ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው 11 የሜቴክ ሀላፊዎችና ሁለት ነጋዴዎች የአገልግሎት ጊዜያቸውን ያገባደዱ መርከቦችን በማሳደስና አክስሮ በመሸጥ ተከሰሱ

እነሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ከ544 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ የሕዝብ እና የመንግስት ገንዘብ ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል ተከሰሱ፡፡

ከሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ጋር 11 የሜቴክ ሀላፊዎችና ሁለት ነጋዴዎች አብረው ተከስሰዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በመሰረተው ክስ፣ ተከሳሾቹ እነሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው፣ “አባይ”ና “አብዮት” የተሰኙ የአገልግሎት ጊዜያቸውን ያገባደዱ መርከቦችን በማሳደስና አክስሮ በመሸጥ ከሷቸዋል፡፡

ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ አገልግሎት፣ ከ28 አመታት በላይ ያገለገሉትን “አባይ” እና “አብዮት” መርከቦች ብረታቸው ተቆራርጦ ለሌላ አገልግሎት መጠቀሚያ እንዲሆኑ ለሜቴክ በ3.2 ሚሊዮን ዶላር ይሸጥለታል፡፡

ሜቴክ ግን፣ ለቁርጥራጭ ብረታቸው ሲል የገዛቸውን ወደ ስራ አስገባቸዋለሁ ብሎ 7.3 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ እድሳት ማድረጉ በዐቃቤ ሕግ ክስ ላይ ተጠቅሷል፡፡

ይሁንና ለአገልግሎት እንዲውሉ ተብለው 7.3 ሚሊዮን ዶላር ለእድሳት በሚል የፈሰሰባቸው መርከቦች ብቁ ሊሆኑ ባለመቻላቸው፣ ሜቴክ በ607,432 ዶላር በኪሳራ ሸጧቸዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ አመልክቷል፡፡

ስለዚህ 544 ሚሊዮን 702 ሺህ 623 ብር በህዝብና በመንግስት ሀብት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ሲል ዐቃቤ ህግ ጉዳዩን ለሚያየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ክስ መስርቷል፡፡

ባለፈው ጥር 2 ቀን 2011 ሜጀር ጀኔራል ክንፈን ጭምሮ፣ በአምስት የሜቴክ ሀላፊዎችና በሶስት በግል ስራ በተሰማሩ ግለሰቦች ላይ ከ319 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ብሎ ዐቃቤ ህግ ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE