አስገዳጅ የሥራ ሁኔታ ላይ እያሉ በአድማ ሥራቸውን በማቆማቸው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ክስ ተመሠረተባቸው

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ስምንት ሠራተኞች፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ክሱ የተመሠረተባቸው ረቡዕ ጥር 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ ክሱን የመሠረተው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ  ሕግ ነው፡፡

ተከሶሾቹ አስገዳጅ የሥራ ሁኔታ ላይ እያሉ በአድማ ሥራቸውን በማቆማቸውና ዓለም አቀፍ በረራዎችን በማስተጓጎላቸው፣ አየር መንገዱ 56 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንደደረሰበት ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡ በተከሶሾቹ ምክንያት አየር መንገዱ 14.9 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ በማድረግ ለጉዳት መዳረጉ በክሱ ተመልክቷል፡፡

ተከሳሾቹ ከአሥር ወራት በፊት በዚህ ጉዳይ በቁጥጥር ሥር ውለው ከአንድ ወር እስር በኋላ፣ እያንዳንዳቸው በ20 ሺሕ ብር ዋስትና መለቀቃቸውንና ከአገር እንዳይወጡ ዕግድ እንደተጣለባቸው ጠበቃው አስረድተዋል፡፡ ስለሆነም ዋስትና የሚከለክል ክስ ስላልተመሠረተባቸው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ እያንዳንዳቸው በ15 ሺሕ ብር ዋስ በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ፈቅዷል፡፡