የሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ወደ ደቡብ ጎንደር ሊያቀኑ ነው

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ወደ ደቡብ ጎንደር ሊያቀኑ ነው። ጉዞው ወንጀል ፈጻሚዎች በህግ እንዲጠየቁ ጫና ለማሳደር ፡ በሁለቱ ሃይማኖቶች ምእመናን ላይ ያለው ወንድማማችነት እንደቀደመው እንዲቀጥል እና መስጂዶቹን ዳግም ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ የታቀደ መሆኑን ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ ለDW ተናግረዋል

ወንጀል ፈጻሚዎች በህግ እንዲጠየቁ ጫና ለማሳደር ፡ በሁለቱ ሃይማኖቶች ምእመናን ላይ ያለው ወንድማማችነት እንደቀደመው እንዲቀጥል እና መስጂዶቹን ዳግም ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ ሊያቀኑ ነው፡፡

Image result for የሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት

የሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ለ DW እንደነገሩት ድርጊቱ በተለይ በአሁኑ ወቅት ሊደረግ የማይገባ እንደነበር አውስተው ምክንያቱ ምንም ቢሆን በውይይት መፈታት ነበረበት ብለዋል፡፡ በህዝቡ ውስጥ መቃቃር እንዲፈጠር ሃላፊነት የጎደለው ስራ የሚያከናውኑ የንግድ ተቋማትም የማያዳግም እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላቱ ወደ ስፍራው በማቅናትም ከሁለቱም ሃይማኖቶች ምእመናን እና ከወረዳወ መስተዳድር አካላት ጋር እንደሚወያዩና ዘላቂ የሰላም መፍትሄ ሃሳቦችንም እንደሚለዋወጡ ነግረውናል፡፡

እንዲህ አይነቱ ክስተት ከዚህ በፊትም በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች እንደተስተዋለ ያብራሩት ኡስታዝ አቡበከር አዝማሚያው አሳሳቢ እንደሆነና በተለይ ለውጥ የማይፈልጉ አካላት ህዝብን ለማቃቃር እና ለማናከስ ብሄር እና ሃይማኖት የተባሉ ሁለት ጠብ አጫሪ ካርዶች ያላቸው መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ወገን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡