ሥጋት ለመወሰን መቸገር እንዳለ፣ ለፖለቲካ ወገንተኛ የሆኑ ዳኞች መኖር በአሁኑ ወቅት በፍርድ ቤት ውስጥ በግልጽ የሚታይ ችግር እንደሆነና በብሔር፣ በሃይማኖት፣ እንዲሁም በጓደኝነት የሚከናወኑ ሥራዎች የፍርድ ቤቶችን ተዓማኒነት የሚገዳደሩ እንደሆኑም ተመልክቷል፡፡

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ተከራክሮ አሸንፋለሁ የሚለው ነገር እያከተመለት ነው የሚሉት አቶ ደበበ፣ መንግሥት እንደ ማንኛውም ሰው መዳኘት ሲኖርበት ለመንግሥት ወግነው የሚከራከሩ ዳኞች መኖር ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ሰበር ድረስ የሄዱ የፍርድ ቤት መዛግብትን መመልከት ይቻላል ብለዋል፡፡ ባለጉዳዮችን በቀጠሮ ማመላለስ፣ ግልጽ ችሎት አለማስቻል፣ ዳኞች በአደባባይ ወጥተው የመንግሥትን ፖሊሲና አሠራር አቋም ይዞ መከራከርና የመሳሰሉት የፍርድ ቤት ተዓማኒነትን እያሳጡ ከሚገኙ የዳኞች ባህሪ መካከል ተብለው የተዘረዘሩ ናቸው፡፡

በጠበቆች፣ በነገረ ፈጆችና በአማካሪዎች በኩልም የራሳቸውን ድክመት በዳኞች ማሳበብ፣ የፍርድ ቤትና የዳኞችን ነፃነት አሳልፎ መስጠት፣ መንግሥትን በአሉታዊ መንገድ ማማከር፣ የዕውቀት ችግር፣ የፍርድ ሒደት እንዲጓተት ማድረግ፣ የሐሰት ማስረጃዎችን ማቀነባበር፣ ለጉዳይ እንጂ ለምክንያት አለመሥራት ችግሮች እንዳሉባቸው ተነስቷል፡፡

‹‹ልጆቼን ላሳድግ እያለ የሰው ሕይወት ሲበጠብጥ የነበረ ጠበቃ ዛሬ ማልያውን ቀይሮ እኛን እየወቀሰን ነው፤›› ያሉ አስተያየት ሰጪ፣ የሚታየው ችግር ከሁሉም ወገን የመነጨ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለሌላው ወገን ሲወሰን ዳኛው ገንዘብ በልቶ ነው እያሉ ስም የሚያጠፉ ጠበቆችም፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ተዓማኒነት እንዲያጣ እያደረጉ እንደሆነ ከመድረኩ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የፍትሕ ሥርዓቱን ማጠናከር ግድ እንደሚል፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡

FacebookTwitterLinkedIn


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE