ጭንቀት፣ ንዴት፣ ግራ መጋባት እና ፍርሀትን በሦስት ደቂቃ የሚያስወግድ መሣሪያ ተፈለሰፈ

በሦስት ደቂቃ ከጭንቀት ስሜት የሚገላግል የቴክኖሎጂ ውጤት ተዋወቀ፡፡(አብመድ)

የፈረንሳዩ ኒዉራል አፕ ኩባንያ ከጭንቀት አውጥቶ የመዝናናት ስሜትን የሚፈጥር የቴክኖሎጂ ውጤት አስተዋውቋል፡፡

ቴክኖሎጂው ድምጽ እና ምስልን በመጠቀም ጥልቅ የመዝናናት ስሜት ውስጥ ያስገባል ተብሏል፡፡ ይህም በስርዓተ ነርቭ ውስጥ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ጭንቀትን የሚዋጉ ንጥረ ነገሮች እንዲመረቱ በማድረግ ነው፡፡

ጭንቀት፣ ንዴት፣ ግራ መጋባት እና ፍርሀትን የመሳሰሉ አሉታዊ ስሜቶችን በማስወገድ የስሜት መዛባትን እንደሚያስቀርም ተገልጿል፡፡

ቴክኖሎጂው ጊዜያዊ መፍትሄ ቢሆንም በድግግሞሽ ጥቅም ላይ ሲውል የመንፈስ ጭንቀት እና እንደ ራስን ማጥፈት ያሉ ተያያዥ ችግሮችን ለመቀነስ ይጠቅማል ተብሏል፡፡

‹‹በብል ዜን››የሚል ስያሜ የተሰጠው መንፈስ ማነቃቂያ መሳሪያ ክብ እና አንድ ሰው ውስጡ ማስገባት የሚችል መጠን አለው፡፡

በጆሮ ማዳመጫ መሳሪያ (ኤርፎን) እና 360 ዲግሪ በተገጠመ ምስል መመልከቻ ሰሌዳ ዘና የማድረግ ስራውን ይሰራል፡፡

የስራ ውጥረት በሚበዛባቸው አካባቢዎች አንዲሁም በአውሮፕላን ማረፊያዎች እና በባቡር መናህሪያዎች ቢገጠም ሰዎችን ዘና በማድረግ ውጤታማ ይሆናል ተብሏል፡፡
ዋጋውን በተመለከተ እስከ 15 ሺህ ዶላር ወይም 4 መቶ 60 ሺህ ብር አካባቢ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡

ምንጭ፡- ዴይሊ ሜል