ኢትዮጵያዊነት ላይ ሳይሆን ዘር ላይ ዜጎች እንዲያተኩሩ ያደረገው ሕገ መንግስቱና አወቃቀሩ ነው #ግርማካሳ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


“የአማራ፣ የትግሬ፣ የኦሮሞ መሬት ነው የሚለው ነገር ድንቁርና ነው ”

አንዳንዴ በምስልና በፎቶ ነገሮች በቀላሉ ግልጽ የመሆን እድላቸው በጣም ሰፊ ነው። አንድ ብዙ ጊዜ የምንጽፍበትና የምንከራከርበት ጉዳይ አለ። እርሱም ዜጎች በአገራቸው እንደ መጤና አገር አልባ የመቆጠራቸው ችግር ነው። “አገራችሁ አይደለም፣ መጤ ናችሁ፣ ውጡልን ..” መባሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና እየሆነ ነው።

“መጤ ናችሁ፣ አገራችሁ አይደለም..” ተብለው ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት በተለይም በደቡብ፣ በኦሮሞና በቤኔሻንጉል ክልል አማራዎች፣ አማራ ያልሆኑ አማርኛ ተናጋሪ የሆኑ ከተለያዩ ብሄረሰብ የተወለዱ፣ ጉራጌዎች፣ ከንባታዎች …ከቅያቸው ተፈናቅለዋል። አሁን በቅርቡ እንኳን በምስራቅ ሸዋ ዞን በፈንታሌ ወረዳ በአክራሪ ኦሮሞዎች ከአገራችን ውጡልን ተብለው በጭካኔ ብዙ አማራዎች ተፈናቅለው። በአሁኑ ወቅት በአዋሳ በአክራሪ ሲዳሞዎች የጉራጌ ማህበረሰብ አባላት ሱቃቸው እየተዘጋ ከአገራችን ዉጡልን እየተባሉ ነው። ብዙ ከንባታዎች ከአርሲ ተፈናቅለዋል።በሌሎች አካባቢዎች ያሉትን ስንመለከት ደግሞ ወደ ስድስት መቶ ሺህ ኦሮሞዎች ከሶማሌ ክልል፣ አራት መቶ ሺህ ሶማሌዎች ከኦሮሞ ክልል፣ ሁለት መቶ ሺህ ኦሮሞዎችና አማራዎች ከቤኔሻንጉል ክልል፣ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ጌዴዎኦች ከኦሮሞ ክልል፣ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ጋሞዎች አሁንም ከኦሮሞ ክልል….መጤ፣ አገራችሁ አይደለም ተብለው ተፈናቅለዋል። ብዙዎች በዘር ተኮር ጥቃት ተገድለዋል።

ይሄን ዜጎች መጤ የማለትና የማፈናቀል መንፈስ ያመጣው ፣ ያመጣው ብቻ ሳይሆን ያጠናከረው፣ በሕወሃትና በኦነግ የተረቀቀው ዘረኛ ሕገ መንግስትና ዘረኛ የፌዴራል አወቃቀር ነው።

በፌዴራሉ አወቃቀር መሰረት አገሪቷ በዘርና በጎሳ ነው የተሸነሸነችው። ስለዚህ አማራው ከአማራ ክልል ውጭ፣ ጉራጌው ከጉራጌ ዞን ውጭ፣ ከንባታው ከከንባታና ጥንባሮ ዞን ውጭ አገራቸው እንዳለሆነ ነው ሕግ መንግስቱ የሚያስቀምጠው። በአንቀጽ ስምንት መሰረት የኢትዮጵያ ሉአላዊነት ለኢትዮጵያ ህዝብ ወይንም ለዜጎቿ ሳይሆን ለብሄር ብሄርሰብና ሕዝቦች ለሚሉት ነው። አንድ ዜጋ ባለ አገር ተደርጎ የሚወሰደው ለርሱ ብሄር ብሄረሰብ በተወሰነለት ቦታ ብቻ ነው። ከዚያ ውጭ ከኖረ መጤ ነው የፖለቲካ ዉክልና የለዉም።

ከዚህ በታች በቀረበው ቻርት ላይ እንደሚታየው 44% ጉራጌዎች የሚኖሩት ከጉራጌ ዞን ውጭ ነው። 24% አማርኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሆኑ፣ 20% አማራዎች የሚኖሩት ከአማራ ክልል ውጭ ነው። 23% ከንባታዎች የሚኖሩት ከከንባታና ጥንምባሮ ዞን ውጭ ነው።

እንግዲህ ይሄ የሚያሳየው፣ መብቶ ተረግጦ፣ ዉክልና ተነፍጎ፣ በአገሩ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥሮ ፣ ለርሱ ጎሳ ወይንም ዘር ከተመደበው ቦታ ውጭ የሚኖረው ማሀህበረሰብ ምን ያህል ብዙ እንደሆነ ነው። ያ ብቻ አይደለም፣ ከተለያዩ ብሄረሰቦች የሆኑ፣ ራሳቸው የኢትዮጵያ ብሄረተኞች ነን የሚሉ በአገሪቷ የትም ቦታ የፖለቲካ ዉክልና የላቸውም። በአንድ ብሄር ብሄረሰብ ጆንያ ውስጥ አንድ ዜጋ ካልገባ አሁን ባለው ስርዓታ ሕግ መንግስት ምንም አይደለም።

አንዳንድ ወገኖች ሕገ መንግስቱ ማንም ዜጋ በሁሉም ቦታ በነጻነት የመኖር መብትን ደንግጓል ይላሉ። አዎን ደንግጓል። እንደ አሜሪካ ፣ እንግሊዝ ባሉ አገሮች የሚኖሩ ስደተኞች የመኖሪያ ፍቃድ ካላቸው፣ በነጻነት የመኖር መብት አላቸው። ጃዋር መሐመድም ይሄን ብዙ ጊዜ ይለዋል። አንድ ጊዜ እንደዉም “ኬኒያ ኢትዮጵያዉያን በሰላም ይኖሩ የለም ወይ? በኦሮሚያ ልክ እንደ ኬኒያ ኢትዮጵያዉያን መኖር ይችላሉ” ነበር ያለው። ሕገ መንግስቱ በዚያ መልሉ ነው ዜጎች በሁሉም ቦታ መኖር ይችላሉ ያለው ። በክልላቸውና ወረዳቸው ወይንም ለነርሱ በታጠረው አጥር እንደ ባለአገርና አንደኛ ዜጋ፣ ከዚያ ውጭ ደግሞ የዉጭ አገር ዜጎች እንደሚኖሩት እንደ ሁለተኛ ዜጋ ፣ አንደኛ ዜጋ በተባሉት በጎ ፍቃድ መኖር ይችላል።

ይሄ አይነት አሰራር ለአገር ትልቅ አደጋ ነው። አገሪቷን የበለጠ ትልቅ ቀዉስ ውስጥ ነው የሚከታት ። የሚከታት ብቻ ሳይሆን እየከተታትም ነው። የጎሳ ግጭቶች የዘር መካረሩ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ከመምጣቱ የተነሳ፣ የደሃዴን ሊቀመንበር የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈርያት ካሚል “ኢትዮጵያዊነት እና ማንነት መቼም አይጋጩም፣ ተጋጭተውም አያውቁም! እኛ ነን ‘ኢትዮጵያዊነት ይቆየን’ ብለን፣ የመንደርና የብሔርን ፓለቲካ ቅድሚያ ሰተን መለያየትን ያመጣነው። እኛ ነን ‘ብሔር ብሔር ብሔር’ ብቻ እያልን፣ ኢትዮጵያዊነትን ያደበዘዝነው! ከዚህ በኋላ ‘ኢትዮጵያዊነታች’ የማንነታችን ዋስትና እንደሆነ ለማረጋገጥ በርትተን እንሠራለን” ሲሉ ከዚህ በፊት የነበረው ጎሳና መንደርተኝነትን እንጂ ኢትዮጵያዊነት እንዳደበዘዘነው የገለጹት።

ሌላው የኢሕአዴግ ዓባል ፓርቲ ሊቀመነበር፣ ህወሃቱ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ደግሞ፣ ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር በአማራና ትግራይ ክልል መካከል ያሉት ችግሮች በሰላም እንደሚፈቱ በጋራ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ “እኛ ነን በሕዝብና በህዝብ መካከል አጥር ያደረገነው” ሲሉ ሕዝብ ከክልል በላይ መሆኑ የገለጹት። “ህዝብ ከክልል በላይ ነው። በኢትዮጵያ የተጣላ ህዝብ የለም። ህዝቡ እየተበደለ አብሮ ለመኖር ይፈልጋል። የተጣሉት ጥቂት ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ እኛ ለፖለቲካ ክልል አጠርን እንጅ ህዝቡ ግን አልታጠረም የምንጋጭ ቢሆን እስካሁን እንጋጭ ነበር፡፡ ከግጭት ያስቆመን ህዝቡ እራሱ ነው፡” ነበር ዶ/ር ደብረጽዮን ያሉት።

የኢሕአዴግ አመራሮች ችግሮች እንዳሉ የገባቸው ይመስላል። ዘረኝነት መንደርተኝነት አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ያወቁ ይመስላል። መፍትሄ ለማግኘት እየተሯሯጡ ነው። የሰላም ኮንፍራንሶ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች የመሳሰሉትን እያደረጉ ነው። ችግር በሽታ፣ ነቀርሳ መኖሩን ማመናቸው ትልቅ ነገር ሆኖ አሁንም ግን ነቀርሳዉን ቆርጦ ከመጣልና ለአገሪቷ ዘላቂ መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ ፣ ማስታገሻ መድሃኒት በመስጠት ላይ ነው የሚሯሯጡት። የሰላም ኮንፍራንስ፣ ሕዝብ ለሕዝብ ..የሚሉት ሁሉ ማስታገሻዎች ኪኒኖች ናቸው።

እኛ እንደ አገር የሚያስፈልገን ካንሰራችንን ቆርጦ የሚጥልልን ቀዶ ጥገና ነው።ካንሰራችን ሕግ መንግስቱ፣ የፌዴራል አወቃቀሩ በአጠቃላይ ዘርን መሰረት ያደረገው ስርዓቱ ነው። ይሄ መስተካከል አለበት። ሕገ መንግስቱ መቀየር አለበት። የጎሳ በሉት የዘር አወቃቀር መፍረስ አለበት። እያንዳንዱ ዜጋ በሁሉም የአገሪቷ ክፍል መድልዎ፣ ልዩነት ሳይደረግበት እንደ ባለ አገር መኖር መስራት፣ መነገድ፣ መማር. መመረጥ፣ መምረጥ፣ ኢንቨስት ማድረግ፣ መዉጣት፣ መግባት መቻል አለበት። የትግሬ መሬት፣ የአማራ መሬት፣ የኦሮሞ ምድር የጉራጌ ምድር የሚለው ነገር ድንቁርና ነው !!!! ከድንቁርና መውጣት አለብን!!!