የዜግነት ፖለቲካ ይሰራል፣ አሸናፊም ነው- ምላሽ ለአብኖች – ግርማ_ካሳ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

ዋልታ ከአብን ም/ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላና ከሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊው አቶ ክርስቲያን ታደለ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ፣ ሁለቱንም ክፍሎች አደመጥኩ።

ወደ ቃለ መጠይቆቹ ይዘት ከመግባቴ በፊት ስለ ዋልታ ጋዜጠኛው ትንሽ ማለት ፈለኩ። የቤት ስራውን በደንብ ሳይሰራ የመጣ ነው የሚመስለው። ያ ብቻ አይደለም እንደ ገለልተኛ ጋዜጠኛ ሳይሆን የሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካይ ነበር የሚመስለው። በግለሰቦች የሚታተመውን የበረራ ጋዜጣ የአብን እንደሆነ እድርጎ መግለጹን እንደ አንድ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል። ካልጠፋ አጀንዳ፣ በአብን አርማ ላይ ስላለው የንስር ምልክት በማንሳት “የንስር ምልክት ያላችሁት ከሌላው የበላይ ነን ለማለት ብላችሁ ነው” የሚል መላምታዊ አስተያየት መስጠቱንም እንደሌለ ሁለተኛ ምሳሌ ልንጠቅሰው እንችላለን። በአጠቃላይ በኤልቲቪ የቤቲ ታፈሰ ዝግጅት ላይ እንደበረው፣ አብኖች ከዋልታ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ “hostile” ቃለ ምልልስ ነበር ማለት ይችላል።

አንዳንድ “ታዋቂና በሳል” የሚባሉ የፖለቲካ አመራሮች ለነርሱ አመለካከት ቅርብ የሆኑ ሜዲያዎች ላይ ብቻ እየመረጡ እንደሚቀርቡ ይታወቃል። አብኖች ” hostile” በሆኑ ሜዲያዎች ላይ ቀርበው ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት መቻላቸው ምን አልባት ከነርሱ ጋር የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ስላለን ላይታየን ይችል ይሆናል እንጂ ጥንካሪያቸውን በአንድ ጎኑ የሚያሳይ ነው።

ወደ ቃለ ምልልሱ ይዘት ስንመለስ ብዙ ጥያቄዎች ያጠነጠኑት ከአማራነትና በአማራ ማንነት ዙሪያ በእደራጀት አስፈላጊነት ዙሪያ ላይ ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝ የግል አቋም በፊትም የነበረኝ፣ አሁንም ያለኝ ወደፊት ይኖረኛል ብዬ የማስበው አቋም ያው ነው። ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ..እየተባባሉ በዘር መደራጀት አይጠቅምም፣ ጎጂ ነው የሚል እምነት ነው ያለኝ።

ሆኖም ሌሎች ኢትዮጵያዊያን በአማራነት፣ በኦሮሞነት፣ በትግሬነት፣ በሴትነት፣ በሞያ ማህበራት ..በተለያዩ ቡድኖች ቢደራጁ ፣ የኔም መብት፣ የሌላዉን መብት እስካልነኩ ድረስ፣ ችግር የለብኝም። ሊኖረኝም አይገባም። እኔ ስላልፈለኩም አስተዳደጌ እንደ ሽገር ባሉ ብዙዎች ተደባልቀው በሚኖሩበት አካባቢ ከመሆኑ የተነሳ በዘር መደራጀት ስላልተመቸኝ፣ ሌላው እንደኔ ካልሆነ ልል አልችልም።

ዜጎች በኦሮሞነት፣ በአማራነት. በትግሬነት ..ባይደራጁ ጥሩ ነበር። ሆኖም ግን መብታቸውን መጋፋት ስለሌለብን ለምን በዚህ መልክ ተደራጃችሁ ብለን መናገራና መክሰስ ግን ያለብን አይመስለኝም። በተለይም ደግሞ ኦሮሞዎች በኦሮሞነት ሲደራጁ ምንም ያላልን፣ እንደዉም በኦሮሞነት ከተደራጁ ጋር ግንባር ፈጥረን ታንጎ ስንደስ የነበረን፣ አሁን መልሰን ሌላ ሚዛን በማምጣት በአማራ ስም ለምን ተደራጃችሁ ብለን ክስ ማቅረባችን አያምርበንም። ግብዝነታችንንና አደርባይነታችንን ነው የሚያሳይ ነው።

አብኖች በአማራነት መደራጀታቸው መብታቸው ነው። ኦሮሞዎች በኦሮሞነት መደራጀታቸው መብታቸው እንደሆነ። እነ ዶ/ር መራራ ጉዲና በኦሮሞነት ሲደራጁ፣ እነ አቶ ለማ መገርሳ በዘር የተደራጀ የኦህዴድ መሪ ሲሆኑ ጸረ-ኢትዮጵያ አልተባሉም። አብኖች ግን ለምን በአማራ ስም ተደራጃችሁ በሚል ጸረ-አማራ፣ ዘረኛ የሚል ስም አንዳንዶች ሊለጥፉባቸው ሲሞክሩ እየታዘብን ነው። ይሄ ተቀባይነት የለውም። አንድ ድርጅት በሐሳብ መሞገት ሲያቅተን፣ በራሳችን መተማመን ሲሳነን ወደ ስድብና ስም ማጥፋት መሰማራት ትንሽነት ነው።

ዜጎች በቡድን የመደራጀት መብታቸው እንደተጠበቀ፣ በማንነት ተደራጅተው የኔን ወይንም የሌላውን መብት የሚነኩ ከሆነ ግን የመብትና የነጻነት ጉዳይ ነዉና እነርሱን መታገል ግድ ነው የሚሆነው።ለኦነጎች፣ ለኦሮሞ አክራሪ ጽንፈኛ ቄሮዎችና ለኦህዴድ የወረዳና የቀበሌ አመራሮች … ኦሮሞነት ሌላውን ማህበረሰብ መጤ ብሎ ማባረር ነው። ለነርሱ ኦሮምኛን ማስፋፋት አማርኛ እንዳይነገር ማድረግ ነው። ለነርሱ ለኦሮሞ መብት መቆም ማለት ሌላውን መጨፍለቅ ማለት ነው። ለነርሱ ኦሮሙማ ከሌላው ጋር በእክሉነት መኖር ሳይሆን ሌላውን oromized ማድረግ ነው። ለዚህ ነው አማርኛ ተናጋሪዎች በብዛት በሚኖሩባቸው የኦሮሞ ክልል ከተሞችም ወረዳዎች፣ ዞኖች ከኦሮምኛ ውጭ በምንም ሌላ ቋንቋ አገልግሎት እንዳይሰጥ ያገዱት። ለምን ከኦሮምኛ ሌላ ቋንቋ መናገር ኦሮምኛን ማሳነስ ስለሚመስላቸው። ይሄን አይነት ሌላውን ጠል ብሄረተኝነት እንታገለዋለን።

አብኖች ጋር ግን ያለው ሁኔታ የተለየ ነው። አቶ በለጠ ስለ “አማራዊ አድማስ” ያለው አባባል ነበር። አማራዊነት አድማሱ ሰፊ ነው ባይ ነው። “በአማራ ጠል ድርጅቶችና ስርዓት አማራው ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት እንደ ጠላት በመታየቱና በመጠቃቱ የግድ ራሳቸውን አለብን ” ከሚል ሕሳቤ በአማርነት ስር እንደተሰባሰቡ የገለጸው አቶ በለጠ “ተስፋ ቢስ አይደለንም” ሲል ያላቸው ራእይ፣ አድማሳቸውን ማስፋት እንደሆነ ነው የገልጸው።

“ተስፋ ቢስ የሆኑትን አይተናቸዋል።በነርሱ ልክ ብቻ ተሰፍቶ፣ ልክ ጉድጓድ ውስጥ እንዳለ እንቁራሪት ከውስጥ ሆኖ ሰማይን ሲያየው አለም ማለት በዚያ በምትታየው አድምስ ልክ የጠበበች አድርጎ እንደሚያስበው የሚያስቡ ናቸው።ይሄ ተስፋ ቢስነት ነው። ከዚያ ውጭ ያለውን አለም አያውቁቱም። ለማወቅም ዝግጁ አይደለም።አማራነት ግን የአለም መጨረሻ አማራነት ነው ብሎ አያስብም። እኛ ከአማራነትም የሰፋ ሰፊ አድማስ አለና በዚያ ውስጥ ተዋናይ ለመሆን ዝግጁ ነን። እየሰራን ያለነውን ይሄንኑ ነው” ሲል አሁን እንደ መነሻ በአማራነት ስም ቢንቀሳቀሱም መዳረሻቸው ግን ከዚያ የሰፋና የወጣ እንደሆነ ነው ለማሳየት የሞከረው። (በነገራችን ላይ እኔም አንዱ ተስፋዮ አብን አድማሱን አስፍቶ ከአማራነት ወደ አማርኛ ተናጋሪዎች፣ ከዚያም እያለ አድማሱን እያሰፋ ወደ አገር አቀፋዊነት ይሄዳል የሚል ነው)

አቶ በለጠ አሁን ያለው ስርዓትና ሕግ መንግስት የኢትዮጵያዊነትን እሴት እንደሸረሸረ አስረድቶ፣ የዜግነት ፖለቲካን ማራመድ አስቸጋሪ ነው ሲል የሕግ መንግስቱን ትልቅ ግድፈት ሳይጠቁም አላለፈም።

ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተወለዱ፣ “ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት ነው” የሚሉ፣ ለነርሱ ብሄረሰብ ከተሸነሸነው ዉጭ የሚኖሩ ዜጎች በሕገ መንግስቱና አሁን ባለው ስርዓት ዉክልና እንደሌላቸው በሰከነ መልኩ ያስረዳው አቶ በለጠ፣ ሕግ መንግስቱ አብዛኛው ሕዝብ ያልተስማማበት በጥቂቶች በሌላው ላይ የተጫነ እንደሆነ በመገልጽ ድርጅታቸው አብን አጥብቆ ሕግ መንግስቱ መሻሻል አለበት የሚል አቋም እንዳለው ተናግሯል።

በሕግ መንግስቱ ዙሪያ አቶ በለጠ የተናገረው በጣም ትክክለኛና እኔ በተለያዩ መድረኮች የተከራከርኩበትና የጻፍኩበት ጉዳይ ነው። እኔው የተናገርኩ ነበር አድርጌ ያሰብኩት።

መቀመጫው አሜሪካን አገር የሆነው ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ዶ/ር አብይ አህመድ በአሜሪካ ጉብኘት አድርገው በነበረ ጌዜ፣ “አሁን ያለው ሕግ መንግስቱ እርስዎ የሚሰብኩትን ታላቂቷን ኢትዮጵያ ያንጸባርቃል ብለው ያሰባሉ ወይ? ” የሚል ጥያቂ አቀርቦላቸው ነበር። ሆኖም ዶ/ር አብይ ምላሽ ሳይሰጡ ወደፊት እመለስበታለሁ ብለው እንዳለፉት ብዙዎችን የምናስታወሰው ነው። ህግ መንግስቱ አምስት ሳንቲም ለኢትዮጵያዊነት፣ ለአንድነትና ለመደመር ቦታ የሚሰጥ ሕግ መንግስት እንዳልሆነ ዶ/ር አብይ ልባቸው ጠንቅቆ ያውቀዋል። መዋሸት ስላልፈለጉ ነው ሌላ ጊዜ እንመለስበታለን ብለው ያለፉት።

ስርዓቱ፣ ሕገ መንግስቱ፣ አወቃቀሩ፣ ኢትዮጵያዊነትንና አንድነት ያሳነሰ ብቻ ሳይሆን ለማጥፋት የሞከረ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት በወጣቱ አይምሮ ውስጥ የተረጨው ጸረ-ኢትዮጵያ ፕሮፖጋንዳ የብዙዎችን አይሞር አቆሽሿል። በክሏል።፡ከዚህም የተነሳ በአንዳንድ ቦታዎች የዜግነት ፖለቲካ ማራመድ አስቸጋሪ መሆኑ ግልጽ ነው። አንድ ሰው በዘሩና በጎጡ እንዲያስብ ከተደረገ ከዚያ አጥር ያንን ሰው ለማስወጣት አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።ስለኢትዮጵያ መጥፎ ሲነገረው ያደገ የደምቢዶሎና የአዳባ ወጣት ከሲያድ ባሬ ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን ሲያደማ ስለነበረው ሽፍታ ስለዋቆ ጉቱ ስትነገረው እንጂ ስለ ባልቻ አባነስፎ ስትነግረው ደስ አይለውም። አቶ በለጠም “ኦሮሞ ክልል የዜግነት ፖለቲካ ብታራመድ ማን ይሰማሃል? የዜግነት ፖለቲካ exhausted ሆኗል” ያለው ከዚህ የተነሳ ይመስለኛል።

እንግዲህ አንዱ ከአቶ በለጠና አቶ ክርስቲያን ጋር ያለኝ ትልቁ ልዩነት ይሄ ነው። ለዜገነትና ኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ያላቸው አመለካከት። አንደኛ የዜግነት ፖለቲካ ካልሆነ በቀር ሌላ ፖለቲካ፣ ያዉም ደግሞ በአንድ ዘዉግ ማንነት ላይ ያተኮረ ፖለቲካ ለመቀበል የሚከብዳቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች አሉ።

– እንዳለ ደቡብ ክልል ያለው ሕዝብ የዜግነትና የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ደጋፊ የሆነ ህዝብ ነው። ምን አልባት አንዳንድ የደሃዴን ካድሬዎች በነ አቶ ሚሊዮን ላይ ባላቸው ችግር ምክንያት በየዞኑ ክልል እንሁን የሚል ድምጽ አሰምተው ሊሆን ይችላል። ሃቁ እዉነቱ ግን በደቡብ ክልል ኢትዮያዊነት ስር የሰደደ መንፈስ ነው። ወደ አምሳ ሁለት ብሄረሰቦች ስለሚኖሩ፣ በአንድ ብሄረሰብ ታጥሮ መቀጠል እንደማያዋጣቸው ያወቃሉ። አርባ ምንጭ፣ ቦንጋ፣ ጂንካ ….ከኢትይጵያዊነት ውጭ ሌላ ይሰማል የሚል ካለ አካባቢዉን የማያውቅ መሆን አለበት።፡ከዳንኤል ሺበሺና ከግርማ በቀለ ጋር ቢገናኙ ደቡብ ክልል ስላለው ሁኔታ በቂ መረጃ ማግኘት ይችላሉ።

– አዲስ አበባና በኦሮሚያ ውስጥ ባሉት የሸዋ ዞኖች በተለይም ምስራቅ ሸዋ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞኖች ከአዲስ አበባ አቅራቢያ ስለሆኑ፣ ሕብረ ብሂራዊ አካባቢዎች ናቸው። የአዳማ፣ የዱከም፣ የሞጆ፣ የወሊሶ፣ የቢሾፍቱ ፣ የሰበታ፣ የቡራዮ፣ የለገጣፎ፣ የገፍርሳ፣ የሱልሉታ የሰንዳፋ…ሕዝቦች፣ ከአዲስ አበባ ህዝብ ጋር የተገናኙና የተሳሰሩ እንደመሆናቸው ሕብረብሄራዊ አካባቢዎች ናቸው። የተደባለቀ ፣ የተዋለደ ማሀብረሰብ ያለበት። ከተለያዩ የአገሪቷ ግዛት ለስራ ለመሻሻል ሰው አዲስ አበባ አዲስ አበባ ዙሪያ ነው የጎረፈው። ያ ማለት ያለ ምንም ጥርጥር አዲስ አበባና በኦሮሚያ ውስጥ ያሉ የሸዋ ዞኖችን ብንጠቀልላቸው ከስድሳ በመቶ በላይ የሚሆነው ማህበረሰብ አማርኛ ተናጋሪ፣ ለኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ቅርብ የሆነ፣ ዘዉጋዊ አመለካከት የሌለው ማህበረሰብ ነው።፡ እንደ አሰላ፣ ጂማ፣ ጎባ፣ ሻሸመኔ ያሉ በኦሮሞ ክልል ያሉ ከተሞችም ለዜግነት ፖለቲካ ቅርብ ናቸው።

እርግጥ ነው እንደ ወለጋ፣ ምእራብ ሸዋ፣ ሃረርጌ፣ ምእራብ አርሲ፣ ባሌ ባሉ የኦሮሞ ክልል አካባቢዎች የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ አይሰራም። ሌላ ትውልድ እስኪመጣ ድረስ። ላለፉት ሁለት ሶስት አመታት የኦሮሞ ፕሮቴስት በሚል ተቃዉሞ ሲደረግ የነበረው በዋናነት በነዚህ አካባቢዎች ነው። አንድ ቦታ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ሲያነሱ፣ ኢትዮጵያዊ ጥያቄዎችን ሲያቀረቡ ያየንበት ሁኔታ አልነበረም። እነዚህ አካባቢዎች ሞዛምቢክ ፣ ጋና ወይም የመን የኖራችሁ ይመስል ነው የኢትዮጵያዊነት ነገር ለምልክት እንኳ ይታይባቸው ያልነበሩት።

ነገር ግን ብዙ ጊዜ የምንዘናገው ነገር፣ ጩኸት ከነዚህ አካባቢዎች በጣም ስለተሰማ ሁሉ የኦሮሞ ክልል እንደዚያ ነው፣ ሁሉም ኦሮሞ እንደዚያ ነው ማለት አይደለም።

በኦሮሞ ክልል ካሉ ከ175 ወረዳዎች ወደ ግማሹ የአንድነት ሃይሉ ጠንክሮ ከሰራ ድጋፍ ሊያገኝባቸው የሚችሉ ወረዳዎች ናቸው። ፈርተው ድምጻቸውን አጠፉ እንጂ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆች አቶ ለማ መገርሳ እንዳለው ኢትዮጵያዊነት ሱሳቸው ነው።

አቶ በለጠ ኦሮሞ ክልል ሲል፣ እነ ወለጋን አስበው እንደሆነ ይገባኛል። ግን ኦሮሞ ክልል ስንል እንደ ደራ፣ እነ ቅምብቢት፣ እነ አቢቹ፣ እነ አሰላ፣ እነ ኡሩርታ እነ አዳማ፣ እነ አዳ፣ እነ ቡራዩ፣ እነ ጂማ ልዩ ..እንዳለኡም ባይረሳ ጥሩ ነው። የኦሮሞ ልጆች ስንል እነ መሳይ ተኩ፣ እነ ሰለሞን ስዩም ፣ እነ አበባየሁ ደሜ ፣ እነ ደራርቱ ቱሉ ፣ እነ ጀነራል ዋሲሁን ንጋቱ፣ እነ ጀነራል ካሳዬ ገመዳ..ኢትዮጵያ ሲባል ውስጣቸው እንደ ሰም የሚቀጥልጥባቸው እንዳሉ መረሳት የለበትም። ጥቂቶች ስለጮኹ ኦሮሞ የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካን አይቀበልም ብሎ በጥቅሉ መደምደም ትልቅ፣ እጅግ በጣም ትልቅ ስህተት ነው። አንደኛ ከእውነት የራቀ ነው። ሁለተኛ እዉነትም ነው ብንል፣ ያንን ሁኔታ ለመⷀር የበለጠ ኢትዮጵያዊነት አንገበን እንነሳለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም።

በኔ እይታ የዜገነት ወይንም የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ በአሁኑ ወቅት እንደማይሰራ ተደርጎ እየታየ ያለው፣ የአንድነት ወይንም የዜግነት ፖለቲካ የሚያራመዱ፣ ኢትዮጵይዊነትን ይዘው ደፍረው ወደ ሕዝቡ በበቂ ሁኔታ የሚቀርቡ ደርጅቶች ባለመኖራቸው ነው። አለን ካሉም በበቂ ሁኔታ ስራቸውን ስላልሰሩ ነው። ስራ ማለት ኢትዮጵያዊነት በገነነበት አካባቢ ኢትዮጵያዊነትን እንዘክር ብሎ የሙዚቃ ዝግጅት ማዘጋጀት አይደለም። ስራ ማለት የአንድነት፣ የፍቅር፣ የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ለምን እንደሚያዋጣ ታች ህዝብ ድረስ ወርዶ ማንቃት ማለት ነው። ስራ ማለት ኢትዮጵያዊነት የማያንጸባረቀው ህግ መንግስትና የጎሳ አወቃቀር እንዲቀየር፣ እነ ታምራት ነገራ እንደሚያደረጉት፣ ግፊት ማድረግ ማለት ነው።

በቃለ ምልልሱ አቶ ክርስቲያን ታደለም ሆነ አቶ በለጠ የዜግነት ፖለቲካን ለማካሄድ ሕጉ ስርዓቱ አይፈቅድም ይላሉ። እንደውም አቶ ክርቲያን በምሳሌ ሲከርከር “በአማርኛ ዘፈን ወላይትኛ አይጨፈረም” ነገር ነበር ያለው። እውነቱን ነው። እንደውም እኔም ሌላ ምሳሌ አለኝ። በቅርጫት ኳስ ጨዋታ እግር ኳስ ይመስል አስራ አንድ ተጫዋች ማሰለፍ አንችልም። በዚህ ረገድ አብኖች ትክክል ናቸው።

እንደ ዜገነትና ኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ አራማጅ ግን አብኖችን በዚህ ጉዳይ ልሞግት ፈለኩ። “ልክ ናችሁ ሕግ መንስግቱ፣ የጨዋታው ህግ የዘዉግ ፖለቲካ ነው። ነገር ግን እኛ የአንድነት ሃይሎች ትግላችን የሚሆነው የጨዋታውን ሕግ ለመቀየር ነው። ሕግ መንግስቱ ኢትዮጵያዊነትን፣ እኩልነትን እንዲያንጸባረቅ ማድረግ ነው፤ የጎሳ አወቃቀር ተቀይሮ ዜጎች በዘራቸው ወይም በጎጣቸው ሳይሆን በስብእናቸው እንዲከበሩ ነው፡፡በትግሪኛ ዘፈን ወላያትኛ ለመጨፈር ሳይሆን ፣ በትግሪኛ ዘፈን ትግሪኛ፣ በወላይትኛ ዘፈን ወላይተኛ ለመጨፈር ነው። ሜዳው የእግር ኳስ ሜዳ ሆኖ እነ አዳነ ግርማን ለማሰለፍ ነው” የሚል ምላሽ ነው የምሰጣቸው፡

ለነርሱ የዜግነት ፖለቲካ አሁን ባለው ሁኔታ አይዋጣም ካሉ፣ ችግር የለውም። አንቃወማቸውም። እንደዉም የጋራ አብረን ልንሰራባቸው የምንችላቸው አጀንዳዎች ካሉ አብረን ልንሰራም እንችላለን። ነገር ግን አብኖች የዜግነት ፖለቲካ አይሰራም ወይም exhausted ሆኗል የሚለውን አባባሎቻቸውን ያቆሙ ዘንድ እመክራቸዋልሁ። ለምን ቢባል በቀጥታ ከአስር ሚሊዮኖች ጋር የሚያላትማቸው ነው የሚሆነው። ብዙ ጊዜ እንደሚሉት መዳረሻቸው ኢትዮጵያዊነት ከሆነ፣ አቶ በለጠም እንዳለው በአማራነት ብቻ ተወስነው ሳይሆን አድማሳቸውን የማስፋት ራእይ ካላቸው ፣ የዜገነትና የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ለምናራመደው፣ ቢችሉ ከኛ ጋር መስራት፣ ካልቻሉም ደግሞ ለትግላችን እውቅና ቢሰጡ ጥሩ ነው ባይ ነኝ።

በሚቀጥለው ክፍል አቶ ክርስቲያን ታደለ በተናገራቸው ሌሎች ሁለትሐሳቦች ላይ ተጨማሪ አስተያየት ይዤ እመጣለሁ። አማራነትን ሲተነትን “ደማዊ ትስስር” ባለውና ስለ አማራ ‘እርስት በተናገረው ባልተመቹኝ ሁለት ሐሳቦች ዙሪያ የምለው ይኖረኛል። ምን አልባት በነዚህ ሁለት ሐሳቦች ዙሪያ አቶ ክርስቲያን የተናገረው የርሱን ሐሳብ የሚያንጸባርቅ እንጂ የአብንን አቋም የሚያንጸባርቅ ላይሆን ይችላል። ለምን ቢባላ አቶ በለጠ አቶ ክርስቲያን የተናገራቸውን ቀስ ብሎ ያስተካከለበት ሁኔታ ያለ ስለመሰለኝ።