ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በግጭት ምክንያት በየሳምንቱ በአማካይ 320 ተፈናቃዮች ወደ አማራ ክልል ይገባሉ

አዲስ አድማስ

ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በግጭት ምክንያት በየሳምንቱ፣ በአማካይ 320 ያህል የአማራ ተወላጆች እየተፈናቀሉ ወደ አማራ ክልል እንደሚገቡ የገለፀው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፤ ተፈናቃዮቹን ለመርዳት በክልሉ መንግስት በኩል የ8 ሚሊዮን ዶላር (280 ሚ. ብር ገደማ) አስቸኳይ የእርዳታ ጥሪ መቅረቡን አስታውቋል።

የክልሉን መንግስት መረጃ ዋቢ ያደረገው ፅ/ቤቱ፤ የአማራ ተወላጆች በአመዛኙ ከአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልል የተለያዩ ጥቃቶችን በመሸሽ ወደ አማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች እየተሰደዱ ነው ብሏል። ክልሉ በየሳምንቱ በአማካይ 320 ያህል ስደተኞችን ያስተናግዳል ያለው ሪፖርቱ፤ በአሁኑ ወቅት የተፈናቃዮቹ ቁጥር ከ14 ሺህ በላይ መድረሱን ጠቁሞ፣ ለሚቀጥሉት 6 ወራት የምግብና መሰረታዊ ፍላጎቶች አቅርቦት 8 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አመልክቷል፡፡

ተፈናቃዮቹ በማዕከላዊ፣ ደቡብና ምዕራብ ጎንደር፣ በምዕራብ ጎጃም፣ በኦሮሞ ዞን፣ በደቡብና ሰሜን ወሎ፣ በባህርዳር፣ በሰሜን ሸዋ፣ በዋግኧሞራና አዊ ዞን ውስጥ በተለያዩ ካምፖች ተጠልለው እንደሚገኙም ሪፖርቱ ጠቁሟል። የተፈናቃዮች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ ለክልሉ መንግስት አዳጋች ሁኔታዎች መፍጠሩን ያመለከተው ሪፖርቱ፤የረድኤት ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ መቅረቡን አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በመላ ሃገሪቱ 2.4 ሚሊዮን የግጭት ተፈናቃዮች በተለያዩ ካምፖች ተጠልለው እርዳታ እየጠበቁ መሆናቸውን የገለፀው የተባበሩት መንግስታት፤ በአጠቃላይ 9.4 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የሰው እጅ ጠባቂ ናቸው ብሏል፡፡ ለእነዚህ ተረጅዎች በሚቀጥሉት 6 ወራት ምግብ ነክ ያልሆኑ ህክምና የመሳሰሉ እርዳታዎችን ለማቅረብ ብቻ ከ1.4 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡

በርካታ ኢትዮጵያውያን በግጭት ሳቢያ ከተፈናቀሉባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል የሶማሊያ – ኦሮምያ አዋሳኝ ድንበር፣ ደቡብ ክልል፣ቤኒሻንጉል፣ ሞያሌ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። እንደተባበሩት መንግስታት ሪፖርትም፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በአገር ውስጥ በማፈናቀል ኢትዮጵያ ከዓለም ቀዳሚዋ አገር ናት ተብሏል፡፡