ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ወጥተው የቆዩ ተማሪወች መንግሥት የሰጣቸውን አቅጣጫ እና መፍትሔ ካልተቀበሉ ከተማዋን ለቀው ይውጡ- የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር

ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ወጥተው የቆዩ ተማሪወች መንግሥት የሰጣቸውን አቅጣጫ እና መፍትሔ ካልተቀበሉ ከተማዋን ለቀው ይውጡ- የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ወጥተው የቆዩ ተማሪዎች መንግሥት የሰጣውን አቅጣጫ እና መፍትሔ የማይቀበሉ ከሆነ ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በፀጥታ ችግር ምክንያት ወጥተው በባሕር ዳር በተቀመጡ ተማሪዎች እና በከተማዋ በሚስታዋሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከተማ አስተዳደሩ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ ‹‹የባሕር ዳር ከተማ ከየትኛው ሀገር በችግር ለሚመጡ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እየተቀበለ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ቆይቷል፡፡ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የመጡ ተማሪዎችንም ከሁለት ሳምንት በላይ ተንከባክቦ አስቀምጧቸዋል›› ብለዋል፡፡Image may contain: 1 person, standing

አቶ ሙሉቀን የከተማዋ ማኅበረሰብ የተማሪዎችን ችግር በመረዳት አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያርግ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ተማሪዎች ግን በፍቀር የተቀበላቸውን ማበረሰብ እጁን አመድ አፋሽ አድርገውታል›› ነው ያሉት ከንቲባው፡፡

ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በፀጥታ ችግር ወደ ከተማዋ የመጡ ተማሪዎች መቀመጫቸውን በባሕር ዳር አድርገው የክልሉን መንግሥት ምላሽ እንዲሰጣቸው ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡የክልሉ መንግሥትም ከተማሪዎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመምከር ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ከትላንት ጀምሮ ግን ጥያቄያቸውን በኃይል በማደረግ የከተማዋን ሰላም ለመበጥበጥ ጥረት ሲያርጉ እንደነበር ነው ከንቲባው የተናገሩት፡፡ ‹‹ተማሪዎቹ በከተማዋ እየተዘዋወሩ ቤት መትተዋል፤ ንበረት ላይ ጉዳት አድረሰዋል፡፡ በአጠቃላይ የፈጸሙት ተግባር አሳፋሪ እና የሽፍትነት ነው›› ብለዋል ከንቲባው፡፡

ተማሪዎቹ ሲንከባከባቸው የሰነበተውን ማኅበረሰብ ሲማቱ የፀጥታ ኃይሉ በመታገስ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋና ንብረት እንዳይወድም በጥንቃቄ ኃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት ማድረጉን ነው ከንቲባው የገለጹት፡፡

‹‹በዛሬው ዕለትም ተማሪዎቹ ከተማዋን ሲያበጣብጡ የከተማዋ ወጣቶች ችግሩን በትብብር አብርደውታል›› ነው ያሉት አቶ ሙሉቀን፡፡ ከንቲባው ወጣቶች፣ ማኅበረሰቡ እና የፀጥታ ኃይሉ ለሰላም ላደረጉት ትብብር ምስጋና እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡

‹‹ተማሪዎቹ ከአቅም በላይ ስለሆኑ መንግሥት በሰጣቸው አቅጣጫ የማይጓዙ ከሆነ ከተማችን ለቀው ይውጡ›› ሲሉ ነው ከንቲባው ያሳሰቡት፡፡ ወላጆቻቸው ልጆቻቸውን እንዲመክሩም ከንቲባው ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሰላም ግንባታ እና የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘውዱ ዘለቀ ‹‹ተማሪዎቹ መንግሥት በሚሰጣቸው መፍትሔ ላይ ሊስማሙ አልቻሉም፤ የሰላም መማር ማስተማር ሥርዓት እያከናወነ ያለውን የባሕር ዳር
ዩኒቨርሲቲን ጭምር እየገቡ ረብሸዋል›› ነው ያሉት፡፡

ኃላፊው በከተማዋ ስምንት ያክል መኪኖች የጫኑት እህል ያለአግባብ በተማሪዎቹ ምክንያት እንደተራገፈባቸው አስታውቀዋል፡፡ አቶ ዘውዱ ‹‹የፀጥታ ኃይሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ለሕዝቡ ደኅነነት እየሠራ ነው›› ሲሉም አመሥግነዋል፡፡

ተማሪዎቹን የሚገፋፋ ኃይል እንዳለ ያነሱት አቶ ዘውዱ ‹‹ሰላም ወዳዱ የከተማዋ ወጣት ተማሪዎቹ ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ ወስኗል›› ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል የሰላም ግንባታ እና የሕዝብ ደኅንነት ምክትል ኃላፊ አቶ ገደቤ ኃይሉም የተማሪዎችን ችግር ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡‹‹ተማሪዎች ግን በሚሰጣቸው አቅጣጫ ሁሉ ተስማሚ አልሆኑም›› ብለዋል፡፡

ተማሪዎቹ በየቤተሰቦቻቸው እንዲቆዩ እንጂ በአንድ ላይ እንዲሰበሰቡ ተፈቅዶ እንዳልነበር ያመለከቱት አቶ ገደቤ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተማሪዎቹ የሚያነሱትን ችግር በመፍታት በጉጉት እየጠበቃቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አቶ ገደቤ ‹‹መንግሥት ችግሩን ተረድቶ ሲወያይ ቆይቷል፤ አሁንም መፍትሔ አስቀምጧል›› ነው ያሉት፡፡በዚህም ‹‹ወደነበሩበት ዩኒቨርሲቲ መመለስ ካፈለጉ ወደየቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ ተወስኗል›› ብለዋል ምክትል ቢሮ ኃላፊው፡፡ በክልሉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ሕዝብን በባለቤትነት በመያዝ እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ ጎንደር ተከስቶ የነበረው ችግር አንጻራዊ ሰላም እንደታየበት ገልጸው አካባቢው የተጠናከረ ጥበቃ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል።

ምንጭ፦ አብመድ